በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምድርን እንደ ጋሻ ሆነው የሚከልሉ አስደናቂ ነገሮች

ምድርን እንደ ጋሻ ሆነው የሚከልሉ አስደናቂ ነገሮች

ምድርን እንደ ጋሻ ሆነው የሚከልሉ አስደናቂ ነገሮች

ፈር ገዳይ በሆኑ ጨረሮችና በሚቲሮይድስ የተሞላ ስለሆነ ለሕይወት አደገኛ ቦታ ነው። ሰማያዊ ቀለም ያላት ፕላኔታችን ግን እነዚህ ከጠፈር የሚመጡ አደገኛ ነገሮች በሚወረወሩበት ቀጠና ውስጥ ብታልፍም ብዙም ጉዳት አያገኛትም። ከጉዳት ልታመልጥ የቻለችው ለምንድን ነው? ምድር አስደናቂ የሆኑ መከላከያዎች ስላሏት ነው፤ እነሱም ኃይለኛ የሆነው መግነጢሳዊ መስክ (ማግኔቲክ ፊልድ) እና ለእሷ ታስቦ የተሠራው ከባቢ አየር ናቸው።

የምድር መግነጢሳዊ መስክ ከምድር እምብርት ጀምሮ እስከ ጠፈር የተዘረጋው መግነጢሳዊ መስክ ለምድር እንደ ጋሻ ሆኖ የሚያገለግለውን በዓይን የማይታየውን ማግኔቶስፌር (በስተቀኝ ያለውን ሥዕል ተመልከት) ፈጥሯል። ይህ ጋሻ ከጠፈር የሚመጣው ጎጂ ጨረር ከፍተኛ ጉዳት እንዳያደርስብን እንዲሁም ከፀሐይ የሚመነጩ ነገሮች አደጋ እንዳያስከትሉብን ይከላከልልናል። ከፀሐይ ከሚመነጩት አደገኛ ነገሮች መካከል ያለማቋረጥ የኤሌክትሪክ ቅንጣቶች የሚፈሱበትን ጅረት የያዘው የፀሐይ ነፋስ፣ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሃይድሮጂን ቦምቦችን ያህል ኃይል በደቂቃዎች ውስጥ ማመንጨት የሚችሉት ከፀሐይ የሚወጡ ፍንጣሪዎች እንዲሁም ከፀሐይ ከላይኛው ክፍል ላይ በቢሊዮን ቶን የሚቆጠሩ ቁሶች ተነስተው ወደ ጠፈር እንዲወረወሩ የሚያደርጉት ኮሮናል ማስ ኢጀክሽንስ ይገኙበታል። ከፀሐይ የሚወጡ ፍንጣሪዎችም ሆኑ ኮሮናል ማስ ኢጀክሽንስ በምድር መግነጢሳዊ ዋልታዎች አካባቢ በሚገኘው የላይኛው የከባቢ አየር ክፍል ላይ በቀለም ያሸበረቀ ደማቅ ብርሃን ማለትም አውሮራ (በስተቀኝ በኩል ከታች ያለውን ሥዕል ተመልከት) እንዲታይ ያደርጋሉ።

የምድር ከባቢ አየር ለምድር ተጨማሪ ከለላ ሆኖላታል። የከባቢ አየር የላይኛው ክፍል ማለትም ስትራቶስፌር ወደ ምድር ከሚመጣው አልትራቫዮሌት ጨረር ውስጥ 99 በመቶ የሚሆነውን ውጦ የሚያስቀረውን ኦዞን የተባለ የኦክስጅን ቅንብር ይዟል። በመሆኑም ይህ የኦዞን ሽፋን ሰዎችንና ፕላንክተን የሚባሉትን በባሕር ውስጥ የሚገኙ ጥቃቅን እጽዋትንና እንስሳትን ጨምሮ ሕይወት ያላቸውን ነገሮች በሙሉ ከአደገኛ ጨረር ይከላከላል። የሚያስገርመው ነገር በከባቢ አየር የላይኛው ክፍል የሚገኘው ኦዞን የተወሰነ መጠን የለውም፤ ይሁንና የአልትራቫዮሌቱ ጨረር ኃይል በጨመረ ወይም በቀነሰ መጠን ይህ የኦዞን ክፍልም በተመሳሳይ ይጨምራል ወይም ይቀንሳል። ይህም የኦዞን ሽፋን ለምድር አስደናቂና አስተማማኝ ከለላ እንዲሆናት አስችሏል።

ከዚህም በተጨማሪ ከባቢ አየር በየዕለቱ በሚሊዮን በሚቆጠሩ ሚቲሮይድስ በተባሉ ተወርዋሪ አካላት እንዳንደበደብ ይከላከልልናል፤ እነዚህ ሚቲሮይድስ ከትንሽ ቅንጣት እስከ ትልቅ ድንጋይ የሚደርስ መጠን አላቸው። ደግነቱ ከእነዚህ ሚትሮይድስ መካከል አብዛኞቹ በከባቢ አየር ውስጥ ተቃጥለው ይጠፋሉ፤ በዚህ ጊዜ ኃይለኛ ብርሃን ስለሚፈጥሩ ሚቲዮር ወይም ተወርዋሪ ኮከቦች ተብለው ይጠራሉ።

ለምድር ጋሻ ሆነው የሚያገለግሉት እነዚህ ከለላዎች እንደ ሙቀትና ብርሃን የመሳሰሉት ለሕይወት አስፈላጊ የሆኑ ጨረሮች እንዳያልፉ አይከለክሉም። ከዚህም በተጨማሪ ከባቢ አየር፣ ሙቀት ለሁሉም የምድር ክፍል እንዲዳረስ የሚረዳ ከመሆኑም በላይ ምሽት ላይ ደግሞ ብዙ ሙቀት እንዳይወጣ እንደ ብርድ ልብስ በመሆን ይከላከላል።

የምድር ከባቢ አየርና መግነጢሳዊ መስክ በሚያስደንቅ መንገድ የተሠሩ ከመሆናቸውም በላይ ሰዎች እስከ አሁንም ድረስ ስለ እነዚህ ነገሮች አሠራር ሙሉ በሙሉ አልተረዱም። ስለ ሌላኛው የምድር ገጽታ ማለትም በላይዋ ላይ ስለሚገኘው ውኃ በምናነብበት ጊዜም መደመማችን አይቀርም።