በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በደም የተጻፈ ታሪክ

በደም የተጻፈ ታሪክ

በደም የተጻፈ ታሪክ

ከጥቂት ዓመታት በፊት ሽብርተኝነት በሰሜን አየርላንድ፣ ሰሜን ስፔን በሚገኘው ባስክ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ በሚገኙ አንዳንድ ስፍራዎችና በመሳሰሉት የተወሰኑ አካባቢዎች ብቻ ያለ ችግር ይመስል ነበር። በአሁኑ ጊዜ በተለይ ደግሞ በኒው ዮርክ የሚገኙት መንትዮቹ ሕንጻዎች ከወደሙበት ከመስከረም 11, 2001 ወዲህ ችግሩ በዓለም ዙሪያ በጣም እየተስፋፋ ነው። ገነት በምትመስለው ባሊ የተባለች ደሴት፣ በስፔን ዋና ከተማ በማድሪድ፣ በእንግሊዝ ዋና ከተማ በለንደን፣ በስሪ ላንካና በታይላንድ አልፎ ተርፎም በኔፓል የአሸባሪዎች ጥቃት ደርሷል። የሆነ ሆኖ ሽብርተኝነት አዲስ የተፈጠረ ነገር አይደለም። “ሽብርተኝነት” ሲባል ምን ማለት ነው?

ሽብርተኝነት “ኃይልን በሕገወጥ መንገድ ወይም ሌሎችን ለማስፈራራት መጠቀም አሊያም አንድ ግለሰብ ወይም የተደራጀ ቡድን ካለው አስተሳሰብና የፖለቲካ አቋም ጋር በተያያዘ ሕብረተሰቡን ወይም መንግሥትን ለማስፈራራት ወይም አንድ ነገር እንዲደረግለት ለማስገደድ ሲል በሰዎችና በንብረት ላይ የሚፈጽመው ጥቃት” የሚል ፍቺ ተሰጥቶታል። (ዚ አሜሪካን ሄሪቴጅ ዲክሽነሪ ኦቭ ዚ ኢንግሊሽ ላንጉዊጅ) ጄሲካ ስተርን የተባሉ ደራሲ ግን እንዲህ ብለዋል:- “ስለ ሽብርተኝነት የሚያጠና ተማሪ ለቃሉ ብዙ ትርጉሞች ያጋጥሙታል . . . ሆኖም ሽብርተኝነትን ከሌሎች የዓመጽ ድርጊቶች የሚለዩት ሁለት ዋነኛ ባሕርያት ናቸው።” እነዚህ ገጽታዎች ምንድን ናቸው? “አንደኛው፣ ሽብርተኝነት የሚያነጣጥረው በሰላማዊ ሰዎች ላይ መሆኑ ነው። . . . ሁለተኛው ደግሞ ሽብርተኞች ዓመጽ የሚፈጽሙት ዒላማዎቻቸውን ለማስደንገጥ ሲሆን ብዙውን ጊዜ የሚፈጠረው ፍርሃት ከሚደርሰው አካላዊ ጉዳት ይልቅ ተፈላጊ ነው። በዚህ መንገድ ሆን ብሎ በሰዎች ላይ ስጋት መፍጠር ሽብርተኝነትን ከተራ ግድያ ወይም ጥቃት የተለየ ያደርገዋል።”

ሽብርተኝነት ጥንትም ነበር

በመጀመሪያው መቶ ዘመን በይሁዳ ምድር የነበረ ዜሎትስ የሚባል የዓማጺያን ቡድን አይሁዳውያንን ከሮማውያን አገዛዝ ነጻ ለማውጣት ይፈልግ ነበር። ከዚህ ቡድን አክራሪ ደጋፊዎች መካከል አንዳንዶቹ ሲካሪ ወይም ባለ ጩቤዎች ይባሉ ጀመር፤ ይህ ስያሜ የተሰጣቸው ልብሳቸው ውስጥ ሸሽገው ይይዙት በነበረው አጭር ጎራዴ ምክንያት ነው። ሲካሪ የሚባሉት ሰዎች በዓል ለማክበር በኢየሩሳሌም ከተሰበሰቡ ሰዎች ጋር ይቀላቀሉና የጠላቶቻቸውን ጉሮሮ ይቆርጡ ወይም ከኋላቸው በጩቤ ይወጉ ነበር። *

