በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከእልቂት አውድማ አምልጬ ሕይወትን አገኘሁ

ከእልቂት አውድማ አምልጬ ሕይወትን አገኘሁ

ከእልቂት አውድማ አምልጬ ሕይወትን አገኘሁ

ሳም ታም እንደተናገረው

እኔና ቤተሰቤ የትውልድ አገራችንን ጥለው ከሚሰደዱ 2,000 የሚያህሉ ሌሎች ካምቦዲያውያን ጋር ሆነን ታይላንድ ድንበር አካባቢ በሚገኝ አንድ ወንዝ አጠገብ ደረስን። ከዚያም ሰዎችን ወደ ሰላማዊ ቦታ በሚያሻግሩ ትንንሽ ጀልባዎች ላይ እንደምንም ብለን ተሳፈርን፤ የተሳፈርንባት ጀልባ በጣም ብዙ ሰዎችን አጭቃ ነበር። ልክ የመጨረሻዋ ጀልባ እንደተንቀሳቀሰች የክሜር ሩዥ ወታደሮች ደርሰው መተኮስ ጀመሩ።

ሁን እንጂ ሁላችንም ወንዙን አቋርጠን በሰላም ታይላንድ ደረስን፤ በዚህ ጊዜ የተሰማንን እፎይታ በቃላት መግለጽ ያስቸግረናል። አባቴና አጎቴ አብረውን ስላልነበሩ ከእኛ በስተቀር ሁሉም ሰው ተደስቶ ነበር፤ አባቴና አጎቴ ከእኛ ጋር መጓዝ ያልቻሉት ከጥቂት ወራት በፊት ወታደሮች መጥተው ወስደዋቸው ስለነበረ ነው። እናቴም እነሱን አስታውሳ ቁጭ ብላ ማልቀስ ጀመረች። ታሪኬን ከመቀጠሌ በፊት እስቲ ስለ አስተዳደጌ ትንሽ ላጫውታችሁ።

ቡድሂስት ሆኜ ያሳለፍኩት የልጅነት ሕይወት

የተወለድኩት በ1960 በካምቦዲያ ሲሆን አንድ ወንድምና አንዲት እህት አሉኝ። የዘጠኝ ዓመት ልጅ ሳለሁ እኔና ወላጆቼ በቡድሂስት ቤተ መቅደስ ውስጥ ገብቼ እንዳገለግል ተስማማን፤ በዚያን ጊዜ ወንዶች ልጆች በቤተ መቅደስ ውስጥ ማገልገላቸው የተለመደ ነገር ነበር። አንድ መነኩሴ የዕለቱን እንቅስቃሴ የሚጀምረው ማለዳ 12 ሰዓት ገደማ ከቤተ መቅደስ ወጥቶ ከቤት ወደ ቤት እየዞረ ምግብ በመለመን ነው። ይሁንና አንዳንድ ቤተሰቦች በጣም ድሃ መሆናቸው በግልጽ ያስታውቅ ስለነበር እነሱን ምግብ መለመን ይከብደኝ ነበር። ከዚያ በኋላ እኛ ወጣቶቹ መነኮሳት ለምነን ያመጣነውን ምግብ እናዘገጃጅና ትልልቆቹን መነኮሳት እናስተናግዳለን። እኛ የምንመገበው እነሱ ከበሉ በኋላ ነበር።

ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ትልልቆቹ መነኮሳት ተሰብስበው ጥቂቶች ካልሆኑ በስተቀር ብዙ ሰዎች በማይረዱት ቋንቋ ይጸልያሉ። ከሁለት ዓመት በኋላ ‘ትንሽ መነኩሴ’ የሚል ማዕረግ የተሰጠኝ ሲሆን ይህም በዕድሜ ትላልቅ የሆኑት መነኮሳት ያላቸውን አንዳንድ መብቶች አስገኝቶልኛል። በተጨማሪም ከእነሱ ጋር እንድጸልይ ተፈቀደልኝ። በዚያ ወቅት በዓለም ላይ ከቡድሂዝም ሌላ ሃይማኖት ያለ አይመስለኝም ነበር።

