በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የማስታወስ ችሎታህን ማሻሻል ትችላለህ!

የማስታወስ ችሎታህን ማሻሻል ትችላለህ!

የማስታወስ ችሎታህን ማሻሻል ትችላለህ!

“የማስታወስ ችሎታ ሕይወታችን ይበልጥ ጣዕም ያለው እንዲሆን ያደርጋል። ይህ ችሎታ ባይኖረን ኖሮ ያሳለፍነውን ነገር ሁሉ እንረሳና መልካችንን በመስታወት ስንመለከት እንኳ ራሳችንን ማወቅ አዳጋች ይሆንብን ነበር። እያንዳንዱ ቀንና እያንዳንዱ ክስተት ከሌላው ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት ስለማይኖረው ካሳለፍነው ነገር መማርም ሆነ የወደፊቱን ጊዜ በተስፋ መጠበቅ አንችልም ነበር።”—“ሚስትሪስ ኦቭ ዘ ማይንድ”

አንዳንድ ወፎች ለክረምት ብለው ያከማቹት ጥራጥሬ ያለበትን ቦታ ከወራት በኋላ ማስታወስ የሚችሉ ሲሆን ሽኮኮዎች ደግሞ ለውዝ የቀበሩበትን ቦታ አይረሱም፤ እኛ ግን ከአንድ ሰዓት በፊት ያስቀመጥነው ዕቃ የት እንዳለ ማስታወስ ይቸግረን ይሆናል። አዎን፣ አብዛኞቻችን የመርሳት ችግር እንዳለብን በመናገር እናማርራለን። ሆኖም የሰው አንጎል ፍጽምና የጎደለው ቢሆንም አስደናቂ የሆነ የመማርና የማስታወስ ችሎታ አለው። ሚስጥሩ ያለው አእምሯችንን ሙሉ በሙሉ በመጠቀሙ ላይ ነው።

ከፍተኛ ችሎታ

ተለቅ ያለ ብርቱካን የሚያህለው የሰው ልጆች አንጎል የሚመዝነው 1.4 ኪሎ ግራም ያህል ነው። ይሁን እንጂ አንጎላችን በአስደናቂ ሁኔታ እርስ በርስ የተጠላለፉ 100 ቢሊዮን የሚያህሉ ኒውሮኖችን ወይም የነርቭ ሴሎችን ይዟል። እንዲያውም አንዱ የነርቭ ሴል ብቻ 100,000 ከሚያህሉ የነርቭ ሴሎች ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል። ነርቮቹ እንዲህ ባለ ሁኔታ እርስ በርስ የተያያዙ መሆናቸው አእምሯችን እጅግ ብዙ መረጃዎችን የመያዝ ችሎታ እንዲኖረው አስችሎታል። ተፈታታኙ ነገር ግን አንድ ሰው በአንጎሉ ውስጥ የተቀመጠውን መረጃ በፈለገው ጊዜ ማስታወስ የመቻሉ ጉዳይ ነው። ያልተማሩ ሰዎችን ጨምሮ አንዳንዶች ከፍተኛ የማስታወስ ችሎታ አላቸው።

ለምሳሌ ያህል፣ በምዕራብ አፍሪካ የሚኖሩት ግሪዮ ተብለው የሚጠሩት ማንበብና መጻፍ የማይችሉ የጎሣ ታሪክ አዋቂዎች በመንደሮቻቸው ውስጥ የሚኖሩ ሰዎችን የዘር ሐረግ እስከ ብዙ ትውልድ ድረስ ወደኋላ መጥራት ይችላሉ። ሩትስ በተሰኘው መጽሐፉ የፑሊትዘርን ሽልማት ያገኘው አሌክስ ሃሌይ የተባለው አሜሪካዊ ደራሲ ስድስት ትውልድ ያህል ወደኋላ በመመርመር በጋምቢያ የሚገኘውን የዘር ሐረጉን እንዲያገኝ ያስቻሉት ግሪዮዎች ነበሩ። ሃሌይ እንዲህ ብሏል፦ “በአፍሪካ የሚኖሩት የግሪዮዎች ውለታ አለብኝ። አንድ ግሪዮ ሲሞት አንድ ቤተ መጻሕፍት ተቃጥሎ የወደመ ያህል ነው መባሉ ተገቢ ነው።”

