በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ቡካሬስት—ሁለት ገጽታዎች ያሏት ከተማ

ቡካሬስት—ሁለት ገጽታዎች ያሏት ከተማ

ቡካሬስት—ሁለት ገጽታዎች ያሏት ከተማ

ሩማንያ የሚገኘው የንቁ! ጸሐፊ እንዳዘጋጀው

ቡካሬስትን ከርቀት ለተመለከታት በከተማዋ ውስጥ ጎልቶ የሚታየው የፓርላማው ቤተ መንግሥት (1) ነው፤ ይህ ሕንፃ በኮሚኒስት አገዛዝ ወቅት የሕዝብ ምክር ቤት ተብሎ ይጠራ ነበር። በዓለም ላይ ከሚገኙት እጅግ ግዙፍ ሕንፃዎች አንዱ የሆነው ይህ ሕንፃ እምብዛም የሚማርክ ውበት ባይኖረውም በከተማዋ ውስጥ አሉ ከሚባሉት የቱሪስት መስህቦች መካከል የሚመደብ ነው።

የፓርላማው ቤተ መንግሥት በአንዳንድ መንገዶች የቡካሬስትን ዘመናዊ ገጽታ ያንጸባርቃል። ይሁንና የከተማዋ ነዋሪዎች ስለዚህ ግዙፍ ሕንፃ የተለያየ አመለካከት አላቸው። የከተማዋን ጥንታዊ ገጽታ የሚያንጸባርቁትን ሌሎቹን ማራኪ ሕንፃዎችም ጎብኚዎች እንዲያደንቁላቸው ይፈልጋሉ።

አስደናቂ አጀማመር የነበራት ዋና ከተማ

በ1862 ቡካሬስት የሩማንያ ዋና ከተማ እንድትሆን ተወሰነ። ከዚያ በኋላ በነበሩት አሥርተ ዓመታት ከተማዋ ፈጣን እድገት አደረገች። በፈረንሳይ የሥነ ሕንፃ ባለሞያዎች የተነደፉ ማራኪና ግርማ ሞገስ የተላበሱ ሕንፃዎች፣ ዛፎች በተተከሉባቸው አውራ ጎዳናዎች ግራና ቀኝ መገንባት ጀመሩ። ቡካሬስት በርካታ መናፈሻዎች፣ የአትክልት ቦታዎች እንዲሁም አደባባዮች ያሏት በመሆኗ አትክልቶች የሞሉባት ከተማ የሚል ስያሜ አግኝታለች። በዓለም ላይ በላምባ የሚነዱ የመንገድ መብራቶች ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅም ላይ ከዋሉባቸው ከተሞች አንዷ ቡካሬስት ናት። በ1935 በፓሪስ፣ ሻንዛሊዛ ጎዳና የሚገኘውን አርክ ደ ትሪዮምፌ የተባለ የመታሰቢያ ቅስት ንድፍ የተከተለ አርክ ኦቭ ትራያምፍ (2) የተባለ ቅስት ውብ በሆነው የኪስሌፍ አውራ ጎዳና ላይ ተገነባ። በዚያ ወቅት የቡካሬስትን ውበት የተመለከተ ፈረንሳዊ አገሩ እንዳለ ሊሰማው ይችል ነበር። እንዲያውም ቡካሬስት፣ በስተ ምሥራቅ ያለችው ትንሿ ፓሪስ የሚል ቅጽል ስም ተሰጥቷት ነበር።

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በኮሚኒስት አገዛዝ ሥር የወደቀችው ቡካሬስት ከፍተኛ ለውጦችን አስተናገደች። አፓርታማዎችን ለመገንባት ሲባል በመሃል ከተማ ከሚገኙት በርካታ ታሪካዊ ሕንፃዎችና ሐውልቶች አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት እንዲፈርሱ ተደረገ። በ1960ና በ1961 ብቻ 23,000 የሚያህሉ ቤቶችን የያዙ አፓርታማዎች ተገነቡ። በ1980 የሕዝብ ምክር ቤት ሕንፃን ለመገንባት ዝግጅት መደረግ ጀመረ። ከጊዜ በኋላ ይህ ሕንፃ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአምፖል ማቀፊያ ጌጦች እንዲኖሩት ተደረገ፤ ከዚህም ሌላ ወደታች 90 ሜትር ርዝመት ያለው ከቦምብ ድብደባ ለመጠለል የሚያገለግል ምድር ቤት ተሠርቶለታል። በ360,000 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈው ይህ ሕንፃ 11 ፎቅና 1,100 ክፍሎች ያሉት ሲሆን በግዙፍነቱ የፈረንሳዩን የቨርሳይሊስ ቤተ መንግሥት ሦስት እጥፍ ይሆናል። ይህንን ሕንፃ እንዲሁም ወደ ሕንፃው የሚያመራውን ከፓሪሱ ሻንዛሊዛ ጎዳና የሚበልጥ በጣም ሰፊ አውራ ጎዳና ለመሥራት ሲባል በከተማዋ የቀድሞ ክፍል የነበሩ ሕንፃዎች ፈርሰዋል። ቡካሬስትን ቀድሞ ለሚያውቋት ሰዎች ሙሉ በሙሉ ተለውጣ ነበር።

