ያላስወረድንበት ምክንያት
ያላስወረድንበት ምክንያት
በመጀመሪያው ርዕሰ ትምህርት ላይ የተጠቀሰችው ቪክቶሪያ ለወንድ ጓደኛዋ ለቢል እንደማታስወርድ ነገረችው። ቪክቶሪያ “በውስጤ ሕይወት እንዳለ ተሰምቶኝ ነበር” ስትል ተናግራለች። አክላም “ከቢል ጋር መኖር ከቀጠልኩ በእርግዝናዬ ወራት ድጋፍ እንደማያደርግልኝ ስለተገነዘብኩ ትቼው ሄድኩ” ብላለች።
ይሁን እንጂ ከዚያ በኋላ ቢል ሐሳቡን ለውጦ ቪክቶሪያን እንድታገባው ጠየቃት። ይሁንና ልጃቸውን ለማሳደግ አቅም ያላቸው አይመስልም ነበር። ቪክቶሪያ እንዲህ ብላለች፦ “መኪናም ሆነ ገንዘብ አልነበረንም፤ ልብሶቻችንም ቢሆኑ ጥቂቶች ነበሩ። ሁሉም ነገር የነበረን በጥቂቱ ብቻ ነበር። የቢል ደመወዝ አነስተኛ ስለነበር አነስተኛ ኪራይ በሚከፈልበት
ቤት ውስጥ ለመኖር ተገደድን፤ ሆኖም አንድ ላይ መኖራችንን ቀጠልን።”ባልታሰበ እርግዝና የተነሳ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን መጋፈጥ ግድ ሆኖባቸው ሌሎች ሰዎችም አሉ። እነሱም ቢሆኑ ፅንስ ለማስወረድ ፈቃደኞች አልሆኑም። ከእቅድ ውጪ የሆነ ሌላው ቀርቶ ያልተፈለገ እርግዝና ቢያጋጥማቸውም እንኳ በውሳኔያቸው እንዲጸኑና ልጅ ማሳደግ የሚያስከትለውን ውጥረት እንዲቋቋሙ የረዳቸው ምንድን ነው? ከመጽሐፍ ቅዱስ ያገኙት ውድ የሆነ ጥበብ ነው።
ቸኩላችሁ አትወስኑ—ተግባራዊ እቅድ አውጡ
መጽሐፍ ቅዱስ “የትጉህ ሰው ዕቅድ ወደ ትርፍ ያመራል፤ ችኮላም ወደ ድህነት ያደርሳል” በማለት ጥበብ ያዘለ ምክር ይሰጣል።—ምሳሌ 21:5
የአካል ጉዳተኛ የሆነን አንድ ልጅ ጨምሮ ሦስት ወንዶች ልጆች የነበሯት ኮኒ የምትባል አንዲት ሴት፣ ሌላ ልጅ የመውለዱ ሐሳብ የማይዋጥ ነገር ሆኖባት ነበር። እንዲህ ብላለች፦ “ሌላ ቀለብተኛ መጨመር አልፈለግንም ነበር። ስለዚህ ለማስወረድ አሰብን።” ይሁን እንጂ ኮኒ የችኮላ ውሳኔ ከማድረጓ በፊት ኬይ ለምትባል የሥራ ባልደረባዋ ጉዳዩን አዋየቻት። ኬይ በኮኒ ማህፀን ውስጥ ያለው ፅንስ ሰው መሆኑን እንድታስተውል በረዳቻት ጊዜ የኮኒ አስተሳሰብ ተለወጠ።
ይሁን እንጂ ኮኒ እቅድ ለማውጣት ተግባራዊ የሆነ እርዳታ ያስፈልጋት ነበር። ኮኒ በአካባቢዋ የምትኖር አክስት ስለነበረቻት ሄዳ እንድታነጋግራት ኬይ ሐሳብ አቀረበችላት። አክስቷን ሄዳ ስትጠይቃት ልትረዳት ፈቃደኛ ሆነች። የኮኒ ባልም ተጨማሪ ሥራ የያዘ ሲሆን አነስተኛ ኪራይ ወደሚከፈልበት አፓርታማ ተዛወሩ። በዚህ መንገድ አዲስ ለተወለደው ልጅ አስፈላጊውን እንክብካቤ ማድረግ ቻሉ።
በተጨማሪም ኬይ፣ ከእቅዳቸው ውጪ ልጅ ለወለዱ ሰዎች እርዳታ የሚሰጡ አንዳንድ ድርጅቶችን በማፈላለግ ኮኒን ረዳቻት። በብዙ አገሮች ውስጥ ችግር ላለባቸው አራስ ሴቶች እርዳታ የሚያደርጉ እንዲህ ዓይነት ድርጅቶች አሉ። ኢንተርኔትና የስልክ ማውጫዎችን ተጠቅሞ እነዚህን ድርጅቶች ማግኘት ይቻላል። እርዳታ ማግኘት የሚቻልበትን መንገድ ማፈላለግ ጥረት የሚጠይቅ ቢሆንም ወደ ስኬት የሚያደርሰው “የትጉህ ሰው ዕቅድ” መሆኑን ማስታወስ ያስፈልጋል።
