በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የወደፊቱ ዕጣህ አስቀድሞ ተወስኗል?

የወደፊቱ ዕጣህ አስቀድሞ ተወስኗል?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

የወደፊቱ ዕጣህ አስቀድሞ ተወስኗል?

ብዙ ሰዎች ሕይወታቸውና የወደፊቱ ዕጣቸው ከእነሱ በላይ የሆነ ኃይል ባለው አንድ አካል አስቀድሞ እንደተወሰነ ያምናሉ። እነዚህ ሰዎች፣ ከውልደት እስከ ሕልፈት ድረስ የሚያጋጥሙንን ነገሮች አምላክ አስቀድሞ እንደጻፈና ሁላችንም በተጻፈልን መሠረት እንደምንኖር ይሰማቸዋል። ‘ደግሞም እኮ አምላክ የሚሳነው ነገር የለም፤ ሁሉንም ነገር ያውቃል። በመሆኑም ቀደም ሲል ስለነበሩት፣ አሁን ስላሉትና ወደፊት ስለሚኖሩት ሁኔታዎች እያንዳንዷን ነገር በዝርዝር እንደሚያውቅ ጥርጥር የለውም’ ይላሉ።

አንተስ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይሰማሃል? አምላክ ሕይወታችንንና የመጨረሻ ዕጣችንን አስቀድሞ ወስኗል? በሌላ አነጋገር የራሳችንን ምርጫ የማድረግ ነፃነት አለን ወይስ እንዲህ ያለው አመለካከት ተጨባጭነት የሌለው ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ይህን አስመልክቶ ምን ይላል?

የማወቅ ችሎታውን የሚጠቀምበት እንደ አስፈላጊነቱ ነው ወይስ ሁልጊዜ?

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ አስቀድሞ የማወቅ ችሎታ እንዳለው በግልጽ ይናገራል። ኢሳይያስ 46:10 አምላክ “የመጨረሻውን ከመጀመሪያው” ያውቃል ይላል። ሌላው ቀርቶ በርካታ ትንቢቶችን ለማስጻፍ በሰው ልጆች ተጠቅሟል። (2 ጴጥሮስ 1:21) በተጨማሪም ያስጻፋቸው ትንቢቶች ሁልጊዜ ፍጻሜያቸውን ያገኛሉ፤ ምክንያቱም አምላክ በትንቢት ያስነገራቸውን ዝርዝር ጉዳዮች አንድም ሳይቀር ለማስፈጸም የሚያስችል ጥበብና ኃይል አለው። ስለሆነም አምላክ ወደፊት የሚሆኑትን ነገሮች ማወቅ ብቻ ሳይሆን አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ አስቀድሞ መወሰንም ይችላል። ይህ ሲባል ግን አምላክ የእያንዳንዱን ሰው የወደፊት ዕጣ አልፎ ተርፎም የሚድኑትን ሰዎች ቁጥር አስቀድሞ ወስኗል ማለት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ እንደዚያ ማለት እንዳልሆነ ይናገራል።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ አስቀድሞ የመወሰን ችሎታውን የሚጠቀምበት ሁልጊዜ ሳይሆን አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ብቻ እንደሆነ ይናገራል። ለምሳሌ ያህል፣ አምላክ ጻድቅ የሆኑ “እጅግ ብዙ ሕዝብ” በዚህ ሥርዓት መጨረሻ በክፉዎች ላይ ከሚደርሰው ጥፋት እንደሚተርፉ አስቀድሞ ተናግሯል። (ራእይ 7:9, 14) ይሁን እንጂ አምላክ፣ እጅግ ብዙ ሕዝብ የተባሉት ቁጥራቸው ስንት እንደሆነ አለመግለጹን ልብ በል። እንዲህ ያላደረገው ለምንድን ነው? የእያንዳንዱን ግለሰብ የመጨረሻ ዕጣ አስቀድሞ ስላልወሰነ ነው። አምላክ ብዙ ልጆች እንዳሉት አፍቃሪ አባት ነው። ከልጆቹ መካከል የተወሰኑት ለሚያሳያቸው ፍቅር ጥሩ ምላሽ እንደሚሰጡ ቢያውቅም ቁጥራቸውን ግን አስቀድሞ አይወስንም።

