በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ማስጠንቀቂያ መስማት ሕይወትን ያድናል

ማስጠንቀቂያ መስማት ሕይወትን ያድናል

ማስጠንቀቂያ መስማት ሕይወትን ያድናል

ረቡዕ፣ ነሐሴ 24, 2005 በዩናይትድ ስቴትስ፣ ሉዊዚያና ግዛት በምትገኘው በኒው ኦርሊየንስ ቀኑ በጣም ሞቃት ከመሆኑም በላይ ይወብቅ ነበር። አለንና ቤተሰቡ ኒው ኦርሊየንስ ከሚገኘው ቤታቸው በስተ ምዕራብ 300 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ቴክሳስ ውስጥ ባለችው በቦማውት ጥቂት ቀናት ለማሳለፍ ሄደው ነበር። ቤተሰቡ ለአምስት ቀናት የሚበቃውን ልብስ ይዟል። አለን እንዲህ ይላል:- “በዚያን ጊዜ ከፍሎሪዳ በስተ ምሥራቅ በኩል ኃይለኛ አውሎ ነፋስ እየተነሳ መሆኑን አላወቅንም ነበር። ዓርብ ዕለት ማታ ግን ኒው ኦርሊየንስ በኃይለኛ አውሎ ነፋስ እንደምትመታ ታወቀ።”

ነሐሴ 28 እሁድ ዕለት ካትሪና የተባለችው አውሎ ነፋስ በከፍተኛ ኃይል እየገሰገሰች እንደሆነ ተረጋገጠ። የኒው ኦርሊየንስ ከንቲባ ሕዝቡ ከተማውን በግዴታ ለቅቆ እንዲወጣ ትእዛዝ ሰጡ። በመሆኑም በሺዎች የሚቆጠሩ ተሽከርካሪዎች ወደ ሰሜንና ወደ ምዕራብ በመንቀሳቀሳቸው አውራ ጎዳናዎቹ ተጨናነቁ። መኪና የሌላቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ መጠለያ ቦታዎች ወይም ሱፐርዶም ተብሎ ወደሚጠራው ትልቅ ስታዲየም ሸሹ። አንዳንዶች ደግሞ ከተማውን ሳይለቁ አውሎ ነፋሱ እስኪያልፍ ድረስ በቤታቸው ለመቆየት ወሰኑ።

‘በሚቀጥለው ጊዜ ውጡ ሲባል መጀመሪያ የምወጣው እኔ እሆናለሁ!’

በቤታቸው ከቀሩት መካከል ጆ የተባለ የይሖዋ ምሥክር ይገኝበታል። በቤቱ ተጠልሎ ከአውሎ ነፋሱ መዳን እንደሚችል ተሰምቶት ነበር። ከዚያ በፊት የተከሰቱት አውሎ ነፋሶች ያደረሱት ጉዳት ባለ ሥልጣናቱ የፈሩትን ያህል ከባድ እንዳልነበረ በማስታወስ፣ ከዚህኛውም “እተርፋለሁ ብዬ አሰብኩ” በማለት ተናግሯል። “ይሁንና መሳሳቴ ወዲያው ገባኝ! ነፋሱና ዝናቡ በኃይል እያስገመገመ መጣ። በቅጽበት የቤቴ ጣራ ተገንጥሎ ሄደ። ከዚያም ውኃው በሚያስደነግጥ ፍጥነት ከፍታውን በመጨመር በሦስት ሰዓት ውስጥ 3 ሜትር ከፍታ ላይ ደረሰ! ውኃው በፍጥነት እየሞላ ስለነበር ወደ ሁለተኛው ፎቅ ለመውጣት ተገደድኩ። ነፋሱ በኃይል ሲያፏጭ ግድግዳውን የሚደረምሰው ይመስል ስለነበር በጣም ፈራሁ። ኮርኒሱ መፈራረስ ጀመረ። በዚህ ጊዜ እንዴት እንደምተርፍ እያሰብኩ ነበር።

