በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ታይሮይድ ዕጢህ እንዴት ነው?

ታይሮይድ ዕጢህ እንዴት ነው?

ታይሮይድ ዕጢህ እንዴት ነው?

ብራዚል የሚገኘው የንቁ! ጸሐፊ እንዳዘጋጀው

ሣራ ካረገዘች ሦስት ወር እንኳ ሳይሞላት ጽንሱ በመጨንገፉ በጣም አዝና ነበር። ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላም በድጋሚ አስወረዳት። አያሌ የሕክምና ምርመራዎች ቢደረጉላትም የውርጃው መንስኤ ሊታወቅ አልቻለም። ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ የሣራ ክብደት እየጨመረ መጣ፤ ሣራ አመጋገቧን የምትቆጣጠር ከመሆኑም ሌላ አዘውትራ የሰውነት እንቅስቃሴ ብታደርግም ክብደቷ መጨመሩን አላቆመም። በተጨማሪም እግሯን ይቆረጥማት እንዲሁም ብርድ መቋቋም ያቅታት ጀመር። በመጨረሻም በታይሮይድ ዕጢዋ ላይ የተደረገው የደምና የአልትራ ሳውንድ ምርመራ ሐሺሞቶስ ታይሮይዳይተስ የሚባል በሽታ እንዳለባት አመለከተ፤ በተደጋጋሚ የጽንስ መጨንገፍ ያጋጠማት በዚህ ሕመም የተነሳ ሊሆን ይችላል። *

እንደ አብዛኞቹ ሰዎች ሁሉ ሣራም ስለ ታይሮይድ ዕጢዋ ተጨንቃ አታውቅም ነበር። ይሁን እንጂ እያደር ጤና እያጣች መሄዷ ይህ ዕጢ ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ በግልጽ የሚያሳይ ነው።

ታይሮይድ ዕጢ

ታይሮይድ ዕጢ፣ አንገታችን ላይ ከማንቁርት በታች የሚገኝ የቢራቢሮ ቅርጽ ያለው ትንሽ ዕጢ ነው። ታይሮይድ ዕጢ በአየር ቧንቧችን ዙሪያ የሚገኙ ሁለት ክፍሎች ያሉት ሲሆን ጠቅላላ ክብደቱ ሩብ ግራም ገደማ ይሆናል። ታይሮይድ ዕጢ በሰውነት ውስጥ ከሚገኙት ኢንዶክሪን ተብለው የሚጠሩ የአካል ብልቶችና ሕብረ ሕዋሳት አንዱ ነው፤ እነዚህ የአካል ብልቶችና ሕብረ ሕዋሳት ሆርሞኖችን ማለትም ኬሚካላዊ መልእክተኞችን ይሠራሉ፣ ያከማቻሉ እንዲሁም ሆርሞኖቹ በቀጥታ ወደ ደም ውስጥ እንዲገቡ ያደርጋሉ።

ታይሮይድ ዕጢ የተገነባው የታይሮይድ ሆርሞኖችን በያዘ ዝልግልግ ፈሳሽ በተሞሉ በርካታ ጥቃቅን ቀረጢቶች ነው። በሆርሞኖቹ ውስጥ ከፍተኛ የአዮዲን ክምችት ይገኛል። እንዲያውም በሰውነታችን ውስጥ ካለው አዮዲን ውስጥ 80 በመቶ የሚሆነው የሚገኘው በታይሮይድ ዕጢ ውስጥ ነው። አዮዲን ያለበት ምግብ እጥረት የታይሮይድ ዕጢ ማበጥ ወይም እንቅርት ሊያስከትል ይችላል። የአዮዲን ማነስ ትንንሽ ልጆች ሰውነታቸው በቂ ሆርሞን እንዳያመነጭ እንቅፋት ሊሆን ስለሚችል አካላዊ፣ አእምሯዊና ጾታዊ ዕድገታቸው እንዲጓተት ያደርጋል፤ ይህ ዓይነቱ የጤና እክል ክሪትኒዝም ይባላል።

