በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወፎች ከሕንፃዎች ጋር ሲጋጩ

ወፎች ከሕንፃዎች ጋር ሲጋጩ

ወፎች ከሕንፃዎች ጋር ሲጋጩ

ግንደ ቆርቁር የሚባለው ወፍ ሰማይ ጠቀስ ከሆነ አንድ ፎቅ ጋር ተጋጨና መሬት ላይ ወደቀ። ቀኑ ገና ባይመሽም ወፉ የሕንፃውን መስታወት አላየውም ነበር። አንድ መንገደኛ ወፉን ወድቆ ሲያየው ስላሳዘነው ሊተርፍ እንደሚችል በማሰብ ይንከባከበው ጀመር። ብዙም ሳይቆይ ሰውየው እንዳሰበው ሆነለት፤ ወፉ ድምፅ ካሰማ በኋላ ቆመና ሰውነቱን አራግፎ በረረ። *

የሚያሳዝነው ነገር ከሕንፃ ጋር ተጋጭተው ከከባድ ጉዳት የሚያመልጡት ሁሉም ወፎች አይደሉም። እንዲያውም ከቤት ጋር ከሚጋጩት ወፎች ውስጥ ግማሾቹ ይሞታሉ። ኦዱቦን የተባለው ማኅበር እንደገለጸው ከሆነ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ብቻ በየዓመቱ ከ100 ሚሊዮን የሚበልጡ ወፎች ከተለያዩ ሕንፃዎች ጋር ተጋጭተው እንደሚሞቱ ጥናቶች ያመለክታሉ። እንዲያውም አንዳንድ ተመራማሪዎች ይህ አኃዝ ወደ አንድ ቢሊዮን ሊጠጋ እንደሚችል ይናገራሉ! ይሁንና ወፎች ከሕንፃዎች ጋር የሚጋጩት ለምንድን ነው? ወፎች እንዲህ ያለ ጉዳት እንዳይደርስባቸው ማድረግ ይቻል ይሆን?

መስታወትና ብርሃን ለአእዋፍ ጠንቅ ናቸው

መስታወት በወፎች ላይ አደጋ ያስከትላል። መስኮቶች ንጹሕ በሚሆኑበት ጊዜ በአካባቢው ያሉትን ዕፅዋትና ሰማዩን ያንጸባርቃሉ፤ ወፎቹ ይህንን ስለማያውቁ በፍጥነት እየበረሩ ከመስታወቱ ጋር ይላተማሉ። በተጨማሪም ወፎች በቤት ውስጥ ለጌጥ የተቀመጡ ተክሎችን በመስታወቱ ውስጥ ሊያዩና በእነሱ ላይ ለማረፍ ሲሞክሩ ሊጋጩ ይችላሉ።

ቀለም የተቀባ የሚያንጸባርቅ መስታወትም እንኳን በወፎች ላይ አደጋ ሊያስከትል ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ወፎች የሚያዩት መስታወቱን ሳይሆን የአካባቢውን ወይም የሰማዩን ነጸብራቅ ስለሚሆን ለጉዳት ይዳረጋሉ። ሌላው ቀርቶ ወፎች፣ በዱር አራዊትና በአእዋፋት መጠለያ ማዕከሎች ውስጥ በሚገኙ እንግዶች በሚያርፉባቸው ሕንጻዎችና በመመልከቻ ማማዎች ላይ ካሉት መስታወቶች ጋር ተጋጭተው ይሞታሉ! በወፎች ጥናትና በሥነ ሕይወት መስክ የተሰማሩት ፕሮፌሰር ዳንኤል ክሌም እንዳሉት ከሆነ በአእዋፋት መኖሪያ ላይ የሚደርሰውን ውድመት ሳይጨምር ለወፎች መሞት ምክንያት ከሆኑት የሰው ልጅ እንቅስቃሴዎች መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀሰው ከመስታወት ጋር እየተላተሙ መሞታቸው ነው።

