በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ማር—ንቦች ለሰዎች የሚሰጡት ገጸ-በረከት

ማር—ንቦች ለሰዎች የሚሰጡት ገጸ-በረከት

ማር—ንቦች ለሰዎች የሚሰጡት ገጸ-በረከት

ሜክሲኮ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

በድካም እጅግ የዛለ አንድ እስራኤላዊ ወታደር ጫካ ውስጥ ከማር እንጀራ ላይ የሚንጠባጠብ ወለላ ተመለከተና በያዘው ዘንግ ከወለላው አጥቅሶ ጥቂት ማር በላ። ከዚያም ወዲያውኑ ‘ዐይኑ በራ፤’ ኃይሉም ታደሰ። (1 ሳሙኤል 14:25-30) ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ማር ለሰው ልጅ ከሚሰጠው በርካታ ጥቅሞች ውስጥ አንዱን ይጠቁማል። ማር ከያዛቸው ንጥረ ነገሮች ውስጥ 82 በመቶ ያህሉ ካርቦሃይድሬት መሆኑ ፈጣን የኃይል ምንጭ አድርጎታል። የሚገርመው፣ በሐሳብ ደረጃ ሲታይ አንዲት ንብ 30 ግራም ብቻ ከሚመዝን ማር በምታገኘው ኃይል ዓለምን ትዞራለች!

ንቦች ማር የሚሠሩት ለሰዎች ጥቅም ሲሉ ነው? በጭራሽ፣ ከዚህ ይልቅ ሕልውናቸው የተመካው በማር ላይ ስለሆነ ነው። አንድ መካከለኛ መጠን ያለው ቀፎ ውስጥ የሚኖሩ ንቦች የክረምቱን ወራት በሕይወት ለማለፍ ከ10 እስከ 15 ኪሎ ግራም የሚመዝን ማር ያስፈልጋቸዋል። ሆኖም ምቹ በሆነ ወቅት በአንድ ቀፎ ውስጥ የሚገኙ ንቦች 25 ኪሎ ግራም የሚያህል ማር ሊያመርቱ ይችላሉ፤ በዚህ ወቅት ከንቦቹ የተረፈውን ሰዎችን ጨምሮ እንደ ድብ ያሉ እንስሳት ይበሉታል።

ንቦች ማር የሚሠሩት እንዴት ነው? ንቦች ከቦታ ወደ ቦታ በመዘዋወር ከአበቦች ላይ ፈሳሽ የአበባ ወለላን ቱቦ በመሰለው ምላሳቸው እየቀሰሙ በሆዳቸው ውስጥ ባለ የማር ቋት ውስጥ ያጠራቅማሉ። ከዚያም ተሸክመው ወደ ቀፏቸው ይወስዱታል። ቀጥሎም ፈሳሽ የአበባ ወለላውን ወደ ሌሎች ንቦች ያዛውሩታል። ወለላውን የተቀበሉት ንቦች በአፋቸው ውስጥ ካሉት እጢዎች ከሚመነጭ ኢንዛይም ጋር እያዋሃዱ ለአንድ ሰዓት ከግማሽ ያህል “ያላምጡታል።” ከዚያም ከሰም በተሠሩ ባለ ስድስት ማዕዘን ክፍሎች ውስጥ ያስቀምጡትና እርጥበቱ እንዲተን በክንፎቻቸው ያራግቡታል። * የውኃው መጠን ከ18 በመቶ በታች ሲሆን ክፍሎቹን በሰም በስሱ ይሸፍኗቸዋል። በዚህ መልኩ የተሸፈነ ማር ሳይበላሽ ለዘመናት ሊቆይ ይችላል። ከዛሬ 3,000 ዓመታት ገደማ በፊት እንደተሠሩ በሚነገርላቸው የፈርዖኖች መቃብር ቤቶች ውስጥ ለምግብነት ሊውል የሚችል ማር ተገኝቷል።

ማር የመድኃኒትነት ባሕርይ አለው

ማር ግሩም ምግብ ከመሆኑም ባሻገር በቫይታሚን ቢ፣ በተለያዩ ማዕድናትና አንቲኦክሲደንትስ በተባሉ ንጥረ ነገሮች የበለጸገ መሆኑ እስከ አሁን ድረስ ጥቅም ላይ ከሚውሉ ጥንታዊ መድኃኒቶች ውስጥ አንዱ እንዲሆን አድርጎታል። * በዩናይትድ ስቴትስ የኢሊኖይ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑትና በነፍሳት ላይ ምርምር የሚያደርጉት ዶክተር ሜይ ብሪንበም “ማር ለብዙ መቶ ዘመናት ቁስልን፣ የተቃጠለ የአካል ክፍልን፣ የዓይን ቆዳ መሸብሸብንና በቆዳ ላይ የሚወጣ ቁስልን ጨምሮ ሌሎች የተለያዩ የጤና ችግሮችን ለማከም ሲያገለግል ቆይቷል” በማለት አስተያየት ሰጥተዋል።

