በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የቀዳማዊት ንግሥት ኤልሳቤጥ ወርቃማ ዘመን አፈ ታሪክ ነው ወይስ እውነት?

የቀዳማዊት ንግሥት ኤልሳቤጥ ወርቃማ ዘመን አፈ ታሪክ ነው ወይስ እውነት?

የቀዳማዊት ንግሥት ኤልሳቤጥ ወርቃማ ዘመን አፈ ታሪክ ነው ወይስ እውነት?

ዘመኗ ዝነኛ ነበረች። ደራሲዎች፣ ፀሐፊ ተውኔቶችና ዘመናዊ የፊልም አዘጋጆች ዝናዋ ሳይደበዝዝ እንዲቀጥል አድርገዋል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ስለ እሷ የሚተርኩ መጻሕፍት ተጽፈዋል፤ እንዲሁም ኤግዚቢሽኖች ታይተዋል። አንድ ዓለም አቀፍ የሕዝብ አስተያየት እንዳመለከተው በብሪታንያ ውስጥ ታላላቅ ከሚባሉት 10 ሰዎች መካከል አንዷ ተደርጋ ትታያለች። ይህች ሴት የእንግሊዟ ንግሥት ቀዳማዊት ኤልሳቤጥ ናት።

በዘመኗ ድንግል ንግሥት እና ጥሩዋ ንግሥት ቤስ በመባል ትታወቅ የነበረችው ይህች ንግሥት ለዚህን ያህል ጊዜ የብዙዎችን ቀልብ ልትስብ የቻለችው ለምንድን ነው? የግዛት ዘመኗ በእርግጥ ወርቃማ ነበር?

ብዙ ችግሮችን ወረሰች

ኤልሳቤጥ ቱደር በ1533 ስትወለድ አልጋ ወራሽ የሚሆን ወንድ ልጅ እንዲወለድለት በጉጉት ሲጠብቅ የነበረው አባቷ ሄንሪ ስምንተኛ እጅግ ተበሳጨ። የንጉሥ ሄንሪ ሁለተኛ ሚስት የነበረችው እናቷ አን ቦሊን ለንጉሡ ወንድ ልጅ ልትወልድለት አልቻለችም። ከጊዜ በኋላ ሄንሪ፣ ንግሥቲቱ በሰይፍ ተቀልታ እንድትገደል አደረገ፤ ብዙዎች የተደገለችው በሐሰት ክስ እንደሆነ ይሰማቸዋል። በዚያን ጊዜ ኤልሳቤጥ ገና የሁለት ዓመት ልጅ ነበረች።

ሄንሪ በዚህ ወቅት ከሮም ጳጳስ ጋር የነበረውን ግንኙነት አቋርጦ ራሱን የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን ራስ አድርጎ ሾመ። ሄንሪ በ1547 ከሞተ በኋላ ኤድዋርድ ስድስተኛ የሚባለው የትንሽ ልጁ መንፈሳዊ አማካሪዎች እንግሊዝ ሙሉ በሙሉ የፕሮቴስታንት አገር እንድትሆን ሙከራ አደረጉ። ኤድዋርድ ለስድስት ዓመት ያህል ብቻ ገዝቶ ከሞተ በኋላ ሕዝቡ የኤልሳቤጥ የአባት ልጅ በነበረችው በቀዳማዊት ሜሪ አጭርና ደም መፋሰስ በበዛበት የግዛት ዘመን ተመልሶ በሮማ ካቶሊክ እምነት እጅ ወደቀ። * ኤልሳቤጥ በ1558 በ25 ዓመቷ ዙፋን ላይ በወጣችበት ጊዜ እንግሊዝ በሃይማኖታዊ ግጭት ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚ ድቀትም ተጠቅታ ነበር። አገሪቷ በቁጥጥሯ ሥር ከነበሩ የፈረንሳይ ግዛቶች ውስጥ የመጨረሻውን ከማጣቷም በላይ ስፔን ከፍተኛ ስጋት ሆናባት ነበር።