በተለይም አንዳንድ ወፎች ለእንደዚህ ዓይነቱ አደጋ የተጋለጡ ናቸው። ለምሳሌ ያህል፣ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የሚፈልሱ አብዛኞቹ ዘማሪ ወፎች የሚጓዙት በሌሊት ሲሆን በተወሰነ መጠንም ቢሆን አቅጣጫቸውን የሚለዩት ከዋክብትን በመመልከት ነው። በመሆኑም በረዣዥም ሕንፃዎች ላይ ያሉ መብራቶች ሊያደናግሯቸው ይችላሉ። እንዲያውም አንዳንዶቹ ወፎች በጣም ከመደናገራቸው የተነሳ፣ ዝለው እስኪወድቁ ድረስ በሕንፃው ዙሪያ ይበራሉ። በተጨማሪም ዝናብ በሌሊት ሲዘንብ ወይም ሰማዩ በድቅድቅ ደመና ሲሸፈን ወፎች ይበልጥ ለአደጋ ይጋለጣሉ። እንዲህ ባሉት ጊዜያት ወፎች ዝቅ ብለው መብረር ስለሚቀናቸው ከረዣዥም ሕንፃዎች ጋር የመላተም አጋጣሚያቸው ይሰፋል።

በወፎች ብዛት ላይ ያስከተለው ተጽዕኖ

አንድ ሪፖርት እንደገለጸው ከሆነ በቺካጎ፣ ኢሊዮኒስ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሚገኝ አንድ ረዥም ሕንፃ ብቻ በወፎች ፍልሰት ወቅት በአማካይ 1,480 ወፎችን ለሞት ዳርጓል። በመሆኑም ይህ ሕንጻ በ14 ዓመታት ውስጥ 20,700 ወፎችን ገድሏል ማለት ነው። ከሕንጻው ጋር የተጋጩት ወፎች ትክክለኛ ቁጥር ከዚህ በእጅጉ እንደሚበልጥ ግልጽ ነው። ከዚህም በላይ ፋታል ላይት አዌርነስ ፕሮግራም የተሰኘው በቶሮንቶ፣ ካናዳ የሚገኘው ድርጅት ዳይሬክተር የሆኑት ማይክል መሱር እንዳሉት ከሆነ እነዚህ ወፎች “እርግብ፣ የባሕር ጭላት ወይም ዝይ” ሳይሆኑ “ዝርያቸው ሊጠፋ የተቃረቡ” ናቸው።

ለምሳሌ ያህል፣ በአውስትራሊያ 2,000 ብቻ እንደቀሩ ከሚነገርላቸው ትንንሽ በቀቀኖች መካከል 30 የሚያህሉት ከመስታወት ጋር በመጋጨታቸው ሳቢያ በአንድ ዓመት ውስጥ እንደሞቱ በቅርቡ ተገልጿል። ከምድር ገጽ እንደጠፋ የሚነገረው ባችማንስ ዋርብለር የሚባለው ወፍ ቅሪተ አካል በዩናይትድ ስቴትስ ባሉ ሙዚየሞች ውስጥ የሚገኝ ሲሆን ቅሪተ አካሉ በአብዛኛው የተሰበሰበው በፍሎሪዳ ካለ የወደብ መብራት ማማ ሥር ነው።

ከሕንፃ ጋር ተላትመው ከሞት ከተረፉት ወፎች መካከል ብዙዎቹ ከባድ ጉዳት ይደርስባቸዋል። ይህ ደግሞ በተለይ ከቦታ ወደ ቦታ ለሚፈልሱ ወፎች አደገኛ ሊሆን ይችላል። እነዚህ ወፎች ቆስለው በሕንፃዎች መካከል ከወደቁ በረሃብ ሊሞቱ አሊያም ይህን አጋጣሚ መጠቀም የለመዱ እንዳንድ እንስሳትን ጨምሮ ለጠላቶቻቸው ሲሳይ ሊሆኑ ይችላሉ።

ሕንፃዎች በወፎች ላይ የሚያደርሱትን ጉዳት መከላከል ይቻላል?

ወፎች ከመስታወት ጋር እንዳይጋጩ ከተፈለገ መስታወቱን ሊለዩትና ጥሰውት ማለፍ እንደማይችሉ ሊያውቁ ይገባል። ለዚህም ሲባል አንዳንድ ሰዎች አካባቢያቸውን በመስኮት እያዩ የመደሰት መብታቸውን መሥዋዕት በማድረግ፣ ወፎች ሊጋጩ በሚችሉበት የቤታቸው መስኮት ላይ ሥዕል አሊያም ሌላ ምልክት ይለጥፋሉ፤ ወይም ደግሞ ወፎች በቀላሉ ሊያዩት የሚችሉትን ነገር ከውጭ በኩል ያስቀምጣሉ። ክሌም እንደተናገሩት ከሆነ ዋናው ነገር ሥዕሎቹ ወይም ምልክቶቹ መለጠፋቸው ሳይሆን መስታወቱን ምን ያህል ይሸፍኑታል የሚለው ነው። ክሌም ያደረጉት ጥናት እንዳመለከተው በምልክቶቹ መካከል ያለው ርቀት በአግድም ከ5 ሴንቲ ሜትር፣ ወደታች ደግሞ ከ10 ሴንቲ ሜትር መብለጥ የለበትም።

