በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በአውሮፓ በብዛት ይገኙ የነበሩት ግዙፍ አራዊት

በአውሮፓ በብዛት ይገኙ የነበሩት ግዙፍ አራዊት

በአውሮፓ በብዛት ይገኙ የነበሩት ግዙፍ አራዊት

ጣሊያን የሚገኘው የንቁ! ጸሐፊ እንዳዘጋጀው

በ1932 በመንገድ ሥራ ላይ የተሠማሩ ሰዎች በሮም በሚገኘው ኮሎሲየም አቅራቢያ ያለውን አካባቢ ሲቆፍሩ ከመካከላቸው አንዱ ጠንከር ያለ ነገር አጋጠመው። ይህ ሰው ያገኘው ነገር የዝሆን ጥርስና የራስ ቅል ነበር። እንዲህ ያለ ነገር ሲገኝ ይህ የመጀመሪያው አይደለም። በ17ኛው መቶ ዘመን የመጀመሪያው የዝሆን ቅሪተ አካል ከተገኘ ወዲህ ባሉት ዓመታት ውስጥ በሮምና በአካባቢዋ ወደ 140 የሚጠጉ የዝሆን ቅሪተ አካላት ተገኝተዋል።

አንዳንዶች እነዚህ አጥንቶች በአንድ ወቅት የጥንቷ ሮም ከሌሎች አገሮች ያስመጣቻቸው ዝሆኖች አሊያም ደግሞ የካርቴጁ ጄነራል ሃኒባል ወደ ጣሊያን ያመጣቸው ዝሆኖች ቅሪተ አካላት እንደሆኑ ይሰማቸዋል። ይሁን እንጂ በ19ኛው መቶ ዘመን የኖሩትና በቪቴርቦ፣ ጣሊያን የተፈጥሮ ሳይንስ ፕሮፌሰር የነበሩት ቄስ ጆቫኒ ባቲስታ ፕያንቻኒ በዚህ ሐሳብ አይስማሙም። እኚህ ሰው፣ አጥንቶቹ በአብዛኛው የተገኙት በደለል አካባቢ በመሆኑ በሌላ ቦታ የሞቱ እንስሳትን ጎርፍ ጠራርጎ ወደዚህ አምጥቷቸው መሆን አለበት የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል።

በጣሊያን የተገኙት በርካታ የዝሆን ቅሪተ አካላት ዛሬ ከምናውቃቸው ዝሆኖች የተለዩ ናቸው። እነዚህ ቅሪተ አካላት፣ ኤለፋስ ኣንቲከስ ወይም የጥንት ዝሆን ከሚባለው ከምድር ገጽ የጠፋ የዝሆን ዝርያ የሚመደቡ ናቸው። (ገጽ 15ን ተመልከት።) ይህ እንስሳ ቀጥ ያለ ጥርስ ያለው ሲሆን ቁመቱ ከትከሻው አካባቢ ሲለካ እስከ 5 ሜትር ሊደርስ ይችላል፤ ይህም አሁን ካሉት ዝሆኖች በ2 ሜትር ገደማ ይረዝማል ማለት ነው።

የእነዚህ ግዙፍ እንስሳት ብዛት ምን ያህል ነበር? ማሞዝ በመባል እንደሚታወቁት ከምድር ገጽ የጠፉ ትልልቅ የዝሆን ዝርያዎች ሁሉ እነዚህ እንስሳትም በአንድ ወቅት በመላው አውሮፓና በእንግሊዝ በብዛት ይኖሩ እንደነበር ከተገኙት ቅሪተ አካላት መመልከት ይቻላል። ከዚህም በላይ የዝሆኖቹ ቅሪተ አካላት ከሌሎች በርካታ የአራዊት ዝርያዎች ቅሪተ አካላት ጋር የተገኙበት ጊዜም ነበር፤ ከእነዚህ አራዊት አንዳንዶቹ እርስ በርስ ጠላት ናቸው።

