በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ገንዘብ ጌታህ ነው ወይስ አገልጋይህ?

ገንዘብ ጌታህ ነው ወይስ አገልጋይህ?

ገንዘብ ጌታህ ነው ወይስ አገልጋይህ?

በገንዘብ ሕመም እየተሠቃየህ ነው? ከዓለም ሕዝብ መካከል አብዛኛዎቹ በዚህ ሕመም መጠቃታቸውን ሪፖርቶች ያሳያሉ። ለመሆኑ ይህ ሕመም ምንድን ነው?

በዩናይትድ ኪንግደም የአእምሮ ጤና ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ሮጀር ሄንደርሰን ስለ ገንዘብ በማሰብ የሚጨነቁ ሰዎች የሚያጋጥማቸውን አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ቀውስ ለመግለጽ በቅርቡ “የገንዘብ ሕመም” የሚለውን ስያሜ ፈጥረዋል። ከዚህ ሕመም ምልክቶች መካከል የመተንፈስ ችግር፣ ራስ ምታት፣ ማቅለሽለሽ፣ ሽፍታ፣ የምግብ ፍላጎት ማጣት፣ በሆነው ባልሆነው መቆጣት፣ የመረበሽ ስሜትና አፍራሽ አስተሳሰብ ይገኙበታል። ሄንደርሰን “ስለ ገንዘብ መጨነቅ ለውጥረት ዓይነተኛው መንስኤ ነው” በማለት ተናግረዋል።

ከቅርብ ወራት ወዲህ ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ ሰዎች ከገንዘብ ጋር ተያይዞ ለሚመጣ ጭንቀት መዳረጋቸው ምንም አያስገርምም። በአሁኑ ጊዜ በብዙ አገሮች ውስጥ የተከሰተው የገንዘብ ቀውስ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰዎች ሥራቸውን፣ መኖሪያ ቤታቸውንና ያጠራቀሙትን ገንዘብ እንዲያጡ አድርጓል። ትላልቅ የገንዘብ ተቋማት ከስረው የተዘጉ ከመሆኑም በላይ የበለጸጉ አገራት ሳይቀር የገንዘብ ቀውሱን ለመግታት ፈጣን እርምጃ መውሰድ አስፈልጓቸዋል። በማደግ ላይ በሚገኙ አገሮች ውስጥ ደግሞ የምግብና የሌሎች መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች ዋጋ መናር በሰዎች ላይ ከፍተኛ ጭንቀት አስከትለዋል።

የተትረፈረፈ ሀብት በሚኖርበት ጊዜም ከገንዘብ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ችግሮች መከሰታቸው የተለመደ ነው። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ገንዘብ እንደ ልብ ማግኘት የተቻለ ቢሆንም ብዙ ሰዎች ገንዘብ በሚያስከትለው ጭንቀት ተውጠዋል። ለምሳሌ በደቡብ አፍሪካ የሚታተመው ዘ ዊትነስ የተባለው ጋዜጣ አፍሪካ ውስጥ “የፍጆታ መጠን ማሻቀብ፣ ለትርፋማነት የተጋነነ ትኩረት መስጠትና ለቁሳዊ ነገሮች መስገብገብ እንደ ወረርሽኝ” ተዛምቶ እንደነበር ዘግቧል። ጋዜጣው “የበሽታው” ምልክቶች ናቸው ብሎ ከዘረዘራቸው ነገሮች መካከል “ውጥረት፣ ዕዳ ውስጥ መግባት፣ አባካኝነት፣ ከመጠን በላይ መሥራት፣ እርካታ ማጣት፣ ቅናትና የመንፈስ ጭንቀት” ይገኙበታል። አፍሪካ ውስጥ የሰዎች ሕይወት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበላሸ ለመሄዱ መንስኤ ተደርጎ የተወሰደው ገንዘብ ነው።