በሌሊት የሚበሩ ከቦታ ወደ ቦታ የሚፈልሱ ወፎችን ለመርዳትስ ምን ማድረግ ይችላል? “ወፎች በሌሊት ሲበርሩ ከሕንፃዎች ጋር እንዳይጋጩ ለማድረግ . . . አብዛኛውን ጊዜ መብራቶችን ማጥፋት ብቻ በቂ ሊሆን ይችላል” በማለት የሥነ ምሕዳር ምርምር አማካሪ የሆኑት ሌስሊ ኢቫንስ ኦግደን ይናገራሉ። በአሁኑ ጊዜ በአንዳንድ ከተሞች፣ ሰማይ ጠቀስ ፎቆች ላይ ለጌጥ የሚደረጉ መብራቶች በተለይ ወፎች በሚፈልሱበት ወራት በሌሊት ከተወሰነ ሰዓት በኋላ እንዲደበዝዙ ወይም እንዲጠፉ ይደረጋል። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ወፎች በረዣዥም ሕንፃዎች መስታወቶች ላይ በሚያዩት የሰማይ ነጸብራቅ ተታልለው እንዳይጋጩ መስኮቱ ላይ የሽቦ ወንፊት ይደረጋል።

እንዲህ ዓይነቶቹን እርምጃዎች መውሰድ የወፎችን ሞት 80 በመቶ እንደሚቀንሰውና በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወፎችን ሕይወት ሊታደግ እንደሚችል ይታመናል። ይሁን እንጂ ሰዎች ብርሃንና መስታወት ስለሚወዱ መሠረታዊው ችግር አይወገድም። ስለዚህ እንደ ኦዱቦን ማኅበር ያሉ የወፎችን ደህንነት ለማስጠበቅ የተቋቋሙ ድርጅቶች አርክቴክቶችና ባለሀብቶች ተፈጥሮን ከግምት እንዲያስገቡ ለማሳመን ጥረት እያደረጉ ናቸው።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.2 ጉዳት የደረሰባቸውን ወፎች ለመያዝ መሞከር አደገኛ ሊሆን ይችላል፤ ምክንያቱም ልትረዳቸው መሆኑን አያውቁም። በተጨማሪም አንዳንድ ወፎች ወደ ሰዎች ሊተላለፍ የሚችል በሽታ ሊኖርባቸው ይችላል። ስለዚህ ጉዳት የደረሰበትን ወፍ ለመርዳት የምትፈልግ ከሆነ ጓንት አድርግ፤ ከጨረስክ በኋላም እጅህን ታጠብ። ለጤንነትህ የምትሰጋ ከሆነ ወደ ወፉ አትጠጋ። አስፈላጊ ከሆነ የባለሙያ እርዳታ መጠየቅ ትችላለህ።

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ወፎቹ ሁሉ የት ደረሱ?

በዩናይትድ ስቴትስ ከሰው ልጆች እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ በየዓመቱ የሚሞቱትን ወፎች በተመለከተ የቀረበ ግምታዊ አኃዝ።

ራዲዮን ጨምሮ ሌሎች የመገናኛ ብዙሐን ማሰራጫ ጣቢያ ማማዎች—40 ሚሊዮን

ፀረ ተባይ መድኃኒቶች—74 ሚሊዮን

የቤትና የዱር ድመቶች—365 ሚሊዮን

የመስኮት መስታወቶች —ከ100 ሚሊዮን እስከ 1 ቢሊዮን

የአእዋፋት መኖሪያ ውድመት—በትክክል ባይታወቅም ከሁሉ የከፋው የሞት መንስኤ እንደሆነ ይገመታል

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በየዓመቱ ቢያንስ 100 ሚሊዮን የሚሆኑ ወፎች ከመስኮቶች ጋር በመላተም ይሞታሉ

[ምንጭ]

© Reimar Gaertner/age fotostock