በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከሰሜን አትላንቲክ ውቅያኖስ ወለል ላይ “እስከ ዛሬ ከታወቁት ሁሉ የበለጠ ረጅም ዕድሜ የኖረ” ክላም የሚባል ባለ ቅርፊት የባሕር እንስሳ እንደተገኘ ሪፖርት ተደርጓል። የሳይንስ ሊቃውንት የእንስሳውን ዕድገት የሚጠቁሙትን የቅርፊቶች ንብርብር በመቁጠር ዕድሜው 405 ዓመት እንደሆነ ተናግረዋል።—ሰንዴይ ታይምስ፣ ብሪታንያ

“የኢኮኖሚ ማሽቆልቆል በሚኖርበት ጊዜ፣ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ያላቸው ሰዎች ሳይቀሩ የሥነ ልቦና አማካሪዎቻቸው እርዳታ እስኪያስፈልጋቸው ድረስ ሁኔታው ያስጨንቃቸዋል።”—ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ፣ ዩናይትድ ስቴትስ

ቴሌቪዥን በወሲባዊ ባሕርይ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል

“ወጣቶች በቴሌቪዥን የሚተላለፉ ወሲባዊ ይዘት ያላቸውን ፊልሞች በተደጋጋሚ መመልከታቸው ለወሲብ ያላቸውን አመለካከትና ከወሲብ ጋር በተያያዘ ያላቸውን ባሕርይ እንደሚቀርጸው የሚያሳዩ ማስረጃዎች እየጨመሩ ነው” በማለት ፔዲያትሪክስ በተሰኘ መጽሔት ላይ የወጣ አንድ ርዕስ ይናገራል። እንዲያውም አንድ ጥናት እንደገለጸው እንደዚህ ያሉትን ፕሮግራሞች በብዛት የሚመለከቱ ወጣቶች “የማርገዝ አጋጣሚያቸው” እምብዛም ከማይመለከቱት ወጣቶች “በእጥፍ ይጨምራል።” ለዚህ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል የተገለጸው አንዱ ነገር ቴሌቪዥን፣ የጾታ ግንኙነት ምንም መዘዝ የማያስከትል ድርጊት እንደሆነ አድርጎ ማቅረቡ ሲሆን ያልተፈለገ እርግዝናንና በጾታ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎችን የመሰሉ በገሃዱ ዓለም የሚያጋጥሙ እውነታዎችን በግልጽ አያሳይም። እርግጥ ነው፣ ቴሌቪዥን የወጣቶችን ወሲባዊ ባሕርይ ከሚቀርጹት መገናኛ ብዙኃን ውስጥ አንዱ ብቻ ነው። ከዚህ በተጨማሪ መጽሔቶች፣ ኢንተርኔትና ሙዚቃ በወጣቶች ላይ የሚያሳድሩት ተጽዕኖ በቀላሉ ሊታይ እንደማይገባ ተመራማሪዎች ይናገራሉ።

የሥጋ ደዌ በሽተኞች አሁንም እየተገኙ ነው

በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ሦስት ሺህ የሚሆኑ ሰዎች ለሥጋ ደዌ በሽታ ወይም ለሃንሰንስ ዲዚዝ ሕክምና እየተሰጣቸው ነው። በየዓመቱ 150 ገደማ የሚሆኑ ሰዎች ይህ በሽታ እንደሚገኝባቸው ሪፖርት ተደርጓል። ብዙዎቹ የዚህ በሽታ ተጠቂዎች ከሌሎች አገሮች የመጡ ናቸው። ይሁን እንጂ ዚ አሜሪካን ሶሳይቲ ኦቭ ትሮፒካል ሜዲሲን ኤንድ ሃይጂን የተሰኘው ድርጅት እንደተናገረው በባተን ሩዥ፣ ሉዊዚያና የሚገኘው የሐንሰንስ ዲዝዝ ብሔራዊ ፕሮግራም “በየዓመቱ በደቡባዊ ሉዊዚያናና በቴክሳስ ባሕረ ሰላጤ አካባቢ የሚኖሩ 30 የሚያህሉ የዚህ በሽታ ተጠቂዎችን ያገኛል፤ እነዚህ ሰዎች በዩናይትድ ስቴትስ የተወለዱና ይህ በሽታ በብዛት ወደሚገኝበት አካባቢ ሄደው የማያውቁ ናቸው።” ተመራማሪዎች ይህ በሽታ እንዴት እንደሚሰራጭ እስካሁን ድረስ ሙሉ በሙሉ አልተረዱም። የሥጋ ደዌ በሽታ ቀደም ብሎ ከታወቀ ሙሉ በሙሉ ሊድን ይችላል። ይሁን እንጂ በሽታው ሥር ከሰደደ በነርቭ ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ማስተካከል አይቻልም።

