በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከመድኃኒት የተሻለ መፍትሔ

ከመድኃኒት የተሻለ መፍትሔ

ከመድኃኒት የተሻለ መፍትሔ

በመጀመሪያው ርዕስ ላይ የተጠቀሰችው ሊና ዕድሜዋ 32 ዓመት በሆነ ጊዜ በአብዛኛው ከመድኃኒት ጋር ተያያዥነት ባለው ችግር የተነሳ ‘በጥፋተኝነትና በተስፋ መቁረጥ ስሜት የተዋጠች ከመሆኑም በላይ ሁልጊዜ ሞቷን ትመኝ ነበር።’ እንዲህ ስትል ጽፋለች፦ “ባለትዳርና የልጆች እናት እንደመሆኔ መጠን ለቤተሰቤ ጥሩ ሰው ለመሆን እፈልግ ነበር። ይሁን እንጂ በራሴ ሕይወትም ሆነ በዓለም ውስጥ የማያቸው ነገሮች በሙሉ በጣም አሳዛኝና ተስፋ አስቆራጭ በመሆናቸው ጥሩ እንድሆን የሚያነሳሳኝ ምክንያት ያለ አይመስልም ነበር። የተወሰኑ ጊዜያት ጥሩ ሰው ለመሆን ሞክሬ ነበር፤ ሆኖም አልተሳካልኝም።”

ከጊዜ በኋላ ሊና ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመረች። ብዙም ሳይቆይ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ውስጣዊ ሰላምና እፎይታ ያስገኘላት ሲሆን ይህን ስሜት “ከዚህ በፊት ተሰምቶኝ የማያውቅ ልዩ ስሜት” በማለት ገልጻዋለች። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሠፈሩትን መሠረታዊ መመሪያዎች ማስተዋሏና ስለ ወደፊቱ ጊዜ ብሩሕ ተስፋ ማግኘቷ ሕይወቷን እንድትለውጥና ሱሷን እንድታሸንፍ ረድቷታል።

የሕይወት መመሪያዎች

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት ሕጎችና መመሪያዎች ፈጣሪያችን የሆነው ይሖዋ አምላክ ለእኛ እንዲስማሙ አድርጎ ያወጣቸው ናቸው። መዝሙር 19:7, 8 “የእግዚአብሔር ሕግ ፍጹም ነው፤ ነፍስንም መልሶ ያለመልማል፤ . . . የእግዚአብሔር ሕግጋት ትክክል ናቸው፤ ልብን ደስ ያሰኛሉ። የእግዚአብሔር ትእዛዝ ብሩህ ነው፤ ዐይንን ያበራል” ይላል።

ለምሳሌ ያህል፣ 2 ቆሮንቶስ 7:1 “ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ነገር ሁሉ ራሳችንን እናንጻ” ይላል። ሊና ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ መገንዘቧ ከሚያረክሱ ልማዶች እንድትላቀቅ ረድቷታል። በዚህ ተከታታይ ርዕሰ ትምህርት መጀመሪያ ላይ ተጠቅሳ የነበረችው ሚራም ተመሳሳይ ነገር አጋጥሟታል። ሚራ ለራስ ምታቷ የታዘዘላት መድኃኒት ሱሰኛ እንዳደረጋት የሚታወስ ነው። ታዲያ ከዚህ ችግር ለመላቀቅ ምን አደረገች? ከሐኪሟ ጋር በግልጽ የተወያየች ሲሆን እሱም ሌላ ሕክምና እንድትከታተል ረዳት። * ከዚህም ሌላ ሚራ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የሚሰጠውን መንፈሳዊ ማበረታቻ ጥሩ አድርጋ ተጠቅማበታለች።

በተጨማሪ ሊናም ሆነች ሚራ በጸሎት አማካኝነት አምላክን እርዳታ ይጠይቁ ነበር። ፊልጵስዩስ 4:6, 7 “ስለ ምንም ነገር አትጨነቁ፤ ከዚህ ይልቅ ስለ ሁሉም ነገር በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር ልመናችሁን ለአምላክ አቅርቡ፤ ከማሰብ ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነው የአምላክ ሰላም በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት ልባችሁንና አእምሯችሁን ይጠብቃል” ይላል። በጥንት ዘመን የኖረና እንዲህ ዓይነቱን ውስጣዊ ሰላም ያገኘ አንድ የአምላክ አገልጋይ ‘የውስጡ ጭንቀት በበዛ መጠን’ የአምላክ አጽናኝ ቃላት መረጋጋት፣ መጽናኛና ውስጣዊ ሰላም እንደሰጡት ጽፏል። (መዝሙር 94:19) እንዲህ ያሉ አጽናኝ ቃላትን ከመጽሐፍ ቅዱስ እንዲሁም የጉባኤ ሽማግሌዎችን ጨምሮ ጥሩ ባሕርይ ያላቸው ክርስቲያን ባልንጀሮቻችን በግል ከሚሰጡን ማበረታቻና ድጋፍ ማግኘት እንችላለን።