“ዘልዬ በማዕበል በሚናወጠው ውኃ ውስጥ ልገባ አሰብኩ። ነገር ግን ውጪ ኃይለኛ ሞገድ ነበረ። ነፋሱ ውኃውን እያነሳ በአቅራቢያዬ ካለው መንገድ ጋር ሲያላትመው አረፋ ይፈጥር ነበር። ዘልዬ ውኃው ውስጥ ብገባ ልሰጥም እንደምችል ገባኝ።”

በመጨረሻም ጆ አንድ ጀልባ ደረሰለትና በአካባቢው ወደነበረ ድልድይ ወሰደው። ከድልድዩ ሥር ባለው ውኃ ላይ አስከሬኖች ይንሳፈፉ ነበር፤ ዓይነ ምድር በየቦታው ይታያል። ጆ የዚያን ዕለት በአንድ መኪና ኮፈን ላይ ተኝቶ አደረ። በኋላም በሄሊኮፕተርና በአውቶቡስ ተጉዞ በኒው ኦርሊየንስ ወደሚገኝ የሕዝብ ማዕከል ተወሰደ። ጆ “እዚያ የነበሩት ሰዎች በጥሩ ሁኔታ ተንከባከቡኝ” በማለት ይናገራል። “አንድ ወቅት ላይ ሁሉ ነገር ግራ ገብቶኝ እቀባጥር ነበር። ከመጠን በላይ ያሳሰበኝ ነገር ‘ከአሁን በኋላ የምጠጣው ውኃ የት አገኛለሁ?’ የሚለው ነበር።”

ጆ የደረሰበትን ሁሉ መለስ ብሎ ሲያስበው ይህን ሁሉ ችግር ሊያስወግደው ይችል እንደነበር ተገንዝቧል። “መከራ መክሮኛል” ይላል። “በሚቀጥለው ጊዜ ‘ከተማዋን ለቃችሁ ውጡ’ ሲባል መጀመሪያ የምወጣው እኔ እሆናለሁ!”

ማስጠንቀቂያ ባለመስማቷ ዛፍ ላይ ለመውጣት ተገደደች

በሚሲሲፒ ባሕር ዳርቻ ያሉት የበለክሲ እና ገልፍፖርት ከተሞች ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን የብዙዎች ሕይወትም ጠፍቷል። ነሐሴ 31, 2005 የወጣው ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ እንደገለጸው ከሆነ ቪንሰንት ክሪል የተባሉት የበለክሲ ከተማ የሕዝብ ግንኙነት ቢሮ ሥራ አስኪያጅ “ብዙ ሰዎች ከተማዋን ለቀው እንዲወጡ የተሰጣቸውን ማስጠንቀቂያ ችላ ያሉት [በ1969 ከተከሰተችው] ከሚል የሚል ስያሜ ከተሰጣት አውሎ ነፋስ ሕይወታቸውም ሆነ ቤታቸው በመትረፉ ነው” ብለዋል። ከሚል የተባለችው አውሎ ነፋስ ከካትሪና የበለጠ ኃይለኛ እንደሆነች ታስቦ የነበረ ቢሆንም ካትሪና “ከፍታው ከሱናሚ ጋር ሊወዳደር የሚችል ኃይለኛ ማዕበል አስነስታለች” በማለት ክሪል ተናግረዋል።