ከጅብ አንስቶ እስከ ግዙፉ ጉማሬ

በመካከለኛው ጣሊያን በላዚዮ (ሮምንም ያካትታል) የተገኙት ቅሪተ አካላት አካባቢው በአንድ ወቅት ከአፍሪካ ጋር ተመሳሳይ የአየር ንብረት እንደነበረው ይጠቁማሉ፤ እንደ ጉማሬ፣ ሚዳቋ ሌላው ቀርቶ እንደ አንበሳ ያሉ ትልልቅ የድመት ዝርያዎች እንኳ በዚህ አካባቢ በብዛት ይኖሩ ነበር። እንዲያውም የሞንቴ ሳክሮ ሊዮፓርድ ተብሎ የተጠራ አንድ የድመት ዝርያ ቅሪተ አካል ሮም ውስጥ ተገኝቷል። ከከተማዋ ወጣ ብላ በምትገኝ ፖሌድራራ በተባለች መንደር የተለያየ ዝርያ ያላቸው እንስሳት ቅሪተ አካላት በቁፋሮ ሊወጡ ችለዋል፤ በዚህ አካባቢ በአጠቃላይ ከ9,000 በላይ የሚሆኑ ቅሪተ አካላት የተገኙ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ጥንታዊ ዝሆኖች፣ ጎሽ፣ አጋዘን፣ ባርበሪ ዝንጀሮዎች፣ አውራሪሶች እና አውራክስ የሚባለው ከአራት መቶ ዓመት በፊት ከምድር ላይ የጠፋ ግዙፍ የበሬ ዝርያ ይገኙበታል። በዚህ አካባቢ ቤተ መዘክር የተከፈተ ሲሆን ጎብኚዎች ቅሪተ አካላቱን በተገኙበት ቦታ ማየት እንዲችሉ በቦታው ላይ ከመሬት ከፍ ያለ መረማመጃ ተሠርቷል።—ገጽ 16ን ተመልከት።

ከዚህም ሌላ በፓሌርሞ፣ ሲሲሊ አቅራቢያ ባለ ዋሻ ውስጥ ብዙ ቶን የሚመዝን የቅሪተ አካላት ክምችት ተገኝቷል፤ ከእነዚህም መካከል የአጋዘን፣ የበሬና የዝሆኖች እንዲሁም ገና ያልተወለዱትን ጨምሮ በተለያየ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ጉማሬዎች ቅሪተ አካል ይገኝበታል። ከዚህ ግኝት በኋላ በነበሩት ስድስት ወራት ውስጥ 20 ቶን የሚመዝኑ ቅሪተ አካላት ለገበያ ቀርበው ነበር!

በቅሪተ አካል ጥናት ላይ የተሠማሩት ማንሰን ቫለንታይን፣ ጅብንና በሰሜን ዋልታ የሚገኘውን ድብ ጨምሮ ከላይ የተገለጹትን የአብዛኞቹን እንስሳት የተሰባበሩ አጥንቶች ክምችት በደቡብ እንግሊዝም አግኝተዋል። እንደነዚህ ያሉ የቅሪተ አካላት ክምችቶች በተለያዩ ቦታዎች የተገኙበት ምክንያት ምንድን ነው?

አንዳንድ የሳይንስ ምሑራን እንስሳቱ የሞቱት በተፈጥሮ አደጋ እንደሆነ ያምናሉ። እነዚህ ሁሉ እንስሳት በአንድ ላይ እንዲሞቱ ያደረገው አደጋ ምንም ይሁን ምን ሁኔታው ያስከተለውን ውጤት በመላው አውሮፓ፣ በሳይቤሪያ እንዲሁም በአላስካ በሚገኙ አካባቢዎች መመልከት ይቻላል።

እነዚህ ቅሪተ አካላት መገኘታቸው ዛሬ ከምናውቀው በጣም የተለየ ስለነበረው ዓለም ያለንን ግንዛቤ ያሰፋልናል። በእርግጥም ጣሊያን ውስጥ እንኳ ከበርካታ ዘመናት በፊት ያለውን ጊዜ መለስ ብለህ ብታስብ በአፍሪካ ዱር ውስጥ ያለህ ሊመስልህ ይችላል።

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ቅሪተ አካል ምንድን ነው?