ሰው መሆኑን አምናችሁ ተቀበሉ
መጽሐፍ ቅዱስ “የጠቢብ ሰው ዐይኖች ያሉት በራሱ ውስጥ ነው፤ ሞኝ ግን በጨለማ ውስጥ ይራመዳል” ይላል።—መክብብ 2:14
በእርግጥ ጠቢብ የሆነች ሴት እውነቱን ላለማየት ዐይኗን ጨፍና ‘በጨለማ ውስጥ አትራመድም።’ ‘በራሷ ውስጥ ያሉትን ዐይኖች’ ማለትም የማመዛዘን ችሎታዋን ትጠቀምበታለች። ይህ ደግሞ የምትወስደው እርምጃ የሚያስከትለውን ውጤት በሚገባ እንድታመዛዝን ያስችላታል። በማሕፀኗ ውስጥ እየተካሄደ ስላለው ነገር እውነታውን ላለማየት ዐይኖቿን ከምትጨፍን ሴት በተቃራኒ ጥበበኛ ሴት ከልብ በመነጨ ርኅራኄ በመገፋፋት በማህፀኗ ውስጥ ያለውን ሕያው ፅንስ ለመጠበቅ እርምጃ ትወስዳለች።
ለማስወረድ ስታስብ የነበረች ስቴፋኒ የምትባል ነፍሰ ጡር ወጣት በማሕፀኗ ያለውን የሁለት ወር ልጅ የሚያሳይ የአልትራሳውንድ ምስል እንድታይ ተደረገች። ስቴፋኒ “ማልቀስ ጀመርኩ” በማለት ተናግራለች። አክላም “ሕይወት ያለውን ነገር የምገድለው ለምንድን ነው? ብዬ አሰብኩ” ብላለች።
ሳታገባ ያረገዘች ዴኒዝ የምትባል ሌላ ነፍሰ ጡር ወጣትም በማህፀኗ ያለው ፅንስ ሕይወት ያለው ሰው መሆኑን አምና ተቀብላለች። ወንድ ጓደኛዋ “አንድ ነገር አድርጊ” ብሎ ገንዘብ ሲሰጣት “ምን? ላስወርድ? በፍጹም አላደርገውም!” በማለት መልስ ሰጠችው። ይህች ወጣት ልጇን ለመግደል ፈቃደኛ አልሆነችም።
ሰውን መፍራት የሚያስከትለው ጣጣ
ሰዎች በሚያሳድሩባቸው ግፊት የተነሳ ውርጃ ለመፈጸም የሚያስቡ ሁሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በምሳሌ መጽሐፍ ላይ የተገለጸውን የሚከተለውን ሐሳብ ቢያስቡበት ጥሩ ነው፦ “ሰውን መፍራት ወጥመድ ነው፤ በእግዚአብሔር የሚታመን ግን በሰላም ይኖራል።”—ምሳሌ 29:25
ሞኒካ በ17 ዓመቷ በንግድ ሥራ ኮሌጅ ትምህርቷን ልትጀምር አካባቢ ከወንድ ጓደኛዋ አረገዘች። አምስት ልጆችን ብቻዋን የምታሳድገው እናቷ እጅግ ከመበሳጨቷ የተነሳ
የምትሆነው ጠፋት። ልጇ አንድ ሞያ ተምራ ከድህነት እንድታላቅቃት ትመኝ ነበር። እናትየው የምታደርገው ነገር ሲጠፋት ሞኒካን እንድታስወርድ ጎተጎተቻት። ሞኒካ “ለማስወረድ እፈልግ እንደሆነ ሐኪሙ ሲጠይቀኝ ‘አልፈልግም!’ አልኩት” ስትል ተናግራለች።የሞኒካ እናት፣ የልጇ ተስፋ መና እንደቀረ መመልከትና ሌላ ልጅ ማሳደግ ስለሚያሳድረው ጫና ማሰብ በጣም ስላስጨነቃት ሞኒካን ከቤት አባረረቻት። ሞኒካ አክስቷ ጋር መኖር ጀመረች። እናትየው ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ንዴቷ በረድ ሲልላት ሞኒካ ወደ ቤት እንድትመለስ ፈቀደችላት። የሞኒካ እናት አዲስ የተወለደውን ልጅ ሊዮንን በመንከባከብ ሞኒካን የረዳቻት ከመሆኑም ሌላ ልጁን እጅግ ወደደችው።