ኤልሳቤጥ አገዛዟን የጀመረችው ብቃት ያላቸው አማካሪዎች በማሰባሰብ ሲሆን ከእነዚህም መካከል አንዳንዶቹ በ44 ዓመት የግዛት ዘመኗ ወቅት አብዛኛውን ጊዜ አብረዋት መቆየት ችለዋል። ኤልሳቤጥ የገጠማት የመጀመሪያው ችግር ሃይማኖት ነበር። ናሽናል ማሪታይም ሙዚየም እንደገለጸው “የተሃድሶውን ንቅናቄ እንደገና በማንቀሳቀስ ካቶሊክም ሆነ ጽንፈኛ ፕሮቴስታንት ያልሆነ የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን ለመመሥረት” መርጣለች። ሴትን እንደ ቤተ ክርስቲያን ራስ አድርገው የማይቀበሉትን ወገኖች ለማረጋጋት ስትል የቤተ ክርስቲያን ራስ በመሆን ፈንታ የቤተ ክርስቲያን የበላይ ገዢ ሆነች። ቀጥሎ ፓርላማው አክት ኦቭ ዩኒፎርሚቲ የተባለ የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን የሚመራባቸውን እምነቶችና ተግባሮች የያዘ ድንጋጌ አወጣ፤ እርግጥ ነው፣ ይህ ድንጋጌ አንዳንድ የካቶሊክ ሥነ ሥርዓቶችን አልሻረም። እንደሚጠበቀው ይህ “የመሐል ሠፋሪነት” አቋም አብዛኞቹን ካቶሊኮችም ሆነ ፒዩሪታንስ የሚባሉትን ጽንፈኛ ፕሮቴስታንቶች አላስደሰተም።

ኤልሳቤጥን የሚያሳስባት ከዚህ የባሰ ሌላ ችግር ነበር። በአሰቃቂው የቀዳማዊት ሜሪ አገዛዝ ናላው ዞሮ የነበረው ሕዝብ እንዲያከብራትና ታማኝ እንዲሆንላት ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? ሴትነቷን እንደ ትልቅ መሣሪያ አድርጋ ልትጠቀምበት ወሰነች። ታሪክ ጸሐፊው ክሪስቶፈር ሄግ ሲገልጹ እንዲህ ብለዋል፦ “ኤልሳቤጥ በዙፋኗ ላይ ድንግል ንግሥት ነበረች፤ በቤተ ክርስቲያን ዘንድ እንደ እናት፣ በመኳንንቷ ዘንድ እንደ አክስት፣ በአማካሪዎቿ ዘንድ ደግሞ እንደ ነዝናዛ ሚስት ትታይ ነበር። ለባለሟሎቿ ደግሞ የምታማልል ሴት ነበረች።” የምትከተለው መርሕ ለሕዝቧ ልዩ ፍቅር እንዳላት ነጋ ጠባ በመግለጽ እነሱን ማረጋጋት ነበር። ሕዝቧም በምላሹ እሷን ወደዳት፤ በሌላ አነጋገር ሕዝቡን እንደምትወደው ደጋግማ በመንገር ሕዝቡ እንደምትወደው እንዲያምን አደረገች።

ፓርላማው ኤልሳቤጥ ባል አግብታ ፕሮቴስታንት የሆነ አልጋ ወራሽ እንድትወልድ ጓጉቶ ነበር። የነገሥታት ዘር የሆኑ ብዙ ወንዶች ለጋብቻ ይጠይቋት ነበር። ኤልሳቤጥም ለማግባት የምትፈልግ መስላ ከቀረበች በኋላ ድርድሩ ለወራት አንዳንድ ጊዜም ለዓመታት እንዲቀጥል ታደርግና ፖለቲካዊ ጥቅም እንደማያስገኝላት ስታውቅ ግንኙነቱ እንዲቋረጥ ታደርጋለች።

