በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሕይወት ያላት ፕላኔት

ሕይወት ያላት ፕላኔት

ሕይወት ያላት ፕላኔት

ድር ሥፍር ቁጥር የሌላቸውን ሕያዋን ፍጥረታትን ምናልባትም በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ዝርያዎችን በጉያዋ አቅፋ የያዘች ፕላኔት ነች። በአፈር፣ በአየርና በውኃ ውስጥ ከሚኖሩት ከእነዚህ ሕያዋን ፍጥረታት መካከል አብዛኞቹ በአጉሊ መነጽር ካልሆነ በስተቀር በዓይናችን ብቻ ልናያቸው አንችልም። ለምሳሌ ያህል፣ በአንድ ግራም አፈር ውስጥ 10,000 የሚደርሱ የባክቴሪያ ዝርያዎች ሊኖሩ ይችላሉ፤ የረቂቅ ተሕዋስያን ጠቅላላ ብዛት ምን ያህል ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም! አንዳንዶቹ ዝርያዎች በምድር ከርስ ውስጥ 3 ኪሎ ሜትር ገደማ ድረስ ጠልቀው ይገኛሉ!

ከባቢ አየርም ቢሆን በተለያዩ የአእዋፍ ዝርያዎችና ነፍሳት ብቻ ሳይሆን በዓይን በማይታዩ ረቂቅ ሕያዋን ፍጥረታትም የተሞላ ነው። ከባቢ አየር በዓመት ውስጥ በተለያዩ ወቅቶች በአበባ ዱቄት፣ በፈንገስ ሕዋሳት እንዲሁም በተለያዩ የእጽዋት ዘሮች ይሞላል፤ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ደግሞ የተለያየ ዝርያ ያላቸው በሺዎች በሚቆጠሩ ረቂቅ ተሕዋስያን ይገኛሉ። “ይህም በአፈር ውስጥ የተለያዩ ረቂቅ ተሕዋስያን ያሉትን ያህል በአየር ውስጥም ብዙ ዓይነት ረቂቅ ተሕዋስያን እንዲገኙ አስችሏል” በማለት ሳይንቲፊክ አሜሪካን የተባለው መጽሔት ገልጿል።

በባሕር ጥልቅ ውስጥ ገብቶ ምርምር ማድረግ አብዛኛውን ጊዜ ውድ የሆነ ቴክኖሎጂ መጠቀም ስለሚጠይቅ የውቅያኖስ አብዛኛው ክፍል እስከ አሁን ድረስ ሚስጥር እንደሆነ ነው። በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ በቀላሉ በሚገኙትና በደንብ ጥናት በተካሄደባቸው በኮራል ሪፎች ውስጥ እንኳ እስካሁን ያልታወቁ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ዝርያዎች ሊኖሩ ይችላሉ።

ያም ሆነ ይህ ፕላኔቷ ምድራችን በጣም ብዙ ሕይወት ያላቸው ነገሮችን በውስጧ የያዘች መሆኗ የማይታበል ሐቅ ነው፤ እነዚህ ሕይወት ያላቸው ነገሮች ደግሞ በፕላኔቷ ምድር በተለይም ሕይወት በሚኖርበት የምድር ክፍል ላይ ኬሚካላዊ ለውጦች እንዲካሄዱ ያደርጋሉ። ለምሳሌ ያህል፣ የዩናይትድ ስቴትስ ናሽናል ኦሺየኒክ ኤንድ አትሞስፌሪክ አድምንስትሬሽን ያወጣው አንድ ዘገባ “አንቲአሲድ የተባለው መድኃኒት በጨጓራ ውስጥ ያለውን የአሲድ መጠን እንደሚያስተካክለው” ሁሉ በዛጎልና በኮራል ውስጥ የሚገኘው ካልሲየም ካርቦኔትም በውቅያኖስ ውስጥ ያለውን ኬሚካላዊ ይዘት እንደሚያስተካክል ይገልጻል። ተክሎች እንዲሁም በሐይቅና በውቅያኖስ የላይኛው ክፍል የሚያድገው ፋይቶፕላንክተን የተባለ ባለ አንድ ሕዋስ አልጌ በውኃም ሆነ በአየር ውስጥ ያለው የካርቦን ዳይኦክሳይድና የኦክስጅን መጠን የተስተካከለ እንዲሆን ይረዳሉ። ባክቴሪያና ፈንገስ ደግሞ በአፈር ውስጥ ያሉ ንጥረ ነገሮችን ወደ ብስባሽ በመለወጥ ለተክሎች ምግብነት ተስማሚ እንዲሆኑ ያደርጋሉ። በእርግጥም፣ ምድር ሕይወት ያላት ፕላኔት መባሏ ተገቢ ነው።