በተጨማሪም ገና በ19 ዓመቱ አንድን የኦርኬስትራ መሪ ተክቶ እንዲሠራ በተጠየቀ ጊዜ ታላቅ ችሎታ እንዳለው ሊታወቅ የቻለውን አርቱሮ ቶስካኒኒ የሚባል ታዋቂ ጣሊያናዊ የኦርኬስትራ መሪ እንደ ምሳሌ እንመልከት። ይህ ሰው የማየት ችሎታው ደካማ ቢሆንም በማስታወስ ችሎታው ብቻ ተጠቅሞ አይዳ የተሰኘውን ኦፔራ ከመጀመሪያው አንስቶ እስከ መጨረሻው ድረስ መምራት ችሏል!

እንደነዚህ ያሉ ልዩ ችሎታ ያላቸው ሰዎች ሊያስገርሙን ይችላሉ። ሆኖም አብዛኞቹ ሰዎች ከሚያስቡት በላይ ከፍተኛ የሆነ የማስታወስ ችሎታ አላቸው። አንተስ የማስታወስ ችሎታህን ለማሻሻል ትፈልጋለህ?

የማስታወስ ችሎታህን ማሻሻል የምትችለው እንዴት ነው?

የማስታወስ ችሎታ ሦስት ደረጃዎችን የያዘ ነው። እነሱም መረጃን ኮድ በመስጠት መመዝገብ፣ ማስቀመጥና ማስታወስ ናቸው። አእምሮህ አንድን መረጃ ኮድ በመስጠት የሚመዘግበው የመረጃውን ምንነት ለይቶ ሲያውቅና ሲገነዘብ ነው። ከዚያም ይህ መረጃ ወደፊት ልታስታውሰው በምትችልበት ሁኔታ ይቀመጣል። አንድን ነገር ማስታወስ የሚያቅተን ከእነዚህ ሦስት ነገሮች መካከል አንዱ ሲጎድል ነው።

የማስታወስ ችሎታ ራሱ በተለያየ መንገድ ሊከፈል የሚችል ሲሆን ከእነዚህ መካከል ከስሜት ሕዋሳት ጋር የተያያዘ የማስታወስ ችሎታ፣ የአጭር ጊዜ የማስታወስ ችሎታ እንዲሁም የረዥም ጊዜ የማስታወስ ችሎታ ይገኙበታል። ከስሜት ሕዋሳት ጋር የተያያዘ የማስታወስ ችሎታ እንደ ማሽተት፣ ማየትና መዳሰስ ባሉ የስሜት ሕዋሳቶች አማካኝነት መረጃዎችን ይቀበላል። የአጭር ጊዜ የማስታወስ ችሎታ የሚባለው አንድን ነገር አከናውነን እስክንጨርስ ድረስ የሚያገለግል ሲሆን ለጥቂት ጊዜ ብቻ የሚቆዩ አነስተኛ መጠን ያላቸው መረጃዎችን እንድናስታውስ ያስችለናል። በመሆኑም ቁጥር መደመር፣ ስልክ እስክንደውል ድረስ ቁጥሮቹን ማስታወስ እንዲሁም በምናነብበት ወይም በምናዳምጥበት ጊዜ የዓረፍተ ነገሩ መጨረሻ ላይ እያለን የመጀመሪያውን ሐሳብ ማስታወስ እንችላለን። ይሁን እንጂ ሁላችንም እንደምናውቀው የአጭር ጊዜ የማስታወስ ችሎታ ያለው ጠቀሜታ ውስን ነው።

