በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

በ1970 እና በ2005 መካከል ባሉት 35 ዓመታት ውስጥ የጀርባ አጥንት ካላቸው የእንስሳት ዝርያዎች ይኸውም ከዓሦች፣ በደረታቸው ከሚሳቡ ፍጥረታት፣ ከአእዋፍ፣ ከአጥቢ እንስሳት እንዲሁም በምድርና በውኃ ውስጥ ከሚኖሩት ፍጥረታት መካከል አንድ አራተኛ የሚሆኑት ከምድር ገጽ ጠፍተዋል።ሱትዶይቸ ጻይቱንግ፣ ጀርመን

ዚምባብዌ 2.2 ሚሊዮን በመቶ የደረሰውን የዋጋ ግሽበት ለመቋቋም በነሐሴ 2008 ከገንዘብ ኖቶች ላይ አሥር ዜሮዎችን ሰረዘች። በመሆኑም የ10 ቢሊዮን የገንዘብ ኖት በአሁኑ ጊዜ አሥሩ ዜሮዎች ተቀንሰውለት አንድ “ዚምዶላር” ሆኗል።—አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ፣ ዚምባብዌ

“በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በ2005 ከ12,000 የሚበልጡ ሰዎች በሽጉጥ እንደተገደሉ ተዘግቧል። ይሁን እንጂ የቆሰሉትና በጥይት ተመትተው በሕይወት የተረፉት ሰዎች ቁጥር ከዚህ በእጅጉ የሚበልጥ ሲሆን በ2006 ወደ 53,000 የሚጠጉ ሰዎች በድንገተኛ የሕክምና ክፍሎች ታክመዋል።—ዘ ሲያትል ታይምስ፣ ዩናይትድ ስቴትስ

የገና ሰሞን “የደስታ” ወቅት ነው?

አውስትራሊያ ውስጥ 20 በመቶ ገደማ የሚሆኑ የፍቺ ጥያቄዎች የሚቀርቡት የገና እና የአዲስ ዓመት በዓል እንዳለፈ መሆኑን የሲድኒው ሰንዴይ ቴሌግራፍ ገልጿል። ከፍቺ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን የሚከታተሉት ባሪ ፍሬክስ የተባሉ የሕግ ባለሞያ እንዲህ ብለዋል፦ “[ከበዓሉ በኋላ] ቢሯችን ገና ከመከፈቱ፣ የተጣሉ ወይም መስማማት የተሳናቸው በርካታ ሰዎች ወደ እኛ ይመጣሉ። ሰዎች የገና በዓል፣ በቴሌቪዥን ፕሮግራሞችና በማስታወቂያዎች ላይ እንደሚታየው አስደሳች እንደሚሆን ይጠብቃሉ።” ፍሬክስ አክለው እንደተናገሩት እነዚህ ሰዎች ሕይወታቸው “አንድ ቤተሰብ ሊኖረው ይገባል ብለው ከሚያስቡት ሕይወት” ጋር አልጣጣም ሲላቸው ለመፋታት ይወስናሉ። ሆኖም የአውስትራሊያ የቤተሰብ ማኅበር ቃል አቀባይ የሆኑት አንጄላ ካንዌ እንደተናገሩት “ብዙውን ጊዜ ፍቺ፣ ሥር የሰደዱ ችግሮችን ለመፍታት አሊያም ሰዎች እንደሚያስቡት ሰላምና ደስታ ለማግኘት አያስችልም።” ከዚህ ይልቅ እኚህ ሴት እንደገለጹት “ትዳራችሁ እንዳይፈርስና የሰመረ እንዲሆን ጥረት ማድረጉ የተሻለ ነው።”

“ማዋለጃ ቤቶች” ሕይወት እያዳኑ ነው

በፔሩ የእናቶችን ሞት ለመቀነስ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው። በአንዲስ ተራራማ አካባቢዎች የሚኖሩ ሴቶች፣ ቤት ውስጥ ከሚወልዱ ይልቅ በክሊኒክ የሚሰጡ የሕክምና እርዳታዎችን እንዲሹ ለማበረታታት ሲባል ባለፈው አሥር ዓመት ውስጥ በፔሩ 390 “ማዋለጃ ቤቶች” ተከፍተዋል። አንዲት ነፍሰ ጡር ሴት የምትወልድበት ጊዜ እስኪደርስ ድረስ በክሊኒክ አቅራቢያ ከተሠሩት ከእነዚህ ማዋለጃ ቤቶች በአንዱ ውስጥ ከቤተሰቧ ጋር መቆየት ትችላለች። ከኩዝኮ የተገኘ የሮይተርስ ዜና እንደገለጸው እነዚህን ክሊኒኮች ተፈላጊ ካደረጓቸው ነገሮች አንዱ “ዘመናዊውን ሕክምና ከአካባቢው ልማድ ጋር” ማዋሃዳቸው ነው። “ቆሞ የመውለድን ልማድ” እንደምሳሌ መጥቀስ ይቻላል፤ እንዲህ ማድረግ ለአንዲት ሴት “ምጡን የሚቀንስላትና ለመውለድ የሚወስደውን ጊዜ የሚያሳጥርላት ከመሆኑም ሌላ . . . ተኝታ ቢሆን ኖሮ ማየት ከምትችለው በተሻለ ልጇ ሲወለድ መመልከት ትችላለች።”

ሁልጊዜ ይዘገያሉ

በ2008 የዩናይትድ ስቴትስ የትራንስፖርት ክፍል ያወጣው ሪፖርት እንደሚያሳየው 30 በመቶ የሚሆኑት የአገር ውስጥ በረራዎች ከ15 ደቂቃ በላይ ዘግይተው ይደርሳሉ። ዘግይተው በመድረስ ከታወቁት በረራዎች መካከል አንዴም እንኳ በሰዓቱ ደርሶ የማያውቀው ከካሊፎርኒያ ወደ ቴክሳስ የሚደረገው በረራ ይገኝበታል።