በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጠላትን መውደድ ይቻላል?

ጠላትን መውደድ ይቻላል?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ጠላትን መውደድ ይቻላል?

ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ብሏል፦ “እኔ ግን እላችኋለሁ፣ ለጠላቶቻችሁ ፍቅር ማሳየታችሁን እንዲሁም ስደት ለሚያደርሱባችሁ መጸለያችሁን ቀጥሉ፤ ይህን ብታደርጉ በሰማያት ላለው አባታችሁ ልጆች ትሆናላችሁ። ምክንያቱም እሱ በክፉና በጥሩ ሰዎች ላይ ፀሐዩን ያወጣል፤ ጻድቅ በሆኑና ጻድቅ ባልሆኑ ሰዎች ላይም ዝናብ ያዘንባል።”—ማቴዎስ 5:44, 45

ይማኖት፣ በሰዎች መካከል ፍቅርና ሰላም እንዲኖር የሚያደርግ እንደሆነ ይሰማሃል? ወይስ ጥላቻና ዓመፅ የሚያስፋፋ እንደሆነ አድርገህ ታስባለህ? በዛሬው ጊዜ ሃይማኖት ከፖለቲካ፣ ከዘርና ከብሔረተኝነት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ ስለሚገባ ብዙዎች የጥላቻና የዓመፅ መንስኤ እንደሆነ ይሰማቸዋል። ሆኖም ኢየሱስ የተናገረው ሐሳብ እንደሚያሳየው እውነተኛ ‘የአምላክ ልጆች’ አምላክን በመምሰል ለጠላቶቻቸውም እንኳ ሳይቀር ፍቅር ያሳያሉ።

አንድ ሌላ የአምላክ አገልጋይም “ጠላትህ ቢራብ አብላው፤ ቢጠማ የሚጠጣ ነገር ስጠው፤ . . . በክፉ አትሸነፍ፤ ከዚህ ይልቅ ምንጊዜም ክፉውን በመልካም አሸንፍ” በማለት ተናግሯል። (ሮም 12:20, 21) ይሁን እንጂ በዚህ በተከፋፈለ ዓለም ውስጥ እንዲህ ዓይነት ፍቅር ማሳየት በእርግጥ ይቻላል? የይሖዋ ምሥክሮች ለዚህ ጥያቄ ያለምንም ማወላወል ‘አዎን!’ የሚል መልስ ይሰጣሉ። እስቲ ኢየሱስና የጥንት ተከታዮቹ የተዉልንን ምሳሌ እንመልከት።

ለጠላቶቻቸው ፍቅር ነበራቸው

ኢየሱስ ስለ አምላክ እውነቱን ያስተማረ ሲሆን ብዙዎችም በደስታ አዳምጠውታል። ሌሎች ሰዎች ግን የተቃወሙት ሲሆን ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ ይህን ያደረጉት ባለማወቅ ነበር። (ዮሐንስ 7:12, 13፤ የሐዋርያት ሥራ 2:36-38፤ 3:15, 17) ያም ቢሆን ኢየሱስ ተቃዋሚዎቹን ጨምሮ ለሁሉም ሰው ሕይወት አድን የሆነውን መልእክት ከማካፈል ወደኋላ አላለም። (ማርቆስ 12:13-34) ለምን? አንዳንዶች ሐሳባቸውን ለውጠው የእሱን መሲሕነት ሊቀበሉና በአምላክ ቃል ውስጥ ከሚገኙት መንፈሳዊ እውነቶች ጋር ተስማምተው ሊኖሩ እንደሚችሉ ያውቅ ስለነበረ ነው።—ዮሐንስ 7:1, 37-46፤ 17:17

