በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትምህርት የመቀበል ችግር ያለባቸውን ልጆች መርዳት

ትምህርት የመቀበል ችግር ያለባቸውን ልጆች መርዳት

ትምህርት የመቀበል ችግር ያለባቸውን ልጆች መርዳት

ሜክሲኮ የሚገኘው የንቁ! ጸሐፊ እንዳዘጋጀው

ስቲቨን የማንበብ ችግር አለበት። በክፍል ውስጥ ጮክ ብሎ እንዲያነብ ሊጠየቅ እንደሚችል ባሰበ ቁጥር ሆዱን ያመዋል።

ማሪያ መምህሯ የእጅ ጽሑፏን አስመልክታ በተደጋጋሚ ጊዜያት ምክር ብትሰጣትም ጥርት አድርጋ መጻፍ አልቻለችም። የቤት ሥራዋን ሠርታ ለመጨረስ ረጅም ሰዓት ይፈጅባታል።

ኖኅ የሚሰጡትን የቤት ሥራዎች ደጋግሞ ያነባቸዋል። ያም ሆኖ ያነበበውን ነገር ስለሚረሳ ፈተና ማለፍ አስቸጋሪ ሆኖበታል።

ስቲቨን፣ ማሪያና ኖኅ ትምህርት የመቀበል ችግር ያለባቸው ሲሆን እንዲህ ያለ እክል ካለባቸው ልጆች መካከል ደግሞ አብዛኞቹ አጥርተው ማንበብ አይችሉም። ለምሳሌ ያህል፣ ዲስሌክሲያ ያለባቸው ልጆች ተመሳሳይ አጻጻፍ ያላቸውን ፊደላት መለየት ብዙ ጊዜ ያስቸግራቸዋል። ትምህርት የመቀበል ችግር ያለባቸው ሌሎች ልጆች ደግሞ ዲስግራፊያ (መጻፍ አለመቻል) እንዲሁም ዲስካልኩሊያ (የሒሳብ ስሌት የመሥራት ችግር) አለባቸው። ያም ሆኖ እንዲህ ዓይነት ችግር ካለባቸው ልጆች አብዛኞቹ መካከለኛ ወይም ከዚያ በላይ የሆነ የመረዳት ችሎታ አላቸው።

ልጆች ትምህርት የመቀበል ችግር እንዳለባቸው ከሚጠቁሙት ምልክቶች መካከል ከሌሎች ልጆች አንጻር ዘግይተው አፍ መፍታት፣ የመጨረሻ ፊደላቸው ተመሳሳይ ድምፅ ያላቸውን ቃላት መለየት አለመቻል፣ ቃላትን በትክክል አለመጥራት፣ ካደጉ በኋላም እንደ ሕፃን ማውራት እንዲሁም ፊደላትንና ቁጥሮችን የመማር ችግር ብሎም ፊደልን በቀላሉ መጥራት፣ ተመሳሳይ ድምፅ ያላቸውን ቃላት መለየትና መመሪያዎችን መከተል አለመቻል ይገኙበታል። *

ልጅህ ችግሩን እንዲቋቋም መርዳት

ልጅህ ትምህርት የመቀበል ችግር እንዳለበት ከተሰማህ ምን ማድረግ ትችላለህ? በመጀመሪያ ደረጃ የልጅህ ችግር ከመስማትና ከማየት ጋር የተያያዘ መሆን አለመሆኑን ለማወቅ አስመርምረው። * ከዚያም የምርመራውን ውጤት ሐኪም እንዲያየው አድርግ። ልጅህ ትምህርት የመቀበል ችግር ካለበት የአንተ ስሜታዊ ድጋፍ ያስፈልገዋል። ይህ ችግር ከልጁ የማሰብ ችሎታ ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው አስታውስ።

ልጅህ በሚማርበት ትምህርት ቤት ውስጥ እንደ ማጠናከሪያ ትምህርት ያሉ ፕሮግራሞች ካሉ ልጅህ በእነዚህ ዝግጅቶች እንዲጠቀም አድርግ። የልጅህ አስተማሪ እንዲተባበርህ ጠይቀው። ክፍል ውስጥ ከፊት እንዲቀመጥ እንዲሁም የክፍል ሥራውን ለመጨረስ ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጠው አስተማሪውን ልታስፈቅድለት ትችላለህ። መምህሩ መመሪያዎችን በቃል ብሎም በጽሑፍ እንዲሰጠው እንዲሁም ልጁ ፈተና ላይ ሲቀርብ በቃል እንዲመልስ ማድረግ ይችላል። ትምህርት የመቀበል ችግር ያለባቸው ልጆች ብዙውን ጊዜ ዝንጉዎችና ያልተደራጁ ስለሆኑ ወደ ትምህርት ቤት የሚወስዷቸውን መጻሕፍት በሙሉ በቤት ውስጥም ማግኘት እንዲችሉ ተጨማሪ ቅጂዎች እንዲኖሩ ማድረግ ይቻላል። ከዚህም በተጨማሪ በክፍል ውስጥ ሲማሩም ይሁን የቤት ሥራዎችን ሲሠሩ የሚጠቀሙበት ኮምፒውተር እንዲኖር ማድረግ ይቻላል።

