በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ቀላልና ሚዛናዊ ሕይወት መምራት

ቀላልና ሚዛናዊ ሕይወት መምራት

ቀላልና ሚዛናዊ ሕይወት መምራት

ላልና ሚዛናዊ ሕይወት መምራት በእርግጥም የሚክስ ነው። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለ ሕይወት ለመምራት ምን ማድረግ ያስፈልጋል? በመጀመሪያ ቅድሚያ ስለምትሰጣቸው ነገሮች ማሰብ ይኖርብህ ይሆናል። ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?

‘እስካሁን ምን ማከናወን ችያለሁ? ምን ማድረግስ ይቀረኛል?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። በጣም አስፈላጊ የምትላቸውን ግቦችህን ከዚህ በታች አስፍር፦

1. ․․․․․

2. ․․․․․

3. ․․․․․

በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች የወደፊት ሕይወታቸውን ያላገናዘበና በቁሳዊ ነገሮች ላይ ያተኮረ ሕይወት ይመራሉ። እነዚህ ሰዎች “ነገ ስለምንሞት እንብላ፣ እንጠጣ” የሚሉ ያህል ነው። (1 ቆሮንቶስ 15:32) በሕይወታቸው ውስጥ የፈለጉትን ለመግዛት የሚያስችላቸው ብዙ ገንዘብ ለማግኘት ከመሥራት የበለጠ ነገር እንደሌለ ይሰማቸዋል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ያለው አስተሳሰብ ትክክል እንዳልሆነ ይገልጻል።

ኢየሱስ ከተናገራቸው ምሳሌዎች በአንዱ ላይ ብዙ ሀብት ካከማቸ በኋላ ሳይጠቀምበት ስለሞተ ሰው ተናግሯል። “ለራሱ ሀብት የሚያከማች በአምላክ ዘንድ ግን ሀብታም ያልሆነ ሰው መጨረሻው ይኸው ነው።” (ሉቃስ 12:16-21) ሰውየው የሚያስፈልገውን ለማሟላት ጠንክሮ መሥራቱ ስህተት ነበር? በፍጹም አልነበረም። ችግሩ ሙሉ ትኩረቱ ያረፈው ቁሳዊ ነገሮች ላይ መሆኑ ነበር። እቅድ ሲያወጣ የአምላክን አመለካከት ግምት ውስጥ አላስገባም። በዚህም ምክንያት ያን ያህል የደከመለት ሀብትና ንብረት በሙሉ ዘላቂ ጥቅም ሊያስገኝለት አልቻለም። እንዴት የሚያሳዝን ነው!—መክብብ 2:17-21፤ ማቴዎስ 16:26

በተቃራኒው ግን ኢየሱስ ዘላለማዊ ሽልማት የሚያስገኝ ሥራ እንድንሠራ ጋብዞናል። “ለሚጠፋ ምግብ ሳይሆን . . . ዘላቂ ለሆነውና የዘላለም ሕይወት ለሚያስገኘው ምግብ ሥሩ” የሚል ማሳሰቢያ ሰጥቶናል። (ዮሐንስ 6:27) ይህን ከማለቱ ቀደም ሲል “አምላክ ዓለምን እጅግ ከመውደዱ የተነሳ በልጁ እንደሚያምን በተግባር የሚያሳይ ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ ሲል አንድያ ልጁን ሰጥቷል” ብሎ ነበር። (ዮሐንስ 3:16) እንዴት ያለ አስደናቂ ሽልማት ነው!

መጨነቅህን ማቆም የምትችለው እንዴት ነው?

ለቁሳዊ ነገሮች መጨነቅ የሰው ልጅ ባሕርይ እንደሆነ ኢየሱስ ተናግሯል። በመሆኑም ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ በማለት አሳስቧቸዋል፦ “ስለምትበሉትና ስለምትጠጡት ነገር ከልክ በላይ ማሰብ አቁሙ፤ እንዲሁም መጨነቃችሁን ተዉ፤ እነዚህ ነገሮች ሁሉ በዓለም ያሉ ሰዎች አጥብቀው የሚፈልጓቸው ናቸው፤ ይሁንና አባታችሁ እነዚህ ነገሮች እንደሚያስፈልጓችሁ ያውቃል። ስለሆነም ዘወትር መንግሥቱን ፈልጉ፤ እነዚህም ነገሮች ይሰጧችኋል።”—ሉቃስ 12:29-31

