በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ድንቅ የግንባታ ሥራዎችን ያከናወነው ታላቁ ሄሮድስ

ድንቅ የግንባታ ሥራዎችን ያከናወነው ታላቁ ሄሮድስ

ድንቅ የግንባታ ሥራዎችን ያከናወነው ታላቁ ሄሮድስ

ከዛሬ ሁለት ሺህ ዓመታት በፊት ለሠላሳ ዓመታት ያህል ገዝቷል። ንጉሥ ሆኖ የገዛው በይሁዳ ተቀምጦ ሲሆን ግዛቱ በዙሪያዋ ያሉ አንዳንድ አካባቢዎችን ይጨምር ነበር። ይህ ንጉሥ በታሪክ ውስጥ የሚታወቀው ታላቁ ሄሮድስ እየተባለ ነው።

ሄሮድስ ብዙውን ጊዜ የሚታወሰው የራሱን ቤተሰብ አባላት ብቻ ሳይሆን ምንም የማያውቁ ሕፃናትን ጭምር በቅናት ተነሳስቶ በመግደሉ ነው። ከምሥራቅ የመጡ ኮከብ ቆጣሪዎች ወደፊት ንጉሥ የሚሆን ልጅ እንደተወለደ ለሄሮድስ ሲነግሩት እሱም ለዚህ ሕፃን አክብሮቱን ሊገልጽለት እንደሚፈልግ በማስመሰል ሕፃኑን ፈልገው ካገኙት በኋላ መጥተው እንዲያሳውቁት ነገራቸው። አምላክ ግን ኮከብ ቆጣሪዎቹ ወደ ሄሮድስ እንዳይመለሱ አስጠነቀቃቸው፤ በዚህ ጊዜ ንጉሡ ኮከብ ቆጣሪዎቹ ኢየሱስን ባገኙባት በቤተ ልሔምና በዙሪያዋ ባሉ አውራጃዎች የሚገኙ ሁለት ዓመትና ከዚያ በታች ዕድሜ ያላቸው ሕፃናት እንዲገደሉ አዘዘ።—ማቴዎስ 2:1-18

ይሁን እንጂ ሄሮድስ ቀደም ሲል አስደናቂ የግንባታ ፕሮጀክቶችን አከናውኖ ስለነበር በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅነትን አትርፎ ነበር። ሄሮድስ ቤተ መቅደሶችን፣ አምፊቲያትሮችን፣ የፈረስና የሠረገላ መወዳደሪያ ስታዲየሞችንና የውኃ መውረጃ ቦዮችን አልፎ ተርፎም የቅንጦት መታጠቢያ ቤቶች ያሏቸው ትላልቅ የቤተ መንግሥት ሕንፃዎችን ገንብቷል። ሄሮድስ ያካሄዳቸው የግንባታ ሥራዎች በዚህ ዘመን ለሚገኙ ፍርስራሾቹን ለሚያጠኑ መሐንዲሶችም እንኳ ሳይቀር እጅግ የሚያስደንቁ ናቸው።

ሄሮድስ፣ የሚሠራቸው ሕንፃዎች ውበታቸው ጎልቶ እንዲወጣ የሚያደርግ መልክዓ ምድሮችን በመምረጥ ረገድ የተዋጣለት ሰው ነበር። የሄሮድስ ቤተ መንግሥቶች ግድግዳዎቻቸው በሥዕልና በስቱኮ በተሠሩ ቅርጾች ያሸበረቁ ሲሆኑ ወለሎቻቸውም በጠጠር ሥዕሎች ያጌጡ ነበሩ። በተጨማሪም ሄሮድስ የሮማውያንን አሠራር የተከተሉ መታጠቢያ ክፍሎችን በይሁዳ አሠርቶ ነበር፤ እነዚህ መታጠቢያ ቤቶች በጣም የሚሞቁ እንዲሁም መለስ ያለ ሙቀት ያላቸው ክፍሎች የነበሯቸው ከመሆኑም በላይ ክፍሎቹ ወለላቸው ሥር ማሞቂያ ተገጥሞላቸው ነበር። ሄሮድስ በርካታ አዳዲስ ከተሞችን ገንብቷል ማለት ይቻላል፤ ከእነዚህ ከተሞች መካከል አንዱ ሰው ሠራሽ ወደብ ነበረው።