ባለ ትዳር የሆነችውን ሮቢንን ፅንስ እንድታስወርድ ግፊት ያደርግባት የነበረው ግን ሐኪሟ ነበር። ሮቢን እንዲህ ብላለች፦ “ያረገዝኩ ሰሞን የኩላሊት ኢንፌክሽን ይዞኝ ስለነበር ሐኪሜ እርግዝና መኖር አለመኖሩን ሳይመረምር መድኃኒት አዘዘልኝ። በኋላም ልጁ ዘገምተኛ ሆኖ የመወለድ አጋጣሚው ሰፊ እንደሆነ ተነገረኝ።” በዚህ ጊዜ ሐኪሙ እንድታስወርድ መከራት። ሮቢን እንደሚከተለው ብላለች፦ “እኔም መጽሐፍ ቅዱስ የሕይወትን ዋጋማነት በሚመለከት ምን እንደሚል ገለጽኩለት። ከዚያም በምንም መንገድ ውርጃ እንደማልፈጽም ነገርኩት።”
ሐኪሙ እንዲህ ያለ ምክር እንዲሰጥ ያደረገው በቂ ምክንያት ቢኖረውም በወቅቱ በሮቢን ሕይወት ላይ ስጋት የሚጥል ነገር አልነበረም። * ሮቢን እንዲህ ብላለች፦ “ሴት ልጄ ከተወለደች በኋላ ምርመራ ተደረገላት። የምርመራው ውጤት በአእምሮ መጎዳት ሳቢያ የሚመጣ መጠነኛ የዘገምተኝነት ችግር እንዳለባት የሚያሳይ ነበር። በአሁኑ ጊዜ ጥሩ እድገት እያደረገች ነው። ዕድሜዋ 15 ዓመት ሲሆን የንባብ ችሎታዋም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ነው። ልጄን በጣም ስለምወዳት ይሖዋ እሷን ስለሰጠኝ በየዕለቱ ደጋግሜ አመሰግነዋለሁ።”
ከአምላክ ጋር ወዳጅ መሆን ያለው ኃይል
መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር ለሚታዘዙት ሁሉ ወዳጃቸው ነው” በማለት ይናገራል።—መዝሙር 25:14 የ1980 ትርጉም
ፅንስ ለማስወረድ ፈቃደኛ የማይሆኑ ሴቶች እዚህ ውሳኔ ላይ እንዲደርሱ በዋነኝነት የሚገፋፋቸው ፈጣሪያቸው ስለ ጉዳዩ ያለውን አመለካከት ከግምት ማስገባታቸው ነው። እንዲህ ያሉት ሰዎች ከምንም በላይ የሚያሳስባቸው ከአምላክ ጋር ያላቸው ወዳጅነትና እሱን የሚያስደስተውን ነገር የማድረጋቸው ጉዳይ ነው። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ቪክቶሪያ ፅንስ ላለማስወረድ እንድትወስን የገፋፋትም ምክንያት ይኸው ነው። እንዲህ ብላለች፦ “ሕይወትን የሚሰጠው አምላክ እንደሆነና እሱ የሰጠውን ሕይወት የማጥፋት መብት እንደሌለኝ ጽኑ እምነት ነበረኝ።”
ቪክቶሪያ መጽሐፍ ቅዱስን ከልብ ማጥናት ስትጀምር ከአምላክ ጋር የነበራት ወዳጅነት እየተጠናከረ መጣ። እንዲህ ብላለች፦ “ልጄን ላለመግደል መወሰኔ ወደ አምላክ ይበልጥ እንደቀረብኩ እንዲሰማኝና በሁሉም የሕይወቴ ዘርፍ እሱን የማስደሰት ፍላጎት እንዲያድርብኝ አድርጎኛል። የእሱን አመራር ለማግኘት ስጸልይ ሁሉም ነገር ይሳካልኝ ነበር።”
