በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የውኃን ችግር ለማስወገድ ምን እየተደረገ ነው?

የውኃን ችግር ለማስወገድ ምን እየተደረገ ነው?

የውኃን ችግር ለማስወገድ ምን እየተደረገ ነው?

ዓለም አቀፋዊ ቀውስ እያስከተለ ያለው የውኃ ችግር በቢሊዮን የሚቆጠሩ የምድር ነዋሪዎችን ጤንነት አስጊ ሁኔታ ላይ ሊጥል ይችላል። ታዲያ ከውኃ አቅርቦትና አጠቃቀም ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለማስወገድ ምን እርምጃዎች እየተወሰዱ ነው?

ደቡብ አፍሪካ፦ ሳይንስ የተባለው መጽሔት “በደርበን የሚኖሩ ድሃ ሰዎች ከበርካታ ዓመታት በኋላ የውኃ አገልግሎት አገኙ” የሚል ዋና ርዕስ ይዞ ወጥቶ ነበር። ይህ ርዕስ በዚያ ከተማ ውስጥ የሚኖሩ ድሃ ሰዎች ቀደም ሲል የነበሩት መንግሥታት ይከተሉት በነበረው የአፓርታይድ ፖሊሲ የተነሳ ለብዙ ዓመታት በቂ የውኃ አቅርቦት እንዳልነበራቸው ሪፖርት አድርጓል። ይኸው ርዕስ እንደገለጸው በ1994 “በደርበን አካባቢ ከሚኖሩት ቤተሰቦች መካከል ሩብ ሚሊዮን የሚሆኑት ንጹሕ ውኃ አያገኙም ወይም ፍሳሽን በተገቢው መንገድ ማስወገድ አይችሉም ነበር።”

በ1996 አንድ ኢንጂነር፣ ለዚህ ችግር እልባት ለማስገኘት ለእያንዳንዱ ቤተሰብ በየቀኑ 200 ሊትር ያህል ውኃ ለማቅረብ የሚያስችል ፕሮግራም ነደፈ። ይህ ምን ውጤት አስገኘ? ሳይንስ የተባለው መጽሔት እንደዘገበው በአሁኑ ጊዜ፣ “3.5 ሚሊዮን ከሚሆኑት የደርበን ነዋሪዎች መካከል የንጹሕ ውኃ አቅርቦት የሌላቸው 120,000 ሰዎች ብቻ ናቸው።” በዛሬው ጊዜ አንድ ሰው ውኃ ለማግኘት ሩቅ መጓዝ አያስፈልገውም፤ ይህ ደግሞ ብዙ ሰዎች ውኃ ለማግኘት ከአንድ ኪሎ ሜትር በላይ ይጓዙ ከነበረበት ወቅት አንጻር ሲታይ ትልቅ መሻሻል ነው።

ሳይንስ የተባለው መጽሔት እንደገለጸው ፍሳሽን ከማስወገድ ጋር በተያያዘ ያለውን ችግር ለመቅረፍ “ቀደም ሲል ከቤት ውጪ ይሠሩ የነበሩት መጸዳጃ ቤቶች . . . ሁለት ጉድጓድ ባላቸው መጸዳጃ ቤቶች” እየተተኩ ነው፤ እነዚህ መጸዳጃ ቤቶች “ሽንቱ ከዓይነ ምድሩ እንዲለይና ዓይነ ምድሩ በፍጥነት ደርቆ እንዲፈረካከስ በሚያደርግ መንገድ” የተሠሩ ናቸው። በ2008 መጀመሪያ ላይ ወደ 60,000 የሚጠጉ እንዲህ ያሉ መጸዳጃ ቤቶች የተሠሩ ሲሆን በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ሁሉም ቤቶች ተገቢው ዓይነት መጸዳጃ ቤት እንዲኖራቸው ለማድረግ እቅድ ተይዟል።

ብራዚል፦ በሳልቫዶር ከተማ ከፍሳሽ ማስወገጃና ከመጸዳጃ ቤት ችግር ጋር በተያያዘ በመቶ የሚቆጠሩ ሕፃናት በተቅማጥ በሽታ ይሠቃዩ ነበር። * ይህን ችግር ለመፍታት በከተማው ውስጥ ከ300,000 በላይ ለሚሆኑ ቤቶች 2,000 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያላቸው የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎች ተዘርግተዋል። ይህ ምን ውጤት አስገኝቷል? በከተማው ውስጥ በተቅማጥ በሽታ የሚጠቁ ሕፃናት ቁጥር 22 በመቶ የቀነሰ ሲሆን በዚህ ችግር ይበልጥ ይጠቁ በነበሩ አካባቢዎች ደግሞ 43 በመቶ ቀንሷል።