ማስጠንቀቂያውን ላለመስማት የመረጠችው ሌላዋ የአካባቢው ነዋሪ ደግሞ አብዛኛውን ሕይወቷን በበለክሲ ያሳለፈችው ኤኔል ነበረች። እሷም እንዲህ ትላለች:- “ባለፉት ዓመታት ከተማችንን ከመቱት አውሎ ነፋሶች ተርፈናል። በመሆኑም ስለ ካትሪና ከወትሮው የተለየ አልተጨነቅሁም።” ኤኔል ሁለት ውሾቿንና ሦስት ድመቶቿን ጨምሮ የ88 ዓመት አረጋዊት አማቷን፣ ወንድ ልጅዋን፣ ሴት ልጅዋንና የሴት ልጅዋን ባል ከሰበሰበች በኋላ ማዕበል መቋቋም በሚያስችል ሁኔታ የተሠራውን ቤታቸውን ለቀው ላለመውጣት ወሰኑ። ነሐሴ 29 ከረፋዱ 4 ሰዓት ላይ አውሎ ነፋሱ በለክሲን መታት። ኤኔል እንደሚከተለው በማለት ታስታውሳለች:- “ከኋላ በኩል ወዳለው አንደኛው መኝታ ቤት ውኃ ሰርጎ እየገባ መሆኑን አስተዋልኩ። ከዚያም ውኃው ቤቱን በሙሉ ማጥለቅለቅ ጀመረ። ከውኃው ለመሸሽ ጣራው ላይ ወዳለችው ትንሽ ክፍል ለመውጣት ወሰንን። ይሁን እንጂ ውኃው እዚያም ድረስ መጣ። እዚህ ክፍል ውስጥ ሆነን መውጫ እንዳናጣ ስለፈራን መውጣት ነበረብን። ግን ከዚያ ወጥተን ወዴት እንሄዳለን?

“ካለንበት ቦታ ዋኝተን ውጭ ወዳለው ውኃ መውጣት እንድንችል ወንዱ ልጄ የነፍሳት መከላከያውን ወንፊት ቀድዶ መሹለኪያ አበጀ። ከዚያም የጣራውን ጠርዝ አጥብቀን በመያዝ ተንሳፈን ቆየን። ከቤተሰባችን መካከል ሦስታችን ከቤቱ በስተ ቀኝ በኩል ስንሆን ሴቷ ልጄ ደግሞ ከቤታችን በስተግራ በኩል ነበረች። በዚህ ጊዜ በአቅራቢያችን አንድ ትልቅ ዛፍ መኖሩን አስተዋልኩ። ወንዱ ልጄ፣ አማቴና እኔ ወደ ዛፉ ዋኝተን በመሄድ ጨምድደን ያዝነው። ከዚያም ሴቷ ልጄ “እማማ! እማማ!” ብላ ስትጮህ ሰማሁ። ከጣራው ሥር ከሁላችንም በኋላ የወጣው ባሏ ሊያድናት እየዋኘ ወደ እሷ ሄደ። ከዚያም ሁለቱ፣ ከዋናው መንገድ ወደ ቤታችን በሚወስደው መንገድ ላይ ቆማ የነበረችና በቤቱ አቅራቢያ የምትንሳፈፍ ጀልባ ውስጥ መግባት ቻሉ። እኔም ጀልባው ላይ እንድሳፈር ይወተውቱኝ ጀመር። አዙሪት ፈጥሮ የሚሽከረከረውን ውኃ ሳይ ወደ ጀልባው መሄድ ፈራሁ። በዛፉ ላይ ተንጠላጥዬ መቆየቱ የተሻለ እንደሆነ ስለተሰማኝ ከዚያ ለመነቃነቅ አልፈለግሁም።

“ዛፉ ላይ ሆኜ ውኃው በመንገዱ ላይና በቤቱ ዙሪያ ሲፈስ ይታየኝ ነበር። ስላለሁበት ሁኔታ ማሰብ ስጀምር፣ ከተማዋን ለቀን እንድንወጣ የተሰጠውን ማስጠንቀቂያ ባለመስማቴ እንደተሞኘሁ ተሰማኝ።

“በመጨረሻም ውኃው መጉደል በመጀመሩ ሁላችንም ጀልባው ውስጥ መግባት ቻልን! የእሳት አደጋ መከላከያ መኪና ደረሰልንና ሁላችንንም ወደ ሆስፒታል ወሰደን። በሕይወት በመትረፋችን ምስጋናችን ወሰን አልነበረውም!”

