በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እውነተኛ ደስታ ማግኘት ትችላለህ!

እውነተኛ ደስታ ማግኘት ትችላለህ!

እውነተኛ ደስታ ማግኘት ትችላለህ!

በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በርካታ ሰዎች ዘመናዊ መኪና፣ ባንክ የተቀመጠ ዳጎስ ያለ ገንዘብ፣ ጥሩ ሥራ፣ ትልቅ ቤትና ዘመናዊ ኤሌክትሮኒክ ዕቃዎች እንዲሁም ማራኪ ተክለ ሰውነት ወይም ጡንቻማ የሰውነት ቅርጽ መያዝ ለደስታ ቁልፎች እንደሆኑ የሚሰማቸው ይመስላል። ይሁንና በእርግጥ ደስታ ማግኘት የተመካው እንዲህ ባሉ ቁሳዊ ነገሮችና በአካላዊ ቁመና ላይ ነው?

ታይም መጽሔት ላይ የወጣ አንድ ልዩ ዘገባ “ደስታን፣ አዎንታዊ አመለካከትን፣ በጎ ስሜቶችንና መልካም ባሕርያትን በሚመለከት የሚደረጉት ጥናቶች በከፍተኛ ሁኔታ ጨምረዋል” በማለት ይገልጻል። የእነዚህ ጥናቶች ውጤት ብዙዎችን አስደንቋል። ሁሉም ጥናቶች ገንዘብ፣ ዝና ወይም ውበት ደስታ ያስገኛሉ በሚል እምነት ኑሯቸውን የሚመሩ ሰዎች ራሳቸውን እያታለሉ እንደሆነ የሚገልጽ ተመሳሳይ ውጤት ማስገኘታቸው ያስገርማል። እንዲያውም እነዚህ ሰዎች ሕይወታቸውን የገነቡት የአእምሯቸውን ጤንነት ሊጎዳና አልፎ ተርፎም የመንፈስ ጭንቀት ሊያስይዛቸው በሚችል መሠረት ላይ ነው።

በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩ በርካታ ሰዎች ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ሀብታም ሆነዋል። “ነገር ግን ይህ ሁኔታ በራሱ የበለጠ ደስተኛ እንድንሆን አላደረገንም” በማለት ታይም መጽሔት ዘግቧል። በሌሎች አገሮች ያሉ ሰዎችም ሁኔታ ተመሳሳይ ነው። የቻይና ኢኮኖሚ ፈጣን እድገት ቢያሳይም በአገሪቱ የሚገኙ ደስታ ያጡ ሰዎች ቁጥር በአሳሳቢ ሁኔታ ጨምሯል። በዚህች አገር ውስጥ “ከ15 እስከ 34 ዓመት ዕድሜ ላይ ለሚገኙ ሰዎች ሞት ዋነኛ መንስኤ” የሆነው ራስን መግደል እንደሆነ በየሦስት ወሩ የሚወጣ አክሰስ ኤዥያ የተባለ ጋዜጣዊ መግለጫ ዘግቧል። እንዲህ ላለው ክስተት ምክንያት ከሆኑት ነገሮች አንዱ፣ ወጣቶች ከባድ በሆነውና ኃይልን በሚያሟጥጠው የሥራው ዓለም ስኬት ለማግኘት እንዲጥሩ የሚደረግባቸው ጫና ሳይሆን አይቀርም።

ቁሳዊ ብልጽግና ጭንቀትንና ውጥረትን እንደማይቀንስ ግልጽ ነው፤ እንዲያውም እነዚህ ችግሮች እንዲባባሱ ያደርጋል። “አሁን አሁን ለስሜትና ለአእምሮ አለመረጋጋት እንድንጋለጥ የሚያደርገን ዋነኛ ምክንያት አኗኗራችን ሆኗል” በማለት አንድ ዩኒቨርሲቲ ባደረገው ጥናት የደረሰበትን መደምደሚያ ገልጿል። ቫን ዊሸርድ የተባሉ የማኅበራዊ ሁኔታዎች ተንታኝ እንዳሉት ከሆነ “በርካታ ድርጅቶች ለጤና ከሚገቧቸው ኢንሹራንሶች ውስጥ ቁጥሩ በፍጥነት እያደገ የመጣው ለአእምሮና ለስሜት ጤንነት የሚገቡት ኢንሹራንስ ነው።”

በፍጥነት በመለወጥ ላይ ያለው ዓለማችን በልጆችም ላይ ሳይቀር ተጽዕኖ እያደረገ ነው። በአሁኑ ጊዜ፣ የስምንት ዓመት ልጆች “ውጥረት እንዳለባቸው የሚጠቁሙ ምልክቶችን ማወቅና ችግሩን መቋቋም የሚችሉበትን መንገድ በተመለከተ” ምክር የሚለግሱ መጻሕፍት እንደሚገኙ ዊሸርድ ተናግረዋል። ጭንቀትን በተመለከተ የወጣ አንድ ዘገባ እንደሚገልጸው በበርካታ ምዕራባውያን አገሮች ጭንቀት ያለባቸው ልጆች ቁጥር በዓመት 23 በመቶ የሚጨምር መሆኑ በጣም አሳሳቢ ነው። እንዲሁም “ለጭንቀት የሚታዘዙ መድኃኒቶችን የሚገዙ ዕድሜያቸው ለትምህርት ያልደረሰ ልጆች ቁጥር በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ ነው።”

ፍርሃት በጣም እየጨመረ የመጣ ሲሆን ለዚህ መንስኤ የሆነው የኢኮኖሚ አለመረጋጋት ብቻ አይደለም። ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ አክራሪነት መስፋፋቱም ሰዎች ነገ ምን ይከሰት ይሆን በማለት እንዲሸበሩ ያደርጋቸዋል። ለዚህ የሚሆን ምን እርዳታ አለ?

ኢየሱስ ክርስቶስ ከሁለት ሺህ ዓመታት ገደማ በፊት ከዚህ በተለየ አስደሳችና ውጥረትን የሚቀንስ የአኗኗር መንገድ አስተምሮ ነበር። የትምህርቱ ፍሬ ነገር ያልተወሳሰበ ቢሆንም ትልቅ እውነት ይዟል። ኢየሱስ “ለመንፈሳዊ ፍላጎታቸው ንቁ የሆኑ ደስተኞች ናቸው” ብሏል። (ማቴዎስ 5:3 NW) አዎን፣ ኢየሱስ አድማጮቹ ለሰው ልጆች ዋነኛ ፍላጎት ማለትም ስለ ፈጣሪያችንና እርሱ ለእኛ ስላለው ዓላማ ለሚናገረው መንፈሳዊ እውነት ትኩረት እንዲሰጡ አበረታቷቸዋል።

በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ እንደምንመለከተው ይህ እውነት፣ ደስተኛና ይበልጥ ትርጉም ያለው ሕይወት ለመምራት በጣም የሚያስፈልገው ነገር ምን እንደሆነ እንድንገነዘብ ይረዳናል። እንዲሁም እንዲህ ያለው መንፈሳዊ እውነት አስደሳች ተስፋ እንዲኖረን ያደርጋል።

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ደስታ በቁሳዊ ሀብት ላይ የተመካ ነው?