ልጅህ ዲስሌክሲያ ካለበት በየቀኑ ለአጭር ጊዜ ማንበብ የሚችልበትን ፕሮግራም አውጣለት። ሐሳብና እርማት ለመስጠት እንድትችል ልጅህ ጮክ ብሎ እንዲያነብ ማድረጉ የተሻለ ነው። በመጀመሪያ አንተ ጮክ ብለህ ስታነብ ልጅህ እንዲከታተልህ አድርግ። ቀጥሎም ያንኑ ጽሑፍ ድምፃችሁን ከፍ አድርጋችሁ አብራችሁ አንብቡት። ከዚያም ልጅህ ብቻውን እንዲያነበው አድርግ። ልጅህ በሚያነብበት ጊዜ የሚያነብበው መሥመር እንዳይጠፋበት ከታች ያለውን ጽሑፍ በማስመሪያ እንዲሸፍን ማድረግ ትችላለህ፤ ለማንበብ የሚያስቸግሩ ቃላት ካሉ ምልክት አድርግባቸው። ይህን ለማድረግ በቀን ውስጥ 15 ደቂቃ ብቻ መመደብ በቂ ሊሆን ይችላል።

ልጅህ የሒሳብ ስሌት የመሥራት ችሎታውን እንዲያሻሽል ለመርዳት ደግሞ ምግብ ስታዘጋጁ የሚያስፈልጉት ነገሮችን መጥኖ እንዲጨምር ወይም ከእንጨት ሥራ ጋር የተያያዙ ነገሮችን ስትሠሩ በማስመሪያ እንዲለካ ማድረግ አሊያም ገበያ አብራችሁ መውጣት ትችላላችሁ። የሒሳብ መልመጃዎችን ለመሥራት በስኩዌር ደብተርና በሥዕላዊ መግለጫዎች መጠቀም ሊረዳ ይችላል። ዲስግራፊያን ማለትም የመጻፍ ችግርን ለማሻሻል ሠፋፊ መሥመሮች ባሏቸው ወረቀቶችና ደመቅ አድርጎ በሚጽፍ እርሳስ መጠቀም ይቻላል። ብረት ነክ በሆኑ ነገሮች ላይ የሚጣበቁ ማግኔትነት ያላቸው ፊደላት መጠቀም ልጅህ ቃላትን በትክክል መጻፍ እንዲችል ለመርዳት ጠቃሚ ሊሆን ይችላል።

አቴንሽን ዴፊሲት ሃይፐርአክቲቪቲ ዲስኦርደር የተባለውን በሽታ ለመቋቋም የሚረዱ ሌሎች ጠቃሚ ዘዴዎችም አሉ። እንዲህ ዓይነት ችግር ካለበት ልጅ ጋር ማውራት ከመጀመርህ በፊት ዓይን ዓይኑን እየው። ልጅህ የቤት ሥራውን ጸጥታ በሰፈነበት ቦታ እንዲሠራ እንዲሁም ቶሎ ቶሎ እንዲያርፍ ማድረግ ያስፈልጋል። ልጅህ አንድ ቦታ ተረጋግቶ መቀመጥ የሚያስቸግረው ከሆነ እንደ መላላክ ያሉ አንዳንድ ሥራዎችን እንዲያከናውን በማድረግ ጉልበቱን ጠቃሚ በሆነ ተግባር ላይ እንዲያውለው ማድረግ ይቻላል።

ሊሳካላችሁ ይችላል

ልጅህ ያለውን ችሎታ ወይም ተሰጥኦ እንዲያዳብር እርዳው። ያከናወነው ነገር ምንም ያህል አነስተኛ ይሁን አመስግነው እንዲሁም ሽልማት ስጠው። ልጅህ አንድን ሥራ በማከናወን የሚገኘውን ደስታ ማጣጣም እንዲችል ከባድ ሥራዎችን በትንሽ በትንሹ እንዲሠራቸው ከፋፍለህ ስጠው። አንድን ሥራ ለማጠናቀቅ ሊያከናውናቸው የሚገቡትን ነገሮች ለማሳየት በሥዕላዊ መግለጫዎች ተጠቀም።

