በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኦርኪድ ማሳደግ ትዕግሥት የሚፈታተን ቢሆንም ይክሳል

ኦርኪድ ማሳደግ ትዕግሥት የሚፈታተን ቢሆንም ይክሳል

ኦርኪድ ማሳደግ ትዕግሥት የሚፈታተን ቢሆንም ይክሳል

ርኪድ ማሳደግ ሱስ ሊሆን ይችላል። አንዳንድ የኦርኪድ አድናቂዎች የሚወዷቸውን ዝርያዎች የላቲን ስም በትክክል ለመጥራት ሲሉ ብቻ ለበርካታ ሰዓታት ስማቸውን ያጠናሉ። ኦርኪዶች የብዙ ሰዎችን ቀልብ ሊስቡ የቻሉት ለምንድን ነው?

በጣም ብዙ የኦርኪድ ዓይነቶች አሉ። ወደ 25,000 የሚጠጉ ወፍ ዘራሽ የኦርኪድ ዝርያዎች የተገኙ ሲሆን የታወቁ ድርጅቶች ከ100,000 ለሚበልጡ ሰው ሠራሽ ዲቃላ ዝርያዎች እውቅና ሰጥተዋል! “ሰው ሠራሽ ዲቃላ” የሚለው ስያሜ የዕፅዋት ሳይንቲስቶች ከአፈር፣ ከውኃና ከአየር አዲስ ሕያው ፍጡር እንዳገኙ የሚያመለክት አይደለም። ከዚህ ይልቅ በሰው ሠራሽ ዘዴ አማካኝነት ዘር በማሠራጨት የተገኘ ዝርያ መሆኑን የሚያመለክት ነው።

በተፈጥሮ ያደጉትም ሆኑ በሰዎች ሠራሽ ዘዴ የተገኙት የኦርኪድ አበባዎች መጠናቸው የተለያየ ነው። በአጉሊ መነጽር ካልሆነ በስተቀር በደንብ ሊታዩ የማይችሉ ኦርኪዶች ሲኖሩ ሌሎቹ ደግሞ መስኮት አጠገብ ተቀምጠው ከርቀት በግልጽ ሊታዩ የሚችሉ ናቸው። በኢንዶኔዥያ ደኖች ውስጥ የሚበቅል አንድ የኦርኪድ ዓይነት ከ500 ኪሎ ግራም በላይ ክብደት አለው!

ኦርኪዶች እንደ ቀስተ ደመና የተለያየ ቀለም ያላቸው ከመሆኑም በላይ ቅርጻቸውም የዚያኑ ያህል የተለያየ ነው። አንዳንዶቹ ከንብ፣ ከእሳት እራትና ከአእዋፍ ጋር በጣም ይመሳሰላሉ፤ ሌሎቹ ደግሞ ከምንም ነገር ጋር የማይመሳሰል ልዩ የሆነ ቅርጽ አላቸው። በተለይ የኦርኪድ አዳቃዮችን ቀልብ የሚስቡት እንዲህ ዓይነቶቹ ናቸው። ለብዙ ዓመታት እነዚህ የሚያማምሩ አበቦች የሚገኙት በጣም ሀብታም በሆኑ ሰዎች እጅ ብቻ ነበር፤ በአሁኑ ጊዜ ግን እምብዛም ሀብታም ባልሆኑ ሰዎች ቤት ጭምር ይገኛሉ። በዛሬው ጊዜ ለብዙ ሰዎች የደስታ ምንጭ የሆኑት እነዚህ የሚያማምሩ አበቦች እንዲህ በብዛት ሊኖሩ የቻሉት እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

ሰዎች ኦርኪዶችን ለማሳደግ የነበራቸው ጉጉት

ሰዎች ከበርካታ ምዕተ ዓመታት በፊት ጀምሮ ኦርኪድን ሲያደንቁ የኖሩ ቢሆንም አብቃዮች እነዚህን አበቦች ማራባት የሚቻልባቸውን ውጤታማ መንገዶች ያወቁት በቅርቡ ነው። የመጀመሪያው ሰው ሠራሽ የኦርኪድ ዲቃላ አበባ ያበበው በ1856 ነበር። እነዚህን የሚያማምሩና ከፍተኛ እንክብካቤ የሚፈልጉ አበቦች ማሳደግ አስደሳች ቢሆንም የሚጠይቀው ድካም ግን ከዚያ የበለጠ ነው።