በ66 ከክርስቶስ ልደት በኋላ የተወሰኑ የዜሎትስ ቡድን አባላት በሙት ባሕር አቅራቢያ የሚገኘውን የማሳዳ ምሽግ ያዙ። ሮማውያን ወታደሮችን ፈጅተው በተራራው ጫፍ ላይ የሚገኘውን ምሽግ የእንቅስቃሴያቸው ማእከል አደረጉ። እነዚህ ሰዎች ለዓመታት ከዚህ ቦታ እየተነሱ ወረራ ያካሂዱና ሮማውያን ገዢዎችን ያስጨንቁ ነበር። በ73 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በገዢው ፍላቪየስ ሲልቫ የሚመራው አሥረኛ የሮም ክፍለ ጦር ማሳዳን በድጋሚ ተቆጣጠረ፤ ነገር ግን የዜሎትስ ዓማጺያንን ድል አላደረጋቸውም። በወቅቱ የነበረ ታሪክ ጸሐፊ እንደተናገረው 960 የሚያህሉ ዓማጺያን ለሮማውያን እጅ ላለመስጠት ሲሉ ራሳቸውን ገድለዋል፤ በሕይወት የተረፉት ሁለት ሴቶችና አምስት ልጆች ብቻ ናቸው።

አንዳንዶች፣ ዛሬ ሽብርተኝነት የምንለው ሁኔታ የጀመረው ዜሎትስ በሚባሉት ዓማጺያን እንደሆነ ያምናሉ። ይህ እውነትም ይሁን ሐሰት ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሽብርተኝነት በታሪክ ሂደት ላይ የማይጠፋ አሻራ ጥሎ አልፏል።

ሽብርተኝነትና ሕዝበ ክርስትና

የመስቀል ጦርነት ተዋጊዎች ከ1095 ጀምሮ ለሁለት መቶ ዓመታት ከአውሮፓ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ በተደጋጋሚ ጉዞ አድርገዋል። የሚዋጉት ከእስያና ከሰሜን አፍሪካ ከመጡ የሙስሊም ኃይሎች ጋር ነበር። ጦርነት እንዲገጥሙ ያደረጋቸው የኢየሩሳሌም ጉዳይ ሲሆን ሁለቱም ኃይሎች ከተማዋን በቁጥጥር ሥር ማዋል ይፈልጉ ነበር። እነዚህ “ቅዱስ ተዋጊዎች” ባደረጓቸው በርካታ ጦርነቶች እርስ በርስ ተጨፋጭፈዋል። እንዲሁም ሰይፋቸውንና መጥረቢያቸውን ሰላማዊ ሰዎችን ለመጨፍጨፍ ተጠቅመውባቸዋል። በ12ኛው መቶ ዘመን ቄስ የነበሩት የጢሮሱ ዊልያም የመስቀል ጦረኞች በ1099 ወደ ኢየሩሳሌም ሲገቡ ሁኔታው ምን ይመስል እንደነበር እንዲህ ብለው ገልጸዋል:-

“ሰይፍና ጦር ይዘው በሕብረት በጎዳናዎች ላይ ይጓዙ ነበር። ወንድ፣ ሴት፣ ሕፃናት ሳይሉ ያገኙትን ሰው ሁሉ ወዲያውኑ ይመቱና ይገድሉ ነበር። . . . በየመንገዱ ብዙ ሰዎችን በመግደላቸው ምክንያት አስከሬን ተከምሮ ነበር፤ አንድ ሰው በመንገድ መሄድ ቢፈልግ በሬሳ ላይ ተረማምዶ ካልሆነ በስተቀር መተላለፊያ አልነበረም። . . . ቦዮች ሁሉ በደም ተሞልተውና የከተማዋ መንገዶች በጠቅላላ በሰዎች በድን ተሸፍነው ነበር።” *