የይሖዋ ምሥክሮችን ከአደጋው ቀጣና ለማውጣት የተነደፈ ዕቅድ

ካትሪና በሜክሲኮ ባሕረ ሰላጤ ጠረፍ አካባቢ በሚገኙት የዩናይትድ ስቴትስ ግዛቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰች ሲሆን ከሉዊዚያና ጀምሮ በስተ ምሥራቅ እስከ አላባማ ድረስ በሺህ የሚቆጠሩ ቤቶች ወድመዋል። ይሁን እንጂ አውሎ ነፋስ በዚያ አካባቢ ለሚገኘው የዩናይትድ ስቴትስ ክፍል አዲስ ነገር አይደለም። በመሆኑም የይሖዋ ምሥክሮች አካባቢውን ለቅቆ ለመውጣት የሚያስችል ዕቅድ ከነደፉ በርካታ ዓመታት አልፈዋል። በየዓመቱ የአውሎ ነፋሱ ወቅት ከመጀመሩ አስቀድሞ (አብዛኛውን ጊዜ በሰኔ ወር ላይ) በኒው ኦርሊየንስ አካባቢ የሚገኙት 21 የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች በአደጋ ጊዜ አካባቢውን ለቅቆ ለመውጣት የሚረዳውን ዕቅድ ይከልሳሉ። በመሆኑም በዚያ አካባቢ የሚኖሩት አብዛኞቹ የይሖዋ ምሥክሮች አደጋ ቢፈጠር ምን እርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው ያውቁ ነበር። በካትሪና አውሎ ነፋስ ወቅት ዕቅዱ በሥራ ላይ የዋለው እንዴት ነበር?

የከተማው ባለ ሥልጣናት ሕዝቡ አካባቢውን ለቅቆ እንዲወጣ ማስጠንቀቂያ እንደሰጡ በየጉባኤው ያሉት ሽማግሌዎች የጉባኤያቸውን አባላት በማግኘት ከተማዋን ለቅቀው እንዲወጡ አበረታቷቸው። ብዙዎቹ ከቤተሰባቸው ወይም ከወዳጆቻቸው ጋር በመሆን አካባቢውን ለቀው ለመውጣት የራሳቸውን ዝግጅት አድርገው ነበር። ለአረጋውያንና ለአቅመ ደካሞች ልዩ የሆነ መጓጓዣ ከመዘጋጀቱም በላይ ድጋፍ ተደረገላቸው። በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀው የአደጋ ጊዜ እርዳታ ኮሚቴ አባል የሆነው ጆን “ይህን ዕቅድ ተግባራዊ በማድረግ የብዙ ሰዎችን ሕይወት እንዳተረፍን አምናለሁ” ብሏል። በመሆኑም አብዛኞቹ የይሖዋ ምሥክሮች አውሎ ነፋሱ ከተማዋን ከመምታቱ በፊት መውጣት ችለዋል። በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ በአውሎ ነፋሱ ለተጠቁት አካባቢዎች መሠረታዊ የሆነ እርዳታ ለመስጠት የአስቸኳይ ጊዜ የእርዳታ ኮሚቴዎችን አቋቋመ።

በአስትሮዶም ስታዲየም የይሖዋ ምሥክሮችን መፈለግ

አብዛኞቹ ከሉዊዚያና የመጡ 16,000 ተፈናቃዮች በሂዩስተን፣ ቴክሳስ ወደሚገኘው የአስትሮዶም ስታዲየም ተወስደው ምግብ፣ ውኃና መጠለያ እንዲያገኙ ተደርገው ነበር። በሂዩስተን የነበረው የይሖዋ ምሥክሮች የእርዳታ ኮሚቴ ጥቂት የይሖዋ ምሥክሮች በአስትሮዶም እንደሚገኙ ተገነዘበ። ከዚህ ሁሉ ሕዝብ መሃል እንዴት ፈልገው ያገኟቸው ይሆን?

