በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክን በማስቀደማችን ተባርከናል

አምላክን በማስቀደማችን ተባርከናል

አምላክን በማስቀደማችን ተባርከናል

ፒየር ቮሩ እንደተናገረው

“ቦንዡር!” በሕይወቴ ሙሉ በዚህ የፈረንሳይኛ ሰላምታ ስጠቀም ቆይቻለሁ። ይሁንና ኅዳር 1975 በዚህ ሰላምታ በመጠቀሜ ታሰርኩ። ይህ የሆነበትን ምክንያትና ከዚያ በኋላ ባሉት ዓመታት የተከናወኑትን ነገሮች እስቲ ላጫውታችሁ።

1, 1944 በማዕከላዊ ቤኒን በምትገኘው በሳቬ ከተማ ዳርቻ ላይ ባለችው በማሌቴ መንደር ተወለድኩ። * ወላጆቼ አቢኦላ የሚል በዮሩባ ቋንቋ በጣም የተለመደ ስም አወጡልኝ። ይሁን እንጂ ገና ልጅ ሳለሁ ስሜን ይበልጥ ዘመናዊና ተወዳጅ ነው ብዬ ባሰብኩት ፒየር በሚለው መጠሪያ ቀየርኩት።

የመንደራችን ሰዎች ለሁሉም ልጆች ቅጽል ስም ያወጡላቸው ነበር። ስወለድ በአካባቢው የሚገኘውን ቄስ እመስል ስለነበር ፓስተር ብለው ጠሩኝ። እኔ ግን ሃይማኖታዊ ትምህርት ወደሚሰጥበት ቦታ ከመሄድ ይልቅ እግር ኳስ መጫወት ያስደስተኝ ነበር።

በ1959 ትምህርቴን ለመቀጠል በደቡባዊ የአገሪቱ ክፍል ወደምትገኘው ሳኬቴ የተባለች ከተማ ሄድኩ። በዚያም አስተማሪ ከሆነው ሲመን የተባለ የአጎቴ ልጅ ጋር መኖር ጀመርኩ፤ በወቅቱ ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ሲመንን መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠኑት ነበር። መጀመሪያ ላይ በጥናቱ መካፈል አልፈለግሁም ነበር። በኋላ ግን ሚሼል የተባለውን የሲመን ታናሽ ወንድም በጥናቱ ላይ አብሮኝ እንዲገኝ ጠየቅኩት። እሱም በሐሳቤ ተስማማ፤ የአምላክ ስም ይሖዋ መሆኑን ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማሁት በዚህ ወቅት ነበር።

አንድ እሁድ ቀን እኔ፣ ሲመን እና ሚሼል ወደ ቤተ ክርስቲያን ከመሄድ ይልቅ በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ ለመገኘት ወሰንን። በስብሰባው ላይ የተገኙት አምስት ሰዎች ማለትም ሁለቱ የይሖዋ ምሥክሮችና እኛ ሦስታችን ብቻ መሆናችንን ስናይ አዘንን። ያም ቢሆን የተማርነው ነገር እውነት መሆኑን ስለተገነዘብን በጥናታችን ቀጠልን። ራሱን ለአምላክ መወሰኑን ለማሳየት መጀመሪያ የተጠመቀው ሚሼል ነበር። በአሁኑ ጊዜ አቅኚ (የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች የሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች የሚጠሩበት ስም ነው) ሆኖ እያገለገለ ነው።

ሲመን በስተ ሰሜን ወደምትገኘው ኮኮሮ የተባለች ከተማ ሲዛወር እኔም አብሬው ሄድኩ። የይሖዋ ምሥክሮች በህዋንሱጎ መንደር ትልቅ ስብሰባ ያደርጉ ነበር። ሲመን በታክሲ የሄደ ሲሆን እኔ ግን በብስክሌት 220 ኪሎ ሜትር ተጉዤ በስብሰባው ላይ ተገኘሁ። መስከረም 15, 1961 በተደረገው በዚህ ስብሰባ ላይ ሁለታችንም ተጠመቅን።

በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ያጋጠሙን ተፈታታኝ ሁኔታዎች

ሥዕል በመሳልና በመሸጥ እንዲሁም በእርሻ ሥራ እተዳደር ነበር። ፊሊፕ ዛኑ የተባለ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ጉባኤያችንን ሲጎበኝ አቅኚ በመሆን በሙሉ ጊዜ አገልግሎት እንድካፈል ሐሳብ አቀረበልኝ። ይህን ጉዳይ ከጓደኛዬ ከአማንዌል ፎቱንቢ ጋር ከተወያየንበት በኋላ ሁለታችንም ከየካቲት 1966 ጀምሮ አቅኚ ሆነን ማገልገል እንደምንችል አሳወቅን። ከጊዜ በኋላ ተጓዥ የበላይ ተመልካች በመሆን የፎን፣ የጉን፣ የዮሩባ እና የፈረንሳይኛ ቋንቋዎች ተናጋሪ የሆኑ ጉባኤዎችን መጎብኘት ጀመርኩ።

ከጊዜ በኋላ፣ ዡልየን ከተባለች ደስ የምትል ክርስቲያን ወጣት ጋር ተዋወቅሁ፤ እሷም እንደ እኔ ቀለል ያለ ሕይወት የመምራት ፍላጎት ነበራት። ነሐሴ 12, 1971 ከዡልየን ጋር ተጋባንና አብረን ጉባኤዎችን መጎብኘት ጀመርን። ልጃችን ቦላ ነሐሴ 18, 1972 ተወለደ። ከአንድ ጉባኤ ወደ ሌላ ጉባኤ የምንሄደው በብስክሌት ሲሆን ዡልየን ቦላን አዝላ ከኋላዬ ትቀመጥ ነበር። በምንጎበኘው ጉባኤ የሚኖር አንድ የይሖዋ ምሥክር አብዛኛውን ጊዜ ጓዛችንን በብስክሌት ያጓጉዝልን ነበር። በዚህ ዓይነት ሁኔታ ለአራት ዓመታት ያህል ጉባኤዎችን ስንጎበኝ ቆይተናል።

አንድ ቀን ዡልየን በጣም ታምማ ሌሊቱን ሙሉ ስትሠቃይ አደረች። በነጋታው እርዳታ ለማግኘት ወደ ዋናው መንገድ ወጣሁ። ወዲያውኑ አንድ ታክሲ ብቅ አለ፤ በዚህ አካባቢ ታክሲ ማግኘት አስቸጋሪ ነበር። ይበልጥ የሚገርመው ደግሞ ታክሲው ምንም ሰው አልጫነም ነበር! ችግሬን ለሹፌሩ ከነገርኩት በኋላ 25 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቃ ወደምትገኘው ወደ ዋና ከተማዋ ፖርቶ ኖቮ ይወስደን እንደሆነ ጠየቅኩት። እሱም ፈቃደኛ መሆኑን ነገረኝ። እዚያ ከደረስን በኋላም ሹፌሩ ፈገግ በማለት “ምንም መክፈል አያስፈልግህም” አለኝ።

ዡልየን በአንድ የይሖዋ ምሥክር ቤት ለሁለት ሳምንታት ያህል መተኛት አስፈልጓት ነበር። ዶክተሩ በየቀኑ እየመጣ በደግነት ይጠይቃት የነበረ ከመሆኑም ሌላ የሚያስፈልጓትን መድኃኒቶችም ይዞ ይመጣ ነበር። ዶክተሩ ዡልየንን ለመጨረሻ ጊዜ ሊመረምራት ሲመጣ በጠቅላላ ያወጣው ወጪ ምን ያህል እንደሆነ ፈራ ተባ እያልኩ ጠየቅኩት። “ምንም መክፈል አያስፈልግህም” በማለት ሲመልስልኝ በጣም ተገረምኩ።

ከፍተኛ ለውጥ

በ1975 ዳሆሚ የማርክሲዝምን ርዕዮተ ዓለም መከተል ጀመረች። አገሪቱም ስሟ ተቀይሮ የቤኒን ሕዝባዊ ሪፑብሊክ የሚል መጠሪያ ተሰጣት። የሕዝቡ የዕለት ተዕለት ሕይወትም ተቀየረ። “ፑር ላ ሬቮልሲዮን?” (ለአብዮቱ ዝግጁ ነህ?) የሚል አዲስ የሰላምታ አሰጣጥ ተጀመረ። ሕዝቡም “ፕሬ!” (ዝግጁ ነኝ!) ብለው እንዲመልሱ ይጠበቅባቸው ነበር። እኛ ግን በመጽሐፍ ቅዱስ በሠለጠነው ሕሊናችን የተነሳ እንዲህ ያሉ ፖለቲካዊ መፈክሮችን ለማሰማት ፈቃደኛ አልነበርንም። ይህም በብዙዎች ዘንድ እንድንጠላ አደረገን።