ቂሳርያ—የወደብ ከተማ

ሄሮድስ በሮማውያን ዘመን ታላላቅ ከሚባሉት የባሕር ወደቦች መካከል አንዱን በቂሳርያ ሠርቷል። አርኪኦሎጂስቶች ይህ ወደብ በነበረው ስፋት ተገርመዋል። ወደቡ በአንድ ጊዜ መቶ መርከቦች መልሕቃቸውን እንዲጥሉ የሚያስችል ስፍራ ነበረው፤ ይህ ደግሞ ቂሳሪያ ዓለም አቀፍ ንግድ የሚካሄድባት ማዕከል እንደነበረች ይመሠክራል።

የዚህ ወደብ መድረኮችና የማዕበል መከላከያ ግንቦች በዘመኑ ከነበረው ቴክኖሎጂ በጣም በተራራቀ የምሕንድስና ጥበብ የተሠሩ ነበሩ። ይሁን እንጂ አይሁዳዊው ታሪክ ጸሐፊ ፍላቪየስ ጆሴፈስ እንደገለጸው ሠራተኞቹ በግምት 15 ሜትር ርዝመት፣ 3 ሜትር ወርድ እንዲሁም 3 ሜትር ውፍረት ያላቸውን በጣም ትላልቅ የማዕዘን ድንጋዮች እንዴት ማንቀሳቀስ እንደቻሉ ለተመራማሪዎቹ እንቆቅልሽ ሆኖባቸዋል። ጠላቂ ዋናተኞች፣ ሄሮድስ የተጠቀመባቸው ድንጋዮች የተጠረቡ ሳይሆኑ ኮንክሪት እንደሆኑ በቅርቡ ደርሰውበታል። ሠራተኞቹ የወደቡን መድረኮችና የማዕበል መከላከያ ግንቦች ለመገንባት የተቦካውን ኮንክሪት ከእንጨት በተሠሩ ቅርጽ ማውጫዎች ላይ በማፍሰስ ይጠቀጥቋቸዋል፤ ከዚያም ወደ ውኃው አስገብተው ይተክሉታል።

በጥሩ ፕላን የተሠራችው ይህች የወደብ ከተማ በአውግስጦስ ቄሣር ስም የተሠራ ቤተ መቅደስ፣ ቤተ መንግሥት፣ የፈረስና የሠረገላ መወዳደሪያ ስታዲየም፣ 4,000 መቀመጫ ያለው ቲያትር ቤትና መሬት ውስጥ የተቀበረ የፍሳሽ ማስወገጃ ነበራት። ቂሳርያ፣ ከከተማዋ ስድስት ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ ባለው የካርሜል ተራራ ላይ ከሚገኙት ምንጮች በቦዮችና በመተላለፊያ ዋሻዎች አማካኝነት ንጹሕ ውኃ ታገኝ ነበር።

ኢየሩሳሌምና የሄሮድስ ቤተ መቅደስ

ከሄሮድስ የግንባታ ፕሮጀክቶች መካከል ትልቁ በኢየሩሳሌም የሠራው ቤተ መቅደስ ነበር። በዚያ ቦታ ላይ ቀደም ሲል ንጉሥ ሰለሞን፣ አባቱ ዳዊት በአምላክ መንፈስ መሪነት የተቀበለውን ንድፍ ተከትሎ የሠራው ቤተ መቅደስ ይገኝ ነበር። (1 ነገሥት 6:1፤ 1 ዜና 28:11, 12) ይህ ቤተ መቅደስ ከተሠራ ከ420 ዓመታት በኋላ በባቢሎናውያን የጠፋ ሲሆን ከ90 ዓመታት በኋላ ደግሞ የይሁዳ ገዢ የነበረው ዘሩባቤል በቦታው አነስ ያለ ቤተ መቅደስ ገንብቶ ነበር።

