በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የመጽሐፍ ቅዱስ ንባቤን አስደሳች ማድረግ የምችለው እንዴት ነው?

የመጽሐፍ ቅዱስ ንባቤን አስደሳች ማድረግ የምችለው እንዴት ነው?

የወጣቶች ጥያቄ

የመጽሐፍ ቅዱስ ንባቤን አስደሳች ማድረግ የምችለው እንዴት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስን የምታነበው እንዴት ነው? (በአንዱ ላይ ምልክት አድርግ)

□ በየቀኑ

□ በየሳምንቱ

□ ሌላ

የሚከተለውን ዓረፍተ ነገር አሟላ።

መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብ የማያስደስተኝ . . . ጊዜ ነው። (መልስ ይሆናሉ በምትላቸው ሁሉ ላይ ምልክት አድርግ)

□ በሚሰለቸኝ

□ በማይገባኝ

□ ትኩረቴ በሚከፋፈልበት

□ ሌላ

መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ እምብዛም አያስደስትህም? ከሆነ የ18 ዓመቱ ዊል “መጽሐፍ ቅዱስ አሰልቺ ሊመስል ይችላል” ሲል በተናገረው ሐሳብ ሳትስማማ አትቀርም። ይሁን እንጂ “እንዲህ ሊሰማህ የሚችለው እንዴት ማንበብ እንዳለብህ ካላወቅክ ብቻ ነው” በማለት አክሎ ተናግሯል።

መጽሐፍ ቅዱስን እንዴት ማንበብ እንዳለብህ ማወቅ ያስፈለገው ለምንድን ነው?

ጥሩ ውሳኔ ማድረግ

እውነተኛ ጓደኞች ማግኘት

ጭንቀትን መቋቋም

የምትችለው እንዴት እንደሆነ ይበልጥ ማወቅ ትፈልጋለህ?

መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህንና ሌሎች ርዕሰ ጉዳዮችን አስመልክቶ እንደ ዕንቁ ውድ የሆኑ ጠቃሚ ምክሮችን ይዟል። እነዚህን ዕንቁዎች ማግኘት ጥረት እንደሚጠይቅ ምንም ጥርጥር የለውም። ዕንቁዎቹን ለመፈለግ የሚደረገው ጥረት ሀብት ለማግኘት ከሚደረግ ጥረት ጋር ይመሳሰላል፤ ፍለጋው ይበልጥ አስቸጋሪ በሆነ መጠን የሚገኘውም ነገር ይበልጥ አስደሳች ይሆናል!—ምሳሌ 2:1-6

ታዲያ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ውድ ሀብት ፈልገህ ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው? በስተ ቀኝ ያለው ተቆርጦ የሚወጣው ሣጥን፣ መጽሐፍ ቅዱስን እንዴት ማንበብ እንዳለብህና በግልባጩ ደግሞ በየትኛው ቅደም ተከተል ልታነብ እንደምትችል የሚጠቁሙ አንዳንድ ሐሳቦችን ይዟል። ከዚህም በተጨማሪ በቀጣዮቹ ገጾች ላይ ከሚገኙት ሐሳቦች መካከል ማራኪ ሆነው ያገኘሃቸውን ተግባራዊ ለማድረግ ሞክር።

ኢንተርኔት የምትጠቀም ከሆነ www.watchtower.org/e/bible ከተባለው ድረ ገጽ ላይ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ትችላለህ።

www.watchtower.org/ype በሚለው ድረ ገጽ ላይ “Young People Ask” በሚል አምድ ሥር ተጨማሪ ርዕሶችን ማግኘት ይቻላል።

ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች

ከአንድ ነገር ጥቅም ማግኘትህ የተመካው በምታደርገው ጥረት ላይ ነው ሲባል ሰምተህ ይሆናል።

መጽሐፍ ቅዱስን ከማንበብ ጋር በተያያዘ ይህ አባባል ምን ያህል እውነት ነው?

የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብህን መቼ ማድረግ ትችላለህ?