ምድር ፍጹም በሆነ መንገድ ተስተካክላ ባትቀመጥ ኖሮ ሕይወት በላይዋ ላይ ባልኖረ ነበር፤ ሕይወት በላይዋ ላይ እንዲኖር አስተዋጽኦ ካደረጉት ነገሮች መካከል አንዳንዶቹ እስከ 20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ ሙሉ በሙሉ አልታወቁም ነበር። ከእነዚህ ነገሮች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፦

1. ምድር ፍኖተ ሐሊብ በተባለው ጋላክሲና በሥርዓተ ፀሐይ ውስጥ ያለችበት ቦታ፣ በራሷ ዛቢያ ላይ መዞሯ፣ ጋደል ማለቷ እንዲሁም የምትሽከረከርበት ፍጥነትና ጨረቃ

2. ምድርን እንደ ጋሻ ሆነው የሚከልሉት መግነጢሳዊ መስክ (ማግኔቲክ ፊልድ) እና ከባቢ አየር

3. ውኃ በብዛት መኖሩ

4. ሕይወት የሚኖርበት የምድር ክፍል እንዲታደስና እንዲጸዳ የሚያደርገው የተፈጥሮ ዑደት

በሚቀጥሉት ርዕሶች ላይ ስለ እነዚህ ጉዳዮች ስታነብ ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘ምድር እንዲህ ያለ የተስተካከለ ሁኔታ ሊኖራት የቻለው እንዲሁ በአጋጣሚ ነው? ወይስ ከፍተኛ የማሰብ ችሎታ ባለው ፈጣሪ ስለተሠራች ነው? ምድር የተፈጠረችው ከፍተኛ የማሰብ ችሎታ ባለው ፈጣሪ ከሆነ ምድርን የሠራበት ዓላማ ምንድን ነው?’ የዚህ ተከታታይ ርዕስ የመጨረሻው ክፍል ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሰጣል።

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

“አምላክ ደጃፋችን ላይ እንዲደርስ አንፈልግም”

ዓለማችን እንዲሁ በአጋጣሚ የተገኘ ሳይሆን የላቀ የማሰብ ችሎታ ባለው ንድፍ አውጪ እንደተሠራ የሚያሳዩ ብዙ ማስረጃዎች ቢኖሩም በርካታ ሳይንቲስቶች ፈጣሪ መኖሩን ማመን አይፈልጉም። የዝግመተ ለውጥ አማኝ የሆኑት ሪቻርድ ሊዎንተን አምላክ የለም የሚሉ ሰዎች ዓለም የተገኘው “በቁስ አካላዊነት ነው” የሚለውን “ማብራሪያ” እንዲቀበሉ የሚያስገድዳቸው ሳይንስ እንዳልሆነ ተናግረዋል። ከዚህ ይልቅ ‘ቀደም ብለው በቁስ አካላዊነት ለማመን ቃል ስለገቡ’ እንዲሁም ‘ይህ ጽንሰ ሐሳብ በሌሎች ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ ለማድረግ’ ቆርጠው ስለተነሱ እንደሆነ ገልጸዋል። በተጨማሪም አብዛኞቹን ሳይንቲስቶች ወክለው ሐሳብ ሲሰጡ ዓለም የተገኘው “በቁስ አካላዊነት ነው” የሚለው ማብራሪያ ምንም እንከን ስለማይወጣለት “አምላክ ደጃፋችን ላይ እንዲደርስ አንፈልግም” ሲሉ ተናግረዋል።

እንዲህ ያለ ድርቅ ያለ አቋም መያዝ የጥበብ አካሄድ ነው? በተለይ ፈጣሪ መኖሩን የሚያሳዩ ሥፍር ቁጥር የሌላቸው ማስረጃዎች እያሉ ይህን ዓይነቱን አመለካከት ማራመድ ተገቢ ነው? አንተስ በዚህ ረገድ ምን ይሰማሃል?—ሮም 1:20