አንድን መረጃ ለብዙ ጊዜ እንዲቆይ ለማድረግ ከፈለግህ መረጃው በረዥም ጊዜ የማስታወስ ችሎታህ ውስጥ መቀመጥ ይኖርበታል። ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? የሚከተሉት መሠረታዊ ሐሳቦች ሊረዱህ ይችላሉ።

ፍላጎት ለርዕሰ ጉዳዩ ፍላጎት እንዲያድርብህ አድርግ፤ እንዲሁም ይህን ርዕሰ ጉዳይ እየተማርክ ያለኸው ለምን እንደሆነ ለራስህ መላልሰህ ንገረው። ከራስህ ተሞክሮ መገንዘብ እንደምትችለው አንድን ነገር በስሜት የምትከታተል ከሆነ ያንን ነገር በቀላሉ ማስታወስ አይቸግርህም። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች እንዲህ ማድረጋቸው በእጅጉ ይጠቅማቸዋል። እነዚህ ግለሰቦች ሁለት ግቦችን ይኸውም ወደ አምላክ የመቅረብና ሰዎችን ስለ እሱ የማስተማር ዓላማን በአእምሯቸው ይዘው መጽሐፍ ቅዱስን ማንበባቸው የማስታወስ ችሎታቸው ይበልጥ እንዲጨምር ያደርጋል።—ምሳሌ 7:3፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16

ትኩረት መስጠት ሚስትሪስ ኦቭ ዘ ማይንድ የተሰኘው መጽሐፍ “እንደ እውነቱ ከሆነ አብዛኛውን ጊዜ ‘የምንረሳው’ ትኩረት ያልሰጠነውን ነገር ነው” በማለት ይናገራል። ታዲያ ለአንድ ነገር ትኩረት መስጠት እንድትችል ምን ሊረዳህ ይችላል? ለርዕሰ ጉዳዩ ፍላጎት አሳድር፤ ከተቻለ ደግሞ ማስታወሻ ጻፍ። ማስታወሻ መጻፍ አእምሯችን በጉዳዩ ላይ እንዲያተኩር ከማድረጉም በላይ የጻፍነውን ነገር በሌላ ጊዜ ለመከለስ ያስችለናል።

በሚገባ መረዳት ምሳሌ 4:7 “ያለህን ሁሉ ብታስከፍልህም ማስተዋልን ገንዘብህ አድርጋት” በማለት ይናገራል። አንድን ሐሳብ ወይም ትምህርት ካላስተዋልከው ወይም በሚገባ ካልተረዳኸው በደንብ ላታስታውሰው ምናልባትም እስከነጭራሹ ልትረሳው ትችላለህ። አንድን ርዕሰ ጉዳይ በሚገባ መረዳት በውስጡ ያሉት የተለያዩ ሐሳቦች እርስ በርሳቸው የሚዛመዱት እንዴት እንደሆነ ማስተዋልን ይጠይቃል። ለምሳሌ ያህል፣ በመካኒክነት ሙያ የሚሠለጥን አንድ ተማሪ ሞተር የሚሠራው እንዴት እንደሆነ በሚገባ ከተረዳ የሞተሩን ክፍሎች በተሻለ ሁኔታ ማስታወስ ይችላል።

ማደራጀት ተመሳሳይ የሆኑ ጽንሰ ሐሳቦችን ወይም ተዛማጅነት ያላቸው ሐሳቦችን በየፈርጁ አስቀምጥ። ለምሳሌ ያህል፣ የምግብ ሸቀጣ ሸቀጦችን ለመግዛት ስታስብ የሥጋ ዓይነቶች፣ አትክልቶች፣ ፍራፍሬዎች ወዘተ . . . በማለት ሸቀጣ ሸቀጦቹን በዓይነት በዓይነታቸው መመደብህ የምትገዛቸውን ነገሮች በቀላሉ ለማስታወስ ያስችልሃል። ከአምስት እስከ ሰባት የሚደርሱ ነገሮችን ብቻ አንድ ላይ በማድረግ መረጃውን መከፋፈልህ ለማስታወስ የሚረዳህ ሌላው መንገድ ነው። አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች የስልክ ቁጥሮችን በቀላሉ ለማስታወስ ሲሉ ቁጥሮቹን በልዩ ልዩ መንገድ ይከፋፍሏቸዋል። በመጨረሻም ዝርዝሩን በቅደም ተከተል ምናልባትም በፊደል ተራ ማስቀመጥህ ሊረዳህ ይችላል።