መስከረም 2 ቀን፣ ዓርብ ዕለት ገና በማለዳው የተወሰኑ የይሖዋ ምሥክሮች ሽማግሌዎች የተፈናቀሉ ወንድሞቻቸውን ለመፈለግ ወደ አስትሮዶም መጡ። እዚያ እንደደረሱም በሺህ የሚቆጠሩ ወንዶች፣ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ ልጆችና ሕፃናት በተንጣለለው ስታዲየም ውስጥ ተኮልኩለው ሲያዩ በጣም ተገረሙ። የእግር ኳስ ሜዳው በሸራ አልጋዎች እንዲሁም ለችግሮቻቸው መፍትሔ ለማግኘት በትዕግሥት በመጠባበቅ ላይ ባሉ ተፈናቃዮች ተሞልቶ ነበር። ሕክምና ለማግኘት የተሰለፉ ብዙ ሰዎች የነበሩ ሲሆን የሕክምና ሠራተኞችም ሕመምተኞችን ወደ አምቡላንሶች ለመውሰድ ይሯሯጣሉ።

የተፈናቀሉ ወንድሞችን ፍለጋ ከሄዱት ሽማግሌዎች አንዱ የሆነው ሳሙኤል “በስደተኞች መጠለያ ካምፕ ውስጥ እንዳለሁ ሆኖ ተሰምቶኝ ነበር” ብሏል። ታዲያ ከዚህ ሁሉ ሕዝብ መሃል ጥቂት የይሖዋ ምሥክሮችን እንዴት ፈልገው ሊያገኙ ነው? ሽማግሌዎቹ፣ ተፈናቃዮቹ ወንድሞች ወደ እነርሱ እንዲመጡ የሚጋብዝ መልእክት የተጻፈባቸው ትላልቅ የማስታወቂያ ሰሌዳዎች ይዘው በመተላለፊያዎቹ ላይ ወዲያ ወዲህ መዘዋወር ጀመሩ። በዚህ ሁኔታ ለሦስት ሰዓታት ያህል ወንድሞችን ለመፈለግ ያደረጉት ጥረት ምንም ውጤት ባለማስገኘቱ የተሻለ ብልሃት መቀየስ እንዳለባቸው ተገነዘቡ። በስታዲየሙ ውስጥ ወዳለው የቀይ መስቀል ማኅበር ቀረቡና በድምፅ መሣሪያው በመጠቀም “የተጠመቃችሁ የይሖዋ ምሥክሮች ሁሉ በስታዲየሙ ምድር ቤት በስተ ምሥራቅ በኩል ወደሚገኘው በር እንድትሄዱ ትጠየቃላችሁ” የሚል ማስታወቂያ እንዲነገርላቸው ጠየቁ።

በመጨረሻም የይሖዋ ምሥክሮቹ ፊታቸው ላይ ደማቅ ፈገግታ እየተነበበ ቀስ በቀስ መምጣት ጀመሩ። ሳሙኤል እንደሚከተለው በማለት ያብራራል:- “ዓይናቸው እንባ አቅርሮና በደስታ ተሞልተው ነበር። እንቅ አድርገው ካቀፉን በኋላ እጆቻችንን ያዙን። በሕዝቡ መሃል እንዳንጠፋፋ ስለፈሩ እጃችንን ሙጭጭ አድርገው ይዘውን ነበር።” ዓርብና ቅዳሜ በተካሄደው ፍለጋ 24 የይሖዋ ምሥክሮች ተገኙና የይሖዋ ምሥክሮች ወዳዘጋጁት የእርዳታ ማዕከል ተወሰዱ።

አብዛኞቹ ከለበሷቸው የቆሸሹ ልብሶች በስተቀር ምንም ሌላ ንብረት አልያዙም ለማለት ይቻላል። አንዲት የይሖዋ ምሥክር የጫማ ካርቶን የሚያህል አንድ አነስተኛ ሣጥን ይዛ ነበር። በዚያ ውስጥ አንዳንድ ጠቃሚ ሰነዶች ያስቀመጠች ሲሆን ከአውዳሚው ማዕበል ማትረፍ የቻለችው ያንን ብቻ ነበር።

በአስትሮዶም ስታዲየም የተፈናቀሉትን የይሖዋ ምሥክሮች ለመፈለግ የሄዱት ሽማግሌዎች የይሖዋ ምሥክሮች አገልጋዮች መሆናቸውን የተገነዘቡ ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች እንዲሰጧቸው ጥያቄ አቀረቡ። በአጠቃላይ 220 መጽሐፍ ቅዱስ ተጠየቀ። የይሖዋ ምሥክሮች ለወቅቱ ተስማሚ የነበረውን “የተፈጥሮ አደጋዎች—እየተባባሱ ነው?” (እንግሊዝኛ) የሚል ርዕስ ያለውን የሐምሌ 22, 2005 ንቁ! እትም ለሕዝቡ አበረከቱ።