ኤልሳቤጥ በሃይማኖት ረገድ የምትከተለው አቋም “ለዘብተኛ” ስለነበረ ብዙ ጊዜ ሴራ ይጠነሰስባት ነበር። አውሮፓውያን ካቶሊኮች የኤልሳቤጥ ዘመድ የነበረችውን ሜሪ ስቱዋርትን የቀዳማዊት ሜሪ ሕጋዊ ወራሽ ለማድረግ ይፈልጉ የነበረ ሲሆን ሜሪም በንግሥቲቷ ላይ ጥቃት መሰንዘር የምትችልበትን አጋጣሚ ትፈልግ ነበር። ሜሪ በ1568 በስኮትላንድ የነበራትን ዙፋን ለቃ ወደ እንግሊዝ ለመሸሽ በተገደደች ጊዜ በኤልሳቤጥ ላይ አጥልቶ የነበረው አደጋ አይሎ ነበር። ሜሪ የቁም እስረኛ እንድትሆን የተደረገ ቢሆንም ካቶሊኮች፣ ፕሮቴስታንት የሆነችውን ንግሥት ለመገልበጥ ሜሪን መሣሪያ አድርገው ለመጠቀም ፈልገው ነበር፤ ይሁን እንጂ ኤልሳቤጥ የንጉሥ ዘር የሆነችውን ሜሪን እንድታስገድል የቀረበላትን ምክር ሳትቀበል ቀረች። በ1570 ፓየስ አምስተኛ የተባሉ ጳጳስ ኤልሳቤጥን እንደሚገዝቷት ብሎም ዜጎቿ እሷን እንዳይታዘዟት ሊያደርጉ እንደሚችሉ የሚገልጽ ማስጠንቀቂያ አስተላለፉ። ቀጥሎ ሥልጣን ላይ የወጡት ግሬጎሪ አሥራ ሦስተኛ የተባሉ ጳጳስ ይባስ ብለው እንግሊዝን መውረርና ንግሥቲቷን በኃይል ማስወገድ ኃጢአት እንደማይሆን ተናገሩ። አንቶኒ ባቢንግተን ኤልሳቤጥን ለመግደል እንዳሴረና በሴራው ውስጥ ሜሪም እንደነበረችበት በታወቀ ጊዜ ግን ኤልሳቤጥ እርምጃ ለመውሰድ ተገደደች። በመጨረሻም ኤልሳቤጥ በሜሪ ላይ ውሳኔ ለማሳለፍ የተገደደች ሲሆን በፓርላማው ግፊት ሜሪ በ1587 እንድትገደል ተስማማች። በዚህ ጊዜ የአውሮፓ ካቶሊኮች በተለይ ደግሞ የስፔኑ ንጉሥ ዳግማዊ ፊሊፕ በንዴት በገነ።

ካቶሊኩ ፊሊፕ በድፍረት ያወጣው እቅድ

በወቅቱ በአውሮፓ እጅግ ኃያል መሪ የነበረው ፊሊፕ፣ ኤልሳቤጥ ንግሥት በሆነችበት ወቅት እንድታገባው በመጠየቅ እንግሊዝ የካቶሊክ አገር ሆና እንድትቀጥል ለማድረግ ሞክሮ ነበር፤ ሆኖም ኤልሳቤጥ ጥያቄውን ሳትቀበል ቀረች። የጠላትን መርከቦች ለማጥቃት ፈቃድ የተሰጣቸው የእንግሊዛውያን መርከቦች ለብዙ ዓመታት የስፔንን መርከቦችና ወደቦች ይዘርፉ ስለነበር የቅኝ ገዥነት ሥልጣኗን ይፈታተኑ ነበር። ይባስ ብሎ ደግሞ ኤልሳቤጥ፣ የደች ሕዝቦች ከስፔን አገዛዝ ነፃ ለመውጣት የሚያደርጉትን ትግል ትደግፍ ነበር። የሜሪ መገደል ፊሊፕ ቁጣው ከቁጥጥሩ ውጪ እንዲሆን አደረገ። ፊሊፕ ከጳጳሱ ጋር ከተመካከረ በኋላ ከፍተኛ ቁጥር ባላቸው የስፔን የጦር መርከቦች ተጠቅሞ እንግሊዝን ለመውረር እቅድ ነደፈ፤ በዚህ እቅድ መሠረት ከ130 በላይ የሆኑ መርከቦች ወደ ኔዘርላንድ ሄደው በዚያ ያለውን ግዙፍ የምድር ጦር ከጫኑ በኋላ የእንግሊዝን የባሕር ወሽመጥ አቋርጠው በማለፍ እንግሊዝን ይወራሉ። ይሁንና የጦር መርከቦቹ ሙሉ በሙሉ ከመንቀሳቀሳቸው በፊት የእንግሊዝ ሰላዮች የተጠነሰሰውን ሴራ ደረሱበት። ኤልሳቤጥ፣ ሰር ፍራንሲስ ድሬክ 30 መርከቦችን ይዞ ካዲዝ ወደሚባለው የስፔን ወደብ እንዲዘምት አደረገች፤ እነዚህ መርከቦች ከፍተኛ ግምት ተሰጥቷቸው የነበሩትን የስፔን መርከቦች ከጥቅም ውጪ አደረጓቸው፤ በዚህም ምክንያት የስፔን ወረራ በአንድ ዓመት ዘገየ።