የታይሮይድ ሆርሞኖች የሚያከናውኑት ሥራ

የታይሮይድ ሆርሞኖች T3፣ RT3 እና T4 የሚል ስያሜ ተሰጥቷቸዋል። * T3 እና RT3 የሚገኙት ከT4 ሲሆን ከT4 ወደ T3 እና RT3 የሚደረገው ለውጥ በዋነኝነት የሚከናወነው ከታይሮይድ ዕጢ ውጪ በሚገኙ ሕብረ ሕዋሳት ውስጥ ነው። በመሆኑም ሰውነት ተጨማሪ የታይሮይድ ሆርሞኖች ሲያስፈልጉት ታይሮይድ ዕጢ T4ን በማመንጨት ደም ውስጥ እንዲገባ ያደርገዋል፤ ደም ውስጥ የገባው T4 እና ከT4 የሚገኙት ሌሎች የታይሮይድ ሆርሞኖች ደግሞ በሁሉም የሰውነት ሴሎች ላይ ተጽዕኖ ይኖራቸዋል።

የአንድ መኪና ነዳጅ መስጫ የመኪናውን ፍጥነት እንደሚቆጣጠር ሁሉ የታይሮይድ ሆርሞኖችም በሰውነት ውስጥ ምግብ ተፈጭቶ ወደ ኃይል እንዲለወጥና አዳዲስ ሕብረ ሕዋሳት እንዲሠሩ የሚያደርገውን ኬሚካላዊ ሂደት (ሜታቦሊዝም) ፍጥነት ይቆጣጠራሉ። በመሆኑም የታይሮይድ ሆርሞኖች፣ ሕብረ ሕዋሳት ትክክለኛ ዕድገት እንዲኖራቸውና በተገቢው መንገድ እንዲታደሱ የሚያደርጉ ከመሆኑም በላይ የልብ ምትን ፍጥነት ይቆጣጠራሉ፤ እንዲሁም ለጡንቻዎች የሚያስፈልገው ኃይል እንዲፈጠርና የሰውነት ሙቀት ተጠብቆ እንዲቆይ ያደርጋሉ።

የታይሮይድ ሆርሞኖች ሌሎች ጠቃሚ ተግባሮችንም ያከናውናሉ። ለምሳሌ ያህል፣ በሰውነታችን ውስጥ ስብና ቅባት እንዲሁም ጥሩ ያልሆነው ኮሌስትሮል ከተገቢው በላይ በሚኖሩበት ጊዜ ጉበታችን እነዚህን ነገሮች ከደም ውስጥ እንዲያስወጣ የሚረዱት የታይሮይድ ሆርሞኖች ናቸው። ጥሩ ያልሆነው ኮሌስትሮል ወደ ሐሞት ከረጢት ይዛወርና ከዓይነ ምድር ጋር ይወጣል። በሌላ በኩል ደግሞ የታይሮይድ ሆርሞኖች ማነስ ጥሩ ያልሆነው ኮሌስትሮል እንዲበዛና ጠቃሚው ኮሌስትሮል እንዲቀንስ ሊያደርግ ይችላል።

የታይሮይድ ሆርሞኖች በጨጓራና በአንጀት ውስጥ የሚገኙትን ለምግብ መፈጨት የሚያስፈልጉ ፈሳሾች የማመንጨት ሂደት እንዲፋጠን ያደርጋሉ፤ ከዚህም በላይ በምግብ መውረጃ ቧንቧ ላይ ያሉት ጡንቻዎች ወጥነት ባለው መንገድ ጭብጥ ዘርጋ እያሉ ምግብ ወደ ጨጓራ እንዲገባ የሚያደርጉበት ሂደት (ፐሪስቶልስስ) እንዲፋጠን ይረዳሉ። በመሆኑም አንድ ሰው በሰውነቱ ውስጥ ከሚገባው በላይ የታይሮይድ ሆርሞን መኖሩ እንዲያስቀምጠው የሚያደርግ ሲሆን በሰውነቱ ውስጥ ያለው የታይሮይድ ሆርሞን ማነሱ ደግሞ ድርቀት እንዲያስቸግረው ሊያደርግ ይችላል።

ታይሮይድ ዕጢን የሚቆጣጠረው ምንድን ነው?