የኦርኪድ ዘሮች በጣም ትናንሽ ሲሆኑ አንዳንዶቹ አቧራ የሚያህሉ ናቸው። ለእነዚህ ጥቃቅን ዘሮች የሚደረገው አያያዝ ቀድሞም ሆነ ዛሬ በጣም ተፈታታኝ ነው፤ ሆኖም ይበልጥ አስቸጋሪ የሚሆነው ይህን ዘር እንዲበቅል ማድረግ ነው። ኦርኪድ የሚያበቅሉ ሰዎች ዘሮቹን ለማፍላት የሚያስችሉ ተስማሚ ነገሮችንና ሁኔታዎችን ለማግኘት ለበርካታ አሥርተ ዓመታት ሙከራ ሲያደርጉ ቆይተዋል። በዩናይትድ ስቴትስ የኮርኔል ዩኒቨርሲቲ ሳይንቲስት የነበሩት ዶክተር ሉዊ ክኑድሰን፣ የኦርኪድ ዘሮች ከውኃ፣ ከስኳርና ከአጋር (በባሕር ውስጥ ከሚበቅሉ ዕፅዋት የተገኘ ዝልግልግ ነገር) ተቀላቅሎ በሚዘጋጅ ፈሳሽ ውስጥ ሲደረጉ እንደሚበቅሉና እንደሚያድጉ በ1922 ደረሱበት። ብዙም ሳይቆይ ኦርኪድ የሚያደንቁ ሰዎች አዳዲስ የኦርኪድ ዲቃላ ዝርያዎችን ማራባት ጀመሩ። አሁንም ቢሆን ሰዎች ኦርኪዶችን የማሳደግ ከፍተኛ ጉጉት ያላቸው ሲሆን ይህም ከዚህ በፊት ታይተው የማይታወቁ አዳዲስ ዲቃላ ዝርያዎች በየዓመቱ ብቅ እንዲሉ ምክንያት ሆኗል።

ይሁን እንጂ የሰው ልጆች ኦርኪድን ማሳደግ ከመጀመራቸው በፊት በየዱሩ ይበቅሉ ነበር። ታዲያ ኦርኪዶች በተፈጥሮ ተዳቅለው አዳዲስ ዝርያዎችን የሚያስገኙት እንዴት ነው?

የዱር ኦርኪዶች

ሁለት ወይም ከሁለት የሚበልጡ የቅርብ ዝምድና ያላቸው የኦርኪድ ዝርያዎች በአንድ አካባቢ በሚያብቡበት ጊዜ በተፈጥሮ የተዳቀለ አዲስ ዝርያ የመገኘቱ አጋጣሚ ከፍተኛ ይሆናል። በዱር ውስጥ የአበቦቹን ዘር የሚያሠራጩት ነፍሳት ወይም ሌሎች ፍጥረታት ናቸው። እነዚህ ፍጥረታት የአበባ ማር ለመቅሰም ኦርኪዶቹ ላይ በሚያርፉበት ጊዜ የአንዱ አበባ ዱቄት ሰውነታቸው ላይ ይጣበቅና ሌላ አበባ ላይ ሲያርፉ ዱቄቱ እዚያ ይራገፋል። በዚህ መንገድ ዘር ያገኘው ኦርኪድ ይዳብራል። ከዚያም ይህ ኦርኪድ የዘር ከረጢት ያወጣል።

ከጊዜ በኋላ የዘሩ ከረጢት ይጎመራና ለሁለት ሲከፈል በሺህ አልፎ ተርፎም በሚሊዮን የሚቆጠር ዘር ይበተናል። ከእነዚህ ዘሮች አብዛኞቹ በነፋስ ተጠራርገው ሲወሰዱ አንዳንዶቹ ግን መሬት ላይ ያርፋሉ። እነዚህ ዘሮች ሥር ቢሰዱ እንኳ ገና ብዙ መከራ ያጋጥማቸዋል፤ በመሆኑም አድገው ለማበብ የሚበቁት በጣም ጥቂት ናቸው። ከአንዱ የኦርኪድ ዝርያ ወደሌላው በተወሰደ የአበባ ብናኝ ተዳቅለው የተገኙ ዝርያዎች የተፈጥሮ ዲቃላዎች ይባላሉ። ይሁንና ሰው ሠራሽ ዲቃላዎች የሚገኙት እንዴት ነው?

