በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ታማኝ የሆኑና ተባብረው የሚሠሩ ወላጆች

ታማኝ የሆኑና ተባብረው የሚሠሩ ወላጆች

ታማኝ የሆኑና ተባብረው የሚሠሩ ወላጆች

በደቡብ አፍሪካ ከፍተኛ ቦታዎች የቅዝቃዜው መጠን ወደ ዜሮ ዲግሪ ሴንቲግሬድ ይጠጋል። ሦስተኛ ፎቅ ላይ በሚገኘው የሞቀ ቢሮዬ ሆኜ የሚያፏጨው የክረምት ንፋስ ቅጠሎቹ የረገፉበትን አንድ ዛፍ ከወዲያ ወዲህ ሲያወዛውዘው እመለከታለሁ። በቅርንጫፎቹ መካከል አንድ ርግብ፣ ከተፈለፈሉ ሦስት ቀናት የሆናቸውን ሁለት ጫጩቶች ታቅፎ ያሞቃል።

ሴቷ ርግብ ለመጀመሪያ ጊዜ እንቁላል ከመጣሏ በፊት፣ ወንዱ ርግብ ጭራሮ እያመጣ ሴቷ ደግሞ ጭራሮውን በቦታው እያስገባች ተባብረው ጎጇቸውን ሠርተዋል። ኃይለኛው የክረምቱ ነፋስ ጎጆውን ከቦታው ሊያነቃንቀው ስላልቻለ ሥራቸው በጣም ጥራት ያለው ነው፤ ይህ ጎጆ እስካሁን ለበርካታ ጫጩቶች መጠለያ ሆኗል። ሴቷ ርግብ እንቁላሎቹን ማታ ማታ የምትታቀፍ ሲሆን ወንዱ ደግሞ በቀን ይታቀፋል። ከሁለት ሳምንት ገደማ በኋላ እንቁላሎቹ ይፈለፈላሉ። ከተፈለፈሉ ሁለት ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ጫጩቶቹ አድገውና ጠንክረው ለመብረር ይደርሳሉ።

እስቲ ለማዳመጥ ሞክሩ! ደስ እንደሚል ዜማ የሚንቆረቆረው የርግቦቹ ዝማሬ ይሰማችኋል? ሴቷ ርግብ በአቅራቢያው ባለ ቅርንጫፍ ላይ ሆና ለተራቡት ጫጩቶቿ ‘ምግብ ይዤ መጥቻለሁ’ እያለች የምትጮህ ትመስላለች፤ በዚህ ጊዜ ወንዱ ርግብ ጎጆውን ለቅቆ ይወጣል። ጫጩቶቹ መብረር ከቻሉ በኋላም እንኳ ራሳቸውን መንከባከብ የሚችሉበት ጊዜ እስኪደርስ ወላጆቻቸው እነሱን መመገባቸውን ይቀጥላሉ።

እነዚህ ርግቦች እርስ በርስ ተባብረው ሲሠሩና ጫጩቶቻቸውን ሲንከባከቡ ስመለከት ሁልጊዜ ያስደንቀኛል፤ አምላክ በተፈጥሮ የሰጣቸው ይህ ስጦታ ደግሞ ከአንድ ትውልድ ወደ ሌላው ትውልድ ይተላለፋል። የተመለከትኩት አስገራሚ ትዕይንት በመዝሙር 86:8 ላይ ያለውን ጥቅስ እንዳስታውስ አድርጎኛል፦ “ጌታ ሆይ፤ . . . እንደ አንተ ያለ የለም፤ ከአንተም ሥራ ጋር የሚወዳደር ሥራ የለም።”

ይሖዋ አምላክ፣ ለርግቦቹ የሰጣቸውን የተፈጥሮ ስጦታ ያህል አስተማማኝ የሆነ መመሪያ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ለሰብዓዊ ወላጆችም ሰጥቷል። ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ እናቶች “ልጆቻቸውን የሚወዱ” እንዲሆኑ ያዛል። (ቲቶ 2:4) ለአባቶች ደግሞ እንዲህ የሚል መመሪያ ይሰጣል፦ “ልጆቻችሁን አታስመርሯቸው፤ ከዚህ ይልቅ በይሖዋ ተግሣጽ እንዲሁም የእሱን አስተሳሰብ በውስጣቸው በመቅረጽ አሳድጓቸው።” (ኤፌሶን 6:4፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:8) አምላክ፣ እነዚህን መመሪያዎች በተግባር የሚያውሉ ወላጆችን እንደሚያደንቃቸው ጥርጥር የለውም።