በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዝሆንን ማላመድ

ዝሆንን ማላመድ

ዝሆንን ማላመድ

ሕንድ የሚገኘው የንቁ! ጸሐፊ እንዳዘጋጀው

ዝሆኖችን ከሚያላምዱ ማሃውት በመባል ከሚታወቁት ሰዎች አንዱ በናርማዳ ወንዝ ዳር ምግቡን ሲያበስል ትንሽ ልጁን በተኛው ዝሆን የፊት እግሮች መካከል ያስቀመጠው ሲሆን ዝሆኑም ልጁን በኩምቢው አቅፎ ይዞታል። ልጁ ከዚያ ወጥቶ ለመሄድ በተደጋጋሚ ቢሞክርም “ዝሆኑ ቀስ ብሎ በኩምቢው እያቀፈ አባቱ ወዳስቀመጠው ቦታ ይመልሰዋል” በማለት ፕሮጀክት ኤለፋንት የተሰኘው መጽሐፍ ተናግሯል። “ምግብ ማብሰሉን የቀጠለው አባት ልጁ ምንም ጉዳት እንደማይደርስበት የተማመነ ይመስላል።”

ዝሆኖች፣ ከ2000 ከክርስቶስ ልደት በፊት ጀምሮ ለሰው ልጆች አገልግሎት ሲሰጡ ኖረዋል። በጥንት ዘመን ዝሆኖች በዋነኝነት የሚሠለጥኑት ለጦርነት ነበር። በዛሬው ጊዜ፣ ሕንድ ውስጥ ዝሆኖች ልዩ ልዩ ሥራዎችን እንዲያከናውኑ ይሠለጥናሉ። ዝሆኖች የተቆረጠ ግንድ ለመሸከም፣ ሃይማኖታዊ በዓላትንና የሠርግ ሥነ ሥርዓቶችን ለማድመቅ፣ የሰርከስ ትርዒት ለማሳየት፣ ማስታወቂያዎችን ለመሥራት አልፎ ተርፎም ለልመና ያገለግላሉ። እነዚህ ዝሆኖች ለማዳ እንዲሆኑ የሚደረገው እንዴት ነው? የሚሠለጥኑትስ?

ዝሆኖች የሚሠለጥኑበት መንገድ

ሕንድ ውስጥ የሚገኙ በርካታ ማዕከላት በሰዎች ለተያዙ፣ ወላጆቻቸው ትተዋቸው ለሄዱ ወይም በዱር ሳሉ ጉዳት ለደረሰባቸው የዝሆን ግልገሎች እንክብካቤ ያደርጋሉ። እንዲህ ካሉት ማሠልጠኛ ማዕከሎች አንዱ የሚገኘው በኬረለ ግዛት ባለው ኮኒ በተባለ አካባቢ ነው። በዚህ ቦታ የዝሆን ግልገሎች ለልዩ ልዩ ሥራዎች ይሠለጥናሉ። አንድ ማሃውት በመጀመሪያ የሚያሠለጥነውን ግልገል አመኔታ ማትረፍ አለበት። አሠልጣኙ ይህን አመኔታ ለማትረፍ ከሚጠቀምባቸው መንገዶች ዋነኛው ግልገሉን መመገብ ነው። አንድ ግልገል የአሠልጣኙን ድምፅ ለይቶ የሚያውቅ ሲሆን ምግቡን እንዲበላ ሲጠራው በፍጥነት በመምጣት የሚሰጠውን ወተትና የማሽላ አጥሚት ይጠጣል። ግልገሉ ብዙውን ጊዜ ለሥራ መሠልጠን የሚጀምረው በአሥራዎቹ ዓመታት መጀመሪያ ላይ ሲደርስ ነው። ከዚያም 25 ዓመት ሲሆነው ሥራ መሥራት ይጀምራል። በኬረለ፣ አንድ ዝሆን 65 ዓመት ሲሆነው ጡረታ መውጣት እንዳለበት የመንግሥት ደንብ ያዛል።