ታይሮይድ ዕጢን የሚቆጣጠረው ሃይፖታላመስ ተብሎ የሚጠራው የአንጎል ክፍል ነው። ሃይፖታላመስ፣ በሰውነት ውስጥ የታይሮይድ ሆርሞን እንደሚያስፈልግ መልእክት ሲደርሰው ከላይኛው ላንቃ በላይ በአንጎል ታችኛ ክፍል ላይ ለሚገኘው ፒቲዩታሪ ዕጢ ምልክት ይሰጣል። ፒቲዩታሪ ዕጢ በምላሹ የታይሮይድ ሆርሞኖች እንዲመረቱ የሚቀሰቅስ ሆርሞን ወደ ደም ውስጥ ይለቃል፤ ይህ ሆርሞን ደግሞ የታይሮይድ ሆርሞኖችን እንዲያመርት ታይሮይድ ዕጢን ያነሳሳዋል።

ሐኪሞች የታይሮይድ ሆርሞኖች እንዲመረቱ የሚቀሰቅሰውን ሆርሞን መጠንና የታይሮይድ ሆርሞኖችን መጠን ከደም ውስጥ በመለካት ታይሮይድ ዕጢያችን በተገቢው መንገድ መሥራት አለመሥራቱንና ጤናማ መሆኑን ለይተው ማወቅ ይችላሉ። ታይሮይድ ዕጢያችን እክል ሊያጋጥመው ስለሚችል ይህ ዓይነቱ ምርመራ አስፈላጊ ነው።

ታይሮይድ ዕጢ እክል ሲያጋጥመው

ታይሮይድ ዕጢ በተገቢው መንገድ እንዳይሠራ ከሚያደርጉት ምክንያቶች መካከል የአዮዲን እጥረት፣ አካላዊ ወይም አእምሯዊ ውጥረት፣ በዘር የሚወረስ ጉድለት፣ በባክቴሪያዎች የሚመጡ ሕመሞችን ጨምሮ ሌሎች በሽታዎች (አብዛኛውን ጊዜ በሽታ ተከላካይ ሕዋሳት ሌሎች ሕዋሳትን እንዲያጠቁ የሚያደርጉ የጤና ቀውሶች) ወይም ለተለያዩ ሕመሞች ከሚታዘዙ መድኃኒቶች ጋር ተያይዞ የሚመጣ የጎንዮሽ ጉዳት ይገኙበታል። * የታይሮይድ ዕጢ ማበጥ ወይም እንቅርት የበሽታ ምልክት ሊሆን ይችላል። ታይሮይድ ዕጢው ሙሉ በሙሉ ወይም የተወሰነው ክፍል ብቻ ሊያብጥ ይችላል። በጥቅሉ ሲታይ እንቅርት ጉዳት የሚያስከትል ባይሆንም እንደ ካንሰር ያለ ከባድ የጤና ችግር መኖሩን የሚያመለክትም ሊሆን ስለሚችል ምንጊዜም ቢሆን የሕክምና ክትትል ማድረግ አስፈላጊ ነው። *

አብዛኛውን ጊዜ የታመሙ የታይሮይድ ዕጢዎች፣ ከመጠን በላይ አሊያም በጣም ትንሽ ሆርሞን ያመነጫሉ። የታይሮይድ ሆርሞኖች ከመጠን በላይ መመንጨት ሃይፐርታይሮይዲዝም ተብሎ የሚጠራ ሲሆን በጣም ትንሽ የታይሮይድ ሆርሞኖች መመንጨት ደግሞ ሃይፖታይሮይዲዝም ይባላል። የታይሮይድ በሽታ ቀስ በቀስና ሳይታወቅ እየተባባሰ ሊሄድ ስለሚችል አንድ ሰው በሽታው ኖሮበትም ለዓመታት ላያውቀው ይችላል። እንደ አብዛኞቹ ሕመሞች ሁሉ በሽታው መኖሩ ቀደም ብሎ ከታወቀ የተሻለ የመዳን አጋጣሚ ሊኖር ይችላል።