መዝሙር 36:9) ከዚህም በላይ አንዲት ሴትና ቤተሰቧ ባልታሰበ እርግዝና ምክንያት የሚመጣውን ኃላፊነት እንዲቋቋሙ ለመርዳት አምላክ ‘ከሰብዓዊ ኃይል በላይ የሆነ ኃይል’ ሊሰጣቸው ይችላል። (2 ቆሮንቶስ 4:7) አምላክ ለሕይወት ላለው አመለካከት አክብሮት ያሳዩ ሰዎች ያደረጉትን ውሳኔ መለስ ብለው ሲያስቡ ምን ይሰማቸዋል?
የሕይወት ምንጭ ከሆነው አምላክ ጋር ወዳጅ መሆን በማሕፀን ውስጥ ላለው ሕይወት ጥልቅ አክብሮት እንዲኖረን ያደርጋል። (በውሳኔያቸው አልተጸጸቱም
እነዚህ ወላጆች በጥፋተኝነት ስሜት አይሠቃዩም ወይም ልጅ ማጣት በሚያስከትለው ከባድ ሐዘን እየተብሰለሰሉ አይኖሩም። ከጊዜ በኋላም ‘የማሕፀን ፍሬ’ እርግማን ሳይሆን በረከት መሆኑን ተገንዝበዋል! (መዝሙር 127:3) ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ኮኒ ይህን የተገነዘበችው ከወለደች ከሁለት ሰዓት በኋላ ነበር! በደስታ ስሜት ተውጣ የሥራ ባልደረባዋ ለሆነችው ኬይ ስልክ ደወለችና ትንሿን ሴት ልጇን የማሳደግ መብት የሚጠብቃት መሆኑ ምን ያህል እንዳስደሰታት ነገረቻት። ኮኒ የደስታ ሲቃ እየተናነቃት “አምላክ እሱን የሚያስደስተውን ነገር የሚያደርጉ ሰዎችን እንደሚባርክ አረጋግጫለሁ” አለቻት።
አምላክ ለሕይወት ካለው አመለካከት ጋር የሚስማማ እርምጃ መውሰድ ይህን ያህል ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው? ምክንያቱም አምላክ የሕይወት ምንጭ እንደመሆኑ መጠን ሕጉንና መሥፈርቶቹን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያስቀመጠልን ‘መልካም እንዲሆንልን’ ወይም ‘ለራሳችን ጥቅም’ ሲል ነው።—ዘዳግም 10:13 የ1980 ትርጉም
ተሞክሯቸው በዚህና በመጀመሪያው ርዕሰ ትምህርት ላይ የተጠቀሱት ቪክቶሪያና ቢል እንደገለጹት ላለማስወረድ ያደረጉት ውሳኔ በሕይወታቸው ላይ ትልቅ ለውጥ አምጥቷል። ውሳኔያቸው በሕይወታቸው ላይ ያስከተለውን ለውጥ እንዲህ በማለት ይገልጹታል፦ “የአደንዛዥ ዕፅ ሱሰኛ ሆነን ስለነበር ለውጥ ባናደርግ ኖሮ እስከ ዛሬ እንሞት ነበር። ይሁን እንጂ ላልተወለደው ልጃችን ሕይወት አክብሮት ማሳየታችን ቆም ብለን ስለ ራሳችን ሕይወት እንድናስብ አደረገን። በይሖዋ ምሥክሮች እርዳታ ለውጥ ማድረግ ችለናል።”
ልጃቸው ላንስ አሁን ዕድሜው 34 ዓመት ሊሞላው የተቃረበ ሲሆን ትዳር ከያዘ ከ12 ዓመት በላይ ሆኖታል። ላንስ እንደሚከተለው በማለት ይናገራል፦ “ከልጅነቴ ጀምሮ ወላጆቼ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ውሳኔ እንዳደርግ አስተምረውኛል። ይህ ደግሞ እኔ፣ ባለቤቴና ልጄ ‘ከዚህ የበለጠ ደስታ ልናገኝ አንችልም’ የሚል ስሜት እስኪሰማን ድረስ ከፍተኛ ጥቅም አስገኝቶልናል።” መጀመሪያ ላይ ቪክቶሪያ እንድታስወርድ ፈልጎ የነበረው አባቱ “ይህን ውድ ልጃችንን ልናጣው ትንሽ ቀርቶን እንደነበር ስናስበው ይዘገንነናል” ብሏል።