ዝሆንን በጥሩ ሁኔታ ለማላመድ ማሃውቱ ጥሩ ሥልጠና ሊያገኝ ይገባል። በትሪኩር፣ ኬረለ የሚገኘው ኤሌፈንት ዌልፌር አሶስየሽን የተባለው ድርጅት እንዳለው ከሆነ አንድ አዲስ ማሃውት ቢያንስ ለሦስት ወር በሚገባ መሠልጠን ይኖርበታል። እንዲህ ዓይነቱ ሥልጠና ለዝሆኖች ትእዛዝ መስጠትን በመማር ብቻ የተወሰነ ሳይሆን መላ አኗኗራቸውን ማወቅንም ያጠቃልላል።

ለአካለ መጠን የደረሰ አንድ ዝሆን ለመሠልጠን ብዙ ጊዜ ይወስድበታል። አሠልጣኙ መጀመሪያ ላይ ከጉረኖው ውጪ ሆኖ በቃል የሚሰጠውን ትእዛዝ መረዳት እንዲችል ዝሆኑን ያስተምረዋል። በኬረለ አንድ ማሃውት የሚፈልገውን ሥራ ዝሆኑ እንዲሠራ ለማድረግ ወደ 20 የሚጠጉ ትእዛዞችንና ምልክቶችን ይጠቀማል። ማሃውቱ ድምፁን ከፍ አድርጎ ግልጽ የሆኑ ትእዛዞችን ለዝሆኑ ይሰጠዋል፤ እንዲሁም በበትር ነካ በማድረግ ምን መሥራት እንዳለበት ያሳየዋል። ዝሆኑ የታዘዘውን ሲፈጽም በሽልማት መልክ የሚበላ ነገር ይሰጠዋል። አሠልጣኙ፣ ዝሆኑ እንደማይተናኮለው ሲያረጋግጥ ወደ ጉረኖው ውስጥ ይገባና ይደባብሰዋል። ይህም በመካከላቸው የመተማመን ስሜት እንዲፈጠር ያደርጋል። ከጊዜ በኋላ ዝሆኑን ወደ ውጪ ይዞት ሊወጣ ይችላል፤ ይሁን እንጂ አሁንም የአውሬነት ባሕርይው ሙሉ በሙሉ ስለማይለቀው ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። ዝሆኑ ለማዳ መሆኑ በደንብ እስኪረጋገጥ ድረስ ገላውን ለመታጠብና ለሽርሽር ወደ ውጪ የሚወሰደው በሁለት አለማማጅ ዝሆኖች መካከል ታስሮ ነው።

አንድ ዝሆን በቃል የሚሰጡትን ትእዛዞች መረዳት ከቻለ በኋላ ማሃውቱ ጀርባው ላይ ተቀምጦ በእግሩ አውራ ጣቶች ወይም በተረከዙ ሰውነቱን በመንካት ለሚሰጠው ትእዛዝ እንዴት መልስ መስጠት እንዳለበት ያስተምረዋል። ዝሆኑ ወደፊት እንዲሄድ ለማድረግ ማሃውቱ በሁለቱ የእግሩ አውራ ጣቶች ዝሆኑን ከጆሮዎቹ በስተኋላ በኩል ነካ ያደርገዋል። ወደኋላ እንዲሄድ ለማድረግ ደግሞ የዝሆኑን ትከሻ በሁለቱ ተረከዞቹ መታ መታ ያደርገዋል። ዝሆኑ ግራ እንዳይጋባ ለማድረግ ሲባል የቃል ትእዛዝ የሚሰጠው አንድ ማሃውት ብቻ ነው። አንድ ዝሆን በሦስት ወይም በአራት ዓመታት ውስጥ ሁሉንም ትእዛዞች መረዳት ይችላል። ትእዛዞቹን አንዴ ከተማረ በኋላ ፈጽሞ አይረሳቸውም። የዝሆን አንጎል ከሰውነቱ ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ ቢሆንም ይህ እንስሳ በጣም ብልህ ነው።

ዝሆንን መንከባከብ

የአንድን ዝሆን ጤንነት መጠበቅና እንዳይከፋ ማድረግ ያስፈልጋል። በየቀኑ ገላውን መታጠቡ አስፈላጊ ነው። ዝሆኑ ገላውን በሚታጠብበት ወቅት ማሃውቱ፣ ወፍራም ሆኖም ለስላሳና በቀላሉ ሊጎዳ የሚችለውን ቆዳውን ለማሸት ድንጋይና በጥሩ ሁኔታ የተከረከመ የኮኮናት ቅርፊት ይጠቀማል።