አምላክ ያለውን አስቀድሞ የመወሰን ችሎታ ኃይሉን ከሚጠቀምበት መንገድ ጋር ለማወዳደር ሞክር። አምላክ ሁሉን ቻይ እንደመሆኑ መጠን በኃይሉ ተወዳዳሪ የለውም። (መዝሙር 91:1፤ ኢሳይያስ 40:26, 28) ይሁንና እንዲህ ሲባል ኃይሉን ያላንዳች ገደብ ይጠቀምበታል ማለት ነው? በፍጹም። ለምሳሌ ያህል፣ የጥንቷ እስራኤል ጠላት በነበሩት በባቢሎናውያን ላይ ትክክለኛው ጊዜ ከመድረሱ በፊት እርምጃ ከመውሰድ ተቆጥቧል። አምላክ “ራሴንም ገታሁ” ሲል ተናግሯል። (ኢሳይያስ 42:14) አምላክ አስቀድሞ የማወቅና የመወሰን ችሎታውን ከሚጠቀምበት መንገድ ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ይሖዋ፣ ምርጫ የማድረግ ነፃነታችንን ለማክበር ሲል ራሱን ይገታል።

ይሖዋ ኃይሉን ይቆጣጠረዋል ሲባል የአቅም ገደብ ወይም ጉድለት አለበት ማለት አይደለም። እንዲያውም እንዲህ ማድረጉ ታላቅነቱን ጎላ አድርጎ የሚያሳይ ነው። አምላክ ሁሉንም ነገር ማወቅ የሚችልና ታላቅ ኃይል ያለው ቢሆንም ሉዓላዊነቱን የሚያሳየው ፍቅራዊ በሆነ መንገድ ነው፤ በተጨማሪም የማሰብ ችሎታ ላላቸው ፍጡራኑ የሰጣቸውን የመምረጥ ነፃነት ያከብራል፤ ይህ ደግሞ እንድንወደው ያደርገናል።

በሌላ በኩል ደግሞ እስከ ዛሬ ድረስ የተከሰቱትን አሰቃቂ አደጋዎችና መጥፎ ድርጊቶች ጨምሮ አምላክ ሁሉንም ነገር አስቀድሞ የወሰነ ቢሆን ኖሮ በዓለም ላይ ለሚታየው አሳዛኝ ሁኔታና መከራ ሁሉ ተጠያቂው እሱ ነው ማለት ነው። ስለሆነም አምላክ ሁሉንም ነገር አስቀድሞ ወስኗል የሚለውን ትምህርት በጥንቃቄ ስናጤነው አምላክን እንድናከብረው ሳይሆን እንድንጠላው ያደርገናል። በተጨማሪም ጨካኝ፣ የሚያዳላና ፍቅር የጎደለው አምላክ እንደሆነ አድርገን እንድንመለከተው ያደርገናል፤ ይህ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እሱ ከሚናገረው ሐሳብ ፍጹም ተቃራኒ ነው።—ዘዳግም 32:4

ምርጫው የአንተ ነው

አምላክ በአገልጋዩ በሙሴ አማካኝነት እስራኤላውያንን እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ ‘ሕይወትንና ሞትን በፊትህ አስቀምጫለሁ፤ ሕይወትን ምረጥ። ይኸውም አምላክህን በመውደድ፣ ቃሉን በማዳመጥና ከእሱ ጋር በመጣበቅ ነው። ምክንያቱም አምላክ ሕይወትህ ነው፤ ረጅም ዕድሜም ይሰጥሃል።’ (ዘዳግም 30:19, 20) አምላክ፣ እስራኤላውያን እሱን በመውደድ ሕይወት እንዲያገኙ አሊያም ሕግጋቱን ችላ በማለት እንዲሞቱ በግለሰብ ደረጃ አስቀድሞ ወስኖ ቢሆን ኖሮ ከላይ ያለው ሐሳብ ትርጉም የለሽና ለይምሰል የተነገረ ይሆን ነበር። ታዲያ ‘ፍትሕን የሚወደውና’ የፍቅር ተምሳሌት የሆነው አምላክ እንዲህ ያለ ግብታዊነት የሚንጸባረቅበት ድርጊት ይፈጽማል ብለህ ታምናለህ?—መዝሙር 37:28፤ 1 ዮሐንስ 4:8