አንድን ነገር ድምፅን ከፍ አድርጎ መደጋገም ወይም መጥራት ልታስታውሰው የምትፈልገውን ነገር (ለምሳሌ ያህል፣ የማታውቀውን ቃል ወይም ሐረግ) ድምፅህን ከፍ አድርገህ ደጋግመህ መጥራትህ በነርቭ ሴሎችህ መካከል ያለው ግንኙነት ይበልጥ እንዲጠናከር ያደርጋል። ይህ የሚሆነው እንዴት ነው? በመጀመሪያ ደረጃ ቃሉን መጥራትህ ትኩረት እንድታደርግበት ያስገድድሃል። በሁለተኛ ደረጃ ቃሉን ስትጠራ አስተማሪህ ቃሉን በትክክል መጥራትህን ወይም አለመጥራትህን ሊነግርህ ይችላል። በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ የምትጠራውን ቃል ራስህ መስማትህ ሌሎቹ የአንጎልህ ክፍሎች እንዲሠሩ ያደርጋል።

በዓይነ ሕሊና መሳል ልታስታውስ የምትፈልገውን ነገር በዓይነ ሕሊናህ ሳለው። በዓይነ ሕሊናህ የሳልከውን ነገር በወረቀት ላይ ማስፈርህ እንደሚረዳ አስተውለህ ይሆናል። አንድን ጉዳይ በዓይነ ሕሊናህ መሳልህ ድምፅን ከፍ አድርጎ እንደመጥራት ሁሉ የአንጎልህ የተለያዩ ክፍሎች ይበልጥ እንዲሠሩ ያደርጋል። ከስሜት ሕዋሳትህ መካከል አብዛኞቹን በተጠቀምክባቸው መጠን መረጃው በአእምሮህ ውስጥ የመታተሙ አጋጣሚ የዚያኑ ያህል ሰፊ ይሆናል።

ማዛመድ አዲስ ነገር ስትማር ከዚህ በፊት ከምታውቀው ሌላ ነገር ጋር አዛምደው። የተማርከውን ነገር ቀደም ሲል ከምታውቃቸው ነገሮች ጋር ማዛመድህ አእምሮህ መረጃውን በቀላሉ ኮድ ሰጥቶ ለመመዝገብና በኋላም ለማስታወስ የሚያስችለውን ፍንጭ ይሰጠዋል። ለምሳሌ ያህል፣ የአንድን ሰው ስም ለማስታወስ እንድትችል ሰውየው ካለው አንድ ለየት ያለ ገጽታ ወይም ስሙን ለማስታወስ ከሚረዳህ ሌላ ነገር ጋር አያይዘው። ነገሩን ይበልጥ አስቂኝ በሆነ መንገድ ባዛመድከው መጠን የማስታወስ አጋጣሚህም የዚያኑ ያህል ይሰፋል። በቀላል አነጋገር ለማስታወስ ስለምንፈልጋቸው ሰዎች ወይም ነገሮች ማሰብ ይኖርብናል።

ሰርቺንግ ፎር ሜሞሪ የተሰኘው መጽሐፍ እንዲህ ብሏል፦ “አብዛኛውን ጊዜ በደመ ነፍስ ብቻ የምንመራ እንዲሁም ስለ አካባቢያችንና ስላደረግናቸው ነገሮች ቆም ብለን የማናስብ ከሆነ ስለነበርንበት ቦታም ሆነ ስላከናወንናቸው ነገሮች እምብዛም ላናስታውስ እንችላለን።”