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ የሚቻልበት መንገድ

ከማንበብህ በፊት . . .

ትኩረትህ እንዳይከፋፈል ጸጥ ያለ አካባቢ ምረጥ።

ያነበብከውን መረዳት እንድትችል ጸልይ።

በምታነብበት ጊዜ . . .

በዘመኑ የነበረውን ሁኔታ በዓይነ ሕሊናህ ለመሳል እንድትችል ከምታነበው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ጋር የተያያዙ ካርታዎችንና ሥዕሎችን ተመልከት።

መቼቱንና ዝርዝር ሁኔታዎችን ለማገናዘብ ጥረት አድርግ።

የግርጌ ማስታወሻዎቹንና ማጣቀሻዎቹን ተመልከት።

በምታነብበት ጊዜ እንደሚከተሉት ያሉ ጥያቄዎችን ጠይቅ፦

እውነታ፦ ይህ የተፈጸመው መቼ ነበር? ይህን ሐሳብ የተናገረው ማነው? የተነገሩትስ ለማን ነው?

የያዘው መልእክት፦ ያነበብኩትን ሐሳብ ለሌላ ሰው እንዴት ማስረዳት እችላለሁ?

ጠቀሜታ፦ ይሖዋ አምላክ ይህን ዘገባ በቃሉ ውስጥ እንዲካተት ያደረገው ለምንድን ነው? ስለ ይሖዋ ባሕርይ ወይም ነገሮችን ስለሚያከናውንበት መንገድ ምን ይገልጻል? በሕይወቴ ውስጥ ተግባራዊ ላደርጋቸው የምችላቸው ምን ትምህርቶችን ይዟል?

ካነበብክ በኋላ . . .

ተጨማሪ ምርምር አድርግ። ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል እና “ቅዱሳን መጻሕፍት ሁሉ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፉና ጠቃሚ ናቸው” እንደሚሉት ያሉ በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጁ መጻሕፍት በቋንቋህ የሚገኙ ከሆነ ተጠቀምባቸው።

በድጋሚ ጸልይ። ምን ትምህርት እንዳገኘህና የቀሰምከውን እውቀት እንዴት በሥራ ላይ ልታውለው እንዳሰብክ ለይሖዋ ንገረው። ቃሉን መጽሐፍ ቅዱስን ስለሰጠህ አመስግነው።

 [በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

መጽሐፍ ቅዱስን በየትኛው ቅደም ተከተል ማንበብ ትችላለህ?

ምርጫዎች . . .

ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው አንብብ።

መጻሕፍቱ በተጻፉበት አሊያም በመጽሐፉ ውስጥ የተጠቀሱት ታሪኮች በተፈጸሙበት ቅደም ተከተል መሠረት አንብብ።

በየቀኑ የተለያዩ የቅዱሳን መጻሕፍት ክፍሎችን አንብብ።

ሰኞ፦ አስደናቂ ክንውኖችን የያዙ ዘገባዎች (ከዘፍጥረት እስከ አስቴር)

ማክሰኞ፦ የኢየሱስን ሕይወትና ያስተማራቸው ነገሮች (ከማቴዎስ እስከ ዮሐንስ)

ረቡዕ፦ ስለ ጥንቶቹ ክርስቲያኖች (የሐዋርያት ሥራ)

ሐሙስ፦ ትንቢትና የሥነ ምግባር መመሪያዎች (ከኢሳይያስ እስከ ሚልክያስ እና ራእይ)

ዓርብ፦ ልብ የሚነኩ ግጥሞችና መዝሙራት (ኢዮብ፣ መዝሙር እና ማሕልየ መሓልይ)

ቅዳሜ፦ ለሕይወታችን የሚጠቅሙ ጥበብ ያዘሉ ምክሮች (ምሳሌና መክብብ)

እሁድ፦ ለጉባኤዎች የተጻፉ ደብዳቤዎች (ከሮም እስከ ይሁዳ)

ለማንበብ የምትፈልገው በየትኛውም ቅደም ተከተል ይሁን ያነበብከውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል መርሳት የለብህም! ይህን ለማድረግ ባነበብከው ምዕራፍ ላይ ✔ ማድረግ አሊያም ሌላ ዓይነት መንገድ መጠቀም ትችላለህ።

ይህን ሣጥን ቆርጠህ በማውጣት መጽሐፍ ቅዱስህ ውስጥ አስቀምጠው!