በጣም የተለመዱት የታይሮይድ ሕመም ዓይነቶች ሐሺሞቶስ ታይሮይዳይተስ እና ግሬቭስ የሚባሉት በሽታዎች ናቸው። እነዚህ ሕመሞች የሚከሰቱት በሰውነት ውስጥ የሚገኙት በሽታ ተከላካይ ሕዋሳት ሌሎች ሴሎችን እንደ ባዕድ በመቁጠር በሚያጠቋቸው ጊዜ ነው። ሴቶች ሐሺሞቶስ ታይሮይዳይተስ በተባለው በሽታ የመያዝ አጋጣሚያቸው ከወንዶች በስድስት እጥፍ የሚበልጥ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜም ይህ ሕመም ሃይፖታይሮይዲዝም ያስከትላል። ሴቶች ግሬቭስ በተባለው በሽታ የመያዝ አጋጣሚያቸው ከወንዶች በስምንት እጥፍ የሚበልጥ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ ይህ ሕመም ሃይፐርታይሮይዲዝም ያስከትላል።

‘ሰዎች የታይሮይድ በሽታ ይኑርባቸው አይኑርባቸው ለማረጋገጥ ምን ያህል አዘውትረው መመርመር አለባቸው?’ በሚለው ጉዳይ ላይ የሚሰነዘሩት አስተያየቶች የሚለያዩ ቢሆንም በጥቅሉ ሲታይ ለአራስ ሕፃናት ይህን ምርመራ ማድረጉ ጠቃሚ እንደሆነ ይታመናል። ( “ለአራስ ሕፃናት አስፈላጊ የሆነ ምርመራ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) የተደረገው የሕክምና ምርመራ ታይሮይድ ዕጢ የሚያመነጨው ሆርሞን ከተገቢው መጠን ያነሰ እንደሆነ ካመለከተ ዕጢውን የሚያጠቁ ፀረ እንግዳ አካላት በሰውነት ውስጥ መኖራቸውን ለማወቅ የሚረዳ ምርመራ ብዙውን ጊዜ ይታዘዛል። በሌላ በኩል ደግሞ ምርመራው ታይሮይድ ዕጢ የሚያመነጨው ሆርሞን ከተገቢው በላይ እንደሆነ ካመለከተ ታይሮይድ ዕጢው ራጅ እንዲነሳ ይደረጋል፤ ይህ ምርመራ የሚደረገው ሕመምተኛዋ ነፍሰ ጡር ወይም ጡት የምታጠባ ካልሆነች ብቻ ነው። ታይሮይድ ዕጢው እንዳበጠ ከታየ ሁኔታው ለሕይወት የሚያሰጋ መሆን አለመሆኑን ለማረጋገጥ ከዕብጠቱ ላይ ቆንጥሮ በመውሰድ ምርመራ ማድረግ ሊያስፈልግ ይችላል።

ሕክምና አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ

የልብ ምት ፍጥነት መጨመር፣ የጡንቻ መንቀጥቀጥና ጭንቀት የመሳሰሉትን የሃይፐርታይሮይዲዝም ምልክቶች መድኃኒት በመውሰድ ማስታገሥ ይቻላል። ታይሮይድ ዕጢው አነስተኛ መጠን ያላቸው ሆርሞኖችን እንዲያመነጭ ለማድረግ የታይሮይድ ሴሎችን በመግደል የሚከናወን ሕክምናም አለ። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ታይሮይድ ዕጢው በቀዶ ሕክምና መወገድ ሊኖርበት ይችላል።

ሃይፖታይሮይዲዝም ላለባቸው ወይም ታይሮይድ ዕጢያቸው እንዲወጣ ለተደረጉ በሽተኞች ሐኪሞች አብዛኛውን ጊዜ በየቀኑ የሚወሰዱ የT4 ሆርሞኖችን ያዙላቸዋል። የሚወሰደው ሆርሞን መጠን ትክክለኛ መሆኑን ለማረጋገጥ ሲባል ሐኪሞች ሕክምናው ለሚደረግላቸው ሕመምተኞች ክትትል ያደርጉላቸዋል። የታይሮይድ ካንሰርን ለማከም ከሚረዱ ሕክምናዎች መካከል መድኃኒቶች፣ ቀዶ ሕክምና፣ ኬሞቴራፒ የሚባል ሕክምና እንዲሁም ራዲዮአክቲቭ አዮዲን የሚባል የጨረር ሕክምና ይገኙበታል።