አንድ ወጣት አጥርቶ ማንበቡ፣ ጥሩ አድርጎ መጻፉና የሒሳብ ስሌት የመሥራት ችሎታውን ማዳበሩ አስፈላጊ ነው። ለልጅህ ተገቢውን ማበረታቻና እርዳታ ከሰጠኸው ትምህርት የመቀበል ችሎታው ሊሻሻል እንደሚችል እርግጠኛ ሁን፤ ይሁን እንጂ ትምህርቱን እንደ ሌሎች ልጆች ቶሎ ላይረዳና አንዳንድ ነገሮችን ለመቀበል ረዘም ያለ ጊዜ ሊወስድበት እንደሚችል መዘንጋት አይኖርብህም።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.7 አቴንሽን ዴፊሲት ሃይፐርአክቲቪቲ ዲስኦርደር የተባለው በሽታ ብዙውን ጊዜ ትምህርት ከመቀበል ችግር ጋር ተያይዞ የሚመጣ ሲሆን ምልክቶቹም መንቀዥቀዥ ወይም አለመረጋጋት፣ ነገሮችን በደመ ነፍስ ማከናወንና በአንድ ነገር ላይ ትኩረት ማድረግ አለመቻል ናቸው። የኅዳር 22, 1997 ንቁ! መጽሔት (እንግሊዝኛ) ገጽ 5-10ን ተመልከት።

^ አን.9 ዲስሌክሲያ እና የመንቀዥቀዥ ወይም ያለመረጋጋት ችግር ያለባቸው ወንዶች ቁጥር ከሴቶች ልጆች በሦስት እጥፍ ገደማ ስለሚበልጥ ይህ ርዕስ ያተኮረው በወንዶች ላይ ነው።

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ትምህርት የመቀበል ችግር ጠቃሚ ነገር ለማከናወን ረድቶኛል

“አንድን የተጻፈ ነገር ለማንበብ ስሞክር የሚታየኝ ነገር ቢኖር የተወለጋገደ መሥመርና የተዘበራረቁ ቃላት ናቸው። በሌላ ቋንቋ የተጻፈ መስሎም ይታየኛል። ሌላ ሰው ጮክ ብሎ ካላነበበልኝ በስተቀር የተጻፉትን ቃላት በትክክል መረዳት አልችልም። መምህሮቼ ሰነፍ እንደሆንኩ፣ ለትምህርቱ ንቀት እንዳለኝ እንዲሁም ምንም ጥረት እንደማላደርግና ትምህርቱን እንደማላዳምጥ ይሰማቸው ነበር። ይህ ግን ፈጽሞ ከእውነታው የራቀ ነው። ትምህርቱን በጥሞና ለማዳመጥና ለመረዳት ከፍተኛ ጥረት ባደርግም የማንበብና የመጻፍ ችሎታዬን ማሻሻል አልቻልኩም። እንደ ሒሳብ ያሉ ሌሎች ትምህርቶች አይከብዱኝም ነበር። ልጅ ሳለሁ ከማንበብና ከመጻፍ ጋር የተያያዘ እስካልሆነ ድረስ ስፖርትንና ሥነ ጥበብን የመሳሰሉ እንዲሁም የእጅ ሞያን የሚጠይቁ ነገሮችን መሥራት ብዙም አይከብደኝም ነበር።

“ዕድሜዬ ከፍ ሲል የእጅ ሞያ የሚጠይቁ ሥራዎችን ለመሥራት ወሰንኩ። ይህ ደግሞ የይሖዋ ምሥክሮች ከሚያካሂዷቸው ዓለም አቀፍ የግንባታ ፕሮጀክቶች መካከል በአምስቱ ላይ የመካፈል መብት እንዳገኝ አስችሎኛል። አንድን ነገር ቶሎ መረዳት ስለማልችል ደጋግሜ ማንበብ አለብኝ፤ ይህም ካነበብኳቸው ነገሮች መካከል አብዛኞቹን ማስታወስ እንድችል ረድቶኛል። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ እንደመሆኔ መጠን ያነበብኩትን ነገር ማስታወስ መቻሌ በተለይ ለክርስቲያናዊ አገልግሎቴ በጣም ጠቅሞኛል። ስለዚህ ማንበብና መጻፍ አለመቻሌን እንደ እክል ሳይሆን ጠቃሚ እንደሆነ ነገር አድርጌ እቆጥረዋለሁ።”—ፒተር፣ ዲስሌክሲያ ያለበት የሙሉ ጊዜ አገልጋይ የሆነ የይሖዋ ምሥክር

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ልጆች በጥሞና ያዳመጡትን ነገር “በሥዕል በመግለጽ” ረገድ ጎበዞች ሊሆኑ ይችላሉ