አንዳንዶች ወደ ቤታቸው ተመለሱ

ከአውሎ ነፋሱ ከተረፉት ሰዎች አንዱ የረዥም ጊዜ ልምድ ያለው የዜና ዘጋቢና የኒው ኦርሊየንስ ቴሌቪዥን ጣቢያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ነበረ። በጋዜጠኝነት ሙያው ከዚያ ቀደም ብዙ ጥፋት ሲደርስ ተመልክቷል። ከአውሎ ነፋሱ የተረፉ አንዳንድ ንብረቶች ባገኝ ብሎ በጄፈርሰን፣ ሉዊዚያና ወደሚገኘው ቤቱ ተመልሶ ሄደ። ሁኔታውን ካየ በኋላ እንዲህ አለ:- “በጣም ደነገጥኩ። የደረሰው ጥፋት ከፍተኛና አውዳሚ ነበር። ጎርፉ ለመከላከያ የተሰሩትን ግድቦች ሲያፈራርሳቸውና ውኃ አካባቢውን ሲያጥለቀልቀው በቴሌቪዥን አይተን ነበር። ሆኖም ኃይለኛ የነበረው አውሎ ነፋስም ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል። የምኖርበት ሕንፃ ሙሉ በሙሉ ወድሟል። እንዲሁም ሻጋታና ብስባሽ ሞልቶታል። አካባቢው ምን ያህል እንደሚገማ ለማመን ያስቸግራል። በጣም ያስጠላል። ደግነቱ ሁላችንም በሕይወት ተርፈናል።”

መግቢያው ላይ የጠቀስነው አለንም ውሎ አድሮ በኒው ኦርሊየንስ ከተማ ምዕራባዊ ዳርቻ ሜተሪ በሚባለው ሥፍራ ወዳለው ቤቱ ተመለሰ። አውሎ ነፋሱ ከፍተኛ ውድመት አድርሶ ነበር። “የተመለከትነው ነገር በጣም የሚረብሽና የሚያስደነግጥ ነበር” ብሏል። “ከተማዋ አቶሚክ ቦምብ የወደቀባት ያህል ሆናለች። ስለ ጥፋቱ በሬዲዮ መስማት ወይም በቴሌቪዥን ማየት አንድ ነገር ነው። በቤታችሁ አካባቢ በእግር ወይም በመኪና ስትዘዋወሩ የደረሰውን መጠነ ሰፊ ጉዳትና ውድመት በዓይናችሁ ማየት ግን ከዚያ ፈጽሞ የተለየ ነገር ነው። ሁኔታው ለመቀበል ያስቸግራል።

“ለምሳሌ ያህል፣ የክርፋቱን ነገር ባነሳ አካባቢው የተበላሸ ሥጋ ዓይነት ሽታ ነበረው፤ የበድን ጠረን አየሩን ሞልቶታል። ብዙ የንግድ ቦታዎች ሙሉ በሙሉ ወድመዋል ወይም በጎርፍ ተጥለቅልቀዋል። በየማዕዘኑ ፖሊሶች ወይም ወታደሮች ይታያሉ። አካባቢው የጦርነት ቀጣና መስሏል።”