ሄሮድስ በዚያው ስፍራ ላይ የሠራውን ቤተ መቅደስ አስመልክቶ ጆሴፈስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “[ቤተ መቅደሱ] በሁሉም አቅጣጫ ከፍተኛ መጠን ባለው ወርቅ ከመለበጡ የተነሳ ፀሐይ እንደወጣች እሳት የመሰለ ጨረር መፈንጠቅ ይጀምራል፤ በመሆኑም ቤተ መቅደሱን ለማየት የሚሞክሩ ሰዎች ፀሐይን የተመለከቱ ያህል ዓይናቸውን ወዲያውኑ ዘወር ለማድረግ ይገደዱ ነበር። ቤተ መቅደሱን ከርቀት ላየው በበረዶ የተሸፈነ ተራራ ይመስል ነበር፤ ይህ ሊሆን የቻለው በወርቅ ያልተለበጠው የቤተ መቅደሱ ክፍል በጣም ነጭ ስለነበረ ነው።”

በቤተ መቅደሱ ዙሪያ የሚገኘውን ግንብ በመገንባቱ ሥራ በሺህ የሚቆጠሩ ሠራተኞች የተካፈሉ ሲሆን ይህ ግንብ በስተ ምዕራብ በኩል ወደ 500 ሜትር የሚጠጋ ርዝመት ነበረው። ግንቡ የተሠራባቸው ግዙፍ ድንጋዮች ተነባብረው የተቀመጡት ያለ ምንም ሲሚንቶ ነበር። አንዱ ግዙፍ ድንጋይ ወደ 4,000 ኩንታል የሚጠጋ ክብደት የነበረው ሲሆን አንድ ምሁር እንደተናገሩት ይህ ድንጋይ “በጥንት ዘመን ከነበሩት ጥርብ ድንጋዮች የሚተካከለው” አልነበረውም። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በግንባታው መደነቃቸው ምንም አያስገርምም! (ማርቆስ 13:1) ከሩቅ ሲታይ እንደ መድረክ ከፍ ብሎ የሚታየው ይህ ቦታ የቤተ መቅደሱ ጉብታ ተብሎ ይጠራል። ይህ መድረክ በጥንት ዘመን ከተሠሩት ሰው ሠራሽ መድረኮች ሁሉ በስፋቱ ተወዳዳሪ የለውም። የቦታው ስፋት ከ18 የሚበልጡ የእግር ኳስ መጫወቻ ሜዳዎች ሊወጣው ይችላል!

ሄሮድስ በኢየሩሳሌም ውስጥ ሌሎች ግንባታዎችንም አከናውኗል። ከእነዚህም መካከል እሱ ከገነባው ቤተ መቅደስ ቀጥሎ የተሠራው የአንቶኒያ ግንብ ይገኝበታል። በተጨማሪም ሄሮድስ አንድ ቤተ መንግሥትና በከተማዋ መግቢያ ላይ የተሠሩ ሦስት ለየት ያሉ ባለ ፎቅ ማማዎችን አስገንብቷል።

ሰማርያና ኢያሪኮ

ሄሮድስ ሰማርያ የምትባለውን የጥንት ከተማ ከአውግስጦስ ቄሳር በስጦታ ተቀብሎ ስሟን በመቀየር ሴባስቴ ብሏታል። ሄሮድስ በየተወሰነ ርቀት የተደረደሩ ዓምዶች እንደነበሩት የሚገመተውን አንድ ስታዲየም ጨምሮ የተለያዩ ሕንፃዎች በመሥራት ይህችን ከተማ አሳምሯታል። በተጨማሪም በሥዕል ያሸበረቁ ግድግዳዎች ያሏቸውን በርካታ ትላልቅ ሕንፃዎች ሠርቷል።

