በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

“በመላው ሩሲያ ከሚገኙ ቤተ መዘክሮች ውስጥ 160,000 የሚሆኑ ለሕዝብ የሚታዩ ዕቃዎች ጠፍተዋል።”—ሪአ ኖቮስቲ፣ ሩሲያ

“የዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ የበረራና የሕዋ አስተዳደር (NASA) ያመጠቃት ፎኔክስ ማርስ ላንደር የተባለች መንኮራኩር በማርስ ላይ የሚገኙት ደመናዎች በረዶ እንደጣሉ አሳይታለች።”—“ናሳ ሚሽን ኒውስ፣” ዩ ኤስ ኤ

“በግሪክ ሕይወታቸውን ከሚያጡት ሾፌሮችና መንገደኞች መካከል 65 በመቶ የሚሆኑት የወንበር ቀበቷቸውን ወይም የአደጋ መከላከያ ቆብ አይጠቀሙም።” —ኢኮኔስ፣ ግሪክ

የጠፉ ሻንጣዎች

በአውሮፕላን ጉዞ ላይ አዘውትሮ የሚያጋጥም ነገር ቢኖር የሻንጣዎች መጥፋት ነው። ኢንተርናሽናል ሄራልድ ትሪቢዩን እንደዘገበው በ2007 “42 ሚሊዮን ሻንጣዎች ጠፍተው የነበረ ሲሆን ይህ ቁጥር በ2006 ከጠፉት በ25 በመቶ ይበልጣል።” ከጠፉት ሻንጣዎች አብዛኞቹ በ48 ሰዓታት ውስጥ ለባለቤቶቻቸው የተመለሱ ቢሆንም ከጠፉት ሻንጣዎች 3 በመቶ የሚያህሉት ከነጭራሹ አልተገኙም። ይህም “ከ2,000 መንገደኞች ውስጥ የአንዱ ሻንጣ ጠፍቶ ይቀራል” ማለት ነው። በ2007 በጠፉ ሻንጣዎች ምክንያት አየር መንገዶች 3.8 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ከፍለዋል። ለሻንጣዎቹ መጥፋት መንስኤ ከሆኑት ነገሮች መካከል “የመንገደኞች ቁጥር በመጨመሩ የሚፈጠረው መጨናነቅ፣ አውሮፕላኑ ጭነቱን ለማራገፍ የሚሰጠው ጊዜ አጭር መሆኑ” እንዲሁም ሻንጣዎች በአግባቡ አለመያዛቸውና ተለጣፊ የመለያ ምልክቶች በተገቢው መንገድ አለመጻፋቸው ይገኙበታል።

ሳይጋቡ እንደ ባልና ሚስት የሚኖሩ ካቶሊኮች

ፖፑላሲዮን ኤ ሶሲየቴ የተሰኘ መጽሔት እንደተናገረው ሰዎች የየትኛውም ሃይማኖት አባል ይሁኑ፣ በሕይወታቸው ውስጥ በሚያደርጓቸው ለውጦችና በሥነ ምግባር እሴቶቻቸው ላይ ሃይማኖት የሚያሳድረው ተጽዕኖ በጣም መቀነሱን በፈረንሳይ የተደረገ አንድ ጥናት አመልክቷል። ለምሳሌ ያህል፣ በፈረንሳይ ከ18 እስከ 24 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙት ወጣቶች መካከል 88 በመቶ የሚሆኑት ካቶሊክ እንደሆኑ ቢናገሩም ከእነዚህ ውስጥ 80 በመቶ የሚሆኑት ለሠርግ፣ ለጥምቀት ወይም ለቀብር ሥነ ሥርዓት ካልሆነ በቀር ወደ ቤተ ክርስቲያን አይሄዱም። ባሕላዊ እሴቶች እያሽቆለቆሉ መሄዳቸው ያስከተለው ውጤት በቤተሰብ ሕይወት ውስጥም ይታያል። ከአርባ ዓመት በፊት፣ ሳይጋቡ እንደ ባልና ሚስት አብረው የሚኖሩት ከ10 ጥንዶች ውስጥ 1 ብቻ ነበሩ፤ ዛሬ ግን ከ10 ጥንዶች መካከል 9ኙ ሳይጋቡ አብረው ይኖራሉ። ጥናቱ እንዳመለከተው “አዘውትረው ወደ ቤተ ክርስቲያን ከሚሄዱት ጥንዶች መካከል 75 በመቶ የሚሆኑት ከመጋባታቸው በፊት አብረው ኖረዋል።”