በመጨረሻ የስፔን የባሕር ኃይል በ1588 ከወደቡ ሲንቀሳቀስ የእንግሊዝ ባሕር ኃይል ዝግጁ ሆኖ ይጠብቀው ነበር። የስፔን መርከቦች ከጠላት ወገን እሳት ቢዘንብባቸውም ብዙ ጉዳት ሳይደርስባቸው የእንግሊዝን የባሕር ወሽመጥ አቋርጠው ካሊዝ በምትባለው የፈረንሳይ ወደብ ላይ መልሕቃቸውን ጣሉ። በቀጣዩ ሌሊት እንግሊዝ ስምንት የእሳት መርከቦችን ወደዚያ ላከች። * በዚህ ጊዜ የስፔን መርከቦች ተደናግጠው ተበታተኑ፤ ከዚያም ከፍተኛ ውጊያ ከተካሄደ በኋላ የደቡብ ምዕራብ ንፋስ መጥቶ ከእንግሊዝ በስተ ሰሜን ወደምትገኘው ወደ ስኮትላንድ ነዳቸው። በስኮትላንድና በአየርላንድ ምዕራባዊ የባሕር ዳርቻ አካባቢ የተነሳው ማዕበል ደግሞ ግማሽ የሚያክሉትን የስፔን መርከቦች እንዳልነበሩ አደረጋቸው፤ የተወሰኑት መርከቦች ግን እንደምንም ብለው ወደ ስፔን አመሩ።

“ወርቃማው ዘመን” ጀመረ

በኤልሳቤጥ ዘመነ መንግሥት መጀመሪያ ላይ እንግሊዝ በባሕር ማዶ ምንም ዓይነት ጥቅም አልነበራትም። በአንጻሩ ደግሞ ስፔን በሰሜን፣ በማዕከላዊና በደቡብ አሜሪካ ሰፋፊ ክልሎችን በቁጥጥሯ ሥር አድርጋ ብዙ ሀብት እያጋበሰች ነበር። እንግሊዝ የዚህ ሀብት ተካፋይ መሆን ፈለገች። በዚህ ምክንያት ጀብደኛ የሆኑ ሰዎች ዝና እና ሀብት እንዲሁም ወደ ቻይናም ሆነ ወደ ሌሎች የሩቅ ምሥራቅ አገሮች የሚያደርሱ አዳዲስ የንግድ መስመሮችን ለማግኘት በውቅያኖሶች ላይ ይጓዙ ጀመር። ሰር ፍራንሲስ ድሬክ የራሱን መርከብ እየቀዘፈ በዓለም ዙሪያ በመጓዝ ብሎም በደቡብና በሰሜን አሜሪካ የባሕር ዳርቻዎች ላይ የሚገኙትን ውድ ሀብት የጫኑ የስፔን መርከቦችን በመዝረፍ ረገድ የመጀመሪያው ካፒቴን ሆነ። ሰር ዋልተር ራሌይ ደግሞ በሰሜን አሜሪካ ምሥራቃዊ ዳርቻ ላይ ቅኝ ግዛት ለመመሥረት የሚደረገውን ሙከራ በመደገፍ አዲሱን ዓለም ብቻዋን ትቆጣጠር የነበረችውን ስፔንን መፈታተን ጀመረ። ከዚያም የያዘውን ክልል ለእንግሊዟ ድንግል ንግሥት ክብር ሲል ቨርጂኒያ ብሎ ሰየመው። ምንም እንኳን በዚያ ጊዜ ቅኝ ግዛት ለመያዝ የተደረጉ ሙከራዎች ሳይሳኩ ቢቀሩም እንግሊዝ ከዚያ በኋላ ሌሎች ሙከራዎችን ለማድረግ እንድትነሳሳ አድርጓታል። “የማይበገረው የስፔን የባሕር ኃይል” ድል ከተመታ በኋላ እንግሊዝ በባሕር ላይ በምታደርጋቸው እንቅስቃሴዎች የልብ ልብ ስለተሰማት ንግሥት ኤልሳቤጥ በደቡብ ምሥራቅ እስያ የሚደረጉትን አዳዲስ የንግድ እንቅስቃሴዎች መደገፍ ጀመረች። ይህ ደግሞ ከጊዜ በኋላ በመላው ዓለም ለተንሰራፋው የብሪታንያ ግዛት መሠረት ጥሏል። *