ኢያሪኮ በዮርዳኖስ ሸለቆ ውስጥ ከባሕር ወለል በታች 250 ሜትር ዝቅ ብላ የምትገኝ ከፊል በረሃማ የአየር ንብረት ያላት ከተማ ነበረች። ኢያሪኮ ከ1,000 ሄክታር በሚበልጥ ቦታ ላይ የምትገኝ ሲሆን በገነት አምሳያ የተሠራች ከተማ ትመስል ነበር። ሄሮድስ በዚህች ከተማ ክረምቱን የሚያሳልፍበት ቤተ መንግሥት ገንብቶ ነበር። እያንዳንዳቸው የእንግዳ መቀበያ አዳራሾች፣ መታጠቢያ ቤቶች፣ የአትክልት ስፍራዎችና መዋኛ ገንዳዎች ያሏቸውን ሦስት ቤተ መንግሥቶች በመገጣጠም አንድ በጣም ትልቅ መኖሪያ ሠርቷል። ኢያሪኮን የክረምት ወቅት ማሳለፊያው አድርጎ መምረጡ የሚያስደንቅ አይደለም!

ድንቅ የቤተ መንግሥት ምሽጎች

ሄሮድስ ክረምቱን የሚያሳልፍበት ሌላም መኖሪያ ነበረው። ከሙት ባሕር 400 ሜትር ከፍ ብሎ በሚገኝ ዓለታማ የሆነ አምባ ላይ ማሳዳ ተብሎ የሚጠራ ምሽግ አሠርቶ ነበር። በዚያ ቦታ ላይ ሰገነትና መታጠቢያ ገንዳዎች ያሉት በጣም የሚያምር ባለ ሦስት እርከን ቤተ መንግሥት ገነባ፤ በተጨማሪም በግድግዳዎቹ ውስጥ የሮማውያን ዓይነት ማሞቂያ ቧንቧዎች የተገጠሙለት መታጠቢያ ቤት እንዲሁም ውኃ መልቀቂያ መጸዳጃ ቤት ያለው ሌላ ቤተ መንግሥት አሠርቶ ነበር!

በዚያ በረሃማ አካባቢ ሄሮድስ ለመዝናናትና ጤንነቱን ለማደስ የሚያገለግል ማረፊያ አሠርቶ ነበር። ይህ ቦታ በጠቅላላው 40,000,000 ሊትር የመያዝ አቅም ያላቸው በርካታ የውኃ ማጠራቀሚያ ገንዳዎች ነበሩት። ምሽጉ ውስጥ የዝናብ ውኃን ለማቆር የሚያስችል ዘዴ ጥቅም ላይ ይውል ስለነበር ሰብል ለማብቀል፣ ለመዋኛና ለመታጠቢያ የሚሆን በቂ ውኃ ይገኝ ነበር።

ሄሮድስ ድንቅ የምሕንድስና ጥበብ እንደነበረው የሚያሳየው ሌላው የግንባታ ሥራ ደግሞ ሄሮዲየም የሚባለው የቤተ መንግሥት ምሽግ ነው፤ ይህ ቤተ መንግሥት የሚገኘው ከቤተ ልሔም በስተ ደቡብ ምሥራቅ አምስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ባለ አንድ ተራራ ላይ ነበር። ቤተ መንግሥቱ ሁለት ዋና ዋና ክፍሎች የነበሩት ሲሆን እነሱም ላይኛው ሄሮዲየም እና ታችኛው ሄሮዲየም ተብለው ይጠራሉ። የላይኛው ክፍል፣ በምሥራቅ በኩል የሚገኘውን ባለ አምስት ፎቅ ማማ የነበረውን ግርማ ሞገስ ያለው የቤተ መንግሥት ምሽግ ይጨምር ነበር፤ በዚያን ወቅት ሰማይ ጠቀስ ሊባል የሚችለው ይህ ማማ በአሁኑ ጊዜ ፈራርሶ ይታያል። ከዚህም በላይ ፍርስራሹ የቀረው የሄሮድስ መቃብር በላይኛው ሄሮዲየም ዳገት ላይ የተገኘ ሲሆን ይህም ጆሴፈስ፣ የሄሮድስ የቀብር ሥነ ሥርዓት በዚህ ስፍራ ስለመፈጸሙ በአንደኛው መቶ ዘመን የጻፈው ሐሳብ እውነት መሆኑን እንዳረጋገጠ ከሁለት ዓመት በፊት ዓለም አቀፍ የዜና ወኪሎች ዘግበዋል።