የራዲዮአክቲቭ ንጥረ ነገሮች ስርቆት

“አሸባሪዎች የኑክሌር ወይም የሌላ ዓይነት ራዲዮአክቲቭ ንጥረ ነገሮችን ማግኘት የሚችሉ መሆናቸው አሁንም ስጋት እየፈጠረ ነው” በማለት የዓለም አቀፉ አቶሚክ ኤነርጂ ኤጀንሲ ዳይሬክተር ጄኔራል፣ ሞሐመድ ኤልባራዴ ይናገራሉ። “የኑክሌር ወይም የራዲዮአክቲቭ ንጥረ ነገሮች እንደተሰረቁ ወይም እንደጠፉ ለኤጀንሲው የሚቀርበው ሪፖርት ቁጥር በአሳሳቢ ደረጃ ጨምሯል፤ በ2008 በመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ውስጥ ብቻ ወደ 250 የሚጠጉ ንጥረ ነገሮች እንደጠፉ ወይም እንደተሰረቁ ሪፖርት ተደርጓል። የዚህን ያህል አሳሳቢ የሆነው ሌላው ነገር ደግሞ፣ እንደተሰረቀ ወይም እንደጠፋ ሪፖርት ከተደረገው ውስጥ አብዛኛው የደረሰበት አለመታወቁ ነው።” ይህ ሁኔታ የተከሰተው የራዲዮአክቲቭ ንጥረ ነገሮች ፍላጎት በመጨመሩ ነው ወይስ አባል አገሮች እነዚህ ንጥረ ነገሮች እንደተሰረቁባቸው ወይም እንደጠፉባቸው ከበፊቱ ይበልጥ በትክክል ሪፖርት በማድረጋቸው? የሚለው በግልጽ አይታወቅም።

ጥንታዊ ጽሑፍ በእስራኤል ተገኘ

የእስራኤል የአርኪኦሎጂ ተመራማሪዎች፣ ከሙት ባሕር ጥቅልሎች 1,000 ዓመታት ቀድሞ የተጻፈ የሚመስል ጥንታዊ ጽሑፍ አግኝተዋል። ጽሑፉ በሸክላ ስባሪ ላይ በቀለም የተጻፉ አምስት መሥመሮችን የያዘ ሲሆን የተገኘውም በእስራኤል አገር በ10ኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. የይሁዳ ምሽግ ከነበረ ኪርቤት ቃያፋ ከሚባል ቦታ ነው። ሰነዱ ገና ሙሉ በሙሉ ፍቺ ያልተሰጠው ቢሆንም በሠለጠነ ጸሐፊ የተጻፈ ሕጋዊ ሰነድ እንደሚመስልና “‘ዳኛ፣’ ‘ባሪያ’ እና ‘ንጉሥ’ ለሚሉት ቃላት መነሻ የሆኑ ቃላትን” እንደያዘ ሂብሪው ዩኒቨርሲቲ ኦቭ ጀሩሳሌም ያወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ ይናገራል።

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Gabi Laron/Institute of Archaeology/Hebrew University © Yosef Garfinkel