እነዚህ የሚያረጋጉ ቃላት በርካታ ክርስቲያኖች ኑሯቸውን ቀላል እንዲያደርጉ አነሳስተዋቸዋል። በማሌዥያ የምትኖረው ጁልየት እንዲህ ትላለች፦ “ሥራዬ በጣም ስለሚያደክመኝ ብስጩ ያደርገኝ ነበር። በመሆኑም እኔና ባለቤቴ ኑሯችንን ቀላል እንድናደርግ ይሖዋ እንዲረዳን ጸለይን። ይሖዋም አፋጣኝ መልስ ሰጠን። በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ፣ አካል ጉዳተኛ የሆኑ ልጆችን በሳምንት ለተወሰኑ ሰዓታት የማስተማር ሥራ አገኘሁ።” በአውስትራሊያ የቤት ጣሪያ ሥራ ተቋራጭ የነበረው ስቲቭ ከቤተሰቡ ጋር በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ተጨማሪ ጊዜ ለማሳለፍ ሲል በሥራው ላይ ማስተካከያ አደረገ። ባለቤቱ ሞሪን እንዲህ ብላለች፦ “አሁን በጣም ደስተኛ ሆኗል፤ እኛም ደስተኞች ሆነናል። [ይህን ለውጥ] ልጆቹ ወደውታል! እኔም ወድጄዋለሁ! ኑሮ ቀላል ሲሆን መላው ቤተሰብ ደስተኛ ይሆናል።”

ይሁን እንጂ ከሥራህ ተፈናቅለህ ከሆነና መኖሪያ ቤትህንም ልታጣ ከሆነ የኢየሱስን ምክር መከተል ጠንካራ እምነት ይጠይቃል። ቢሆንም ለመንፈሳዊ ነገሮች ቅድሚያ ከሰጠህና በአምላክ ከታመንክ አንተም ቀላልና ሚዛናዊ የሆነ ሕይወት መምራት ትችላለህ። እንዲህ ማድረግህ “እውነተኛ የሆነውን ሕይወት” ይኸውም አምላክ በሚያመጣው ጽድቅ የሰፈነበት አዲስ ዓለም ውስጥ የዘላለም ሕይወት እንድታገኝ ይረዳሃል፤ በዚህ አዲስ ዓለም ውስጥ ማንኛውም ሥራ አስደሳችና ፍሬያማ ይሆናል።—1 ጢሞቴዎስ 6:17-19፤ ኢሳይያስ 65:21-23

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተስፋ ስለተሰጠበት ስለዚህ ‘እውነተኛ ሕይወት’ ለመማር ትፈልጋለህ? ከሆነ በአቅራቢያህ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮችን ማነጋገር ወይም በዚህ መጽሔት ገጽ 5 ላይ ከተዘረዘሩት አድራሻዎች አመቺ ወደሆነው መጻፍ ትችላለህ።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

አምላክ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ ማንኛውም ሥራ አስደሳችና ፍሬያማ ይሆናል

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ከቤት ውጭ ሥራ ልትፈጥር ትችላለህ?

ከሥራ የመፈናቀል ችግር በሚያጋጥምበት ጊዜ በአንዳንድ የዓለም ክፍሎች ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ ሐሳቦች፦

ቤት መጠበቅ (ሰዎች ለሥራ ወይም ለእረፍት ወደ ሌላ አካባቢ ሲሄዱ ቤታቸው እንዲጠበቅላቸው በሚፈልጉበት ጊዜ)

ጽዳት፦ ሱቆችን፤ ቢሮዎችን፤ ቤቶችና አፓርታማዎች ከግንባታ፣ ከእሳት አደጋ፣ ነዋሪዎች ከለቀቁ በኋላ መጽዳት በሚያስፈልጋቸው ጊዜ፤ የቤት ውስጥ ሥራ (የሌሎች ሰዎችን ቤት)፤ መስኮቶችን ማጽዳት (የንግድ ድርጅቶችንና መኖሪያዎችን)

ጥገና፦ ብስክሌቶችን፤ የተለያዩ መሣሪያዎችን (ስለ ጥገና በቀላሉ የሚያስተምሩ መጻሕፍትን በቤተ መጻሕፍት ውስጥ ማግኘት ይቻላል)

የእጅ ሙያዎች፦ ቧንቧ መሥራት፤ ኤሌትሪክ መዘርጋት፤ ቁም ሣጥኖችን፣ በሮችን፣ በረንዳዎችን መሥራት፤ ቀለም መቀባት፤ አጥር ማጠር፤ ጣሪያ መጠገን