ሕንድ፦ አንዳንድ የዓለም ክፍሎች በተወሰኑ ወቅቶች ከፍተኛ መጠን ያለው ውኃ ያገኛሉ፤ ይሁንና በአብዛኛው ውኃውን በአግባቡ ለመጠቀም በሚያስችል ሁኔታ አያጠራቅሙትም። ሆኖም በ1985 በሰሜን ምዕራብ የጉጃራት ግዛት በሚገኘው ዶሌረ በተባለ አውራጃ የሚኖሩ የተወሰኑ ሕንዳውያን ሴቶች፣ ውኃን ለማጠራቀም የሚያስችል በጣም ውጤታማ የሆነ ዘዴ ቀየሱ። አንድ የእግር ኳስ ሜዳ የሚያህል ስፋት ያለው ውኃ ማቆሪያ ጉድጓድ ለመሥራት የተወሰኑ ሰዎችን አስተባበሩ። ከዚያም ውኃው ወደ ውስጥ እንዳይሰርግ ጉድጓዱን በወፍራም ፕላስቲክ ሸፈኑት። ያደረጉት ጥረት ስኬታማ ነበር። እነዚህ ሴቶች “ሌሎች ሰዎች የጉድጓዱን ውኃ ለመጠጥ እንዲጠቀሙ ፈቅደውም” እንኳ የዝናቡ ወቅት ካበቃ ከብዙ ወራት በኋላ ውኃው አላለቀም ነበር።

ቺሊ፦ በደቡብ አሜሪካ የምትገኘው ይህች አገር 4,265 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያላት ሲሆን በስተ ምዕራብ ከፓስፊክ ውቅያኖስ፣ በስተ ምሥራቅ ደግሞ ከአንዲስ ተራራ ጋር ትዋሰናለች። የአገሪቱ የውኃ ሀብት በሙሉ በመንግሥት ሥልጣን ሥር ሲሆን የግድቦችንና የቦዮችን ሥራ ይቆጣጠራል። ይህ ምን ውጤት አስገኝቷል? በአሁኑ ጊዜ 99 በመቶ የሚሆኑት የከተማ ነዋሪዎችና 94 በመቶ የሚያህሉት የገጠር ነዋሪዎች በቂ ውኃ ያገኛሉ።

ዘላቂው መፍትሔ

እያንዳንዱ አገር የውኃን ችግር ለማስወገድ የሚጠቀምበት የራሱ ዘዴ አለው። ሁልጊዜ ጥሩ ንፋስ በሚነፍስባቸው አንዳንድ አገሮች በንፋስ የሚሠሩ ኃይል ማመንጫዎች ውኃ ለመሳብ እንዲሁም ኤሌክትሪክ ለማመንጨት ያገለግላሉ። የበለጸጉ አገሮች ደግሞ በባሕር ውኃ ውስጥ ያለውን ጨው በተለያዩ መንገዶች በማስወገድ ውኃውን ጥቅም ላይ ያውሉታል። ብዙ አገሮች ትላልቅ ግድቦችን ሠርተው የወንዝና የዝናብ ውኃን ያጠራቅማሉ። ደረቅ በሆኑ አካባቢዎች፣ በዚህ መንገድ ከሚጠራቀመው ውኃ ውስጥ 10 በመቶ የሚሆነው የሚተን ቢሆንም በአብዛኛው ይህ ዘዴ ውጤታማ ሆኖ ተገኝቷል።

የዚህ መጽሔት አዘጋጆች የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች የውኃን ችግር ለዘለቄታው የሚያስወግደው ሰው ሳይሆን አምላክ እንደሆነ ያምናሉ። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ምድርና በእርሷ ያለው ሁሉ፣ ዓለምና በውስጧ የሚኖር ሁሉ የእግዚአብሔር ነው፤ እርሱ በባሕሮች ላይ መሥርቶአታልና፤ በውሆችም ላይ አጽንቶአታል።”—መዝሙር 24:1, 2