በአገር ውስጥ ደግሞ ትምህርት እየተስፋፋ ነበር። በየጊዜው አዳዲስ ትምህርት ቤቶች መከፈታቸው ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ ተማሪዎች ወደ ሥነ ጽሑፉ ዓለም እንዲገቡ በር ከፈተ። ሰዎች የነበራቸው የሥነ ጽሑፍ ጥማት በሕትመት መስክ ከተገኘው እድገት ጋር ተዳምሮ በባሕል ረገድ ከፍተኛ እድገት አስገኝቷል። ዊሊያም ሼክስፒርና ሌሎች ታላላቅ ጸሐፊ ተውኔቶች ወደ ታሪክ መድረክ ብቅ ያሉት በዚህ ዘመን ነበር። ሕዝቡ እነዚህ ደራሲዎች ባዘጋጇቸው ትያትሮች ለመዝናናት አዲስ ወደ ተከፈቱት ትያትር ቤቶች ይጎርፍ ነበር። አንደበተ ርቱዕ ገጣሚዎች የረቀቁ ግጥሞችን ይጽፉ የነበረ ሲሆን የሙዚቃ ደራሲያን አዳዲስ ሙዚቃዎችን ያዘጋጁ ነበር። የተካኑ ሰዓሊዎች ንግሥቲቷንና ባለሟሎቿን የሚያሳዩ ዕጹብ ድንቅ ሥዕሎችን ይስሉ ነበር። ለአዳዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች በአብያተ ክርስቲያናትም ሆነ በየሰዉ ቤት የክብር ቦታ ይሰጥ ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ወርቃማ ዘመን ብዙም አልዘለቀም።

ወርቃማው ዘመን አበቃ

የኤልሳቤጥ የኋለኞቹ ዓመታት በችግር የተሞሉ ነበሩ። ታማኝ አማካሪዎቿ ቀድመዋት ስለሞቱ ልዩ መብቶችን ለተመረጡ ጥቂት ሰዎች ብቻ ትሰጥ ጀመር፤ ይህ ደግሞ በቤተ መንግሥት ውስጥ ኃይለኛ ፉክክር እንዲፈጠር ከማድረጉም በላይ አልተሳካም እንጂ ዓመፅ እንዲቀሰቀስ አድርጓል። ግዛቷም እንደገና በሃይማኖት ክፍፍል ምክንያት መታመስ ጀመረ። ካቶሊኮች በፕሮቴስታንቶች ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶች ላይ ለመካፈል ፈቃደኞች ሳይሆኑ በመቅረታቸው በእነሱ ላይ የሚደርሰው ስደት እየጨመረ መጣ። በግዛቷ መጨረሻ አካባቢ በግምት ወደ 200 የሚያህሉ ቀሳውስትና ምዕመናን ተገድለው ነበር። ፒዩሪታንስ የሚባሉት አጥባቂ ፕሮቴስታንቶችም ቢሆኑ ከመታሰርና ከመገደል አልዳኑም። አየርላንድ ውስጥ የእንግሊዝን አገዛዝ በመቃወም ዓመፅ የፈነዳ ሲሆን ከስፔን ጋር የሚደረገው ጦርነትም ተፋፋመ። ለአራት ተከታታይ ወቅቶች ጥሩ ምርት ባለመገኘቱ ሥራ አጥነትና ልመና እየጨመረ ከመሄዱም በላይ የምግብ ዋጋ በመወደዱ ምክንያት ሕዝቡ ረብሻ ያስነሳ ነበር። የኤልሳቤጥ ተወዳጅነት እያከተመ መጣ። የእንግሊዝ ሕዝብ ለድንግሏ ንግሥታቸው የነበራቸው ፍቅር ከሰመ።

