በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምድር ያለችበት “አድራሻ”

ምድር ያለችበት “አድራሻ”

ምድር ያለችበት “አድራሻ”

ብዙውን ጊዜ ሰዎች አድራሻቸውን ሲጠየቁ የሚኖሩበትን አገር፣ ከተማ እንዲሁም መንገድ ይጠቅሳሉ። የምድርን አድራሻ ከዚህ ጋር ብናነጻጽር ፍኖተ ሐሊብ የተባለው ጋላክሲ የምድር “አገር” ሲሆን ፀሐይንና በዙሪያዋ የሚገኙትን ፕላኔቶች ያካተተው ሥርዓተ ፀሐይ ደግሞ “ከተማዋ” ነው፤ እንዲሁም ምድር በሥርዓተ ፀሐይ ውስጥ የምትጓዝበት ምሕዋር “በመንገድ” ሊመሰል ይችላል። በሥነ ፈለክ መስክም ሆነ በፊዚክስ ረገድ ከፍተኛ እድገት ላይ በመደረሱ ሳይንቲስቶች በአጽናፈ ዓለም ውስጥ በጣም ትንሽ ስለሆነችው መኖሪያችን ጥልቅ የሆነ እውቀት ማግኘት ችለዋል።

ሳይንቲስቶች የፍኖተ ሐሊብ ክፍል የሆነውንና “በከተማ” የተመሰለውን የእኛን ሥርዓተ ፀሐይ በጋላክሲ ውስጥ ያለ ለመኖሪያነት ምቹ የሆነ ክልል በማለት ይጠሩታል። ይህ ክልል ከጋላክሲው እምብርት 28,000 የብርሃን ዓመት ገደማ ርቆ የሚገኝ ሲሆን በዚህ ክልል ውስጥ ለሕይወት አስፈላጊ የሆኑ ንጥረ ነገሮች በተስተካከለ መጠን ይገኛሉ። ከጋላክሲው እምብርት ከእዚህ በላይ ከራቅን እነዚህን ንጥረ ነገሮችን ማግኘት አዳጋች ነው፤ ይበልጥ ከተጠጋን ደግሞ ጎጂ የሆኑ ጨረሮችና ሌሎች ነገሮች በአካባቢው በመኖራቸው ለሕይወት አደገኛ ነው። ሳይንቲፊክ አሜሪካን የተባለው መጽሔት “የምንኖረው ውብ በሆነ የመኖሪያ ሰፈር ውስጥ ነው” በማለት ዘግቧል።

ምርጥ “መንገድ”

“በከተማ” በተመሰለው በእኛ ሥርዓተ ፀሐይ ውስጥ “ምርጥ” “መንገድ” ወይም ምሕዋር ያላት ምድር ናት። ከፀሐይ 150 ሚሊዮን ኪሎ ሜትር ርቆ የሚገኘው የምድር ምሕዋር የሚያልፍበትን አካባቢ ሳይንቲስቶች በአንድ ኮከብ ዙሪያ ያለ ለመኖሪያነት ምቹ የሆነ ክልል ብለው ይጠሩታል። ይህ ክልል ከመጠን በላይ ቀዝቃዛ ወይም ሞቃት ባለመሆኑ ሕይወት ይኖርበታል። ከዚህም በላይ ምድር የምትጓዝበት መንገድ ክብ በመሆኑ ዓመቱን በሙሉ ከፀሐይ በተመሳሳይ ርቀት ላይ እንድንገኝ አስችሎናል።

በሌላ በኩል ደግሞ ፀሐይ ለምድር ጥሩ “የኃይል ምንጭ” ነች። ፀሐይ ትክክለኛ መጠን ያላት፣ ከቦታዋ ዝንፍ የማትልና የተስተካከለ መጠን ያለው ኃይል የምታመነጭ ኮኮብ ናት። በእርግጥም “ልዩ የሆነች ኮከብ” ተብላ መጠራቷ ተገቢ ነው።

ጥሩ የሆነች ጎረቤት

ለምድር “ጎረቤት” ምረጥ ብትባል ከጨረቃ የተሻለ ጎረቤት ልትመርጥላት ትችላለህ? የጨረቃ ስፋት ከምድር አንድ አራተኛ ጥቂት ከፍ የሚል ሲሆን በእኛ ሥርዓተ ፀሐይ ውስጥ ካሉ ሌሎች ጨረቃዎች ጋር ስትወዳደር የእኛ ጨረቃ ከምድር መጠን አንጻር በጣም ትልቅ ናት ሊባል ይቻላል። ሆኖም ይህ እንዲሁ በአጋጣሚ የሆነ ነገር አይደለም።

እንዲህ የምንልበት አንዱ ምክንያት፣ ጨረቃ በውቅያኖስ ላይ ለሚነሳ ማዕበል ዋነኛ መንስኤ ስለሆነች ነው፤ ይህ ደግሞ በምድር ሥነ ምህዳር ላይ ትልቅ ሚና ይጫወታል። እንዲሁም ጨረቃ፣ ምድር በዛቢያዋ ላይ የምትሽከረከርበት ፍጥነት ቋሚ እንዲሆን አስተዋጽኦ ታደርጋለች። ፕላኔቷ ምድራችን ተመጣጣኝ የሆነ ጨረቃ ባይኖራት ኖሮ አሹረው እንደ ለቀቁት እንዝርት በዛቢያዋ ላይ ትውተረተር የነበረ ከመሆኑም ሌላ ምናልባትም ወድቃ በጎኗ ትሽከረከር ነበር! በዚህ ምክንያት የሚከሰተው የአየር ንብረት ለውጥና ማዕበል እንዲሁም ሌሎች ነገሮች አውዳሚ የሆኑ አደጋዎችን ያስከትሉ ነበር።