ከዚያ በኋላ ባሉት መቶ ዘመናት ሽብርተኞች አሰቃቂ አደጋና ሞት የሚያስከትሉ ፈንጂዎችንና ሌሎች መሣሪያዎችን መጠቀም ጀመሩ።

በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሞተዋል

ታሪክ ተመራማሪዎች ሰኔ 28, 1914 በአውሮፓ ታሪክ ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጣ ዕለት እንደሆነ ይሰማቸዋል። በአንዳንዶች ዘንድ እንደ ጀግና የሚታይ አንድ ወጣት የኦስትሪያውን ልዑል አርክዱክ ፍራንሲስ ፈርዲናንድን ተኩሶ ገደለ። ይህ ክስተት የሰው ዘር ወደ አንደኛው የዓለም ጦርነት ውስጥ እንዲገባ ምክንያት ሆነ። ታላቁ ጦርነት ሲያበቃ ሃያ ሚሊዮን ሰዎች አልቀው ነበር።

አንደኛውን የዓለም ጦርነት ተከትሎ ደግሞ ማጎሪያ ካምፖች የተከፈቱበት፣ ከአየር ላይ በሚፈጸም የቦምብ ድብደባ ሰላማዊ ሰዎች ያለቁበትና በንጹሐን ሰዎች ላይ ብቀላ የተፈጸመበት ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ተደረገ። ከጦርነቱ በኋላም ቢሆን ግድያዎች መፈጸማቸውን ቀጥለዋል። በ1970ዎቹ ዓመታት በካምቦዲያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በጅምላ ተጨፍጭፈዋል። ሩዋንዳውያንም በ1990 የደረሰው የ800,000 ሰዎች እልቂት እስከ አሁን ይሰቀጥጣቸዋል።

በተለያዩ አገሮች የሚገኙ ሰዎች ከ1914 ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ በሽብር ድርጊቶች እየተሰቃዩ ናቸው። ይሁንና አንዳንዶች ከታሪክ ምንም ትምህርት ያላገኙ የሚያስመስልባቸውን ድርጊት ይፈጽማሉ። ሽብርተኞች ጥቃት በመፈጸም በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን መግደላቸው፣ በሺዎች የሚቆጠሩትን የአካል ጉዳተኛ ማድረጋቸው እንዲሁም የሚሊዮኖችን የአእምሮ ሰላምና ደህንነት መንሳታቸው የዕለት ተዕለት ክስተት ሆኗል። በገበያ ቦታዎች ቦምቦች ይፈነዳሉ፣ መንደሮች አመድ እስኪሆኑ ድረስ ይቃጠላሉ፣ ሴቶች ይደፈራሉ፣ ልጆች ታፍነው ይወሰዳሉ፣ ሰዎች ይሞታሉ። ሕግ ቢኖርም እንዲሁም ዓለም አቀፍ ውግዘት ቢደረግም ይህ የተለመደ የጭካኔ ድርጊት አልቆመም። ሽብርተኝነት ይወገዳል እንድንል የሚያስችለን ተስፋ አለ?

^ አን.5 በሐዋርያት ሥራ 21:38 [NW] ላይ ተመዝግቦ እንደሚገኘው፣ ሮማዊው የጦር አዛዥ ሐዋርያው ጳውሎስን የ4,000 “ባለ ጩቤዎች” መሪ እንደሆነ በመግለጽ ያለ አግባብ ወንጅሎታል።

^ አን.10 ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ‘ጠላቶቻቸውን እንዲወዱ’ እንጂ እንዲጠሏቸውና እንዲገድሏቸው አላስተማረም።—ማቴዎስ 5:43-45

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ሰኔ 28, 1914 ዓለም ጦርነት ውስጥ ገባች

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢስታንቡል ኅዳር 15, 2003

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ማድሪድ መጋቢት 11, 2004

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለንደን ሐምሌ 7, 2005

[በገጽ  4, 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኒው ዮርክ መስከረም 11, 2001

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ከግራ ወደ ቀኝ:- AP Photo/Murad Sezer; AP Photo/ Paul White; Photo by Peter Macdiarmid/Getty Images

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Culver Pictures