በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በሞተር ኃይል መብረር

በሞተር ኃይል መብረር

በሞተር ኃይል መብረር

ለብዙ መቶ ዓመታት ሰዎች ስለ መብረር ሲያልሙ ነበር። ይሁን እንጂ የሰው ልጅ የራሱን ክብደት አየር ላይ ሊያንሳፍፍ የሚችል ጥንካሬ ያለው ጡንቻ የለውም። በ1781 ጀምስ ዋት ሽክርክሪት ለመፍጠር የሚችል የእንፋሎት ሞተር ሠራ። በ1876 ደግሞ ኒኮላውስ ኦቶ ይህን በማሻሻል ነዳጅን ወደ ኃይል መቀየር የሚችል ሞተር ሠራ። አሁን የሰው ልጅ የበረራ መሣሪያ ሊያንቀሳቅስ የሚችል ሞተር አገኘ። ይሁን እንጂ ይህን መሣሪያ ማን ይሠራ ይሆን?

ዊልበርና ኦርቪል ራይት የተባሉት ወንድማማቾች፣ ልጆች ሆነው ወላንዶ ካበረሩበት ጊዜ ጀምሮ የመብረር ምኞት አድሮባቸው ነበር። ከጊዜ በኋላ ብስክሌት በመሥራት የምሕንድስና ችሎታቸውን አዳበሩ። ወንድማማቾቹ ለበረራ ወሳኝ የሆነው ትልቁ ተፈታታኝ ነገር እንቅስቃሴውን መቆጣጠር የሚቻል መሣሪያ መፈልሰፍ እንደሆነ ተገነዘቡ። አንድን አውሮፕላን በአየር ላይ ሚዛኑን ጠብቆ እንዲቆይ ማድረግ ካልተቻለ፣ በመሪው ወደተወሰነ አቅጣጫ እንዲሄድ ሊደረግ እንደማይችል ብስክሌት ዋጋ ቢስ ይሆናል። ዊልበር የሚበሩ ርግቦችን ሲመለከት፣ በሚዞሩበት ጊዜ እንደ ብስክሌት ነጂ ወደሚዞሩበት አቅጣጫ ዘመም እንደሚሉ አስተዋለ። ወፎች ወደፈለጉት አቅጣጫ የሚዞሩትና ሚዛናቸውን የሚጠብቁት የክንፎቻቸውን ጫፍ በማዞር እንደሆነ አወቀ። በመሆኑም መዞር የሚችል ክንፍ መሥራት እንደሚኖርበት አሰበ።

በ1900 ወንድማማቾቹ መዞር የሚችል ክንፎች ያሉት አውሮፕላን ሠሩ። የሠሩትን አውሮፕላን መጀመሪያ ብቻውን እንደ ወላንዶ ከዚያም አብራሪ አሳፍሮ እንዲበር አደረጉ። አውሮፕላኑ ወደ ላይና ወደ ታች የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ብሎም የሚያዘምበትንና አቅጣጫ የሚቀይርበትን መንገድ ለመቆጣጠር ሦስት መሠረታዊ መቆጣጠሪያዎች እንደሚያስፈልገው ተገነዘቡ። ይሁን እንጂ ክንፎቹ በበቂ ሁኔታ ወደላይ ሊያንሳፍፉ የሚችሉ አልሆኑም። ስለሆነም ነፋስ ማስተላለፊያ ክንፍ ሠሩና ትክክለኛውን ቅርጽ፣ መጠንና ማዕዘን እስኪያገኙ ድረስ በመቶዎች የሚቆጠሩ የክንፍ ቅርጾችን ሞከሩ። በ1902 አዲስ አውሮፕላን ሠርተው አየር ላይ ሚዛኑን ጠብቆ መንሳፈፍ እንዲችል አደረጉ። ታዲያ አሁን ሞተር ሊጭኑለት ይችሉ ይሆን?

በመጀመሪያ ሞተሩን ራሳቸው መሥራት ነበረባቸው። ከነፋስ አስተላላፊ ክንፍ ያገኙትን እውቀት በመጠቀም መዘውር (ፕሮፔለር) መሥራት የሚጠይቀውን ውስብስብ ችግር መወጣት ቻሉ። በመጨረሻ ታኅሣሥ 17, 1903 ሞተሩ ተነሳ፤ መዘውሩም ተሽከረከረና አይሮፕላኑ ከመሬት ተነስቶ ቀዝቃዛውን አየር ሰንጥቆ መጓዝ ጀመረ። ኦርቪል “ከልጅነታችን ጀምሮ እረፍት ነስቶን የቆየውን ሕልማችንን አሳካን። መብረር ቻልን” ብሏል። የወንድማማቾቹ ዝና በመላው ዓለም ተስፋፋ። ይሁን እንጂ በአየር ላይ መብረር የቻሉት እንዴት ነው? አዎ፣ ተፈጥሮ የራሱ ድርሻ ነበረው።

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዊልበርና ኦርቪል ራይት የሠሩት “ፍላየር” ሰሜን ካሮላይና፣ ዩናይትድ ስቴትስ፣ 1903 (በድጋሚ ሲበር የተነሳ ፎቶ)