ከዚያም ዝሆኑ ቁርሱን የሚመገብበት ሰዓት ይደርሳል። በመሆኑም ማሃውቱ ስንዴ፣ ማሽላና ሆርስ ግራም በመባል የሚታወቅ የከብት መኖ አንድ ላይ በወፍራሙ ለውሶ በማዘጋጀት ይመግበዋል። ዝሆኑ ከሚቀርብለት ዋነኛ የምግብ ዓይነቶች መካከል ቀርከሃ፣ የዘንባባ ቅጠልና ሣር ይገኙበታል። ምግቡ ውስጥ ጥቂት ካሮትና ሸንኮራ አገዳ ቢጨመርለት ደስ ይለዋል። ዝሆኖች አብዛኛውን ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት በመብላት ነው። በየቀኑ 140 ኪሎ ግራም ምግብና 150 ሊትር ያህል ውኃ ያስፈልጋቸዋል! ማሃውቱ ከዝሆኑ ጋር ወዳጅ ሆኖ ለመቀጠል ከፈለገ ቀለቡን በሚገባ ማሟላት ይኖርበታል።

የአያያዝ ጉድለት የሚያስከትለው መዘዝ

ገራም የሆነውን የሕንድ ዝሆን ከአቅሙ በላይ እንዲሠራ ማድረግ አይቻልም። ዝሆኖች በሚጮኹባቸውም ይሁን በሌላ መንገድ ሊቀጧቸው በሚሞክሩ ማሃውቶች ላይ ጉዳት ያደርሳሉ። በሕንድ የሚታተመው ሰንዴይ ሄራልድ የተባለው ጋዜጣ “ማሃውቶች ባደረሱበት በደል የተነሳ . . . እጅግ ስለተቆጣ” አንድ ዝሆን ዘግቧል። ጋዜጣው እንዳለው ከሆነ “ማሃውቱ ሲመታው እጅግ የተቆጣው ዝሆን ከቁጥጥር ውጪ በመሆኑ . . . የሚያደነዝዝ መድኃኒት መወጋት አስፈልጎት ነበር።” በሚያዝያ 2007፣ ኢንዲያ ቱደይ ኢንተርናሽናል የተባለው መጽሔት እንደሚከተለው በማለት ዘግቧል፦ “ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥ ብቻ ከ10 የሚበልጡ ተባዕት ዝሆኖች በበዓላት ላይ ከቁጥጥር ውጭ ሆነው ነበር፤ ካለፈው ዓመት ጥር ወር ወዲህ 48 ማሃውቶች በተቆጡት አውሬዎች ተገድለዋል።” እንዲህ ዓይነት ነገሮች በአብዛኛው የሚከሰቱት የተባዕቶቹ ዝሆኖች የፆታ ፍላጎት በሚያይልበት መስት ተብሎ በሚጠራው ወቅት ነው። በዓመት አንዴ የሚከሰተው ይህ ሁኔታ ከዝሆኖች የመራቢያ ወቅት ጋር የተያያዘ ሲሆን በዚህ ጊዜ ለአካለ መጠን በደረሱ ተባዕት ዝሆኖች ሰውነት ውስጥ የሚገኘው ቴስቶስትሮን የተባለ ሆርሞን መጠኑ ከፍ ይላል። በመሆኑም ዝሆኖቹ ሌሎቹን ተባዕት ዝሆኖችና ሰዎችን ሊተናኮሉ ብሎም እንግዳ ጠባይ ሊያሳዩ ይችላሉ። ይህ ወቅት ከ15 ቀን እስከ ሦስት ወር ድረስ ሊቆይ ይችላል።

አንድን ዝሆን የሚያስቆጣው ሌላው ነገር ደግሞ ተሸጦ በሌላ ማሃውት እጅ መግባቱ ነው። በዚህ ጊዜ ዝሆኑ የሚያሳየው ባሕርይ ከቀድሞው ጌታው ጋር ጥብቅ ትስስር እንደነበረው በግልጽ ያሳያል። በመሆኑም ዝሆኑ አዲሱ መኖሪያውን እንዲለምድ ለማድረግ ቀድሞ ሲንከባከበው የነበረው ሰው አብሮት ወደ አዲሱ መኖሪያው ይሄዳል። ከዚያም አዲሱ ማሃውት የዝሆኑን ባሕርይ እስኪለምድ ድረስ ሁለቱ ማሃውቶች አብረው ሲሠሩ ይቆያሉ። አንድ ማሃውት ሲሞትና ዝሆኑ በሌላ ሰው እጅ ሲገባ ችግሩ ከዚህ የባሰ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ዝሆኑ አዲሱን ሁኔታ እየተገነዘበ መሄዱና መልመዱ አይቀርም።