ማዋሐድ ውኃ ወደ አፈር ውስጥ የሚገባው ቀስ በቀስ እንደሆነ ሁሉ አንተም ያገኘኸው መረጃ ወደ አእምሮህ እስኪሰርጽ ድረስ ጊዜ ስጠው። ይህን ማድረግ የሚቻልበት ከሁሉ የተሻለው መንገድ የተማርከውን ነገር መከለስ ምናልባትም ለሌላ ሰው መናገር ነው። ጥሩ ተሞክሮ ካገኘህ ወይም በመጽሐፍ ቅዱስ አሊያም መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት በሚረዱ ጽሑፎች ውስጥ የሚያንጽ ነገር ካነበብክ ለሌላ ሰው አካፍለው። ይህን ስታደርግ የማስታወስ ችሎታህ ይበልጥ የሚሻሻል ከመሆኑም ሌላ መረጃውን ያካፈልከው ሰው ይበረታታል፤ በመሆኑም ሁለታችሁም ትጠቀማላችሁ። መደጋገም የአእምሮ ማኅተም ነው መባሉ በእርግጥም ተገቢ ነው።

ለማስታወስ የሚረዱ ጠቃሚ ዘዴዎች

በጥንቶቹ ግሪክና ሮም ይኖሩ የነበሩ አንደበተ ርቱዕ ተናጋሪዎች ምንም ማስታወሻ ሳይመለከቱ ረጅም ንግግሮችን ያቀርቡ ነበር። እንዲህ ማድረግ የቻሉት እንዴት ነው? ለማስታወስ የሚረዱ ዘዴዎችን ይጠቀሙ ስለነበር ነው። እነዚህ ዘዴዎች፣ መረጃን በረዥም ጊዜ የማስታወስ ችሎታችን ውስጥ ለማስቀመጥና በፈለግንበት ጊዜ ለማስታወስ የሚረዱን ስልቶች ናቸው።

የጥንቶቹ ግሪካውያን ተናጋሪዎች ለማስታወስ የሚጠቀሙበት አንዱ ስልት ከቦታ ጋር የማያያዝ ዘዴ ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ የተገለጸውም በ477 ከክርስቶስ ልደት በፊት ሲሞኒዴስ በሚባል የጥንቷ ኬኦስ ተወላጅ የሆነ ግሪካዊው ገጣሚ ነበር። ይህ ዘዴ የማደራጀትና በዓይነ ሕሊና የመሳል ስልቶችን የያዘ ሲሆን መረጃውን በመንገድ ላይ ከሚገኝ ምልክት ወይም በቤት ውስጥ ካለ ዕቃ አሊያም በደንብ ከሚታወቅ ሌላ ነገር ጋር ማዛመድንም ይጨምራል። ይህን ዘዴ የሚጠቀሙ ሰዎች በሐሳባቸው ጉዞ በማድረግ ሊያስታውሱት የሚፈልጉትን እያንዳንዱን መረጃ በመንገዱ ላይ ከሚገኝ ጉልህ ምልክት ወይም ከአንድ ዕቃ ጋር ያያይዙታል። መረጃውን ለማስታወስ በሚፈልጉበት ጊዜ ያንኑ የሐሳብ ጉዞ ደግመው ይጓዙታል።— “የሐሳብ ጉዞ አድርግ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