ይሁንና አንዳንድ ጊዜ አንድ ሰው መድኃኒት አላግባብ በመውሰዱ ምክንያት ምንም ዋጋ እንደሌለው ይሰማው ይሆናል። ለብዙ ዓመታት በሐኪም ትእዛዝ ትወስደው የነበረው መድኃኒት ሱስ የሆነባት ጃኒስ የምትባል ክርስቲያን እንደሚከተለው በማለት ጽፋለች፦ “ሱሰኞች ከፍተኛ መንፈሳዊ ኪሳራ ሊደርስባቸውና ራሳቸውን እጅግ ሊጠሉ ስለሚችሉ እርዳታ ለማግኘት በራሳቸው ተነሳስተው ወደ ይሖዋ መጸለይ አዳጋች ሊሆንባቸው ይችላል።” እንዲህ ባለው ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች የጎለመሱ ክርስቲያኖች እርዳታ እንዲያደርጉላቸው መጣራቸው አስፈላጊ ነው። እነዚህ የጎለመሱ ክርስቲያኖች በፍቅርና በትዕግሥት የሚሰጡት ማበረታቻና የሚያቀርቡት ጸሎት “የታመመውን ሰው ይፈውሰዋል።” (ያዕቆብ 5:15) እርግጥ ነው፣ ሱሰኛ የሆነው ትንሽ ልጅ ከሆነ ከሱሱ እንዲላቀቅ አልፎ ተርፎም እንዳያገረሽበት ወላጆቹ የልጁን መንፈሳዊ ጤንነትም ሆነ የሚወስደውን ሕክምና በንቃት መከታተል ይገባቸዋል።

ጃኒስ ሕክምና ማዕከል ገብታ ከሱሷ የተላቀቀች ሲሆን ከዚያን ጊዜ ወዲህ ከመድኃኒት ሱስ ነፃ ሆናለች። ጃኒስ እንዲህ በማለት ጽፋለች፦ “ይሖዋ ከሚያጋጥመኝ አስቸጋሪ ሁኔታ እንደሚያወጣኝ እተማመናለሁ። አሁን የተረጋጋሁ ከመሆኑም ሌላ የዱሮው የተጨዋችነት ባሕርዬ እየተመለሰ ነው።”

ችግሮች የማይኖሩበት ጊዜ

በመድኃኒት መጠቀም ታሪክ የሚሆንበት ጊዜ እየመጣ ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ራእይ 21:3, 4 እንዲህ በማለት መልሱን ይሰጠናል፦ “የአምላክ ድንኳን ከሰዎች ጋር ነው፤ . . . እሱም እንባን ሁሉ ከዓይኖቻቸው ላይ ይጠርጋል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም። [በዛሬው ጊዜ ያሉትን ችግሮች ጨምሮ] ቀድሞ የነበሩት ነገሮች አልፈዋል።”

መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያናዊውን ተስፋ ‘እርግጠኛና ጽኑ ከሆነው የነፍስ መልሕቅ’ ጋር ያመሳስለዋል። (ዕብራውያን 6:18, 19) በጥንት ዘመን መርከበኞች ማዕበል ሲያስቸግራቸው የመርከቡን መልሕቅ ወደ ባሕር ይጥላሉ። መልሕቁ በባሕሩ ወለል ላይ ከተቸከለ መርከቧ ማዕበሉን እንድትቋቋምና አደገኛ ከሆኑ ዓለቶችና የባሕር ዳርቻዎች ጋር እንዳትላተም ይረዳታል። በተመሳሳይም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸው “እርግጠኛና ጽኑ” ተስፋ በማናችንም ሕይወት ሊከሰቱ የሚችሉ እንደ ማዕበል ያሉ ችግሮች በሚያጋጥሙን ጊዜ ደግሞም መከሰታቸው አይቀርም ስሜታዊ፣ አእምሯዊና መንፈሳዊ ሚዛናችንን እንዳንስት ሊረዳን ይችላል።