በ1975 መገባደጃ አካባቢ አንድ እሁድ ቀን በሴንት ሚሼል አቅራቢያ ከቤት ወደ ቤት ሳገለግል ተይዤ ታሰርኩ። ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት የታሰርኩት “ፑር ላ ሬቮልሲዮን?” የሚል ሰላምታ ለሰጠኝ ሰው “ቦንዡር!” በማለት ስለመለስኩ ነበር። ወደ ፖሊስ ጣቢያ ከተወሰድኩ በኋላ ፖሊሶቹ ደበደቡኝ። በኋላ ላይ ግን በአካባቢው የሚኖሩ ሦስት የይሖዋ ምሥክሮች አስፈቱኝ።

በቤኒን ከታሰሩት የይሖዋ ምሥክሮች የመጀመሪያው እኔ ነበርኩ። ብዙም ሳይቆይ በአገሪቱ ያሉ በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች ታሰሩ። የአገሪቱ መንግሥት የይሖዋ ምሥክሮችን የመንግሥት አዳራሾች የወረሰ ሲሆን ሚስዮናውያንንም አባረራቸው። የቅርንጫፍ ቢሮው እንኳ የተዘጋ ሲሆን ብዙ የይሖዋ ምሥክሮችም አገሪቱን ለቅቀው በስተ ምዕራብ ወደ ቶጎ ወይም በስተ ምሥራቅ ወደ ናይጄሪያ ተሰደዱ።

በናይጄሪያ የቤተሰባችን ቁጥር ጨመረ

ሚያዝያ 25, 1976 ሁለተኛው ልጃችን ኮላ ተወለደ። ከሁለት ቀን በኋላ የቤኒን መንግሥት፣ በአዋጅ ቁ. 111 መሠረት የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ እንዲታገድ አደረገ። እኛም ወደ ናይጄሪያ የተሰደድን ሲሆን በዚያም በስደተኞች በተጨናነቀ የመንግሥት አዳራሽ ውስጥ አረፍን። በማግስቱ በአቅራቢያው የሚገኙ ጉባኤዎች እንዲቀበሉን ዝግጅት ተደረገ። በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ ያረፉት ስደተኞች ቦታውን ሲለቁ ሌሎች ይተኩ ነበር። በናይጄሪያ የሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች የጭነት መኪናዎችን በመጠቀም ስደተኞቹን በሌላ አካባቢ ወደሚገኙ ጉባኤዎች ያደርሷቸው ነበር።

በናይጄሪያ የሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ከቤኒን የመጡትን የይሖዋ ምሥክሮች በሙሉ እንድጎበኝ ጠየቀኝ። ከዚያም ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆኜ በናይጄሪያ የሚገኙትን የዮሩባ ቋንቋ ጉባኤዎች እንድጎበኝ የተመደብኩ ሲሆን በኋላ ላይ ደግሞ በጉን ቋንቋ የሚመሩ ጉባኤዎችን መጎብኘት ጀመርኩ። ወደ ተለያዩ ጉባኤዎች የምንጓዘው በሞተር ብስክሌት ነበር። ቦላ ከፊቴ የሚቀመጥ ሲሆን ዡልየን ደግሞ ኮላን አቅፋ ከኋላዬ ትቀመጥ ነበር።

በ1979 ጀማይማ የተባለችው ልጃችን እንደተጸነሰች አወቅን። በዚህም ምክንያት የተጓዥ የበላይ ተመልካችነት ሥራችንን ማቆም ግድ ሆነብን። ፔፔ የተባለችው የዡልየን ታናሽ እህት ከቤኒን መጥታ ከእኛ ጋር መኖር ጀመረች። የቤተሰባችን ቁጥር እየጨመረ ሄደ። በ1983 ካሌብ፣ በ1987 ደግሞ ሲላስ የተባሉ ወንዶች ልጆችን ወለድን። በመሆኑም የቤተሰባችን ቁጥር ስምንት ደረሰ። እኔና ዡልየን ጥሩ ወላጆች ለመሆንና ከቻልን ደግሞ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመቀጠል እንፈልግ ነበር። ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? አንድ የእርሻ ቦታ ከተከራየን በኋላ ካሳቫ፣ በቆሎና ኮኮያም የተባሉትን ተክሎች ማምረት ጀመርን። ከዚያም ኢሎግቦኤሬሚ በሚባል መንደር ውስጥ አነስ ያለች ቤት ሠራን።