ወደ ታይላንድ ተሰደድኩ

በቤተ መቅደስ ሕይወት ስላልተደሰትኩ የ14 ዓመት ልጅ ሳለሁ ወደ ቤት ተመለስኩ። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ፖል ፖት የተባለ አንድ የፖለቲካ መሪ ሥልጣን ላይ ወጣ። ከ1975 እስከ 1979 በሥልጣን ላይ የቆየው ፖል ፖት የሚመራው የክሜር ሩዥ አገዛዝ ካምቦዲያን የኮምኒስት አገር ለማድረግ ከነበረው ፍላጎት የተነሳ የከተማ ነዋሪዎችን በሙሉ እያስገደደ ወደ ገጠር እንዲገቡ የሚያደርግ ፖሊሲ ይከተል ነበር። በዚህም የተነሳ ቤተሰቤ ከመኖሪያው ተፈናቀለ። ከጊዜ በኋላ የፖል ፖት ወታደሮች መጥተው አባቴንና አጎቴን ወሰዷቸው። ከዚያ በኋላ ዓይናቸውን አይተን አናውቅም። እንዲያውም በክሜር ሩዥ አገዛዝ ወቅት ወደ 1.7 ሚሊዮን የሚጠጉ ካምቦዲያውያን የእልቂት አውድማ ተብለው በሚጠሩ ቦታዎች ላይ ተጨፍጭፈዋል፤ አንዳንዶች ደግሞ በከባድ ሥራ፣ በበሽታ አሊያም በረሃብ ምክንያት አልቀዋል።

በመግቢያዬ ላይ እንደጠቀስኩት 2,000 የምንሆን ሰዎች ወደ ታይላንድ ድንበር ለመድረስ ተራራ በሚበዛባቸው መንገዶች ለሦስት ቀናት አደገኛ ጉዞ እንድናደርግ ያስገደደን ይህ ዓይነቱ ሁኔታ ነበር። በመንገድ ላይ የተወለደውን ልጅ ጨምሮ ሁላችንም በሰላም ወዳሰብንበት ደረስን። ብዙዎቻችን የካምቦዲያ ገንዘብ ይዘን ነበር፤ ሆኖም በወቅቱ የካምቦዲያ ገንዘብ ታይላንድ ውስጥ ምንም ዋጋ ስላልነበረው ገንዘባችንን ለመጣል ተገደናል።

ታይላንድ ውስጥ ያሳለፍኩት ሕይወት

ቤተሰቤ ታይላንድ ውስጥ የሚኖሩ ዘመዶቻችን ጋር ያረፈ ሲሆን እኔም በዓሣ አጥማጅነት ተቀጥሬ መሥራት ጀመርኩ። ብዙውን ጊዜ ዓሣ በብዛት ወደሚገኝበት የካምቦዲያ ክልል በጀልባ እንገባ ነበር፤ ይሁንና የክሜር ሩዥ ወታደሮች በጀልባ እየተዘዋወሩ ቅኝት ስለሚያደርጉ ሁኔታው በጣም አደገኛ ነበር። ብንያዝ ጀልባችንንም ሆነ ሕይወታችንን እናጣ ነበር። እንዲያውም ሁለት ጊዜ ለጥቂት አምልጠናል። ተይዞ አንገቱ የተቀላውን አንድ ጎረቤቴን ጨምሮ አንዳንዶች ግን ከመያዝ አላመለጡም። የእሱ ሞት በእጅጉ ቢያሳዝነኝም በካምቦዲያ ክልል ውስጥ ገብቼ ዓሣ ማጥመዴን አላቆምኩም፤ እንደዚያ ባይሆን ኖሮ እኔም ሆንኩ ቤተሰቤ በረሃብ እናልቅ ነበር።

የእኔም ሆነ የቤተሰቤ ሁኔታ ያሳስበኝ ስለነበር ታይላንድ ወደሚገኘው የስደተኞች ካምፕ ለመግባትና ወደ ሌላ አገር ለመሄድ የሚያስችለኝን ማመልከቻ ለማስገባት ወሰንኩ፤ ይህ ከተሳካልኝ ከዚያ ሆኜ ለቤተሰቦቼ ገንዘብ ለመላክ አስቤ ነበር። ሁኔታውን ለዘመዶቼ ሳማክራቸው አጥብቀው ተቃወሙኝ። ሆኖም እንደዚያ ለማድረግ ቆርጬ ነበር።

በስደተኞች ካምፕ ውስጥ ያገኘኋቸው አልፎ አልፎ የሚመጡ እንግሊዝኛ ተናጋሪ ሰዎች ክርስቲያን እንደሆኑ ሲናገሩ ሰማሁ። በዚህ ጊዜ ከቡድሂዝም ሌላ ሃይማኖት የለም የሚለው እምነቴ ተናጋ። እኔና በካምፕ ውስጥ የተዋወቅሁት ቴንግ ሃን የተባለ ጓደኛዬ “ከክርስቲያኖች” ጋር መቀራረብ ጀመርን፤ እነዚህ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ያሳዩን ከመሆኑም በላይ ምግብ ይሰጡን ነበር። በዚህ ካምፕ ውስጥ ለአንድ ዓመት ከኖርኩ በኋላ ወደ ኒው ዚላንድ ለመሄድ ማመልከቻ አስገባሁ።