የግብርና ሥራ፦ ዘር መዝራት፣ ፍራፍሬ መልቀም፣ ምርት መሰብሰብ

ቤት ማሳመርና አትክልት መንከባከብ፦ በመሥሪያ ቤቶች፣ በእንግዳ መቆያ ቦታዎች፣ በገበያ ማዕከሎች

ሕንፃን መጠበቅና ንጽሕናውን መከታተል፦ (አንዳንድ ጊዜ ግለሰቡ በነፃ እዚያው መኖር ይችላል)

ምንጣፍና የወለል ሳንቃ ማንጠፍ፣ ማጽዳት

ጋዜጣ ማዞር (አዋቂዎችና ልጆች ሊሠሩት ይችላሉ) እንዲሁም ማስታወቂያዎችን ማሰራጨትና የሒሳብ ማስከፈያ ደረሰኞችን ማድረስ

ዕቃ ማጓጓዝ፣ ዕቃ ማስቀመጫ ቦታ ማከራየት

ግቢ ማስዋብ፣ ዛፎችን መከርከም፣ ሣር ማጨድ፣ እንጨት መፍለጥ

የትምህርት ቤት አውቶቡስ መንዳት፣ ተማሪዎችን ማመላለስ

ፎቶግራፍ ማንሳት (የግለሰቦችን እንዲሁም በግብዣዎች ላይ)

ዓሣ አጥማጆች ዓሣዎችን ለማጥመድ የሚጠቀሙበትን ምግብ መሸጥ

በሙያ ያለ ገንዘብ መረዳዳት፦ የመኪና ጥገና ሙያ እና የኤሌክትሪክ ሥራ ሙያ እንዲሁም የልብስ ስፌትና የቧንቧ ሥራ ሙያ ያላቸው ሰዎች ገንዘብ መክፈል ሳይኖርባቸው በሙያቸው አንዳቸው ሌላውን መርዳት

ለተጨማሪ መረጃ የመጋቢት 8, 1996 ንቁ! (እንግሊዝኛ) (ከጥር-መጋቢት 1997 ንቁ!) ከገጽ 3-11ን ተመልከት።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

በቤት ውስጥ ሥራ ለመፍጠር የሚያስችሉ አማራጮች

በአካባቢህ ምን እንደሚያስፈልግ አስተውል። ጎረቤቶችህን ጠይቅ። አዳዲስ ሥራዎችን ፍጠር።

ሕፃናትን መጠበቅና መንከባከብ

ግቢ ውስጥ አትክልቶችን ወይም አበባዎችን አሳድጎ መሸጥ፤ ጭማቂዎች መሸጥ

ልብስ መስፋት፣ ማስተካከልና መጠገን

ቤት ውስጥ ጥሬ ዕቃዎችን ሠርቶ ለአምራቾች ማስረከብ

ዳቦ መጋገር፣ ምግብና የባልትና ውጤቶችን ማዘጋጀት

የአልጋ ልብስ፣ ጥልፍ፣ ሹራብ መሥራት፤ በገመድ ዘንቢሎችን፣ ቦርሳዎችን፣ የግድግዳ ጌጦችንና ሌሎች ነገሮችን መሥራት፤ ሸክላ ሥራና ሌሎች የዕደ ጥበብ ሙያዎች

ሶፋና ወንበር ማደስ

የሒሳብ መዝገብ መያዝ፣ ታይፕ መጻፍ፣ የቤት ውስጥ የኮምፒውተር አገልግሎት መስጠት

የስልክ መልእክት መቀበል

ፀጉር ሥራ

ቤት ማከራየት

ማስታወቂያ ለሚሠሩ ሰዎች ፖስታው ላይ አድራሻ መጻፍና አሽጎ መላክ

መኪና ማጠብና በሰም መወልወል (ደንበኛው መኪናውን ቤትህ ድረስ ያመጣል)

ውሻና ድመት ማጠብና ማንሸራሸር

ቁልፍ መጠገንና መቅረጽ (ቤት ውስጥ መሥራት ይቻላል)

ማስታወሻ፦ ከላይ ከተጠቀሱት ሥራዎች መካከል የአብዛኞቹን ማስታወቂያ በገበያ አዳራሾች ውስጥ በማስታወቂያ ሰሌዳው ላይ በነፃ ወይም በአነስተኛ ክፍያ መለጠፍ ይቻል ይሆናል።