ሣራ T4 የሚባለውን ሆርሞን በመውሰድ ሆርሞን የሚተካ ሕክምና እየተከታተለች ሲሆን አንድ የሥነ ምግብ ባለሙያ ለጤናዋ የሚረዳትን የአመጋገብ መርሐ ግብር እንድትከተል ረድታታለች። በዚህም ምክንያት ጤንነቷ ሊሻሻል ችሏል። እንደ ሣራ ያሉ በታይሮይድ ሕመም የተጠቁ ሰዎች መገንዘብ እንደቻሉት ታይሮይድ ዕጢ አነስተኛ የሰውነታችን ክፍል ቢሆንም ጠቀሜታው ግን ትልቅ ነው። ስለዚህ በቂ መጠን ያለው አዮዲን ያለባቸውን ለሰውነት ጠቃሚ የሆኑ ምግቦች በመብላት፣ ሥር የሰደደ ውጥረትን ለማስወገድ ጥረት በማድረግ እንዲሁም በአጠቃላይ ጥሩ ጤንነት እንዲኖርህ የቻልከውን ሁሉ በማድረግ ታይሮይድ ዕጢህን ተንከባከበው።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.3 ከተገቢው መጠን ያነሰ ሆርሞን የሚያመነጭ ታይሮይድ ዕጢ እርግዝናን የሚያወሳስብ ቢሆንም የታይሮይድ ዕጢ ሕመም ያለባቸው አብዛኞቹ ሴቶች ጤነኛ ልጅ ይወልዳሉ። ይሁን እንጂ እናቲቱ የሆርሞን መተኪያ ሕክምና ማግኘቷ በጣም አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም ጽንሱ መጀመሪያ ላይ የታይሮይድ ሆርሞን ማግኘት የሚችለው ከእናቱ ብቻ ነው።

^ አን.9 T3 ተብሎ የተሰየመው ትራይአዮዶታይሮኒን የሚባለው ሆርሞን ሲሆን T4 የተባለው ደግሞ ታይሮክሲን የሚባለው ሆርሞን ነው። 3 እና 4 የሚሉት አኃዞች የሚያመለክቱት በሆርሞኑ ውስጥ የሚገኙትን የአዮዲን አቶሞች ብዛት ነው። በተጨማሪም ታይሮይድ ዕጢ፣ ካልሲቶኒን የሚባለውን በደም ውስጥ ያለውን የካልሲየም መጠን ለመቆጣጠር የሚረዳ ሆርሞን ያመነጫል።

^ አን.17 ንቁ! ማንኛውንም የሕክምና ዓይነት የሚደግፍ ሐሳብ አያቀርብም። የታይሮይድ ዕጢህ ችግር እንዳለበት ከጠረጠርክ ከዚህ ጋር የተያያዙ ሕመሞችን በመከላከልና በማከም ረገድ ተሞክሮ ያለው ሐኪም አማክር።

^ አን.17 በጭንቅላታቸውና በአንገታቸው ላይ የጨረር ሕክምና የተደረገላቸው ወይም ካንሰር ይዟቸው የነበሩ ግለሰቦች አሊያም የታይሮይድ ዕጢ ካንሰር የያዛቸው ዘመዶች ያሏቸው ሰዎች በካንሰር የመያዝ አጋጣሚያቸው ከፍ ያለ ነው።

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

የአንድ መኪና ነዳጅ መስጫ የመኪናውን ፍጥነት እንደሚቆጣጠር ሁሉ የታይሮይድ ሆርሞኖችም በሰውነት ውስጥ ምግብ ተፈጭቶ ወደ ኃይል እንዲለወጥና አዳዲስ ሕብረ ሕዋሳት እንዲሠሩ የሚያደርገውን ኬሚካላዊ ሂደት ፍጥነት ይቆጣጠራሉ

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

የታይሮይድ በሽታ ቀስ በቀስና ሳይታወቅ እየተባባሰ ሊሄድ ስለሚችል አንድ ሰው በሽታው ኖሮበትም ለዓመታት ላያውቀው ይችላል

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የተለመዱ ምልክቶች

ሃይፐርታይሮይዲዝም፦ ከልክ ያለፈ የመረበሽ ስሜት፣ ምክንያቱ ያልታወቀ የክብደት መቀነስ፣ የልብ ምት መፍጠን፣ ቶሎ ቶሎ ዓይነ ምድር መውጣት፣ የወር አበባ መዛባት፣ መነጫነጭ፣ ጭንቀት፣ የስሜት መለዋወጥ፣ የዓይን ኳስ ከቦታው ወጣ ብሎ መታየት፣ የጡንቻ መዛል፣ እንቅልፍ ማጣት እንዲሁም ስስና በቀላሉ የሚሰባበር ፀጉር። *