በየዓመቱ በሚደረገው የማስታወስ ችሎታ ውድድር ላይ አሸናፊ በሆኑ ሰዎች ላይ የተደረገ አንድ ጥናት እንዳመለከተው እነዚህ ሰዎች ከፍተኛ የማስታወስ ችሎታ ሊኖራቸው የቻለው ከሌሎች የላቀ የማሰብ ችሎታ ስላላቸው አይደለም። ከዚህም በላይ አብዛኞቹ ተሳታፊዎች ከ40 እስከ 50 ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ነበሩ። ታዲያ ሚስጥሩ ምንድን ነው? ብዙዎቹ ይህን ችሎታ ያገኙት ለማስታወስ የሚረዱ ዘዴዎችን ውጤታማ በሆነ መንገድ በመጠቀማቸው እንደሆነ ተናግረዋል።

አንተስ ብዙ ቃላትን ማስታወስ ትፈልጋለህ? ለዚህ የሚረዳህ ውጤታማ ዘዴ ምሕፃረ ቃል መጠቀም ይኸውም ቃላቱ የሚጀምሩበትን ፊደል ወይም ፊደላት በመውሰድ አዲስ ቃል መፍጠር ነው። በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ ብዙ ሰዎች ሂዩሮን (Huron)፣ ኦንቴሪዮ (Ontario)፣ ሚሺገን (Michigan)፣ ኢይሬ (Erie) እና ሱፒሪየር (Superior) የሚባሉትን የአምስቱን ታላላቅ ሐይቆች ስም ለማስታወስ “ሆምስ” (“HOMES”) የሚለውን ምሕፃረ ቃል ይጠቀማሉ። ከዚህ ጋር የሚመሳሰለው ለማስታወስ የሚረዳ ሌላው ዘዴ ደግሞ ፊደላትን በቅደም ተከተል ማስቀመጥ ሲሆን የጥንት ዕብራውያን ይህን ዘዴ በስፋት ይጠቀሙበት ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በመዝሙር መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙት የአብዛኞቹ መዝሙሮች ስንኞች ወይም አንጓዎች የሚጀምሩት በዕብራይስጥ ፊደላት ቅደም ተከተል ነው። (የመዝሙር 25ን34ን37ን111ን112ን እና 119ን የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።) ይህ ጠቃሚ ዘዴ፣ መዘምራኑ በመዝሙር ምዕራፍ 119 ውስጥ የሚገኙትን 176 ስንኞች በሙሉ እንዲያስታውሱ ያስችላቸው ነበር!

አዎን፣ አንተም የማስታወስ ችሎታህን ማሠልጠንና ማሻሻል ትችላለህ። ጥናቶች እንዳመለከቱት የማስታወስ ችሎታ ከጡንቻ ጋር በጣም ይመሳሰላል። ብዙ በተጠቀምንበት መጠን ይበልጥ እየዳበረ የሚሄድ ሲሆን የዕድሜ መግፋት እንኳ አይገድበውም።

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ተጨማሪ ነጥቦች

አንድ ዓይነት ሙያ፣ አዲስ ቋንቋ ወይም የሙዚቃ መሣሪያ በመማር የማስታወስ ችሎታህ እንዲነቃቃ አድርግ።

በጣም አስፈላጊ በሆኑ ነገሮች ላይ አተኩር።

ለማስታወስ የሚረዱ ዘዴዎችን ተማር።

በቂ ውኃ ጠጣ። በሰውነትህ ውስጥ በቂ ፈሳሽ አለመኖሩ ሐሳብህ እንዲከፋፈል ያደርጋል።

በቂ እንቅልፍ ተኛ። አእምሯችን መረጃዎችን የሚያስቀምጠው በእንቅልፍ ወቅት ነው።

በምታጠናበት ጊዜ ዘና በል። ውጥረት፣ ኮርቲሶል የተባለው ሆርሞን እንዲመነጭ ያደርጋል፤ ይህ ሆርሞን ደግሞ በነርቮች መካከል ያለው ግንኙነት እንዲስተጓጎል ያደርጋል።