በሰው ሠራሽ ዘዴ ማዳቀል

አንድ የተዳቀለ የኦርኪድ ዝርያ ከሁለቱም ወላጆቹ የተለያዩ ባሕርያትን ይወርሳል። በመሆኑም አንድ ኦርኪድ የሚያበቅል ሰው ምን ዓይነት አበባ ማግኘት እንደሚፈልግ አስቀድሞ ይወስናል። አንድ የሚፈልገው ዓይነት ቀለም፣ መስመር ወይም ነጠብጣብ ይኖር ይሆናል። እነዚህን የሚፈልጋቸውን ገጽታዎች ትላልቅ ወይም ትናንሽ አበባዎች ላይ ማዋሃድ ይፈልግ ይሆናል። ሌላው የሚመርጠው ነገር ደግሞ አንድ ኦርኪድ ያለውን መዓዛ ሊሆን ይችላል። አብቃዩ እነዚህን የተለያዩ ገጽታዎች ግንዛቤ ውስጥ ካስገባ በኋላ ለዘራቸው ተፈላጊዎቹን ባሕርያት ያስተላልፋሉ ብሎ የሚያምንባቸውን ሁለት ኦርኪዶች ይመርጣል። ለምሳሌ ያህል፣ ኦርኪድ የሚያዳቅል አንድ ሰው ጎልደን ስሊፐር ኦርኪድ (ፓፊዮፐዲለም አርመኒያኩም) የተባለውን ዝርያ ለመጠቀም ይመርጥ ይሆናል። ይህ ኦርኪድ የተገኘው በ1979 በቻይና ነው። ብዙ ጊዜ ይህ ኦርኪድ ለዘሮቹ በጣም ውብ የሆነ ወርቃማ ቢጫ ቀለም ያስተላልፋል።

ኦርኪድ የሚያበቅለው ሰው እንደ ወላጅ የሚሆኑትን ሁለት ዝርያዎች ከመረጠ በኋላ በዘር ከረጢት ወላጅ ውስጥ የሚገኘውን የአበባ ዱቄት በሙሉ ያስወግዳል፤ የዘር ከረጢት ወላጅ የሚባለው ከሌላ ተክል ላይ የአበባ ዱቄት የሚቀበለው አበባ ነው። የአበባ ዱቄቱን የሚሰጠው ኦርኪድ የአበባ ዱቄት ወላጅ ይባላል። ሰውየው በስንጥር ወይም በሌላ ቀጭን ነገር አማካኝነት ከአበባ ዱቄት ወላጁ ላይ የአበባ ዱቄት ከወሰደ በኋላ በዘር ከረጢት ወላጁ አበባ የታችኛው ግንድ ላይ ይበትነዋል። ከዚያም በዚህ ሁኔታ በተዳቀለው አበባ ላይ የሁለቱን ወላጆች ስምና የተዳቀለበትን ቀን ይለጥፋል።

መታገሥ የግድ አስፈላጊ ነው

ግለሰቡ ተሳክቶለት የወንዴውና የሴቴው ዘር ተገናኝቶ ዘሩ ከዳበረ፣ በዘር ከረጢት ወላጅ አበባ ውስጥ አስደናቂ ነገር ይከናወናል። ከአበባው ግንድ አንስቶ ኦቫሪ እስከሚባለው የአበባው ሴቴ ክፍል ድረስ ክር የመሰሉ ቱቦዎች ይዘረጋሉ። ከዚያም ኦቫሪው ያብጥና የዘር ከረጢት ይፈጠራል። በዘር ከረጢት ውስጥ እያንዳንዳቸው ከአንድ የአበባ ዱቄት ቱቦ ጋር የተገናኙ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ጥቃቅን ዘሮች ማደግ ይጀምራሉ። የዘር ከረጢቱ እስኪጎመራ ድረስ በርካታ ወራት ወይም ከአንድ ዓመት የበለጠ ጊዜ ሊፈጅ ይችላል። የዘር ከረጢቱ በሚጎመራበት ጊዜ ኦርኪድ የሚያበቅለው ሰው ዘሮቹን ከዘር ከረጢቱ ውስጥ ያወጣል። ከዚያም እነዚህን ዘሮች አጋርና ሌሎች አልሚ ንጥረ ነገሮች ያለበት ፈሳሽ በያዘ ከጀርም ነጻ በሆነ ዕቃ ውስጥ ያስቀምጣቸዋል። ሰውየው ተሳክቶለት ዘሮቹ ከበቀሉ ትናንሾቹ ኦርኪዶች ልክ እንደ አረንጓዴ ሣር እጅብ ብለው ይታያሉ።