በሕንድ ገበሬዎች ዘንድ የተስፋፋ ራስን የመግደል አባዜ

ሕንድ ውስጥ ከ2002 ወዲህ በየዓመቱ ከ17,000 የሚበልጡ ገበሬዎች የራሳቸውን ሕይወት እንዳጠፉ ዘ ሂንዱ የተሰኘው ጋዜጣ ዘግቧል፤ አብዛኞቹ ሰዎች ሕይወታቸውን ያጠፉት የተባይ ማጥፊያ መርዞችን በመዋጥ ነበር። ገበሬዎቹን ከገጠሟቸው ችግሮች መካከል ድርቅ፣ የሰብል ዋጋ ማሽቆልቆል፣ ለእርሻ የሚያስፈልጋቸው ወጪ መጨመር እንዲሁም የባንክ ብድር ማግኘት አስቸጋሪ መሆኑ ይገኙበታል። በዚህም ምክንያት ብዙዎቹ ገበሬዎች ከፍተኛ ወለድ ወደሚጠይቋቸው አራጣ አበዳሪዎች ይሄዳሉ፤ ይህ ደግሞ በከባድ ዕዳ ውስጥ እንዲዘፈቁ ያደርጋቸዋል። አንዳንዶቹ ገበሬዎች ዕዳቸውን ለመክፈል ሲሉ የሰውነታቸውን ክፍሎች አውጥተው እስከመሸጥ ይደርሳሉ። ይሁን እንጂ ይህ ሳይሳካ ሲቀር ወይም ምንም ዓይነት መላ ሲታጣ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ራስ ማጥፋትን ብቸኛ አማራጭ አድርገው ይወስዱታል።

የናይል አዞዎች ከእንቁላላቸው ውስጥ ከመቀፍቀፋቸው በፊት ይነጋገራሉ

የለንደኑ ዘ ታይምስ እንደዘገበው “አዞዎች ገና በእንቁላል ውስጥ እንዳሉ እርስ በርሳቸው በመነጋገር” በተመሳሳይ ጊዜ ይቀፈቀፋሉ። ተመራማሪዎች የናይል አዞዎች ከእንቁላላቸው ከመቀፍቀፋቸው በፊት የሚያሰሙትን ድምፅ ከቀረጹ በኋላ አንድ ላይ ያሉ ሌሎች የአዞ እንቁላሎች ይህን ድምፅ እንዲሰሙት አደረጉ። በዚህ ጊዜ በእንቁላሎቹ ውስጥ ያሉት ያልተቀፈቀፉ አዞዎች ለጥሪው ምላሽ የሰጡ ከመሆኑም ሌላ ይህን ድምፅ ካልሰሙት ሌሎች እንቁላሎች ይበልጥ ይንቀሳቀሱ ነበር። “ያልተቀፈቀፉ አዞዎች ያሰሙትን ድምፅ የሰሙት ሌሎች አዞዎች በሙሉ በአሥር ደቂቃ ውስጥ እንደተቀፈቀፉ” ዘገባው ይገልጻል። ምንም ድምፅ ያልሰሙት ወይም ሌላ ዓይነት ድምፅ እንዲሰሙ የተደረጉት እንቁላሎች ግን በተመሳሳይ ጊዜ አልተቀፈቀፉም።