ይሁንና በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች ይህንን ግዙፍ ሕንፃ ሲመለከቱ ሕንፃው ስለተገነባበት ዘመን ደስ የማይሉ ትዝታዎች ይቀሰቀሱባቸዋል፤ ሕንፃውን ያስገነባው አምባገነን ገዢ የነበረው ኒኮላይ ቻውሼስኩ ነበር። ኒኮላይ ቻውሼስኩ ለራሱ መታሰቢያ የሚሆን ነገር ለማሠራት ስለፈለገ 700 የሚያህሉ የሥነ ሕንፃ ባለሞያዎች እንዲሁም በቀን ውስጥ በሦስት ፈረቃ የሚሠሩ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በግንባታው ላይ እንዲሰማሩ አድርጎ ነበር። በ1989 የኒኮላይ ቻውሼስኩ አገዛዝ ባበቃበት ወቅት ለሕንፃው ግንባታ ከአንድ ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚበልጥ ገንዘብ የወጣ ቢሆንም ግንባታው ገና አልተጠናቀቀም ነበር።

የከተማዋ ሌላ ገጽታ

አሁንም ድረስ ባለው የከተማዋ የቀድሞ ክፍል የቡካሬስትን ሌላ ገጽታ ማየት ይቻላል። የድሮዋን ቡካሬስት ያስዋቧት የሚያስደንቁ ሕንፃዎች በዚህ አካባቢ አሁንም ይታያሉ። ከዚህም በተጨማሪ በቡካሬስት ከሚገኙት በርካታ ቤተ መዘክሮች አንዱ በሆነው ባሕላዊ መንደር ቤተ መዘክር (3) የገጠሪቷን ሩማንያ የተለያየ ባሕላዊ አኗኗር መቃኘት ይቻላል። የተንጣለለውን ሐይቅ ለማየት በሚያስችል ቦታ ላይ በተሠራው እርጋታ የሰፈነበት መናፈሻ ውስጥ ከ50 በላይ የገጠር ቤቶች የሚገኙ ከመሆኑም ሌላ በመላው ሩማንያ የሚገኙ የተለያዩ ሕንፃዎች ወደዚህ ቦታ መጥተው እንደገና ተገንብተዋል። ይህም መናፈሻው አስደናቂ በሆኑ ነገሮች እንዲሞላ አድርጎታል። እያንዳንዱ ቤት በራሱ ቤተ መዘክር ነው ማለት ይቻላል፤ በእነዚህ ቤቶች ውስጥ ከዛሬዋ ቡካሬስት ፈጽሞ በምትለየው በቀድሞዋ ሩማንያ የነበሩ የዕደ ጥበብ ሙያዎችን እንዲሁም የሰዎችን አኗኗርና ይገለገሉባቸው የነበሩ መሣሪያዎችን ማየት ይቻላል።

የቀድሞውና ዘመናዊው የቡካሬስት ክፍሎች የሚገኙት በተለያየ አካባቢ አይደለም። በጣም በተለያዩ ዘመናት የተገነቡ ሕንፃዎችን ጎን ለጎን (4) መመልከት የተለመደ ነው። በመሆኑም የቀድሞውንም ሆነ የአሁኑን ዘመን አጣምራ የያዘችውን የቡካሬስትን ሁለት ገጽታዎች በከተማዋ ውስጥ መመልከት ይቻላል።

[በገጽ 10 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

1 የፓርላማው ቤተ መንግሥት

2 አርክ ኦቭ ትራያምፍ

3 ባሕላዊ መንደር ቤተ መዘክር

4 በጣም በተለያዩ ዘመናት የተገነቡ ሕንፃዎችን ጎን ለጎን

[ምንጭ]

© Sari Gustafsson/hehkuva/age fotostock