እናቷ ብትገፋፋትም ለማስወረድ ፈቃደኛ ሳትሆን የቀረችው ሞኒካ የሰጠችውን አስተያየት ተመልከት። እንዲህ ብላለች፦ “ወንድ ልጄን ከወለድኩ ከሁለት ሳምንት በኋላ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኘሁና ከአምላክ ሕግ ጋር ሙሉ በሙሉ የሚስማማ ሕይወት መምራት የምችለው እንዴት እንደሆነ ተማርኩ። ብዙም ሳይቆይ ልጄን ሊዮንን አምላክን መታዘዝ ያለውን ጠቀሜታ ማስተማር ጀመርኩ፤ ከጊዜ በኋላ እሱም ለአምላክ ጠንካራ ፍቅር እያዳበረ መጣ። ሊዮን በአሁኑ ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች ተጓዥ የበላይ ተመልካች ነው።”
ሊዮን እናቱ ያደረገችለትን መለስ ብሎ በማሰብ እንደሚከተለው ሲል ተናግሯል፦ “እናቴ ለእኔ ካላት ጥልቅ ፍቅር የተነሳ፣ የደረሰባትን ከፍተኛ ግፊት በመቋቋም በሕይወት እንድኖር መፍቀዷን ማወቄ አምላክ ለሰጠኝ ለዚህ ውድ ስጦታ ያለኝን አድናቆት ለመግለጽ ስል ሕይወቴን ከሁሉ በተሻለ መንገድ እንድመራ ገፋፍቶኛል።”
አምላክ ሕይወትን እንደ ውድ ነገር አድርጎ እንደሚመለከተው የተረዱ ሰዎች አሁን እጅግ የሚወዱትን ልጅ ሕይወት ላለማጥፋት በመወሰናቸው ፈጽሞ አይቆጩም። ልባቸው በአመስጋኝነት ስሜት ተሞልቶ “እንኳን ያላስወረድን!” ለማለት ይችላሉ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.20 በምጥ ወቅት ከእናቲቱና ከልጁ ሕይወት አንዱን መምረጥ የሚያስገድድ ሁኔታ ቢፈጠር ውሳኔ የማድረግ ኃላፊነቱ የሚወድቀው ጉዳዩ በቀጥታ በሚመለከታቸው ግለሰቦች ላይ ነው። ይሁን እንጂ በብዙ አገሮች በሕክምና መስክ ከፍተኛ እመርታ በመገኘቱ ይህ ሁኔታ እምብዛም አያጋጥምም።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ስቴፋኒ በማህፀኗ ውስጥ ያለውን የሁለት ወር ልጅ የሚያሳይ የአልትራሳውንድ ምስል መመልከቷ ላለማስወረድ እንድትወስን ረድቷታል
(በፅንሱ ዙሪያ ያለው መስመር ተጨማሪ ነው)
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቪክቶሪያና ላንስ
[በገጽ 8 እና 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በዛሬው ጊዜ ቪክቶሪያና ቢል፣ ከላንስና ከቤተሰቡ ጋር
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሞኒካና ልጇ ሊዮን ከ36 ዓመት በፊት እንድታስወርደው የተደረገባትን ግፊት በመቋቋሟ እጅግ ደስተኞች ናቸው