አንዳንድ ሰዎች ይህን ኃያል እንስሳ ሊፈሩት ቢችሉም በጥሩ ሁኔታ የሠለጠነ ዝሆን በደግነት የሚይዘውን ጌታውን ይታዘዛል። ዝሆኑ በደግነት ከተያዘ ማሃውቱ ለጊዜው በማይኖርበት ጊዜም እንኳን በሰንሰለት መታሰር አያስፈልገውም። ማሃውቱ ማድረግ የሚጠበቅበት ነገር ቢኖር የበትሩን አንድ ጫፍ በዝሆኑ እግር ላይ፣ ሌላውን ጫፍ ደግሞ በመሬት ላይ አድርጎ ለእንስሳው እንዳይነቃነቅ መንገር ብቻ ነው። ዝሆኑ በታዛዥነት ከቆመበት ቦታ ንቅንቅ ሳይል ይጠብቃል። መግቢያው ላይ እንደተገለጸው በዝሆንና በማሃውቱ መካከል ያለው ተባብሮ የመሥራት መንፈስ የሚያስደንቅና ልብ የሚነካ ሊሆን ይችላል። አዎን፣ አንድ ጥሩ ማሃውት በዝሆኑ ላይ እምነት ሊጥል ይችላል።

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

የሰው ልጅና ዝሆን—ብዙ ዘመናት ያስቆጠረ ታሪክ አላቸው

የሰው ልጅ ዝሆኖችን ማላመድ የጀመረው ከረዥም ጊዜ በፊት ነው። በዚህ ረገድ በብዙዎች ዘንድ የሚታወቀው ጥንታዊ ታሪክ በካርቴጁ ጄኔራል በሃኒባል ዘመን የተፈጸመው ሳይሆን አይቀርም። በሦስተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት፣ በሰሜን አፍሪካ ትገኝ የነበረችው የካርቴጅ ከተማ ከሮም ጋር የፒዩኒክ ጦርነቶች ተብለው የሚጠሩ በርካታ ዓመታት የፈጁ ተከታታይ ውጊያዎችን አድርጋ ነበር። ሃኒባል በሮም ላይ ለመዝመት በማቀድ ሠራዊቱን ስፔን ውስጥ በምትገኘው በካርታጄና ከተማ ሰበሰበ። በመጀመሪያ ፒረኒዝ የሚባሉትን የተራራ ሰንሰለቶች በማቋረጥ በአሁኑ ወቅት ፈረንሳይ ተብላ ወደምትታወቀው አገር ገባ። ከዚያም አርኪኦሎጂ መጽሔት “በታሪክ ዘመናት ውስጥ የተፈጸመ እጅግ ታላቅ ወታደራዊ ጀብድ” ብሎ በጠራው ዘመቻ 25,000 ተዋጊዎችን ያቀፈው የሃኒባል ሠራዊት 37 የአፍሪካ ዝሆኖችንና ቀለብ የጫኑ ብዙ የጋማ ከብቶችን አስከትሎ የአልፕስ ተራሮችን በማቋረጥ ወደ ጣሊያን ዘለቀ። በጉዟቸው ላይ ብርዱን፣ በረዶ የቀላቀለውን ኃይለኛ ነፋስና ከተራራው ላይ የሚወርደውን የድንጋይ ናዳ መቋቋም እንዲሁም በተራራዎቹ ላይ ከሚኖሩት ጎሣዎች ጋር መዋጋት ነበረባቸው። ጉዞው ለዝሆኖቹ እጅግ አድካሚ ነበር። ሃኒባል ጣሊያን በገባ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ሁሉም ዝሆኖች ሞቱ።

[ምንጭ]

© Look and Learn Magazine Ltd/The Bridgeman Art Library

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ማሃውቱ የዝሆኑን ወፍራም፣ ሆኖም ለስላሳና በቀላሉ የሚጎዳ ቆዳ ሲያጥብ

[ምንጭ]

© Vidler/mauritius images/age fotostock

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

© PhotosIndia/age fotostock