እርዳታ ለማቅረብ የተደረጉ አንዳንድ ጥረቶች

የከተማው፣ የግዛቱና የፌደራል መንግሥት ባለ ሥልጣናት እርዳታዎችን አደራጁ። በዚህ ረገድ በዋነኝነት እርዳታ ያበረከተው የፌደራሉ የድንገተኛ አደጋ እርዳታ ድርጅት (ፌማ) ነበር። ሌሎች ድርጅቶችም በሺህ ለሚቆጠሩት የአደጋው ተጠቂዎች እርዳታ ለማቅረብ ተንቀሳቅሰዋል። ከፍተኛ መጠን ያለው ምግብ፣ ልብስና ውኃ በማዕበል በተጥለቀለቁት አካባቢዎች ለሚኖሩት ሰዎች በጭነት መኪና ተላከላቸው። ፌማ ከአደጋው በኋላ ለነበሩት የመጀመሪያዎቹ ጥቂት ቀናት ወይም ሳምንታት የሚሆን የባንክ ቼኮችን ለሕዝቡ የሰጠ ከመሆኑም በላይ የገንዘብ እርዳታ አድርጓል። የይሖዋ ምሥክሮችስ እንዴት ሆኑ?

ጉዳቱን መገምገምና እደሳ ማካሄድ

አደጋው እንደደረሰ የይሖዋ ምሥክሮች የግምገማ ቡድኖች አደራጁና በማዕበል ወደ ተመቱ አካባቢዎች ሄደው ምን ያህል የይሖዋ ምሥክሮች ቤቶችና የመንግሥት አዳራሾች ጉዳት እንደደረሰባቸው ወይም ሙሉ በሙሉ እንደወደሙ እንዲያጣሩ አደረጉ። ሆኖም ይህን ታላቅ ሥራ እንዴት ሊወጡት ነው? በብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ የሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል በዩናይትድ ስቴትስ ቅርንጫፍ ኮሚቴ ሥር ሆኖ የሚንቀሳቀስ የእርዳታ ኮሚቴ እንዲቋቋም ፈቃድ ሰጠ። ከዚያም ከብዙ የአሜሪካ ግዛቶች የተውጣጡ የአካባቢ የግንባታ ኮሚቴዎች የፈረሱትን መልሶ የመገንባት ሥራ እንዲጀመር ጥሪ ቀረበላቸው። * እነዚህ ኮሚቴዎች ምን አከናውነዋል?

እስከ የካቲት 17, 2006 ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ በሎንግቢች፣ ሚሲሲፒ የተቋቋመው የእርዳታ ቡድን በአካባቢው ጉዳት ከደረሰባቸው 632 የይሖዋ ምሥክሮች ቤቶች ውስጥ 531 የሚያክሉትን ሙሉ በሙሉ እንዳደሰና እድሳት የሚያስፈልጋቸው 101 ቤቶች እንደሚቀሩ ሪፖርት ተደርጓል። የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ ጎረቤቶችም እርዳታ ተደርጎላቸዋል። አሥራ ሰባት የመንግሥት አዳራሾች በጣሪያቸው ላይ ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን በየካቲት ወር አጋማሽ ለ16ቱ አዲስ ጣሪያ ተሠርቶላቸዋል። በባተን ሩዥ፣ ሉዊዚያና ያለው ኮሚቴስ ምን አከናውኗል?

ይህ ቡድን የሚንቀሳቀሰው የካትሪና ማዕበል ገፈት ቀማሽ በሆነችው የሉዊዚያና አካባቢ ነው። እድሳት ከሚያስፈልጋቸው 2,700 የይሖዋ ምሥክሮች ቤቶች ውስጥ እስከ የካቲት ወር አጋማሽ ድረስ የ1,119 ቤቶች እድሳት ቢጠናቀቅም የእርዳታ ቡድኑ ገና ብዙ ሥራ ይጠብቀዋል። በሌላ አካባቢ እንደሚደረገው ሁሉ እዚህም ለይሖዋ ምሥክሮች ብቻ ሳይሆን ለጎረቤቶቻቸውና በጣም ለተጎዱ ቤተሰቦች እርዳታ ተደርጎላቸዋል። ሃምሳ የመንግሥት አዳራሾች መጠነ ሰፊ ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን እስከ የካቲት ድረስ ከእነዚህ ውስጥ 25ቱ ታድሰዋል። በቴክሳስ ግዛት ያለው የሂዩስተን ቡድን ደግሞ በመስከረም ወር ሪታ በተባለችው አውሎ ነፋስ ጉዳት የደረሰባቸውን 871 ቤቶች መጠገን ያስፈልገው ነበር። እስከ የካቲት 20 ድረስ የ830ዎቹ እድሳት ተጠናቋል።