በኒው ዚላንድ አዲስ ሕይወት ጀመርኩ

ግንቦት 1979 ማመልከቻዬ ተቀባይነት ያገኘ ሲሆን ከጥቂት ጊዜ በኋላ ኦክላንድ ውስጥ ወደሚገኝ የስደተኞች ካምፕ ተዛወርኩ። እዚያም አንድ ደግ ሰው ወደ ዌልንግተን ከተማ እንድሄድና በዚያ በሚገኝ አንድ ፋብሪካ ውስጥ እንድሠራ ሁኔታዎችን አመቻቸልኝ። እዚያ ከደረስኩ በኋላ ጠንክሬ በመሥራት ቃል በገባሁት መሠረት ለቤተሰቦቼ ገንዘብ መላክ ጀመርኩ።

ስለ ክርስትና ሃይማኖት ለማወቅ ከነበረኝ ፍላጎት የተነሳ ሁለት የፕሮቴስታንት ቤተ ክርስቲያኖች በሚያደርጉት ስብሰባ ላይ መገኘት ጀመርኩ። በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ መጽሐፍ ቅዱስ የሚጠቀሰው ከስንት አንዴ ነበር። በደንብ መጸለይ እፈልግ ስለነበር አንድ ጓደኛዬ በተለምዶ የጌታ ጸሎት ወይም አባታችን ሆይ ተብሎ የሚጠራውን ጸሎት አስተማረኝ። (ማቴዎስ 6:9-13) ሆኖም ይህ ጸሎት ምን ትርጉም እንዳለው ያብራራልኝ ሰው አልነበረም። ቡድሂስት ሳለው አደርግ እንደነበረው የምናገረው ነገር ምን ትርጉም እንዳለው ባይገባኝም እንኳ ቃላቶቹን ደግሜ ደጋግሜ አነበንባቸው ነበር።

በትዳሬ ውስጥ ችግር አጋጠመኝ

በ1981 ትዳር መሠረትኩ። ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላ አንድ አገልጋይ አናታችን ላይ ውኃ በመርጨት እኔንና ባለቤቴን አጠመቀን። በዚያን ጊዜ ካምቦዲያ እያለሁ ኖረውኝ የማያውቁ ነገሮች ማለትም ከአንድም ሁለት ሥራ፣ ጥሩ ቤትና የተመቻቸ ኑሮ ነበረኝ። ቢሆንም ደስተኛ አልነበርኩም። በትዳራችን ውስጥም ችግሮች መከሰት ጀመሩ፤ ቤተ ክርስቲያን የምናዘወትር መሆናችን ለእነዚህ ችግሮቻችን መፍትሄ አላስገኘልንም። ሌላው ቀርቶ የባሕርይ ለውጥ እንዳደርግ እንኳ አልረዳኝም፤ ቁማር እጫወት፣ ሲጋራ አጨስ፣ ከመጠን በላይ እጠጣና ወደ ሌሎች ሴቶች እሄድ ነበር። በዚህ ምክንያት ሕሊናዬ ይረብሸኝ የነበረ ከመሆኑም ሌላ ጥሩ ሰዎች ሁሉ ሲሞቱ ይሄዱበታል ወደሚባለው ወደ ሰማይ ለመሄድ ብቃቱን የማሟላ መሆኔን እንኳ በጣም መጠራጠር ጀምሬ ነበር።

በ1987 እናቴና እህቴ ወደ ኒው ዚላንድ እንዲመጡ ሁኔታዎችን አመቻቸሁላቸው፤ ከመጡም በኋላ ለጥቂት ጊዜ አብረውን ኖሩ። ከዚያም እነሱ ከቤት ሲለቁ እኔም አብሬያቸው በመሄድ ኦክላንድ ውስጥ ሦስታችንም አብረን መኖር ጀመርን።