ከጥቂት ወራት በኋላ ግለሰቡ ችግኞቹን ከዕቃው ውስጥ አውጥቶ ሰፋ ባለ ዕቃ ውስጥ እጅብ አድርጎ ያስቀምጣቸዋል። የችግኞቹን ሁኔታ በየቀኑ እየተከታተለ እንዳይደርቁ ቶሎ ቶሎ ውኃ ያጠጣቸዋል። ከጊዜ በኋላ ሰውየው ችግኞቹን ለብቻ ለብቻ በዕቃ ላይ ይተክላቸዋል። ከዚህም በኋላ ቢሆን ኦርኪድን ማሳደግ ከፍተኛ ትዕግሥት ይጠይቃል። ኦርኪዶች ለማበብ የተወሰኑ ዓመታት አሊያም ከአሥር ዓመት በላይ ሊፈጅባቸው ይችላል።

አንድ ኦርኪድ የሚያበቅል ሰው ከዚህ ሁሉ ልፋት በኋላ ተክሉ አብቦ ሲያይ ምን ያህል እርካታ እንደሚሰማው አስብ! ከሁለት ኦርኪዶች ተዳቅሎ የተገኘው ዝርያ አዲስ ዓይነት ከሆነ ሰውየው የፈለገውን ስም አውጥቶ እንዲመዘገብለት ሊጠይቅ ይችላል። ከዚህ አዲስ ዝርያ ጋር ተዳቅለው የሚገኙ ተመሳሳይ ባሕርይ ያላቸው አዳዲስ ዝርያዎች በሙሉ ከዚህ ዝርያ ስም ጋር የተያያዘ መጠሪያ ይወጣላቸዋል።

አንድ ኦርኪድ የሚያበቅል ሰው የኦርኪድ አድናቂዎችን በሙሉ የሚያስደስት ልዩ ባሕርይ ያለው የኦርኪድ ዝርያ የሚያገኝበት ጊዜ ይኖራል። ይህ ዝርያ ሽልማት ሊያስገኝለት አልፎ ተርፎም ተክሉ በውድ ዋጋ ሊሸጥለት ይችላል። ሆኖም ሰውየውን ከገንዘቡ ይበልጥ የሚያስደስተው ራሱ ያዳቀለው ኦርኪድ አብቦ ማየቱ ነው።

አሁን፣ በአድናቆት የምትመለከተውን ውብ ኦርኪድ ለማሳደግ ምን ያህል ጊዜና ትዕግሥት እንደሚጠይቅ ሳትገነዘብ አትቀርም። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ሰዎች የተዳቀሉ የኦርኪድ አበባዎችን ለማግኘት የሚያደርጉት ጥረት የሕያዋን ፍጥረታት ሁሉ ፈጣሪ የሆነው ይሖዋ ካደረገው ነገር ጋር ሲወዳደር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። እያንዳንዱ ተክል በጣም የሚያምሩ አበባዎች እንዲያበቅል የሚያስችሉትን ውስብስብ የሆኑ የጂን ኮዶች የፈጠረው እሱ ነው። እኛ ተዳቅለው በተገኙ የተለያዩ የኦርኪድ ዝርያዎች ላይ የታየውን ጥበበኛነት የተንጸባረቀበት ፍቅር ተቀባዮች ብቻ ነን። በእርግጥም ሁኔታው መዝሙራዊው ዳዊት እንደሚከተለው ብሎ እንደጻፈው ነው፦ “እግዚአብሔር ሆይ፤ ሥራህ እንዴት ብዙ ነው! ሁሉን በጥበብ ሠራህ፤ ምድርም በፍጥረትህ ተሞላች።”—መዝሙር 104:24

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“ቤላራ” የተባለ ዲቃላ

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“ዶሪታኖፕሲስ” የተባለ ዲቃላ

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“ብራሲዲየም” የተባለ ዲቃላ