በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘የራስ ወዳድነትን ዝንባሌ መዋጋት’

‘የራስ ወዳድነትን ዝንባሌ መዋጋት’

‘የራስ ወዳድነትን ዝንባሌ መዋጋት’

● ጅብራልተር የምትገኘው በአይቤሪያ ባሕረ ገብ መሬት ደቡባዊ ጫፍ ላይ ሲሆን በአገሪቱ ውስጥ ጦርነትና ግጭት ነግሦ በነበረባቸው ዘመናት በርካታ ወረራዎችን አስተናግዳለች። በጥቅምት 2008 ደግሞ ቁጥራቸው ወደ አንድ ሺህ በሚጠጋ ስፔናውያን “ተወረረች”፤ ሆኖም “ወረራው” ሰላማዊ ነበር። እነዚህ ሰዎች የመጡት በጅብራልተር ለሚገኙት ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች መሰብሰቢያ የሚሆን የመንግሥት አዳራሽ ለመገንባት ነበር።

አንድ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን ለንቁ! መጽሔት እንደገለጹት ጅብራልተር፣ በፕሮጀክቱ ለመካፈል የመጡትን በመቶዎች የሚቆጠሩ እንግዶች በደስታ ተቀብላለች። እኚህ ባለሥልጣን እንግዶቹ “ለአካባቢው እድገት አስተዋጽኦ እንዳደረጉ” ተናግረዋል። አክለውም “የይሖዋ ምሥክሮች፣ በአንድ ፕሮጀክት ላይ ብቻ ያውም በፈቃደኝነት የሚሠሩ ይህን ያህል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎችን በማምጣት በጅብራልተር ታሪክ የመጀመሪያውን ቦታ ይዘዋል” በማለት ተናግረዋል።

የአካባቢው ባለሥልጣናት፣ ይህ የአምልኮ ቤት የሚገነባበትን ተስማሚ ቦታ ለይሖዋ ምሥክሮች በደግነት በመስጠት ፕሮጀክቱን ገና ከጅምሩ ደግፈው ነበር። ባለሥልጣናቱ እንዲህ ያለ ለጋስነት እንዲያሳዩ ያነሳሳቸው ምን ነበር?

“ፈሪሃ አምላክ ማንኛውም ኅብረተሰብ ሊያዳብረው የሚገባ ጠቃሚ ባሕርይ እንደሆነ ይሰማኛል” በማለት ከፍተኛ ባለሥልጣኑ ገልጸዋል። አክለውም እንዲህ ብለዋል፦ “በጅብራልተር ያሉት ሁሉም ሃይማኖቶች አምልኳቸውን በነፃነት የማራመድ ሕገ መንግሥታዊ መብት አላቸው፤ በመሆኑም መንግሥት በሃይማኖታዊ ጉዳዮች ረገድ አድልዎ ባለማድረግ ሥነ ምግባራዊ ግዴታውን መወጣት አለበት። ከዚህም በላይ የይሖዋ ምሥክሮች የአምልኮ ቤት የሚገነቡበት ተስማሚ ቦታ መስጠት ለማኅበረሰቡ ትልቅ እሴት ነው።”

“በብዙዎች ዘንድ የሚታየውን የራስ ወዳድነት ዝንባሌ ልንዋጋው ያስፈልጋል” ሲሉ እኚሁ ባለሥልጣን ተናግረዋል። ቀጥለው “በቅንዓት የሚያገለግሉ ፈቃደኛ ሠራተኞችን ያቀፈው ቡድናችሁ የራስ ወዳድነትን ዝንባሌ ማሸነፍ እንደሚቻል አሳይቷል” ብለዋል።

ዝናብ የቀላቀለ ኃይለኛ ነፋስ ተነስቶ ስለነበር ሥራው በታሰበው ጊዜ ባይጀመርም የመንግሥት አዳራሹ ግንባታ በተጀመረ በሦስተኛው ቀን ማለትም ሰኞ ዕለት ተጠናቀቀ። “አብዛኞቹ ፈቃደኛ ሠራተኞች ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ በጅብራልተር አንድ ተጨማሪ ቀን ለመቆየት ራሳቸውን በፈቃደኝነት አቅርበዋል” በማለት ሥራውን በበላይነት ይከታተል የነበረው ሴኩንዲኖ ኖጋል ገልጿል። “በየጊዜው የሚያጋጥሙንን ችግሮች እንፈታቸው ነበር። የግንባታ ሥራችን አንዳችን የሌላውን ሐሳብ ለመቀበል ፈቃደኞች እንድንሆን ይጠይቅብን ነበር። ከሁሉ በላይ ግን ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ ስሜት ማገልገል ነበረብን፤ ሥራችን ትልቅ እርካታ ያመጣልንም ለዚህ ነው።” *

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.7 ጅብራልተር ክሮኒክል የተባለ በአካባቢው የሚታተም አንድ ጋዜጣ “ነፋሱ ብዙ ጉዳት እያደረሰ በነበረበት በሳምንቱ መጨረሻ ላይ የጅብራልተር የይሖዋ ምሥክሮች ከፈቃደኛ ሠራተኞች ሠራዊት ጋር በመሆን ቤተ መቅደሳቸውን [የመንግሥት አዳራሻቸውን] በሦስት ቀናት ውስጥ አጠናቀቁ” በማለት ዘግቧል።