ኢየሱስ የጦር መሣሪያ በታጠቁ ተቃዋሚዎቹ ፍትሕ በጎደለው ሁኔታ በተያዘበት ሌሊትም እንኳ ለጠላቶቹ ፍቅር አሳይቷል። እንዲያውም እሱን ሊይዙት ከመጡት ሰዎች መካከል አንዱን ሐዋርያው ጴጥሮስ በሰይፍ በመታው ወቅት ኢየሱስ ሰውየውን ፈውሶት ነበር። በዚያ ወቅት ኢየሱስ በዛሬው ጊዜ ያሉ እውነተኛ ተከታዮቹም ጭምር ሊመሩበት የሚገባ አንድ በጣም አስፈላጊ የሆነ መመሪያ ሰጥቷል። “ሰይፍ የሚመዙ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉ” ብሏል። (ማቴዎስ 26:48-52፤ ዮሐንስ 18:10, 11) ጴጥሮስ፣ ወደ 30 የሚጠጉ ዓመታት ካለፉ በኋላ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ ‘ክርስቶስ የእሱን ፈለግ በጥብቅ እንድትከተሉ አርዓያ ትቶላችሁ ለእናንተ መከራ ተቀብሏል። መከራ ሲደርስበት አልዛተም፤ ከዚህ ይልቅ ለአምላክ ራሱን አሳልፎ ሰጠ።’ (1 ጴጥሮስ 2:21, 23) ከዚህ በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው ጴጥሮስ፣ እውነተኛ የክርስቶስ ተከታዮች ፍቅር ማሳየት እንጂ አጸፋ መመለስ እንደሌለባቸው ተምሯል።—ማቴዎስ 5:9

‘የኢየሱስን ፈለግ በጥብቅ የሚከተሉ’ ሁሉ የእሱን ፍቅርና ደግነት የተላበሰ ባሕርይ ያንጸባርቃሉ። ሁለተኛ ጢሞቴዎስ 2:24 “የጌታ ባሪያ ግን ሊጣላ አይገባውም፤ ከዚህ ይልቅ ለሰው ሁሉ ገር [እንዲሁም] . . . ክፉ ነገር ሲደርስበት በትዕግሥት የሚያሳልፍ ሊሆን ይገባዋል” ይላል። አንድ ክርስቲያን እነዚህን ባሕርያት በሕይወቱ ውስጥ ማሳየት አለበት፤ በሌላ አባባል ሰላም የሚፈጥርና እርቅ የሚያወርድ መሆን ይኖርበታል።

ሰላማዊ የሆኑ ‘የክርስቶስ አምባሳደሮች’

ሐዋርያው ጳውሎስ ለእምነት ባልንጀሮቹ “እኛ ክርስቶስን ተክተን የምንሠራ አምባሳደሮች ነን፤ . . . ክርስቶስን ተክተን የምንሠራ እንደመሆናችን መጠን ‘ከአምላክ ጋር ታረቁ’ ብለን እንለምናለን” በማለት ጽፎላቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 5:20) አምባሳደሮች፣ በተመደቡባቸው አገሮች ፖለቲካዊና ወታደራዊ ጉዳዮች ውስጥ እጃቸውን አያስገቡም። ከዚህ ይልቅ ገለልተኛ ሆነው ይኖራሉ። የእነሱ ሥራ የላካቸውን መንግሥት በመወከልና በመደገፍ አገራቸውን ማገልገል ነው።

የክርስቶስ አምባሳደሮችንና ልዑካንን በተመለከተም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ኢየሱስን ንጉሥ አድርገው የሚመለከቱት ከመሆኑም በላይ ምሥራቹን ሰላማዊ በሆነ መንገድ በማወጅ በሰማይ ያለውን የእሱን መንግሥት እንደሚደግፉ ያሳያሉ። (ማቴዎስ 24:14፤ ዮሐንስ 18:36) በመሆኑም ጳውሎስ በዘመኑ ለነበሩት ክርስቲያኖች እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “ምንም እንኳ በሥጋ የምንኖር ቢሆንም የምንዋጋው በሥጋዊ መንገድ አይደለም። ምክንያቱም የምንዋጋባቸው የጦር መሣሪያዎቻችን ሥጋዊ አይደሉም።” አክሎም የጦር መሣሪያዎቹ ‘የአምላክን እውቀት የሚጻረሩ የመከራከሪያ ነጥቦችንና ይህን እውቀት ለማገድ የሚገነባውን ማንኛውንም ከፍ ያለ ነገር ለማፍረስ መለኮታዊ ኃይል ያላቸው እንደሆኑ’ ጽፎላቸዋል።—2 ቆሮንቶስ 10:3-5፤ ኤፌሶን 6:13-20