ጠዋት ልጆቹ ወደ ትምህርት ቤት ሲሄዱ እኔና ዡልየን በስብከቱ ሥራ ላይ እንሰማራለን። ሁላችንም ምሳችንን አብረን መመገብ እንድንችል ሁልጊዜ ቀደም ብለን ወደ ቤት እንመለሳለን። ከምሳ በኋላ ትንሽ አረፍ ብለን ወደ እርሻችን እንሄዳለን። ዡልየንና ፔፔ ያመረትናቸውን ነገሮች ገበያ ወስደው ይሸጣሉ። ሁላችንም ጠንክረን እንሠራ ነበር። የሚያስደስተው ነገር በእነዚያ ዓመታት ከበድ ያለ ሕመም አላጋጠመንም።

ከፍተኛ ትምህርት ባይከታተሉም ተባርከዋል

ልጆቻችን ከፍተኛ ትምህርት እንዲከታተሉ አበረታተናቸው አናውቅም። የአምላክን መንግሥት ማስቀደም፣ ክርስቲያናዊ ባሕርያትን ማዳበር እንዲሁም ጠንክሮ መሥራት ስኬታማ ሕይወት ለመምራት እንደሚያስችል እናውቅ ነበር። ይህን ሐቅ በልጆቻችን ልብ ውስጥ ለመቅረጽ የተቻለንን ጥረት አድርገናል። ልጆቻችንን መጽሐፍ ቅዱስ አስጠናቸው የነበረ ሲሆን ለይሖዋ ፍቅር ሲያዳብሩ፣ ራሳቸውን ለእሱ ሲወስኑና ሲጠመቁ ማየቴ እጅግ አስደስቶኛል!

ፔፔ ከልጆቻችን በዕድሜ ትበልጥ ስለነበር ከቤት ቀድማ የወጣችው እሷ ናት። ከእኛ ጋር መኖር ስትጀምር ማንበብ አስተምሬያት ነበር። ፔፔ በመደበኛ ትምህርት ብዙ ባትገፋም ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትና ለሌሎች መንፈሳዊ ነገሮች ትኩረት ትሰጥ ነበር። ለተወሰነ ጊዜ በአቅኚነት ካገለገለች በኋላ መንዴይ ኣኪንራ የተባለ ተጓዥ የበላይ ተመልካች አግብታ አብራው ማገልገል ጀመረች። በአሁኑ ጊዜ ጢሞቴዎስ የሚባል ልጅ አላቸው። ፔፔ እና መንዴይ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የቀጠሉ ሲሆን መንዴይ በትልልቅ ስብሰባዎች ላይ በርካታ ኃላፊነቶች ይሰጡታል።

ቦላ በአንድ ትልቅ ድርጅት ውስጥ ተለማማጅ ሆኖ በመሥራት በምግብ ማብሰል ሙያ መሠልጠን ጀመረ። ብዙም ሳይቆይ ከድርጅቱ አስተዳዳሪዎች አንዱ ቦላ ታታሪ ሠራተኛና ታማኝ እንደሆነ እንዲሁም ሌሎች ግሩም የሆኑ ክርስቲያናዊ ባሕርያት እንዳሉት አስተዋለ። ከጊዜ በኋላ በድርጅቱ ውስጥ የኃላፊነት ቦታ ተሰጠው። በአሁኑ ጊዜ ጄን የተባለች ግሩም ሚስት አግብቶ ሦስት ልጆች የወለደ ሲሆን በሌጎስ፣ ናይጄሪያ በሚገኝ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ውስጥ ሽማግሌ ሆኖ ያገለግላል። ቦላ ጥሩ ባልና አባት ከመሆኑም በላይ በጉባኤ ውስጥ ያለውን ኃላፊነት በሚገባ የሚወጣ ሽማግሌ መሆኑ በጣም ያስደስታል።

ኮላ ደግሞ ከአንድ ልብስ ሰፊ ጋር በመሥራት በዚህ ሙያ የሠለጠነ ከመሆኑም በላይ አቅኚ ሆኖ ያገለግል ነበር። በናይጄሪያ እያለ እንግሊዝኛ ስለተማረ በ1995 በቤኒን በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ በትርጉም ክፍል ውስጥ እንዲያገለግል ግብዣ ቀረበለት። ላለፉት 13 ዓመታት በዚያ ሲያገለግል ቆይቷል።