ሃይፖታይሮይዲዝም፦ የአካልና የአእምሮ መዛል፣ ምክንያቱ ያልታወቀ የክብደት መጨመር፣ የፀጉር መርገፍ፣ የሆድ ድርቀት፣ ብርድ ብርድ የማለት ስሜት፣ የወር አበባ መዛባት፣ የመንፈስ ጭንቀት፣ የድምፅ መለወጥ (መጎርነን ወይም ዝቅ ያለ ድምፅ)፣ የማስታወስ ችሎታ መቀነስና ድካም ናቸው።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.36 አንዳንዶቹ ምልክቶች በሌላ ምክንያትም ሊከሰቱ የሚችሉ በመሆናቸው ጤንነት ካልተሰማህ ሐኪም ማማከር እንዳለብህ አትዘንጋ።

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

 ለአራስ ሕፃናት አስፈላጊ የሆነ ምርመራ

የአንድን አራስ ሕፃን ደም በመመርመር የታይሮይድ ዕጢው ጤነኛ መሆን አለመሆኑን ማወቅ ይቻላል። የደም ምርመራው ችግር መኖሩን ካመለከተ ሐኪሞቹ ችግሩን ለማስተካከል እርምጃ ሊወስዱ ይችላሉ። አንድ ልጅ በሰውነቱ ውስጥ በቂ የታይሮይድ ሆርሞኖች ከሌሉት አካላዊም ሆነ አእምሯዊ ዕድገቱ እንዲጓተት በሚያደርግ ክሪትኒዝም በሚባል የጤና እክል ሊጠቃ ይችላል። በመሆኑም ሕፃናት ብዙውን ጊዜ በተወለዱ በጥቂት ቀናት ውስጥ ምርመራ ይደረግላቸዋል።

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የተመጣጠነ ምግብ እየወሰድክ ነው?

የተመጣጠነ ምግብ መመገብ የታይሮይድ ችግርን ለመከላከል ሊረዳ ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ የታይሮይድ ሆርሞኖች እንዲመነጩ ለማድረግ የሚያስፈልገው አዮዲን በምትመገበው ምግብ ውስጥ በበቂ መጠን ይገኛል? ጨዋማ በሆነ ውኃ ውስጥ በሚኖሩ ዓሦችና ከባሕር በሚገኙ ሌሎች ምግቦች ውስጥ ይህ አስፈላጊ ማዕድን ይገኛል። በአትልክቶችና በሥጋ ውስጥ የሚገኘው አዮዲን መጠን እንደየአካባቢው የአፈር ዓይነት ይለያያል። አንዳንድ መንግሥታት፣ ከምግብ ውስጥ ሊጎድል የሚችለውን ይህን ማዕድን ለማካካስ ጨው አምራቾች በጨዉ ውስጥ አዮዲን እንዲጨምሩ የሚያዝ ሕግ አውጥተዋል።

ለታይሮይድ ዕጢ አስፈላጊ የሆነው ሌላው ነገር ሲሊኒየም ነው። በሰውነታችን ውስጥ እጅግ አነስተኛ በሆነ መጠን የሚገኘው ይህ ንጥረ ነገር T4ን ወደ T3 ለመለወጥ የሚረዳው ኤንዛይም ክፍል ነው። በአትክልቶች፣ በሥጋዎችና በወተት ውስጥ የሚገኘው የሲሊኒየም መጠንም ቢሆን በአካባቢው የአፈር ዓይነት ላይ የተመካ ነው። ከባሕር የሚገኝ ምግብ፣ እንቁላል፣ ጎመንና ቲማቲም ሲሊኒየም በብዛት ከሚገኝባቸው ምግቦች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። በእርግጥ የታይሮይድ ችግር እንዳለብህ ከተጠራጠርክ ሐኪም አማክር እንጂ ራስህን ለማከም አትሞክር።

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

የአየር ቧንቧ

ማንቁርት

ታይሮይድ ዕጢ

የአየር ቧንቧ