ምድር ጋደል ያለችበት መጠንና የምትሽከረከርበት ፍጥነት

ምድር 23.5 ዲግሪ ጋደል ማለቷ በዓመት ውስጥ ወቅቶች እንዲፈራረቁ፣ ተስማሚ የአየር ንብረት እንዲኖር እንዲሁም የተለያየ የአየር ጠባይ ያላቸው ክልሎች እንዲኖሩ አስችሏል። ሬር ኧርዝኋይ ኮምፕሌክስ ላይፍ ኢዝ አንኮመን ኢን ዚ ዩኒቨርስ የተባለው መጽሐፍ “ፕላኔታችን የምትሽከረከርበት ዛቢያ ያዘመመበት መጠን ‘ትክክለኛ’ ነው” ብሏል።

ከዚህም በተጨማሪ ምድር በራሷ ዛቢያ ላይ የምትሽከረከርበት ፍጥነት ትክክለኛ በመሆኑ ቀንና ሌሊት እንዲፈራረቁ አስችሏል። ምድር በዛቢያዋ ላይ የምትሽከረከርበት ፍጥነት ቢቀንስ ኖሮ በፀሐይ በኩል ያለው የምድር ክፍል ከመጠን በላይ የሚሞቅ ሲሆን በሌላ በኩል ያለው የምድር ክፍል ደግሞ በጣም ቀዝቃዛ ይሆን ነበር። ከዚህ በተቃራኒ፣ ምድር የምትሽከረከርበት ፍጥነት ቢጨምርና ቀኑ በጥቂት ሰዓታት እንኳ ቢያጥር ከባድ ነፋስና ሌሎች አደጋዎች ይከሰቱ ነበር።

ስለ ፕላኔቷ ምድራችን የተረዳነው ማንኛውም ነገር ይኸውም ስለ “አድራሻዋም” ሆነ “ጎረቤቷ” ስለሆነችው ስለ ጨረቃ ያገኘነው ግንዛቤ ጥበበኛ የሆነ ፈጣሪ አስቦ እንደሠራት የሚያሳይ ማስረጃ ነው። * የፊዚክስ ሊቅና የዝግመተ ለውጥ አማኝ የሆኑት ፓል ዴቪስ እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል፦ “በአምላክ የማያምኑ ሳይንቲስቶች እንኳ አጽናፈ ዓለም ሚዛኑን የጠበቀ መሆኑን፣ ግርማውን፣ ሥርዓታማነቱን፣ ውበቱንና ፍጹም የተስተካከለ መሆኑን ሲመለከቱ ይደነቃሉ።”

አጽናፈ ዓለም በዚህ መልክ መደራጀቱ እንዲሁ በአጋጣሚ የተገኘ መሆኑን የሚያመለክት ነው? ወይስ በዓላማ የተሠራ መሆኑን? ለሕይወት አስጊ ከሆኑት፣ ከሕዋ ከሚመጡ አደገኛ ነገሮች ምድርን እንደ ጋሻ ሆነው ስለሚከልሉት ሁለት ነገሮች የሚናገረውን ቀጥሎ ያለውን አጭር ርዕስ ስታነብ ስለዚህ ጥያቄ አስብ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.13 ለጽንፈ ዓለም ሕልውና ወሳኝ የሆኑ ቁስ አካልን የሚቆጣጠሩ አራት ኃይሎች ያሉ ሲሆን እነሱም ስበት፣ ኤሌክትሮማግኔቲዝም እንዲሁም ጠንካራና ደካማ የኑክሌር ኃይል ናቸው። እነዚህ ሁሉ ፍጹም በተስተካከለ ሁኔታ ተመጥነው ተቀምጠዋል።—በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ኢዝ ዜር ኤ ክሬተር ሁ ኬርስ አባውት ዩ? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 2ን ተመልከት።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ከጥይት በበለጠ ፍጥነት እየተጓዝክ ነው?

በዚህ ሣጥን ውስጥ ያለውን ሐሳብ አንብበህ ስትጨርስ ያለ ምንም መንገጫገጭ በሺዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮችን ተጉዘሃል! እስቲ ይህን ልብ በል፦

የምድር መጠነ ዙሪያ 40,000 ኪሎ ሜትር ሲሆን በየ24 ሰዓቱ አንዴ በራሷ ዛቢያ ላይ ትሽከረከራለች። በመሆኑም በምድር ወገብ ላይ ወይም በዚያ አካባቢ ቆመህ ቢሆን በሰዓት 1,600 ኪሎ ሜትር ተጉዘሃል ማለት ነው። (እርግጥ የምድር ዋልታዎች የሚሽከረከሩት ባሉበት ነው።)

ምድር ራሷ በሴኮንድ 30 ኪሎ ሜትር እየተጓዘች ፀሐይን ትዞራለች፤ የሚያስገርመው ደግሞ የእኛ ሥርዓተ ፀሐይ ፍኖተ ሐሊብ በሚባለው ጋላክሲ እምብርት ዙሪያ በሴኮንድ 249 ኪሎ ሜትር ይጓዛል። ጥይት ግን በሴኮንድ የሚጓዘው ከ1.6 ኪሎ ሜትር ያነሰ ነው።

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ፍኖተ ሐሊብ፦ NASA/JPL/Caltech

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ምድር፦ Based on NASA/Visible Earth imagery