ወደ ቤኒን ተመልሰን ያከናወንነው አገልግሎት

ጥር 23, 1990 የቤኒን መንግሥት ቀደም ሲል በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ጥሎት የነበረውን እገዳ የሚሽር አዋጅ ማውጣቱን ስንሰማ በጣም ተደሰትን። ብዙ ስደተኞች ወደ አገራቸው ተመለሱ። በተጨማሪም አዳዲስ ሚስዮናውያን ወደ ቤኒን የመጡ ሲሆን ቅርንጫፍ ቢሮውም እንደገና ተከፈተ። በ1994 ቤተሰባችን ወደ ቤኒን ተመለሰ፤ ፔፔና ቦላ ግን ከቤተሰቦቻቸው ጋር በናይጄሪያ ቀሩ።

እኔም በቤኒን በሳምንት ውስጥ ለተወሰኑ ሰዓታት የምሠራው ሥራ አገኘሁ። በናይጄሪያ ያለውን ቤታችንን አከራይተን የምናገኘው አነስተኛ ገቢና ቦላ ያደረገልን ልግስና አንድ ላይ ተዳምሮ ከቅርንጫፍ ቢሮው አቅራቢያ ለአምስታችን የምትሆን አነስ ያለች ቤት ሠራን። ጀማይማ በልብስ ስፌት ራሷን እያስተዳደረች ለስድስት ዓመታት በአቅኚነት አገልግላለች። ከዚያም ኮኩ አሁሜኑ የተባለ የይሖዋ ምሥክር ያገባች ሲሆን በአሁኑ ጊዜ በአቅራቢያችን ባለው ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ እያገለገሉ ነው። ካሌብና ሲላስም ትምህርታቸውን ሊጨርሱ ተቃርበዋል። አምላክ እርዳታ ስላደረገልንና የቤተሰባችን አባላት ስለተባበሩን እኔና ዡልየን ከ40 ለሚበልጡ ዓመታት በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መቀጠል ችለናል።

አምላክ በቤኒን የሚካሄደውን የስብከት ሥራ በእጅጉ ባርኮታል። በ1961 በተጠመቅኩበት ጊዜ በአገሪቱ የአምላክን መንግሥት ምሥራች የሚሰብኩት የይሖዋ ምሥክሮች 871 ነበሩ። በታሰርኩበት ዓመት ይህ ቁጥር ወደ 2,381 አድጎ ነበር። የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ ለ14 ዓመታት ያህል ታግዶ ቢቆይም በ1994 ወደ ቤኒን ስንመለስ ቁጥሩ 3,858 ደርሶ ነበር። በአሁኑ ጊዜ ይህ ቁጥር ከእጥፍ በላይ በመጨመሩ በቤኒን የሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች ከ9,000 በላይ ሆነዋል፤ በ2008 በተደረገው የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ ላይ 35,752 የሚያህሉ ሰዎች ተገኝተው ነበር።

አንዳንድ ጊዜ ከዛሬ 30 ዓመት በፊት ፖሊሶች ወደያዙኝ ቦታ የምሄድ ሲሆን በወቅቱ ስለተከናወኑት ሁኔታዎች መለስ ብዬ አስባለሁ፤ በተለይ ደግሞ አምላክ ቤተሰቤን ስለባረከልኝ አመሰግነዋለሁ። ምንም ነገር አጥተን አናውቅም። አሁንም ድረስ ማንኛውንም ሰው “ቦንዡር” በማለት ሰላም እላለሁ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.4 በወቅቱ ቤኒን ዳሆሚ ተብላ ትጠራ የነበረ ሲሆን ፈረንሳዮች ከሚያስተዳድሯቸው በምዕራብ አፍሪካ የሚገኙ አገሮች አንዷ ነበረች።

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ፈገግ በማለት “ምንም መክፈል አያስፈልግህም” አለኝ

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ልጆቻችን ከፍተኛ ትምህርት እንዲከታተሉ አበረታተናቸው አናውቅም

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1970 ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆኜ ሳገለግል

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1976 ቦላ እና ኮላ ከተባሉት ሁለት ወንዶች ልጆቻችን ጋር

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በአሁኑ ጊዜ ከባለቤቴ፣ ከአምስቱ ልጆቼ፣ ከሦስት የልጅ ልጆቼ እና ከፔፔ ቤተሰብ ጋር