ጳውሎስ ከላይ ያለውን በጻፈበት ወቅት ክርስቲያኖች በብዙ አገሮች ስደት እየደረሰባቸው ነበር። እርግጥ ነው፣ እነዚህ ክርስቲያኖች አጸፋውን መመለስ ይችሉ ነበር። ይሁንና እንዲህ ከማድረግ ይልቅ ጠላቶቻቸውን መውደዳቸውንና ሰዎች ከአምላክ ጋር እንዲታረቁ የሚያሳስበውን መልእክት መስማት ለሚፈልጉ ሁሉ ማካፈላቸውን ቀጥለው ነበር። ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ሪሊጅን ኤንድ ዋር እንደገለጸው “የቀድሞዎቹ የኢየሱስ ተከታዮች በጦርነትና በወታደራዊ አገልግሎት ለመካፈል ፈቃደኞች አልነበሩም።” ምክንያቱም እነዚህ ተግባራት “ኢየሱስ ካስተማረው የፍቅር ሕግና ጠላታቸውን እንዲወዱ ከሰጠው ትእዛዝ ጋር የማይስማሙ እንደሆኑ” ተገንዝበው ነበር። *

እንደ ጥንቶቹ ክርስቲያኖች ሁሉ የይሖዋ ምሥክሮችም ኢየሱስን ንጉሣቸው አድርገው ይቀበሉታል። በተጨማሪም ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ እንደሆነ ያምናሉ፤ ይህ መንግሥት በቅርቡ በምድር ላይ ዘላቂ ሰላምና ደኅንነት የሚያመጣ በሰማይ የተቋቋመ መስተዳድር ነው። (ዳንኤል 2:44፤ ማቴዎስ 6:9, 10) የይሖዋ ምሥክሮች እንደ አምባሳደሮችና ልዑካን የዚህን መንግሥት ክብር ያውጃሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ግብር በመክፈልና ከአምላክ ሕግ ጋር የማይጋጩ እስከሆኑ ድረስ ለሚኖሩባቸው አገሮች ሕጎች በመታዘዝ ጥሩ ዜጎች ለመሆን ጥረት ያደርጋሉ።—የሐዋርያት ሥራ 5:29፤ ሮም 13:1, 7

የሚያሳዝነው ግን እንደ ጥንቶቹ ክርስቲያኖች ሁሉ የይሖዋ ምሥክሮችም አንዳንድ ጊዜ ሰዎች በተሳሳተ መንገድ ይረዷቸዋል፤ የሐሰት ወሬ ያወሩባቸዋል፤ እንዲሁም ስደት ያደርሱባቸዋል። ያም ሆኖ ፈጽሞ አጸፋ አይመልሱም። ከዚህ ይልቅ አንዳንዶቹ ተቃዋሚዎች ‘ከአምላክ ጋር ታርቀው’ ወደፊት ለዘላለም የመኖር ተስፋ እንደሚኖራቸው በማሰብ “ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር” ይጥራሉ። *ሮም 12:18፤ ዮሐንስ 17:3

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.13 ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ሪሊጅን ኤንድ ዋር እንዲህ ይላል፦ “[ከ306-337 ዓ.ም. የሮም ንጉሠ ነገሥት ከነበረው] ከቆስጠንጢኖስ በፊት የነበሩት ክርስቲያን ጸሐፊዎች በሙሉ በጦርነት በመካፈል ሰው መግደልን ያወግዙ ነበር።” ይሁን እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አስቀድሞ የተነገረው ክህደት ሲስፋፋ በዚህ ረገድ የነበረው አመለካከት ተለወጠ።—የሐዋርያት ሥራ 20:29, 30፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:1

^ አን.15 በአንደኛው መቶ ዘመን እንደነበሩት ክርስቲያኖች ሁሉ የይሖዋ ምሥክሮችም አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ሃይማኖታዊ ነፃነታቸውን በሕግ ያስከብራሉ።—የሐዋርያት ሥራ 25:11፤ ፊልጵስዩስ 1:7

ይህን አስተውለኸዋል?

▪ ክርስቲያኖች ለጠላቶቻቸው ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል?—ማቴዎስ 5:43-45፤ ሮም 12:20, 21

▪ ኢየሱስ ስደት ሲደርስበት ምላሽ የሰጠው እንዴት ነበር?—1 ጴጥሮስ 2:21, 23

▪ የጥንቶቹ ክርስቲያኖች በጦርነት የማይካፈሉት ለምን ነበር?—2 ቆሮንቶስ 5:20፤ 10:3-5