በቅርቡ የተፈጠረው የገንዘብ ቀውስ ከመከሰቱ በፊት ሕንድ አስገራሚ የኢኮኖሚ እድገት አሳይታ ነበር። ኢንዲያ ቱዴይ ኢንተርናሽናል የተሰኘው መጽሔት 2007 በአገሪቱ ውስጥ “የሰዎች የፍጆታ መጠን ጉልህ በሆነ ሁኔታ በድንገት ያሻቀበበት” ዓመት እንደነበር ዘግቧል። ይሁንና በዚያ ወቅት የአገሪቱ ባለሥልጣናት በሕንድ የታየው የኢኮኖሚ እድገት በአገሪቱ አለመረጋጋትና ዓመፅ እየጨመረ እንዲሄድ ያደርጋል የሚል ስጋት አሳድሮባው ነበር።

በተመሳሳይ ወቅት በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በጉልምስና ዕድሜ ላይ የሚገኘው አዲሱ ትውልድ ለቅንጦት ዕቃዎች ብዙ ገንዘብ የማውጣት አዝማሚያ ይታይበት ነበር። ይሁን እንጂ እነዚህ ሰዎች የመግዛት አቅም ያላቸው መሆኑ ደስታ አላስገኘላቸውም። ተመራማሪዎች በዚያ አገር ለሚታየው የአልኮል ሱሰኝነት፣ የመንፈስ ጭንቀትና ራስን የማጥፋት ድርጊት ዋነኛ መንስኤ ከሆኑት ነገሮች መካከል አንዱ ብልጽግና መሆኑን ተናግረዋል። አንድ ጥናት እንዳመለከተው ሰዎች የተትረፈረፈ ገንዘብም ሆነ ቁሳዊ ብልጽግና ያላቸው ቢሆንም “በጣም ደስተኛ” እንደሆኑ የተናገሩት “አሜሪካውያን ከሦስት አንድ እንኳ አይሆኑም።”

የሳንቲም ሌላው ገጽታ

በሌላ በኩል ደግሞ ሀብታምም ሆኑ ድሆች፣ በርካታ ሰዎች በጥሩም ሆነ በመጥፎ ጊዜያት ስለ ገንዘብና ስለ ቁሳዊ ሀብት ብዙም አይጨነቁም። እንዲህ ዓይነት ልዩነት ሊኖር የቻለው እንዴት ነው?

የገንዘብ ትርጉም በሚል ርዕስ በተዘጋጀ አንድ ሪፖርት ላይ ተመራማሪዎች አንዳንድ ሰዎች “ሕይወታቸውን የሚመራውና የሚቆጣጠረው ገንዘብ ነው። ይህም ለውጥረትና ለስሜት መቃወስ ሊዳርጋቸው ይችላል” ሲሉ ገልጸዋል። በአንጻሩ ደግሞ እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል፦ “ለገንዘባቸው በጀት አውጥተው በጥንቃቄ የሚጠቀሙበት ሰዎች የዕለት ተዕለት ሕይወታቸውን በሚገባ መቆጣጠርና በሥርዓት መምራት የሚችሉ ከመሆኑም በላይ ለራሳቸው ጥሩ ግምት አላቸው። እነዚህ ሰዎች የገንዘብ ጌታ እንጂ የገንዘብ ባሪያዎች አይደሉም . . . ለገንዘባቸው በጀት አውጥተው በጥሩ ሁኔታ የሚጠቀሙበት ሰዎች እምብዛም ውጥረት ስለማይኖርባቸው ለጭንቀት የመዳረጋቸው አጋጣሚ አነስተኛ መሆኑን አበክረን መግለጽ እንወዳለን።”

አንተ ለገንዘብ ያለህ አመለካከት ምንድን ነው? ተለዋዋጭ የሆነው የዓለም ኢኮኖሚ በአንተ ላይ ምን ተጽእኖ ያሳድራል? ገንዘብ ጌታህ ነው ወይስ ባሪያህ? ምናልባት የገንዘብ ሕመም ምልክቶች አይታዩብህ ይሆናል። ሆኖም ሀብታምም ሆንን ድሃ፣ ሁላችንም ከገንዘብ ጋር ተያይዞ ለሚመጣ ጭንቀት መጋለጣችን አይቀርም። ገንዘብህን በምትይዝበት መንገድ ላይ ማስተካከያዎች ማድረግህ የላቀ የአእምሮ ሰላም የሚያስገኝልህ እንዲሁም ሕይወትህን ይበልጥ አስደሳች የሚያደርግልህ እንዴት እንደሆነ ተመልከት።