በመጨረሻም መጽሐፍ ቅዱስን ተማርኩ

አንድ ቀን ከአንድ ጓደኛዬ ቤት ስወጣ ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ ሰዎችን የሚያነጋግሩ ሁለት ሰዎችን አገኘሁ። አንደኛው ቢል የሚባል ሲሆን “ስትሞት የት እሄዳለው ብለህ ነው ተስፋ የምታደርገው?” በማለት ጠየቀኝ። እኔም “ወደ ሰማይ” ብዬ መለስኩለት። እሱም መጽሐፍ ቅዱስ አውጥቶ ወደ ሰማይ የሚሄዱት 144,000 ብቻ እንደሆኑና እነሱም ነገሥታት ሆነው ምድርን እንደሚገዙ አሳየኝ። በተጨማሪም ምድር ፈሪሃ አምላክ ባላቸው ሰዎች እንደምትሞላና ወደ ገነትነት እንደምትለወጥ አስረዳኝ። (ራእይ 5:9, 10፤ 14:1, 4፤ 21:3, 4) ይህ ትምህርት ከዚህ ቀደም ከማውቀው ነገር ጋር ስለተጋጨብኝ መጀመሪያ ላይ በጣም ተናድጄ ነበር። ቢሆንም ሰዎቹ የተረጋጉና የጠለቀ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ያላቸው መሆኑ አስደነቀኝ። እንዲያውም ከተለየኋቸው በኋላ ሃይማኖታቸው ምን እንደሆነ ባለመጠየቄ ቆጨኝ።

ከጥቂት ሳምንታት በኋላ አንድ ጓደኛዬን ለመጠየቅ ቤቱ ሄድኩ፤ የዚህ ጓደኛዬ ልጆች ዲክና ስቴፋኒ ከሚባሉ ባልና ሚስት ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ያጠናሉ። የሚያጠኑት በምድር ላይ ለዘላለም በደስታ ኑር! የሚል ርዕስ ባለው ብሮሹር እየታገዙ ነበር። ብሮሹሩን ሳነበው ምክንያታዊ ማብራሪያ የሚሰጥ ሆኖ አገኘሁት። እንዲሁም ባልና ሚስቱ የይሖዋ ምሥክሮች መሆናቸውን ተረዳሁ። ከዚህ በፊት ያነጋገሩኝ ሁለት ሰዎች የገለጹልኝ ነገር ብሮሹሩ ከያዘው ሐሳብ ጋር ስለተመሳሰለብኝ እነዚያ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች መሆን አለባቸው ብዬ አሰብኩ።

ተጨማሪ ነገሮችን ለማወቅ ከነበረኝ ጉጉት የተነሳ ዲክና ስቴፋኒ ቤቴ እንዲመጡ የጋበዝኳቸው ከመሆኑም በላይ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችን ጠየኳቸው። በኋላ ላይ ስቴፋኒ የአምላክን ስም አውቅ እንደሆነ ጠየቀችኝና መዝሙር 83:18ን [NW] አውጥታ “ይህም ሰዎች ሁሉ ስምህ ይሖዋ የሆነው አንተ፣ በምድር ሁሉ ላይ አንተ ብቻ ልዑል እንደሆንክ ያውቁ ዘንድ ነው” የሚለውን ሐሳብ አሳየችኝ። ይህ ጥቅስ ልቤን ስለነካው መጽሐፍ ቅዱስን በቋሚነት ማጥናት ጀመርኩ። አብራኝ ትኖር የነበረው ላ የምትባል የላኦስ ተወላጅም በጥናቱ ወቅት ከእኔ ጋር መገኘት ጀመረች። በዚህ ወቅት ወንድሜና ባለቤቱ ወደ ኒው ዚላንድ እንዲመጡ ሁኔታዎችን አመቻቸሁ። እነሱም ከመጡ በኋላ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመሩ።

ብዙም ሳይቆይ እኔና ላ ለሥራ ወደ አውስትራሊያ በመሄዳችን ጥናታችን ተቋረጠ። ዋነኛው ትኩረታችን ያረፈው ገንዘብ በማግኘት ላይ ቢሆንም እናደርገው የነበረው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በመቋረጡ ቅር ይለን ጀመር። በመሆኑም አንድ ቀን ይሖዋ ከሕዝቦቹ ጋር እንዲያገናኘን ከልብ የመነጨ ጸሎት አቀረብን።

ለጸሎታችን መልስ አገኘን

ከጥቂት ቀናት በኋላ ከገበያ ወደ ቤቴ ስመለስ በር ላይ ሁለት የይሖዋ ምሥክሮችን አገኘሁ። በልቤ ይሖዋን ያመሰገንኩ ሲሆን እኔና ላ እንደገና ጥናት ቀጠልን። በተጨማሪም በአካባቢው በሚገኝ የመንግሥት አዳራሽ ውስጥ በሚደረጉ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመርን። ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ አምላክን ለማስደሰት በሕይወቴ ውስጥ ብዙ ለውጦችን ማድረግ እንዳለብኝ ተገነዘብኩ። የነበሩኝን የተለያዩ መጥፎ ልማዶች ያስወገድኩ ሲሆን ረጅም የነበረውን ፀጉሬን ተቆረጥኩኝ። ከዚህ ቀደም የሚያውቁኝ ሰዎች ያሾፉብኝ የነበረ ቢሆንም ንዴቴን መቆጣጠር ተምሬያለሁ። በተጨማሪም ከላ ጋር በሕጋዊ መንገድ ባለመጋባታችንና ከቀድሞዋ ባለቤቴ ጋር በሕግ ባለመፋታታችን የጋብቻዬን ሁኔታ ማስተካከል ነበረብኝ። በመሆኑም በ1990 እኔና ላ ወደ ኒው ዚላንድ ተመለስን።