ኤልሳቤጥ እያደር መኖር ሰለቻት፤ ከቱደር ነገሥታት የመጨረሻዋ ንግሥት የነበረችው ኤልሳቤጥ መጋቢት 24, 1603 ሞተች። የእንግሊዝ ሕዝብ የመሞቷ መርዶ በተሰማበት ወቅት ቢደነግጥም ምሽት ላይ ለአዲሱ ንጉሥ ችቦ በመለኮስና በጎዳና ላይ በመጨፈር አቀባበል አደረገለት። በመጨረሻ የናፈቁትን ንጉሥ አገኙ፤ ይህ ንጉሥ የሜሪ ስቱዋርት ልጅ የሆነው የስኮትላንዱ ጄምስ ስድስተኛ ነበር። ፕሮቴስታንት የነበረው ይህ ንጉሥ ለእንግሊዝ ቀዳማዊ ጄምስ በመሆን ባከናወነው ተግባር ኤልሳቤጥ ማድረግ ያልቻለችውን ነገር ይኸውም በሁለት ነገሥታት ይተዳደሩ የነበሩ ሁለት አገሮች አዋህዶ አንድ ማድረግ ችሏል። ይሁን እንጂ ሕዝቡ መጀመሪያ ላይ የነበረው ብሩሕ ተስፋ ብዙም ሳይቆይ እንደ ጉም በኖ ስለጠፋ የጥሩዋን ንግሥታቸውን ዘመን መናፈቅ ጀመረ።

በእርግጥ ወርቃማ ዘመን ነበር?

የጥንት ታሪክ ጸሐፊዎች በጽሑፎቻቸው ላይ ኤልሳቤጥን አሞጋግሰዋታል። ኤልሳቤጥ ከሞተች ከጥቂት ዓመታት በኋላ ዊሊያም ካምዴን የተባሉ ታሪክ ጸሐፊ የግዛት ዘመኗ በሕዝቧ ልብ ውስጥ ታላቅ የመሆን ምኞት የተቀጣጠለበት ወርቃማ ዘመን እንደነበረ ገልጸዋል። ከዚያ በኋላ በነበሩት መቶ ዘመናት ሁሉ ይህን አመለካከት የተጠራጠረ ሰው አልነበረም። እንዲያውም የብሪታንያ ግዛት የዓለምን ሩብ ሸፍኖ በነበረበት በ19ኛው መቶ ዘመን መጨረሻ ላይ ለዚህ ሁሉ መነሻው የእሷ ግዛት እንደሆነ ተደርጎ ይወደስ ስለነበር በዚህ ወቅትም ዝናዋ ይበልጥ ገንኖ ነበር።

አንዳንድ ዘመናዊ ታሪክ ጸሐፊዎች ግን የኤልሳቤጥን አገዛዝ የሚያዩት በሌላ ዓይን ነው። ዚ ኦክስፎርድ ኢላስትሬትድ ሂስትሪ ኦቭ ብሪትን የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ብሏል፦ “ኤልሳቤጥ ከሞተች በኋላ ያገኘችው ዝና ካከናወነችው ነገር በእጅጉ የሚልቅ ነበር። በእሷ ፕሮፓጋንዳ፣ . . . አጋጣሚ ሆኖ ረጅም ዘመን በመኖሯ፣ ዘመነ መንግሥቷ ከነሼክስፒር ዘመን ጋር በመገጣጠሙና የስፔንን የባሕር ኃይል ለማሸነፍ በመታደሏ ተታለን እሷን ወደ ማወደሱና ማሞገሱ ማዘንበላችን እንግሊዝን ስድ የመልቀቋ ግልጽ ሐቅ ፈጽሞ እንዳይታየን እንዳደረገ እሙን ነው።” ቀደም ሲል የተጠቀሱት ሄግ አንዳንድ ታሪክ ጸሐፊዎች ለምን እንደዚያ እንደጻፉ ሲገልጹ እንዲህ ብለዋል፦ “በ1603 የስቱዋርትን ንጉሥነት በጉጉት በመጠባበቅ ላይ ለነበረው ሕዝብ ኤልሳቤጥ አንዲት ሞኝ አሮጊት መስላ ታይታቸው ነበር። ሰዎች በ1630 የስቱዋርት ነገሥታት አገዛዝ ይባስ ተስፋ አስቆራጭ ሲሆንባቸው ኤልሳቤጥ ከጥሩ መሪ የሚጠበቀውን ምግባር ሁሉ የተላበሰች ሴት ሆና ታየቻቸው።”