አልኮል ከልክ በላይ ከመጠጣትና ከማጨስ ተቆጠብ። አልኮል በአጭር ጊዜ የማስታወስ ችሎታ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር ከመሆኑም ሌላ የአልኮል ሱሰኛ መሆን ታያሚን የተባለው የቫይታሚን ቢ ዓይነት እጥረት እንዲያጋጥም ያደርጋል፤ ታያሚን የማስታወስ ችሎታችን በትክክል እንዲሠራ በማድረግ ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታል። ማጨስ ደግሞ አእምሯችን በቂ ኦክሲጂን እንዳያገኝ ያደርጋል። *

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.36 ብሬይን ኤንድ ማይንድ ከተባለ በኢንተርኔት የሚሠራጭ መጽሔት ላይ የተወሰደ።

[በገጽ 28 እና 29 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

 የሐሳብ ጉዞ አድርግ

እንደ ዳቦ፣ ዕንቁላል፣ ወተትና ቅቤ የመሳሰሉትን የምግብ ሸቀጣ ሸቀጦች ለመግዛት ስታስብ ዝርዝራቸውን ማስታወስ የምትችለው እንዴት ነው? ከቦታ ጋር የማያያዝ ዘዴ ተጠቅመህ በቤትህ ውስጥ ያሉትን ዕቃዎች ከሸቀጣ ሸቀጦቹ ጋር እያዛመድክ በዓይነ ሕሊናህ የሐሳብ ጉዞ ልታደርግ ትችላለህ።

የወንበርህ መቀመጫ በዳቦ እንደተሠራ፣

ከአምፖሉ ሥር ዕንቁላሎች ለመፈልፈል እንደተቀመጡ፣

ቤትህ ውስጥ የሚገኘው ጎልድፊሽ የተባለው ዓሣ በወተት ውስጥ እንደሚዋኝ፣

የቴሌቪዥንህ ስክሪን ደግሞ ቅቤ እንደተቀባ ሆኖ በሐሳብህ ይታይህ።

በሐሳብህ የምትስለው ነገር ይበልጥ አስቂኝ ወይም ያልተለመደ በሆነ መጠን ሸቀጣ ሸቀጦቹን በደንብ ማስታወስ ትችላለህ! ከዚያም መደብሩ ጋ ስትደርስ እንደገና የሐሳብ ጉዞ አድርግ።

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

መርሳት ባንችል ኖሮ ምን ይውጠን ነበር?

አስፈላጊ የሆነውንም ሆነ ያልሆነውን ነገር በሙሉ የምታስታውስ ቢሆን ኖሮ ሕይወትህ ምን ሊመስል እንደሚችል እስቲ አስብ። አእምሮህ በማይረቡ ነገሮች ከመሞላቱ ብዛት ትኩረትህን ለመሰብሰብ መቸገርህ አይቀርም ነበር። ኒው ሳይንቲስት መጽሔት እንደተናገረው በሕይወቷ ውስጥ የተከናወነውን እያንዳንዱን ነገር ማስታወስ የምትችል አንዲት ሴት “ሁኔታውን መርሳት አለመቻሏን ‘ማባሪያ የሌለው፣ ከቁጥጥር ውጭ የሆነና እጅግ አድካሚ’ የሆነ ‘ሸክም’ በማለት ገልጻዋለች።” ደግነቱ፣ አእምሯችን እርባና የሌለውን ወይም ጊዜ ያለፈበትን መረጃ ለቅሞ የማስወገድ ችሎታ ስላለው አብዛኞቻችን ይህ ዓይነቱ ችግር እንደማያጋጥመን ተመራማሪዎች ያምናሉ። ኒው ሳይንቲስት የተባለው መጽሔት እንዲህ ብሏል፦ “መርሳት መቻል፣ በጥሩ ሁኔታ የሚሠራ አንድ አእምሮ ሊኖረው የሚገባ አስፈላጊ ነገር ነው። አንድን ጠቃሚ ነገር መርሳታችን አእምሯችን አላስፈላጊ መረጃዎችን ለቅሞ የማስወገድ ችሎታው ከመጠን በላይ የሚሠራ መሆኑን ያሳያል።”