በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አጥንት—አስደናቂ ጥንካሬ

አጥንት—አስደናቂ ጥንካሬ

ንድፍ አውጪ አለው?

አጥንት አስደናቂ ጥንካሬ

አጥንት “ከፍተኛ የሆነ ጫና የመቋቋም፣ ጭነት የመሸከምና የመለጠጥ አቅም ያለው አስደናቂ የምሕንድስና ውጤት” እንደሆነ ይገለጻል። እንዲህ የሚባለው ለምንድን ነው?

እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ የሰው ልጅ አፅም በግምት 206 በሚያህሉ አጥንቶችና 68 በሚያህሉ መገጣጠሚያዎች የተዋቀረ ነው። በሰውነታችን ውስጥ ረጅሙ አጥንት የጭን አጥንት ሲሆን ከሁሉም የሚያንሰው ደግሞ በጆሯችን ውስጥ የሚገኘው አጥንት ነው። ጥሩ ችሎታ ያላቸው ስፖርተኞች ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ በግልጽ መመልከት እንደሚቻለው በሰውነት ውስጥ ያሉት አጥንቶች፣ ጡንቻዎች፣ ለስላሳ አጥንት (ካርቲሌጅ) እንዲሁም መገጣጠሚያዎች አንድ ላይ ተቀናጅተው ጤናማ የሆነ አካል በጣም አስደናቂ የሆነ እንደ ልብ የመተጣጠፍ ችሎታ እንዲኖረው ያደርጋሉ። ናሽናል ስፔስ ባዮሜዲካል ሪሰርች የተባለው ተቋም “አውራ ጣት ብቻ እንኳ ሰውነታችንን የሠራው መሐንዲስ (ማንም ይሁን ማን) ልዩ ጥበብ እንዳለው ማንም አሌ ሊለው የማይችል ማስረጃ ይሰጣል” ብሏል።

ከዚህም በተጨማሪ በሰውነታችን ውስጥ ያሉት አጥንቶች በጣም ከፍተኛ የሆነ ጭነት መሸከም ይችላሉ። ከላይ የተጠቀሰው ተቋም እንዲህ ብሏል፦ “[አጥንት] የተሠራው ልክ የብረት አርማታ በሚሠራበት መንገድ ነው። . . . አርማታ ውስጥ የሚገባው ብረት አርማታው ጫና መቋቋም የሚያስችል ጥንካሬ እንዲኖረው ሲያደርግ ሲሚንቶው፣ አሸዋውና ጠጠሩ ደግሞ ከፍተኛ ጭነት የመሸከም ኃይል እንዲኖረው ያደርጋል። ይሁን እንጂ አጥንት ያለውን ጭነት የመሸከም ኃይል ከሁሉ የተሻለ የሚባለው ባለ ብረት አርማታ እንኳ አይተካከለውም።” በዩናይትድ ስቴትስ፣ በበርክሌይ የካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ የማቴሪያል ሳይንስ ፕሮፌሰር የሆኑት ሮበርት ሪቺ “የአጥንትን ጥንካሬ መኮረጅ ብንችል ምንኛ መታደል ነበር!” ብለዋል።

ከአርማታ በተለየ መልኩ አጥንት፣ ቁጥር ስፍር የሌላቸው ሕያዋን ፍጥረታት አካል አቢይ ክፍል ነው። ደግሞም በድን አይደለም። ራሱን መጠገን የሚችል ከመሆኑም ሌላ እድገቱን ለሚቆጣጠሩ ሆርሞኖች ምላሽ ይሰጣል፤ አልፎ ተርፎም የደም ሴሎችን በማምረት ረገድ ቁልፍ ሚና ይጫወታል። በተጨማሪም ልክ እንደ ጡንቻ የሚያርፍበት ጭነት እየጨመረ ሲሄድ ቀስ በቀስ ይበልጥ እየጠነከረ ይሄዳል። ከወንበር ወንበር ሲገላበጡ ከሚውሉ ሰዎች ይልቅ ስፖርተኞች ጠንካራ አጥንት የሚኖራቸው በዚህ ምክንያት ነው።

ታዲያ ምን ይመስልሃል? አጥንት እንዲሁ በአጋጣሚ የተገኘ ነው? ወይስ ንድፍ አውጪ አለው?

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአጥንት አወቃቀር (ጎልቶ ሲታይ)

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Leg bone: © MedicalRF.com/age fotostock; close-up: © Alfred Pasieka/Photo Researchers, Inc.; gymnast: Cultura RF/Punchstock