እዚያ እንደደረስን ለዲክና ለስቴፋኒ ስልክ ደወልንላቸው። ስቴፋኒ በሁኔታው በመገረም “ሳም፣ እንደገና እንገናኛለን ብዬ አልጠበቅሁም ነበር!” አለችኝ። ከእነሱ ጋር እንደገና ጥናታችንን የቀጠልን ሲሆን የፍቺው ጉዳይ እንደተጠናቀቀ እኔና ላ በአምላክ ፊት ንጹሕ ሕሊና ይዘን ተጋባን። ከተጋባን በኋላ በኒው ዚላንድ መኖር የቀጠልን ከመሆኑም በላይ ሕይወታችንን ለአምላክ መወሰናችንን ለማሳየት ሁለታችንም ተጠመቅን። የተማርኩትን ነገር ለሌሎች ለማካፈል ከፍተኛ ጉጉት ስለነበረኝ በኦክላንድና በአቅራቢያዋ የሚኖሩ በርካታ ካምቦዲያውያንና የታይላንድ ዜጎችን መጽሐፍ ቅዱስ አስጠና ነበር።

ወደ አውስትራሊያ ተመለስን

ግንቦት 1996 እኔና ላ ወደ አውስትራሊያ ተመልሰን ሰሜን ክዊንስላንድ ውስጥ በምትገኘው ኬርን በምትባል ከተማ መኖር ጀመርን። እዚያም በከተማው ውስጥ ለሚኖሩ የካምቦዲያ፣ የላኦስና የታይላንድ ሕዝቦች የመንግሥቱን ምሥራች የመስበኩን ሥራ የማደራጀት መብት አገኘሁ።

ይሖዋ ውዷን ባለቤቴን እንዲሁም ዳንኤል፣ ማይክልና ቤንጃሚን የሚባሉ ልጆቻችንን ጨምሮ ሌሎች በረከቶችን ስለሰጠኝ እሱን አመስግኜ አልጠግብም። በተጨማሪም እናቴ፣ እህቴ፣ ወንድሜ፣ አማቴ እንዲሁም ታይላንድ በሚገኘው ካምፕ ውስጥ የተዋወቅሁት ቴንግ ሃን የተባለው ጓደኛዬ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በመቀበላቸው በጣም አመስጋኝ ነኝ። እኔም ሆንኩ ቤተሰቤ አባቴንና አጎቴን በሞት በማጣታችን አሁንም ድረስ የምናዝን ቢሆንም ሐዘናችን ከልክ ያለፈ አይደለም። አምላክ በትንሣኤ ወቅት እንዲህ ያሉ የግፍ ድርጊቶች ከሰዎች አእምሮ እንዲፋቁ በማድረግ ከዚያ በኋላ ፈጽሞ ‘እንዳይታሰቡና እንዳይታወሱ’ እንደሚያደርጋቸው እናውቃለን።—ኢሳይያስ 65:17፤ የሐዋርያት ሥራ 24:15

ከጥቂት ዓመታት በፊት የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጉት አንድ ትልቅ ስብሰባ ላይ አንድ የማውቀው ሰው ተመለከትኩ። ይህ ሰው ከረጅም ጊዜ በፊት አነጋግሮኝ የነበረው ቢል ነው። ጠጋ ብዬ “ታስታውሰኛለህ?” ብዬ ጠየቅሁት።

“አዎ፣ ከረጅም ጊዜ በፊት በኒው ዚላንድ ተገናኝተን 144,000 ሰዎች ብቻ ወደ ሰማይ እንደሚሄዱ ነግሬህ ነበር አይደል?” በማለት መለሰልኝ። ብዙ ዓመታት ቢያልፉም ቢል ማንነቴ አልጠፋውም። በመንፈሳዊ ወንድማማቾች እንደመሆናችን ከቢል ጋር ተቃቀፍንና ስለዚያ ጊዜ አንስተን ተጨዋወትን።

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ከበስተጀርባ ያለው ሥዕል፦ AFP/Getty Images