በአንድ ወቅት በታችኛው ሄሮዲየም ተጨማሪ የቤተ መንግሥት ክፍሎችና ቢሮዎች ተሠርተው ነበር። ከታችኛው ሄሮዲየም ውስጥ የተመልካችን ትኩረት የሚስበው ውብ በሆነ መንገድ በረድፍ የተሠሩ ዓምዶች ያሉትና የሮማውያንን አሠራር የተከተለው የአትክልት ስፍራ ነበር። በዚህ የአትክልት ስፍራ መሃሉ ላይ የሚያምር ደሴት ያለው አንድ ሰፊ መዋኛ ነበር። የመዋኛ ገንዳው ስፋት በዛሬው ጊዜ ያሉ የኦሎምፒክ መዋኛ ገንዳዎችን እጥፍ ያክላል። ይህ ገንዳ በዋነኝነት የሚያገለግለው ውኃ ለማጠራቀም ሲሆን ለመዋኛና ለጀልባ ቀዘፋም ያገለግል ነበር። ውኃው በቦይ የሚመጣው 5 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከሚገኝ ምንጭ ነበር።

ከጥቂት ዓመታት በፊት አንድ ጎብኚ በዚያ አካባቢ ስለሚገኘው የመሬት አቀማመጥ እንዲህ ብሏል፦ “በስተ ምሥራቅ እስከ ሙት ባሕር ድረስ ማየት እንችላለን። ከፊት ለፊታችን ደግሞ ዳዊት ከአሳዳጁ ከሳኦል ሸሽቶ ያመለጠበት የይሁዳ ምድረ በዳ ይታየናል። የአካባቢውን ወጣ ገባነት ስናይ ዳዊት ከሳኦል ሊያመልጥ የቻለው ለምን እንደሆነ ተረድተናል፤ ዳዊት በተለይ ከወጣትነቱ ጀምሮ አካባቢውን በደንብ ሳያውቀው አይቀርም። በተጨማሪም ዳዊት እረኛ በነበረበት ጊዜ ዕፁብ ድንቅ የሆነውን የአካባቢውን ውበት ለማየት አሁን እኛ ወዳለንበት ወደዚህ አቀበት አዘውትሮ ይወጣ እንደነበረ አሰብን።”

ሄሮድስ ስላከናወናቸው የግንባታ ሥራዎች የሚናገሩ በርካታ መጻሕፍት ተጽፈዋል። ሄሮድስ እንዲህ ዓይነቱን ሰፊ የግንባታ ሥራ ያካሄደው ለምን እንደሆነ ብዙ ግምታዊ አስተያየቶች ይሰጣሉ። አንዳንዶች ሄሮድስ ይህን ያደረገው ዝና ለማትረፍ ወይም ከፖለቲካ አንጻር ተወዳጅነት ለማግኘት እንደሆነ ይናገራሉ። የተነሳበት ዓላማ ምንም ይሁን ምን፣ ሄሮድስ ያከናወናቸውን የግንባታ ሥራዎች ያስቃኘን ይህ አጭር ዘገባ ታላቁ ሄሮድስ ጨካኝና አምባገነን መሪ ቢሆንም በግንባታው ዘርፍ የተዋጣለት ሰው እንደነበረ ያረጋግጥልናል።

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቂሳርያ

አንድ ሰዓሊ እንዳስቀመጠው

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በኢየሩሳሌም የሚገኝ ቤተ መንግሥት ሞዴል

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሄሮድስ ቤተ መቅደስ ሞዴል

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ማሳዳ

የባለ ሦስቱ እርከን ቤተ መንግሥት ፍርስራሽ

[ምንጭ]

Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሄሮዲየም አንድ ሰዓሊ እንዳስቀመጠው

[በገጽ 25 ላይ የሚገኙ የሥዕል ምንጮች]

ቂሳርያ፦ Hiram Henriquez/National Geographic Stock; ቤተ መንግሥት፦ Courtesy of Israel Museum, Jerusalem, and Todd Bolen/Bible Places.com