ፍጻሜያቸውን እያገኙ ያሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች የዚህ ሥርዓት መጨረሻ በፍጥነት እየቀረበ መሆኑን ስለሚጠቁሙ አምላክ አገልጋዮቹ ሕይወትን እንዲመርጡ ያቀረበውን ጥሪ መቀበላችን በተለይ በዛሬው ጊዜ በጣም አስፈላጊ ነው። (ማቴዎስ 24:3-9፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) ታዲያ ሕይወትን መምረጥ የምንችለው እንዴት ነው? በዋነኝነት ይህን ማድረግ የምንችለው የጥንቶቹ እስራኤላውያን የተዉትን ምሳሌ በመከተል ነው።

‘ሕይወትን መምረጥ’ የምትችለው እንዴት ነው?

ሕይወትን የምንመርጠው ‘አምላክን በመውደድ፣ ቃሉን በማዳመጥና ከእሱ ጋር በመጣበቅ ነው።’ እርግጥ ነው፣ ይህን ማድረግ የምንችለው አምላክን እውን እንደሆነ አካል አድርገን ስናውቀውና ከእኛ የሚፈልገውን ነገር ስንገነዘብ ብቻ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ አምላክ ሲጸልይ “እውነተኛ አምላክ የሆንኸውን አንተንና የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት” ብሏል።—ዮሐንስ 17:3 አዲሱ መደበኛ ትርጉም

ይህ ውድ እውቀት የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛል። (ዮሐንስ 17:17፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16) በእርግጥም ከፈጣሪ ያገኘነው ይህ ስጦታ፣ አምላክ የወደፊት ዕጣችንን አስቀድሞ እንዳልወሰነና በቃሉ ውስጥ ባሰፈረልን ሐሳብ ላይ የተመሠረተ ምርጫ እንድናደርግ እንደሚፈልግ የሚያሳይ ግልጽ ማስረጃ ነው።—ኢሳይያስ 48:17, 18

አምላክ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት እንደሚከተለው ያለን ያህል ነው፦ ‘ለሰው ልጆችና ለምድር ያለኝ ዓላማ ይህ ነው፤ የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ማድረግ የሚኖርባችሁም ይህንኑ ነው። ምክሬን ለማዳመጥም ሆነ ችላ ለማለት መወሰን የራሳችሁ ምርጫ ነው።’ በእርግጥም አምላክ አስቀድሞ የመወሰን ችሎታውን የሚጠቀምበት ምርጫ የማድረግ ነፃነታችንን ሳይጋፋ ነው። አንተስ ‘አምላክን በማዳመጥና ከእሱ ጋር በመጣበቅ’ ሕይወትን ትመርጥ ይሆን?

ይህን አስተውለኸዋል?

አምላክ አስቀድሞ የማወቅ ችሎታውን የሚጠቀመው እስከ ምን ድረስ ነው?—ዘዳግም 30:19, 20፤ ኢሳይያስ 46:10

አምላክ በሰዎች ላይ የሚደርሱትን መጥፎ ነገሮች ጨምሮ እያንዳንዱን ነገር አስቀድሞ የማይወስነው ለምንድን ነው?—ዘዳግም 32:4

የወደፊት ሁኔታችን የሚወሰነው በምንድን ነው?—ዮሐንስ 17:3

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ አስቀድሞ የመወሰን ችሎታውን የሚጠቀምበት ሁልጊዜ ሳይሆን አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ብቻ እንደሆነ ይናገራል