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የምታነበው ጥቅስ ሕያው እንዲሆንልህ አድርግ!

በምታነበው ነገር ተመሰጥ። ለምሳሌ ያህል፦

በምታነበው ታሪክ ላይ የተዘረዘሩትን ስሞች በመጠቀም የዘር ሐረግ ሥራ።

ሥዕላዊ መግለጫ ሥራ። ለምሳሌ ያህል፣ ታማኝ ስለሆነ አንድ ሰው እያነበብክ ከሆነ የግለሰቡን ባሕርያትና ድርጊቶች ካገኛቸው በረከቶች ጋር በመስመር አገናኝ።—ምሳሌ 28:20

[ሥዕላዊ መግለጫ]

የአምላክ ወዳጅ

ታዛዥ

ታማኝ

↑ ↑

አብርሃም

ታሪኩን በሥዕል ለመግለጽ ሞክር።

የተከናወነውን ድርጊት በቅደም ተከተል የሚያሳዩ ሥዕሎች ጫር ጫር አድርግ። እያንዳንዱ ሥዕል ምን እንደሚያሳይ ግለጽ።

የኖኅን መርከብ ወይም ይህን የመሳሰሉ አነስተኛ ሞዴሎችን ሥራ።—ለምሳሌ ያህል፣ የጥር 2007 ንቁ! መጽሔት ገጽ 22ን ተመልከት።

ከጓደኞችህ ወይም ከቤተሰብህ አባላት ጋር በመሆን ድምፅህን ከፍ አድርገህ አንብብ። እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦ አንድ ሰው ትረካውን እንዲያነብ አድርግ። ሌሎች ደግሞ በታሪኩ ላይ የተጠቀሱት ሰዎች የተናገሩትን ሊያነቡ ይችላሉ።

አንድ ታሪክ ምረጥና በዜና መልክ አዘጋጀው። ከዚያም በታሪኩ ውስጥ ለተጠቀሱት ግለሰቦችና የዓይን ምሥክሮች “ቃለ መጠይቅ” በማድረግ ዘገባውን ከተለያየ አቅጣጫ አብራራ።

ጥበብ የጎደለው ውሳኔ ስላደረገ ሰው የሚገልጽ አንድ ታሪክ ምረጥና ግለሰቡ ምን ቢያደርግ ውጤቱ የተለየ ሊሆን ይችል እንደነበረ አስብ! ለምሳሌ፣ ጴጥሮስ ኢየሱስን ስለ መካዱ የሚናገረውን ዘገባ ተመልከት። (ማርቆስ 14:66-72) በዚያ ወቅት ጴጥሮስ ምን ቢያደርግ የተሻለ ይሆን ነበር?

በፊልም ወይም በድምፅ የተዘጋጁ የመጽሐፍ ቅዱስ ድራማዎችን ተመልከት ወይም አዳምጥ።

ባነበብከው ላይ ተመሥርተህ የራስህን ድራማ ጻፍ። ከድራማው ሊገኝ የሚችለውን ትምህርትም ግለጽ።—ሮም 15:4

እንዲህ ማድረግ ትችላለህ፦ ከጓደኞችህ ጋር በመሆን ድራማውን ተውኑት።

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

መጽሐፍ ቅዱስ የማንበብ ፍላጎት እንዲያድርብህ

ግብ አውጣ! የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብህን ለመጀመር ያሰብክበትን ቀን ከዚህ በታች ጻፍ።

․․․․․

ይበልጥ የሚማርክህን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ምረጥ። ( “መጽሐፍ ቅዱስን በየትኛው ቅደም ተከተል ማንበብ ትችላለህ?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) ከዚያም መጀመሪያ ላይ ለማንበብ የመረጥከውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ከዚህ በታች ጻፍ።