ኤልሳቤጥ ወንዶች ባየሉበት ዓለም ውስጥ ለየት ብላ የምትታይ ሴት እንደነበረች ጥርጥር የለውም። ብልህና ቆራጥ የነበረችው ንግሥት ኤልሳቤጥ በሕዝብ ግንኙነት ረገድ ስኬታማ ልትሆን የቻለችው ንግግሮቿን፣ በሕዝብ ፊት የምትቀርብበትን ጊዜና አለባበሷን በሚያቀነባብሩላት ሚኒስትሮቿ እንዲሁም የእሷን የግርማዊነትና የግዛት ዘመኗን ወርቃማነት በሚያንጸባርቅ መንገድ በተሳሉ ሥዕሎች እርዳታ ነው።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.6 በሚያዝያ 2000 ንቁ! መጽሔት ከገጽ 12-14 ላይ የወጣውን “ሃይማኖታዊ አለመቻቻል ነግሦ እንደነበር ያመኑት ዛሬ ነው” የሚለውን ርዕሰ ትምህርት ተመልከት።

^ አን.13 የእሳት መርከብ፣ ፈንጂና ሌሎች ተቀጣጣይ ነገሮች ጭኖ በጠላት መርከቦች መካከል በመግባት በእሳት እየተቀጣጠለ ጥፋት የሚያደርስ መርከብ ነው።

^ አን.15 ጆን ዲ እና የብሪታንያ ግዛት” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ኤልሳቤጥ ከሞተች በኋላ ያገኘችው ዝና ካከናወነችው ነገር በእጅጉ የሚልቅ ነበር”

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

 ጆን ዲ እና የብሪታንያ ግዛት

ኤልሳቤጥ፣ ጆን ዲ የሚባለውን ሰው (1527-1608/9) ፈላስፋዬ ብላ ትጠራው ነበር። ይህ ሰው የተከበረ የሒሳብና የጂኦግራፊ ሊቅ እንዲሁም የሥነ ፈለክ ተመራማሪ የነበረ ሲሆን ለኮከብ ቆጠራና ለጥንቆላም ከፍተኛ ፍቅር ነበረው። ለንግሥቷ በየትኛው ቀን ዘውድ ብትጭን የተሻለ እንደሆነ ምክር የሰጣት ሲሆን የጥንቆላ ሥራዎቹን በቤተ መንግሥቷ ውስጥ ያከናውን ነበር። “የብሪታንያ ግዛት” የሚለው ስያሜ ታዋቂነት እንዲያገኝ እንዳደረገ የሚነገርለት ይህ ሰው፣ ወደፊት ውቅያኖሶችን በመቆጣጠርና አዳዲስ ቅኝ ግዛቶችን በማስፋፋት በሚመሠረተው ታላቅ ግዛት ላይ እቴጌ እንደሆነች አድርጋ ራሷን እንድትመለከት ኤልሳቤጥን ያበረታታት ነበር። ለዚህም ሲባል ለአሳሾች፣ በተለይ ደግሞ በሰሜን ምሥራቅና በሰሜን ምዕራብ በኩል ወደ ሩቅ ምሥራቅ ለማለፍ የሚያስችል መንገድ ለሚፈልጉ ሰዎች ለባሕር ጉዟቸው የሚጠቅማቸውን አቅጣጫ ለመለየት የሚያስችል ትምህርት የሰጠ ሲሆን የሰሜን አሜሪካን አሕጉር በቅኝ ለመግዛት ለተነደፈው እቅድ ድጋፍ ሰጥቷል።

[ምንጭ]

Photograph taken by courtesy of the British Museum

[በገጽ 20 እና 21 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ሀ. የስፔንን መርከቦች ለማጥቃት የተላኩ የእንግሊዝ የእሳት መርከቦች ለ. ሰር ፍራንሲስ ድሬክ ሐ. ንግሥት ኤልሳቤጥ መ. ግሎብ ትያትር ቤት ሠ. ዊሊያም ሼክስፒር

[ምንጮች]

ሀ፦ From the book The History of Protestantism (Vol. III); ለ፦ ORONOZ; ሐ፦ From the book Heroes of the Reformation; መ፦ From the book The Comprehensive History of England (Vol. II); ሠ፦ Encyclopædia Britannica/11th Edition (1911)

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

© The Bridgeman Art Library International