እርግጥ ነው፣ አምላክ ለሰው ልጆች ይህችን ምድር የመንከባከብ ኃላፊነት ሰጥቷቸዋል። (ዘፍጥረት 1:28) ይሁን እንጂ ሰዎች የምድርን ሀብት አላግባብ መጠቀማቸውና ከዚህ ጋር ተያይዘው የመጡት አስከፊ ውጤቶች ‘ሰው አካሄዱን በራሱ አቃንቶ ሊመራ አይችልም’ የሚለውን ሐቅ የሚያረጋግጥ ተጨማሪ ማስረጃ ነው።—ኤርምያስ 10:23

ይሖዋ በምድር ላይ ያሉትን ነገሮች ፍጹም በሆነ መንገድ መልሶ ለማስተካከል ምን እርምጃ ይወስዳል? መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ ‘ሁሉን ነገር አዲስ የማድረግ’ ዓላማ እንዳለው ይገልጻል። (ራእይ 21:5) ድህነት፣ ድርቅና የውኃ እጥረት የሌለበትን ዓለም እስቲ በዓይነ ሕሊናህ ለመሳል ሞክር! በየዓመቱ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት እየቀጠፈ ያለው የጎርፍ አደጋ በዚያን ጊዜ ጨርሶ አይኖርም። የአምላክ መንግሥት ምድርን በሚያስተዳድርበት ጊዜ አምላክ፣ ቃል የገባቸው ነገሮች ፍጻሜያቸውን እንዲያገኙ ያደርጋል! ይሖዋ ራሱ እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ “ከአፌ የሚወጣውም ቃሌ፣ በከንቱ ወደ እኔ አይመለስም፤ ነገር ግን የምሻውን ያከናውናል፤ የተላከበትንም ዐላማ ይፈጽማል።”—ኢሳይያስ 55:11

አምላክ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተገለጸው መሠረት ምድርን መልሶ ለማስተካከል ስላለው ዓላማ ይበልጥ ማወቅ ትፈልጋለህ? ቀጣዩ ርዕስ ይህን ማድረግ የምትችልበትን መንገድ ያብራራል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.6 በዓለም ዙሪያ በየዓመቱ 1.6 ሚሊዮን የሚያህሉ ሕፃናት በተቅማጥ በሽታ ይሞታሉ። ይህ ቁጥር በኤድስ፣ በሳንባ ነቀርሳና በወባ በሽታ ከሚሞቱት ሕፃናት አጠቃላይ ድምር ይበልጣል።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ውኃ ከሌለ ሕይወት አይኖርም። . . . ሕይወታችን የተመካው በውኃ ላይ ነው።”—ማይክል ፓርፊት፣ የናሽናል ጂኦግራፊክ ጸሐፊ

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

አንድ ቶን እህል ለማምረት 1,000 ቶን ውኃ ያስፈልጋል

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰዎች ከሚጠቀሙበት ውኃ ውስጥ 70 በመቶው የሚውለው ለመስኖ ልማት ነው።”በሌስተር ብራውን የተዘጋጀው፣ ፕላን ቢ 2.0

[በገጽ 7 ላይ የሚገኙ ሥዕላዊ መግለጫዎች]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ለመጠጥነት የሚያገለግለው የውኃ መጠን ምን ያህል ነው?

አጠቃላይ የውኃ መጠን

97.5 በመቶው ጨዋማ ውኃ ነው

2.5 በመቶው ጨው አልባ ውኃ ነው

ጨው አልባ ውኃ

99 በመቶው በበረዶ ዐለትና በግግር በረዶ መልክ ወይም ከመሬት በታች ይገኛል

1 በመቶው ወደ ሰባት ቢሊዮን የሚጠጉ ሰዎችና ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሌሎች ሕያዋን ፍጥረታት ይጠቀሙበታል

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በደቡብ አፍሪካ፣ ደርበን ከተማ ውስጥ የንጹሕ ውኃ መስመር ሲዘረጉ

[ምንጭ]

Courtesy eThekwini Water and Sanitation Programme

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ2007 በሕንድ፣ ራጀስታን ግዛት ውስጥ ሴቶች በዝናብ ውኃ በሚካሄድ የልማት ፕሮጀክት ላይ ሲሠሩ

[ምንጭ]

© Robert Wallis/Panos Pictures

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በሆንዱራስ፣ ኮፓን አቅራቢያ በሚገኝ መንደር የአካባቢው ሰዎች አዲስ የውኃ መስመር ሲያስገቡ

[ምንጭ]

© Sean Sprague/SpraguePhoto.com