․․․․․

በትንሽ በትንሹ ማንበብ ጀምር። መጽሐፍ ቅዱስን ምንም ካለማንበብ፣ ለ15 ደቂቃ ማንበብ የተሻለ ነው። መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ የመደብከው ጊዜ ምን ያህል እንደሆነ ከዚህ በታች ጻፍ።

․․․․․

እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦ ለጥናት ብቻ የምትገለገልበት መጽሐፍ ቅዱስ ይኑርህ። ማስታወስ የምትፈልጋቸውን ሐሳቦች ላዩ ላይ ጻፍበት። ልብህን በሚነኩት ጥቅሶች ላይ ምልክት አድርግባቸው።

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

እኩዮችህ የሰጡት አስተያየት

“ሁልጊዜ ከመተኛቴ በፊት ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተወሰኑ ቁጥሮችን ለማንበብ እሞክራለሁ። ይህም ከመተኛቴ በፊት የማሰላስልበት ጥሩ ነገር እንዳገኝ ረድቶኛል።”—ማገን

“በአንድ ጥቅስ ላይ ለ15 ደቂቃ አሰላስላለሁ። የግርጌ ማስታወሻዎቹንና ማጣቀሻዎቹን በሙሉ የማነብ ስሆን ተጨማሪ ምርምርም አደርጋለሁ። አንዳንድ ጊዜ አንድ ጥቅስ አንብቤ አልጨርስ ይሆናል፤ ይሁን እንጂ በዚህ መንገድ ማንበቤ ጠቅሞኛል።”—ኮሪ

“በአንድ ወቅት፣ መጽሐፍ ቅዱስን በ10 ወራት አንብቤ መጨረስ ችዬ ነበር። በዚህ ጊዜ ውስጥ አንብቤ መጨረሴ ከዚያ በፊት አስተውዬው በማላውቀው መንገድ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት ክፍሎች እርስ በርስ ያላቸውን ግንኙነት እንድገነዘብ አስችሎኛል።”—ጆን

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ብዙ ምርጫ አለህ!

አንድ ታሪክ ምረጥ። መጽሐፍ ቅዱስ በርካታ እውነተኛ ታሪኮችን ያያዘ መጽሐፍ ነው። ደስ የሚልህን አንድ ታሪክ ምረጥና ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው አንብብ።

እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦ ካነበብከው ታሪክ ተጨማሪ ትምህርት ማግኘት የምትችለው እንዴት እንደሆነ ለማወቅ በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች—ጥራዝ 2 (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 292 ተመልከት።

አንድ የወንጌል ዘገባ ምረጥ። የማቴዎስ (መጀመሪያ ላይ የተጻፈውን)፣ የማርቆስ (አጠር አጠር ተደርገው የተጻፉ አስደናቂ ክንውኖች ያሉበትን)፣ የሉቃስ (ለጸሎትና ለሴቶች ልዩ ትኩረት የሚሰጠውን) ወይም የዮሐንስ (በሌሎች ወንጌሎች ውስጥ ያልተገለጹ በርካታ ሐሳቦች የሰፈሩበትን) ወንጌል አንብብ።

እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦ የምታነበውን የወንጌል ዘገባ ከሌሎቹ የተለየ የሚያደርገው ምን እንደሆነ ለመገንዘብ ከማንበብህ በፊት ስለ መጽሐፉና ስለ ጸሐፊው ለማወቅ የተወሰነ ምርምር አድርግ።

አንድ መዝሙር ምረጥ። ለምሳሌ ያህል፦

ብቸኝነት ካጠቃህና ጓደኛ እንደሌለህ ሆኖ ከተሰማህ መዝሙር 142⁠ን አንብብ።

ባሉብህ ድክመቶች የተነሳ ተስፋ ከቆረጥክ መዝሙር 51⁠ን አንብብ።

አምላክ ያወጣቸውን መሥፈርቶች በተመለከተ ጥያቄ ከተፈጠረብህ መዝሙር 73⁠ን አንብብ።

እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦ ካነበብካቸው መዝሙራት ውስጥ አንተን ይበልጥ ያበረታቱህን መዝግበህ ያዝ።