የሲ ኤን ኤን የዜና ድርጅት ማር ያለውን የመድኃኒትነት ባሕርይ አስመልክቶ በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት ላይ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥቷል:- “ሰዎች ቁስልን በማከም ረገድ ለማር የነበራቸው ግምት የቀነሰው በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት አንቲባዮቲክ ለዚህ አገልግሎት መዋል በጀመረ ጊዜ ነበር። ያም ሆኖ በቅርቡ የተደረገው ጥናት እንዲሁም አንቲባዮቲክን የመቋቋም ችሎታ ያላቸው ባክቴሪያዎች መብዛታቸው ጥንታዊውን መድኃኒት ወደ ዘመናዊው የሕክምና መድረክ መልሶታል።” ለአብነት ያህል፣ ከተደረጉት ጥናቶች ውስጥ አንዱ የተቃጠለ አካልን ማከምን ያካትት ነበር። ቁስላቸው ላይ ማር ተቀብቶ የታከሙ ሕመምተኞች ቁስሉ ቶሎ እንደዳነላቸው፣ እምብዛም ሕመም እንዳልተሰማቸው እንዲሁም በሰውነታቸውም ላይ የጎላ ጠባሳ እንዳልቀረ ከጥናቱ ለማወቅ ተችሏል።

ንቦች በአበባ ፈሳሹ ላይ ኢንዛይም ስለሚጨምሩበት ማር ለስለስ ያለ የፀረ ባክቴሪያነትና አንቲባዮቲክነት ባሕርይ እንዳለው ጥናቶች ይጠቁማሉ። ይህ ኢንዛይም ጎጂ ባክቴሪያዎችን የሚገድል ሃይድሮጅን ፐርኦክሳይድ እንዲፈጠር ያደርጋል። * በተጨማሪም በቆሰለው የሰውነታችን ክፍል ላይ ማርን መቀባት ቁስሉ እንዳይመረቅዝ እንዲሁም ሥጋውን እንዲተካ የሚረዳ መሆኑ ተደርሶበታል። በመሆኑም ኒው ዚላንዳዊው ባዮኬሚስት ዶክተር ፒተር ሞላን “ማር ዝነኛና ፍቱን መድኃኒት መሆኑ በዘመናዊ የሕክምና ባለሙያዎች ዘንድ ተቀባይነት አግኝቷል” በማለት ተናግረዋል። እንዲያውም የአውስትራሊያ የሕክምና መገልገያዎች አስተዳደር ማር ለመድኃኒትነት እንዲውል እውቅና የሰጠ ከመሆኑም በላይ በዚያች አገር ውስጥ ቁስልን ለማከም የሚያገለግል ማር ለገበያ ይቀርባል።

ገንቢ በሆኑ ንጥረ ነገሮች የበለጸጉ፣ ጣፋጭ እንዲሁም ለሕክምና አገልግሎት የሚውሉ ምን ያህል ሌሎች ምግቦችን ታውቃለህ? ቀደም ባሉት ጊዜያት ንቦችንና የንብ አናቢዎችን ደኅንነት ለመጠበቅ ለየት ያለ ሕግ መውጣቱ ያን ያህል አያስገርምም! በእነዚህ ጊዜያት ንቦች የሚኖሩበትን ዛፍ መቁረጥ ወይም ቀፏቸውን ማውደም ከባድ መቀጫ ያስከፍል አሊያም በሞት ያስቀጣ ነበር። በእርግጥም ማር ለሰው ልጆች የተሰጠ ግሩም ስጦታ ሲሆን ለፈጣሪ ደግሞ ክብር ያመጣል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.5 ንቦች የማር እንጀራ የሚሠሩበትን ሰም የሚያመነጩት በሰውነታቸው ውስጥ ከሚገኙ ልዩ ዕጢዎች ነው። የማር እንጀራው ስድስት ጎን ያለው መሆኑ 0.3 ሚሊ ሜትር ውፍረት ያላቸው የእንጀራው ስስ ግድግዳዎች ከክብደታቸው 30 ጊዜ እጥፍ የሚበልጥ ክብደት እንዲሸከሙ ያስችላቸዋል። በእርግጥም የማር እንጀራ እጅግ አስደናቂ ንድፍ ነው!

^ አን.7 ሕፃናቶች በቀላሉ ለምግብ መመረዝ አደጋ ስለሚጋለጡ ማር እንዲመገቡ አይበረታታም።

^ አን.9 ኢንዛይም ለሙቀትና ለፀሐይ ብርሃን ከተጋለጠ በቀላሉ ስለሚጠፋ ፓስቸራይዝድ የሆነ ማር ለሕክምና አገልግሎት አይውልም።

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ማር ጨምሮ ማብሰል

ማር ከስኳር የበለጠ ጣፋጭነት አለው። በመሆኑም በስኳር ፋንታ ማር ስትጠቀም ትጨምረው ከነበረው የስኳር መጠን ከግማሽ እስከ ሦስት አራተኛ ያህል ማር ብቻ አድርግ። በተጨማሪም ማር ከያዛቸው ንጥረ ነገሮች ውስጥ 18 በመቶ ያህሉ ውኃ ስለሆነ ልትሠራ ካሰብከው ምግብ ውስጥ ተመጣጣኝ መጠን ያለው ውኃ ቀንስ። የምትሠራው ምግብ ውኃ የማይጨመርበት ከሆነ ለአንድ ስኒ (ለ200 ሚሊ ሊትር) ማር ሁለት የሾርባ ማንኪያ ዱቄት ጨምር። ለሚጋገሩ ምግቦች ደግሞ ለአንድ ስኒ ማር ግማሽ የሻይ ማንኪያ ቤኪንግ ሶዳ መጨመርና የምድጃውን ሙቀት በ15 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ያህል መቀነስ ያስፈልጋል።

[ምንጭ]

ናሽናል ሃኒ ቦርድ

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአበባ ወለላ የምትቀስም ንብ

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የማር እንጀራ

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኅብረ ንብ

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ንብ አናቢው ከቀፎ ውስጥ ያወጣውን ፍሬም ደኅንነት ሲመረምር