በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ውጥረት የበዛባቸው ልጆች

ውጥረት የበዛባቸው ልጆች

ውጥረት የበዛባቸው ልጆች

የስምንት ዓመት ልጅ የሆነው ፓብሎ የቤት ሥራውን ለምን እንዳልሠራ አስተማሪው ስትጠይቀው “ጊዜ አልበቃኝም፤ በጣም ደክሞኛል” በማለት መለሰላት። የፈዘዙት የፓብሎ ዓይኖች በቂ እንቅልፍ እንዳላገኘ ይጠቁማሉ። በስፔን እንደሚኖረው እንደ ፓብሎ ሁሉ በርካታ ልጆች ትምህርታቸውን በመከታተልና የቤት ሥራቸውን በመሥራት በየቀኑ 12 ሰዓት ወይም ከዚያ የበለጠ ጊዜ ስለሚያሳልፉ በጣም ይደክማቸዋል። ልጆች ይህን ያህል የትምህርት ቤት ሥራ የሚበዛባቸው ለምንድን ነው?

አንዳንድ ልጆች ከትምህርት ቤት ከወጡ በኋላ ወላጆቻቸው ወደ ቤት እስኪመለሱ ድረስ በተለያዩ እንቅስቃሴዎች እንዲካፈሉ ዝግጅት ይደረጋል። አንዳንድ ወላጆች፣ ልጆቻቸው በትምህርት ቤት ከፍተኛ ውጤት እንዲያመጡና ጥሩ ሥራ እንዲያገኙ ካላቸው ፍላጎት የተነሳ የሚያወጡላቸው ፕሮግራም በጣም የተጣበበ ነው። በደቡብ ኮሪያ የሚኖሩ በርካታ ወላጆች፣ በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆቻቸውን በቀን ውስጥ ለረጅም ሰዓታት ከበድ ያለ ትምህርት ወደሚሰጥባቸው ትምህርት ቤቶች ያስገቧቸዋል። እነዚህ ትምህርት ቤቶች፣ ተማሪዎቹ ሳምንቱን ሙሉ አንዳንድ ጊዜም ከጠዋቱ 1:30 እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ ወይም ከዚያ በላይ ቆይተው እንዲያጠኑ የሚያደርጋቸው ፕሮግራም ያወጡላቸዋል። ኒው ዮርክ ታምይስ ላይ የወጣው ዘገባ እንደገለጸው “ወላጆች ልጆቻቸው ታዋቂ ወደሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲገቡላቸው ሲሉ የማያደርጉት ነገር የለም።”

የስፔን ሳምታዊ መጽሔት የሆነው ሙሄር ኦይ እንዲህ ብሏል፦ “ልጆቻቸው ላይ ግፊት የሚያደርጉ ወላጆች ልጆቹ ከሁሉ የተሻለውን ነገር እንዲያገኙ ስለሚፈልጉ በትምህርታቸው በጣም ከፍተኛ ውጤት እንዲያመጡ ይጠብቁባቸዋል።” ልጆቹም የወላጆቻቸውን ፍላጎት ለማሟላት ሲሉ ከአቅማቸው በላይ ለመሥራት ይጥራሉ፤ ይህ ደግሞ ውጥረት ይፈጥርባቸዋል። ስፔን ውስጥ በጭንቀትና በውጥረት ላይ ጥናት የሚያካሂድ አንድ ድርጅት ፕሬዚዳንት የሆኑት አንቶኒዮ ካኖ “ልጆች ከአቅማቸው በላይ ጫና እንደሚደረግባቸው አስተውለናል” በማለት ተናግረዋል። አንዲት ፕሮፌሰር እንደተናገሩት ደግሞ በስፔን ከሚኖሩ ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች የሆኑ ልጆች መካከል 40 በመቶ የሚሆኑት ከፍተኛ ውጥረት አለባቸው። እንዲህ ያለው ውጥረት በልጆች ላይ ጉዳት የሚያስከትል ሲሆን ምናልባትም ሕይወታቸውን ወደ ማጥፋት ሊመራቸው ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ እንደዘገበው በደቡብ ኮሪያ “ከ10 እስከ 19 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ለሚገኙ ልጆች ሞት ምክንያት ከሆኑት ነገሮች መካከል ከመኪና አደጋ ቀጥሎ ሁለተኛውን ደረጃ የያዘው ራስን መግደል ነው።”

ልጆች በትጋት መማር እንዳለባቸውና ወላጆቻቸውም የሚያስፈልጋቸውን እገዛ ሁሉ ሊያደርጉላቸው እንደሚገባ ምንም ጥርጥር የለውም፤ ምክንያቱም ልጅነት ተመልሶ አይመጣም። ይሁንና “ልጆች እንደ አዋቂ ሊታዩ አይገባም፤ ያለ እረፍት ለረጅም ሰዓታት መሥራት አይችሉም” በማለት ኢሬን አሪማዳስ የተባሉ መምህርት ተናግረዋል። አፍቃሪ የሆኑ ወላጆች ይህንን ስለሚገነዘቡ ልጆቻቸው በቂ እረፍት እንዲያገኙ የሚያደርጉ ከመሆኑም ሌላ ከልጆቻቸው ጋር ሆነው ቤተሰቡን ሊጠቅሙ የሚችሉ እንቅስቃሴዎችን ለማከናወን ጥረት ያደርጋሉ። ጠቢቡ ንጉሥ ሰለሞን ሚዛናዊ መሆን አስፈላጊ እንደሆነ ሲጠቁም “በድካምና ነፋስን በመከተል ከሚገኝ ሁለት ዕፍኝ ይልቅ፣ በርጋታ የሚገኝ አንድ ዕፍኝ ይሻላል” ብሏል።—መክብብ 4:6 *

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.5 በርካታ ልጆች የሚያጋጥማቸውን ውጥረት በተመለከተ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ለማግኘት በሚያዝያ 2009 ንቁ! ላይ በወጣው “በትምህርት ቤትም ሆነ ከዚያ ውጪ የሚያጋጥም ውጥረት” በሚለው ርዕስ ሥር ያሉትን ተከታታይ ትምህርቶች ተመልከት።