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ጥልቅ ምርምር አድርግ

መቼቱን አስብ። ጊዜውን፣ ቦታውንና በጥቅሱ ዙሪያ ያለውን ሐሳብ ለማገናዘብ ሞክር።

ለምሳሌ ያህል፦ ሕዝቅኤል 14:14ን አንብብ። ይሖዋ፣ ዳንኤልን ከኖኅና ከኢዮብ ጋር በጥሩ ምሳሌነት ሲጠቅሰው ዳንኤል ስንት ዓመቱ ሊሆን ይችላል?

ፍንጭ፦ ሕዝቅኤል ምዕራፍ 14 የተጻፈው ዳንኤል ወደ ባቢሎን በግዞት ከተወሰደ ከአምስት ዓመት በኋላ ነው፤ በዚያን ወቅት ዳንኤል በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ሳይሆን አይቀርም።

ምርምር ማድረግህ የሚያስገኝልህ ውድ ሀብት፦ ዳንኤል ገና ልጅ መሆኑ በይሖዋ ዘንድ ታማኝ ተደርጎ እንዳይቆጠር ምክንያት ሆኗል? የይሖዋን በረከት ያስገኙለት የትኞቹን ጥሩ ውሳኔዎች ማድረጉ ነው? (ዳንኤል 1:8-17) ዳንኤል የተወው ምሳሌ ጥሩ ውሳኔ እንድታደርግ ሊረዳህ የሚችለው እንዴት ነው?

ዝርዝር ሁኔታውን ለማስተዋል ሞክር። አንዳንድ ጊዜ በአንድ ወይም በሁለት ቃላት ላይ ብቻ ምርምር ማድረግ ይቻላል።

ለምሳሌ ያህል፦ ማቴዎስ 28:7ን ከማርቆስ 16:7 ጋር አወዳድር። ማርቆስ፣ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱና “ለጴጥሮስ” እንደሚታይ የሚገልጸውን ዝርዝር ሐሳብ ያሰፈረው ለምንድን ነው?

ፍንጭ፦ ማርቆስ እነዚህ ሁኔታዎች ሲፈጸሙ በቦታው አልነበረም፤ ይህን መረጃ ያገኘው ከጴጥሮስ መሆን አለበት።

ምርምር ማድረግህ የሚያስገኝልህ ውድ ሀብት፦ ጴጥሮስ፣ ኢየሱስ ሊያየው እንደሚፈልግ በማወቁ ተጽናንቶ መሆን አለበት የምንለው ለምንድን ነው? (ማርቆስ 14:66-72) ኢየሱስ ለጴጥሮስ እውነተኛ ወዳጅ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው? አንተስ ኢየሱስን መምሰልና ለሌሎች እውነተኛ ወዳጅ መሆን የምትችለው እንዴት ነው?

ተጨማሪ ምርምር አድርግ። ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ላይ ምርምር አድርግ።

ለምሳሌ ያህል፦ ማቴዎስ 2:7-15ን አንብብ። ኮከብ ቆጣሪዎቹ ኢየሱስን ሊጠይቁት የሄዱት መቼ ነበር?

ፍንጭ፦ በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን የጥር 1, 2008 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 31⁠ን ተመልከት።

ምርምር ማድረግህ የሚያስገኝልህ ውድ ሀብት፦ የኢየሱስ ቤተሰቦች ግብፅ በነበሩበት ጊዜ ይሖዋ የሚያስፈልጋቸውን ቁሳዊ ነገር ያሟላላቸው እንዴት ሊሆን ይችላል? በአምላክ መታመንህ አስጨናቂ ሁኔታዎችን ለመቋቋም ሊረዳህ የሚችለው እንዴት ነው?—ማቴዎስ 6:33, 34