በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በእርግጥ ኢየሱስ የተሰቀለው በመስቀል ላይ ነው?

በእርግጥ ኢየሱስ የተሰቀለው በመስቀል ላይ ነው?

የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት

በእርግጥ ኢየሱስ የተሰቀለው በመስቀል ላይ ነው?

መስቀል፣ በሰዎች ዘንድ በጣም ከሚታወቁት ሃይማኖታዊ ምልክቶች መካከል አንዱ ነው። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ኢየሱስ የተገደለበት ቅዱስ ነገር እንደሆነ በማሰብ ለመስቀል ከፍተኛ ክብር ይሰጣሉ። ደራሲና የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ተከታይ የሆኑት አርኪኦሎጂስት አዶልፍ ናፖሊዮን ዲድሮን “መስቀል ከክርስቶስ በማይተናነስ መንገድ ይመለካል። ሌላው ቀርቶ ይህ ቅዱስ እንጨት የአምላክን ያህል ይከበራል” ብለዋል።

አንዳንዶች መስቀልን ተጠቅመው ሲጸልዩ ከአምላክ ጋር ይበልጥ እንደተቀራረቡ እንደሚሰማቸው ይናገራሉ። ሌሎች ደግሞ መስቀል ከክፉ ነገር ይጠብቀናል በሚል ስሜት አንገታቸው ላይ ያንጠለጥሉታል። ይሁን እንጂ ክርስቲያኖች መስቀልን ለአምልኮ መጠቀም ይኖርባቸዋል? በእርግጥ ኢየሱስ የተሰቀለው በመስቀል ላይ ነው? ይህን ጉዳይ በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረው ምንድን ነው?

መስቀል የምን ምልክት ነው?

ክርስትና ከመቋቋሙ ከረጅም ጊዜ በፊት የጥንት ባቢሎናውያን የመራባት አምላክ የሚሉትን ታሙዝን ለማምለክ የመስቀል ቅርጾችን እንደ ምልክት ይጠቀሙ ነበር። ከዚያም መስቀልን ለአምልኮ የመጠቀም ልማድ ወደ ግብጽ፣ ሕንድ፣ ሶርያና ቻይና ተዛመተ። ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ ደግሞ እስራኤላውያን ለይሖዋ የሚያቀርቡትን አምልኮ ከሐሰተኛው አምላክ ከታሙዝ አምልኮ ጋር ይቀላቅሉት ጀመር። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ዓይነቱን አምልኮ “አስጸያፊ ነገር” በማለት ይጠራዋል።—ሕዝቅኤል 8:13, 14

ማቴዎስ፣ ማርቆስ፣ ሉቃስና ዮሐንስ የጻፏቸው የወንጌል ዘገባዎች ኢየሱስ የተገደለበትን መሣሪያ ለማመልከት የተጠቀሙበት የግሪክኛ ቃል ስታውሮስ ይባላል። (ማቴዎስ 27:40፤ ማርቆስ 15:30፤ ሉቃስ 23:26) ስታውሮስ የሚለው ቃል ቀጥ ያለ ምሰሶን፣ እንጨትን አሊያም አጣናን ያመለክታል። በጆን ዴንሃም ፓረሰንዝ የተጻፈው ዘ ነን ክርስቺያን ክሮስ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “አዲስ ኪዳን ተብለው የሚጠሩት በርካታ መጻሕፍት በተዘጋጁበት በመጀመሪያው የግሪክኛ ጽሑፍ ውስጥ፣ ከኢየሱስ ጋር በተያያዘ የተሠራበት ስታውሮስ ቀጥ ያለ እንጨትን ሳይሆን በመስቀል ቅርጽ የተጣመሩ ሁለት እንጨቶችን እንደሚያመለክት የሚገልጽ አንድም ዓረፍተ ነገር የለም፤ ሌላው ቀርቶ እዚህ ላይ የተሠራበት ስታውሮስ ከተራው ስታውሮስ የተለየ መሆኑን በተዘዋዋሪ እንኳ የሚጠቁም ሐሳብ አናገኝም።”