ከካትሪና የሚገኝ ትምህርት

የካትሪናን ቁጣ የቀመሱ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ለማስጠንቀቂያዎች ትኩረት የመስጠትን አስፈላጊነት ከመከራ ተምረዋል። በእርግጥም ብዙ ሰዎች፣ “በሚቀጥለው ጊዜ ‘ከተማዋን ለቃችሁ ውጡ’ ሲባል መጀመሪያ የምወጣው እኔ እሆናለሁ!” በማለት ከተናገረው ከጆ ጋር ይስማማሉ።

የይሖዋ ምሥክሮች በባሕረ ሰላጤው አካባቢ ላሉት የአደጋው ተጠቂዎች እርዳታ መስጠታቸውን ቀጥለዋል። (ገላትያ 6:10) ሆኖም አገልግሎታቸው ሰብዓዊ እርዳታ መስጠት ብቻ አይደለም። ከዚህ በተቃራኒ የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም ዙሪያ በ235 አገሮች እያከናወኑት ያለው ተቀዳሚ ሥራ አውሎ ነፋስ እየመጣ መሆኑን ከማስጠንቀቅ የበለጠ ትርጉም ያለው ማስጠንቀቂያ ማሰማት ነው። አምላክ በቅርቡ ከእርሱ የራቀውን ይህን ሥርዓት እንደሚያጠፋው እንዲሁም ምድራችንን በማጽዳት መጀመሪያ ሲፈጥራት አስቦት ወደነበረው ሁኔታ እንደሚመልሳት መጽሐፍ ቅዱስ ይተነብያል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ የፍርድ ጊዜ ምን እንደሚያስተምር ለማወቅ የምትፈልግ ከሆነ በአካባቢህ ያሉትን የይሖዋ ምሥክሮች አነጋግራቸው፤ ወይም በዚህ መጽሔት በገጽ 5 ላይ ከተገለጹት አድራሻዎች ውስጥ ወደ አንዱ ጻፍ።—ማርቆስ 13:10፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:1-5፤ ራእይ 14:6, 7፤ 16:14-16

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.32 የአካባቢ የግንባታ ኮሚቴዎች የመንግሥት አዳራሾችን በመገንባትና ሕንጻዎችን አፍርሶ በአዲስ መልክ እንደገና በመሥራት ረገድ ብዙ ልምድ ካላቸውና ፈቃደኛ ከሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች የተውጣጡ ቡድኖች ናቸው። በዩናይትድ ስቴትስ 100 የሚያህሉ የዚህ ዓይነት ቡድኖች ያሉ ሲሆን በዓለም ዙሪያ ደግሞ ሌሎች በርካታ ቡድኖች አሉ።

[በገጽ 14, 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የካትሪና አውሎ ነፋስ የሳተላይት ምስል

[ምንጭ]

NOAA

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በጎርፍ የተጥለቀለቀችው ኒው ኦርሊየንስ

[ምንጭ]

AP Photo/David J. Phillip

[በገጽ 15 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

አውሎ ነፋሱ ሕንጻዎችን አውድሟል፤ የብዙዎችን ሕይወትም ቀጥፏል

[ምንጭ]

AP Photo/Ben Sklar

[በገጽ 16, 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በቴክሳስ ሂዩስተን የሚገኘው አስትሮዶም ለ16,000 ተፈናቃዮች መጠለያ ሆኖ ነበር

[በገጽ 17 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ክርስቲያን ሽማግሌዎች ከተፈናቃዮቹ መሃል የይሖዋ ምሥክር የሆኑትን ፈልገው አግኝተዋል

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቤቶቻቸው የታደሱላቸው የይሖዋ ምሥክሮች በጣም አመስጋኞች ነበሩ

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ፈቃደኛ ሠራተኞች በጣም የተጎዳ ጣራ ሲያድሱ

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ፈቃደኛ ሠራተኞቹ ምግብ አቅርበዋል

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አለን