ቅሪተ አካል መጀመሪያ ላይ ሲታይ ተራ አጥንት ሊመስል ይችላል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ቅሪተ አካል የሚፈጠረው የሞቱ እንስሳት አካል መፈራረስ ከመጀመሩ በፊት በሚከሰት ኬሚካላዊ ለውጥ አማካኝነት ነው።

የሞቱ እንስሳት አካል በአብዛኛው ወደ ቅሪተ አካልነት ከሚቀየርባቸው መንገዶች አንዱ ሚነራላይዜሽን በመባል ይታወቃል። ይህ ሂደት የሚከናወነው ውኃ ውስጥ ያሉ ዝቃጭ አለቶችና የተለያዩ ንጥረ ነገሮች፣ በእንስሳው በድን ውስጥ ያሉትን ንጥረ ነገሮች ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ሲተኳቸው ነው። በመሆኑም ቅሪተ አካል እንዲፈጠር በአንድ አካባቢ ለየት ያሉ ሁኔታዎች መኖር አለባቸው ማለት ነው። በአንድ አካባቢ ከፍተኛ መጠን ያለው ዝቃጭ አለት መኖሩ፣ በድኑ ከመፈራረሱ በፊት መቀበሩ እንዲሁም የአካባቢው ሁኔታ በድኑ ሳይፈራርስ እንዲቆይ የሚያደርግ መሆኑ ቅሪተ አካል እንዲፈጠር ከሚያስፈልጉት ሁኔታዎች አንዳንዶቹ ናቸው። ይሁንና አብዛኛውን ጊዜ አንድን በድን ሌሎች እንስሳት ባይበሉት እንኳ ባክቴሪያዎች ይበሉታል፤ እንዲሁም በንፋስና በውኃ ይወሰዳል። በዚህም ምክንያት ቅሪተ አካል የሚፈጠረው ከስንት አንዴ ነው።

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

በሰሜናዊው ንፍቀ ክበብ የተገኙ ትላልቅ የዝሆን ዝርያዎች

ከቅሪተ አካላት ግኝቶች መመልከት እንደሚቻለው ማሞዝ በመባል የሚታወቁት ግዙፍና ረጅም ፀጉር ያላቸው የዝሆን ዝርያዎች እስያን፣ አውሮፓንና ሰሜን አሜሪካን ጨምሮ በበርካታ ቦታዎች ይኖሩ ነበር። በአውሮፓ በስተ ደቡብ ካሉት አገሮች መካከል እነዚህ እንስሳት የነበሩት እስከ ጣሊያን ድረስ ይመስላል።

በዛሬው ጊዜ በእስያ የሚገኙትን ዝሆኖች የሚያክሉት ማሞዝ የሚባሉት ዝርያዎች፣ ፀጉራቸው እስከ 50 ሴንቲ ሜትር የሚደርስ ሲሆን ወንዶቹ 5 ሜትር ገደማ ርዝመት ያለው ቆልመም ያለ ጥርስ ነበራቸው። በሳይቤሪያ ከፍተኛ ብዛት ያለው የዚህ ዝሆን ጥርስ ተገኝቷል፤ የተገኘው የዝሆን ጥርስ በጣም ብዙ ከመሆኑ የተነሳ ከመካከለኛው ዘመን ጀምሮ ለቻይናና ለአውሮፓ ሲሸጥ ቆይቶ ነበር።

[ምንጭ]

Photo courtesy of the Royal BC Museum

[በገጽ 16 እና 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በፖሌድራራ መንደር የተገኘው የቅሪተ አካላት ክምችት

[ምንጭ]

Soprintendenza Archeologica di Roma

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ከላይ፦ Museo di Paleontologia dell’Università degli Studi “La Sapienza” di Roma; ከታች፦ © Comune di Roma - Sovraintendenza Beni Culturali (SBCAS; fald. 90, fasc. 4, n. inv. 19249)