በሐዋርያት ሥራ 5:30 ላይ ተመዝግቦ እንደምናገኘው ሐዋርያው ጴጥሮስ ስታውሮስን ለማመልከት የተጠቀመበት ተመሳሳይ ቃል ዛይሎን ይባላል፤ የቃሉም ፍቺ “ዛፍ” ማለት ሲሆን ቀጥ ያለ አጣናን አሊያም ዛፍን እንጂ በተነባበሩ ሁለት እንጨቶች የሚሠራውን መስቀል አያመለክትም። ክርስቲያን ነን የሚሉ አንዳንድ ሰዎች፣ ኢየሱስ የተሰቀለው ሁለት እንጨቶችን በማነባበር በሚሠራው መስቀል ላይ ነው የሚለውን ሐሳብ ማስፋፋት የጀመሩት ኢየሱስ ከሞተ ከ300 ዓመታት ገደማ በኋላ ነው። ሆኖም ይህ ዓይነቱ አመለካከት የመጣው ስታውሮስ ለሚለው የግሪክኛ ቃል የተሳሳተ ትርጉም ስለተሰጠውና የሕዝቡን ባሕል መሠረት በማድረግ ነው። አንዳንድ ጥንታዊ ሥዕሎች እንደሚያመለክቱት ሮማውያን የሞት ቅጣት ሲያስፈጽሙ የሚጠቀሙበት መሣሪያ ወጥ የሆነ አንድ ምሰሶ ወይም ዛፍ መሆኑ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።

“ራሳችሁን ከጣዖቶች ጠብቁ”

እውነተኛ ክርስቲያኖችን ይበልጥ ሊያሳስባቸው የሚገባው ኢየሱስ የተገደለበትን መሣሪያ ማምለክ ተገቢ ነው ወይስ አይደለም የሚለው ጉዳይ ነው። ይህ መሣሪያ ቀጥ ያለ የመከራ እንጨት፣ መስቀል፣ ቀስት፣ ጦር አሊያም ጩቤ ቢሆን ሊመለክ ይገባዋል?

አንድ የምትወደው ሰው በጭካኔ ተገደለብህ እንበል። ከዚያም የተገደለበት መሣሪያ ለመረጃነት እንዲያገለግል ፍርድ ቤት ተወሰደ። ይህን መሣሪያ የግልህ ለማድረግ፣ ፎቶግራፍ ለማንሳትና ብዙ ኮፒዎች አዘጋጅተህ ለሰዎች ለማሰራጨት ጥረት ታደርጋለህ? ከመሣሪያው ጋር ተመሳሳይ የሆኑ ሌሎች መሣሪያዎችንስ በተለያየ መጠን ታዘጋጃለህ? አንዳንዶቹን ጌጣጌጥ አድርገህ ትሠራቸዋለህ? ወይም እነዚህን ተመሳሳይ መሣሪያዎች በፋብሪካ አሠርተህ ጓደኞችህና ዘመዶችህ ለአምልኮ እንዲጠቀሙባቸው ትሸጥላቸዋለህ? እንዲህ ዓይነቱ ሐሳብ እንኳ ሳይቀፍህ አይቀርም! ይሁንና ከመስቀል ጋር በተያያዘ እየተደረገ ያለው ነገር ይኸው ነው!

ከዚህም በላይ መስቀልን ለአምልኮ መጠቀም ምስሎችን ለአምልኮ ከመጠቀም የተለየ አይደለም፤ መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ ይህንን ድርጊት ያወግዘዋል። (ዘፀአት 20:2-5፤ ዘዳግም 4:25, 26) ሐዋርያው ዮሐንስ የእምነት ባልንጀሮቹን “ራሳችሁን ከጣዖቶች ጠብቁ” በማለት አጥብቆ በመከራቸው ጊዜ የእውነተኛውን ክርስትና ትምህርት በትክክል አስፍሮታል። (1 ዮሐንስ 5:21) እነዚያ ክርስቲያኖች በሮማውያን የትግል መወዳደሪያ ሜዳ ውስጥ ሞት የሚጠብቃቸው ቢሆንም እንኳ ይህን ምክር ሠርተውበታል።

ያም ሆኖ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ለክርስቶስ መሥዋዕታዊ ሞት ከፍተኛ አክብሮት ነበራቸው። ዛሬም በተመሳሳይ እውነተኛ ክርስቲያኖች ኢየሱስ የተሰቃየበትንና የተገደለበትን መሣሪያ ባያመልኩትም እንኳ አምላክ ፍጹማን ላልሆኑ ሰዎች የመዳን ዝግጅት ያደረገበትን የክርስቶስን ሞት መታሰቢያ ያከብራሉ። (ማቴዎስ 20:28) ወደር የማይገኝለት ይህ የአምላክ ፍቅር መግለጫ እውነት ወዳድ ለሆኑ ሰዎች የዘላለም ሕይወትን ተስፋ ጨምሮ ይህ ነው የማይባል ብዙ በረከት ያስገኝላቸዋል።—ዮሐንስ 17:3፤ ራእይ 21:3, 4

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንዳንድ ጥንታዊ ሥዕሎች እንደሚጠቁሙት ሮማውያን የሞት ቅጣትን ሲያስፈጽሙ የሚጠቀሙበት መሣሪያ ወጥ የሆነ የእንጨት ምሰሶ ነበር

[ምንጭ]

Rare Books Division, The New York Public Library, Astor, Lenox and Tilden Foundations