ታዲያ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት ምክሮችና ትምህርቶች ምን ያህል ጠቃሚና የሚያበረታቱ እንደሆኑ ለማወቅ ለምን ራስህ ይህን መጽሐፍ አትመረምርም? የይሖዋ ምሥክሮች በዚህ ረገድ አንተን ለመርዳት ፈቃደኞች ናቸው፤ አንተም መጽሐፉን እንዳሰብከው ሆኖ እንደምታገኘው እርግጠኞች ነን።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.6 የሁሉም ሰው ሁኔታ ከሚራ ጋር ይመሳሰላል ማለት አይደለም። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንድ ሰዎች ካለባቸው በጣም የሚያሠቃይ ሕመም ፋታ የሚያገኙት ሱስ ሊያስይዙ የሚችሉ ኃይለኛ መድኃኒቶችን በሐኪም ክትትል በመውሰድ ሊሆን ይችላል። እንዲህ ያሉ ሕመምተኞች መድኃኒቱን የሚወስዱት ለመመርቀን ወይም የሱስ ተገዢ ለመሆን ፈልገው እንዳልሆነ የታወቀ ነው።—ምሳሌ 31:6ን ተመልከት።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ስለ ምንም ነገር አትጨነቁ፤ ከዚህ ይልቅ ስለ ሁሉም ነገር በጸሎትና በምልጃ . . . ልመናችሁን ለአምላክ አቅርቡ፤ . . . የአምላክ ሰላም በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት ልባችሁንና አእምሯችሁን ይጠብቃል።”—ፊልጵስዩስ 4:6, 7

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ጤንነትን ለማሻሻል የሚረዱ ተግባራዊ መንገዶች

የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረግ “ለጊዜውም ቢሆን ጥሩ ስሜት እንዲሰማህና ከመንፈስ ጭንቀትህ ለጥቂት ጊዜ እፎይታ እንድታገኝ ሊረዳህ ይችላል” በማለት ማኔጂንግ ዮር ማይንድ—ዘ ሜንታል ሄልዝ ጋይድ የተሰኘው መጽሐፍ ይናገራል። በአመጋገብህና አዘውትረህ በምታደርጋቸው ነገሮች ላይ ለውጥ ማድረግህም ሊረዳህ ይችላል። በልጅነቷ ብዙ ሥቃይ የደረሰባትን የቫለሪን ሁኔታ ተመልከት። ቢያንስ 12 የሚያህሉ የመድኃኒት ዓይነቶችን አላግባብ በመጠቀሟ ሱሰኛ ሆና ነበር። ይሁን እንጂ ከሱሷ መላቀቅ የቻለች ሲሆን በአንፃራዊ ሁኔታ ሲታይ ጥሩ ሕይወት እየመራች ነው። እንዲህ ያለ ለውጥ እንድታደርግ የረዳት ምንድን ነው?

ቫለሪ ለውጥ እንድታደርግ የረዳት ቴሌቪዥን ከመመልከትና አጠያያቂ የሆኑ ልብ ወለድ መጻሕፍትን ከማንበብ ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስን የማጥናት ጥሩ ልማድ ማዳበሯና ንቁ! መጽሔትን ጨምሮ በይሖዋ ምሥክሮች የሚዘጋጁ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዱ ጽሑፎች ለማንበብ ጊዜ መመደቧ ነው። በተጨማሪም አምላክ ብርታት እንዲሰጣት ያለማቋረጥ ትጸልይ የነበረ ከመሆኑም በላይ ከክርስቲያን ጉባኤ በምታገኘው እርዳታ ትጠቀም ነበር። እንዲሁም ጊዜዋን አጽናኝ የሆነውን የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ለሌሎች መንገርን በመሳሰሉ አስደሳች እንቅስቃሴዎች በመካፈል ታሳልፍ ነበር። ከዚህም ሌላ ቀደም ሲል ለጤንነት እምብዛም የማይረዱ ምግቦችን ታዘወትር ስለነበር በአመጋገቧ ላይ ከፍተኛ ለውጥ አደረገች። በዚህም ምክንያት ከሱሷ የተላቀቀች ሲሆን ያገኘችው ውጤት ሐኪሞቿንም እንኳ ሳይቀር አስገርሟል። አሁን ቫለሪ ከመድኃኒት ሱሰኝነት ነፃ ከሆነች ብዙ ዓመታት አልፈዋል። *

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.21 ለከባድ የመንፈስ ጭንቀት፣ ባይፖላር ዲስኦርደር ለተባለ ወይም ለሌላ ዓይነት የአእምሮ ሕመም በሐኪም ታዞልህ መድኃኒት እየወሰድክ ከሆነ የአንተ ሁኔታ ከቫለሪ ጋር ተመሳሳይ ላይሆን ይችላል። ስለዚህ ሐኪምህን ሳታማክር ምንም ዓይነት ለውጥ አታድርግ።