በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ተንቀሳቃሽ የሕክምና አገልግሎት

ተንቀሳቃሽ የሕክምና አገልግሎት

ተንቀሳቃሽ የሕክምና አገልግሎት

አንዲት ነፍሰ ጡር ሴት በአንድ ትልቅ የስብሰባ አዳራሽ ተቀምጣ የሚሰጠውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በትኩረት ታዳምጥ ነበር። በድንገት ምጥ ጀመራት። ይሁንና ወዲያውኑ የድንገተኛ ሕክምና እርዳታ ማግኘት ቻለች። በአቅራቢያው አንድ አምቡላንስ ስለነበረ ሴትየዋና ባሏ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ሆስፒታል ደረሱ። በዚያም ሴትየዋ የምታምር ሴት ልጅ ወለደች።

በዛሬው ጊዜ ልዩ የሕክምና እርዳታ የሚሰጡ (አይ ሲ ዩ) አምቡላንሶች በበርካታ አገሮች ውስጥ የጤና አገልግሎት በመስጠት ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታሉ። እነዚህ ተሽከርካሪዎች ብቃት ያላቸው የሕክምና ባለሙያዎች ማለትም ሐኪሞች፣ ነርሶችና ሥልጠና ያገኙ አሽከርካሪዎች አሏቸው። * እነዚህ አምቡላንሶች አፋጣኝ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ለምሳሌ የመኪና አደጋ፣ ድንገተኛ የልብ ድካም፣ በአንጎል ውስጥ ደም የመፍሰስ ችግር ላጋጠማቸው ሰዎች የሕክምና እርዳታ ለመስጠት ወይም ምጥ የያዛቸውን ሴቶች ለማዋለድ የሚያስችሉ የተሟሉ መሣሪያዎች አሏቸው። ፈጣን የሕክምና እርዳታ የሚሰጡት እነዚህ አምቡላንሶች በየዓመቱ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ይታደጋሉ።

በ2004 በስፔን ዋና ከተማ ማድሪድ ውስጥ በአራት የሕዝብ ማመላለሻ ባቡሮች ላይ ጥቃት በደረሰበት ወቅት እነዚህ አምቡላንሶች ፍጥነትና ብቃት የታከለበት የሕክምና አገልግሎት በመስጠታቸው 400 የሚያህሉ ሰዎችን ሕይወት ማዳን ተችሏል። * የማድሪድ ከተማ የድንገተኛ ሕክምና አገልግሎት ክፍል ዲሬክተር የሆኑት ዶክተር ኤርቪኪኦ ኮራል ቶሬስ፣ ያንን አስከፊ ጊዜ አስታውሰው ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል፦ “[ሥራችን] ከፍተኛ የዜና ሽፋን የተሰጠው በዚህ አጋጣሚ ነበር። ይሁን እንጂ ብቃታችን ይበልጥ የሚታየው በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያችን ይኸውም ሰዎችን በጎዳና ላይ ለመርዳት በምናደርገው ጥረት ነው። የዚህ አገልግሎት ዋነኛ ገጽታ ከሞት የመትረፍ አጋጣሚ ያልነበራቸውን ሰዎች በሕይወት እንዲኖሩ መርዳት ነው።”

ዶክተር ኮራል ቶረስ ሥራቸው ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን ምን እንደሚያስፈልግ ሲጠየቁ “ሰዎች ተገቢ ሆኖ በሚታያቸው ጊዜ እኛን መጥራታቸው አስፈላጊ ስለመሆኑ ያላቸውን ግንዛቤ ማስፋት ይኖርብናል” በማለት መልስ ሰጥተዋል። አክለውም “ግባችን ሰዎች እርዳታ በሚያስፈልጋቸው ጊዜና ቦታ ሁሉ ልዩ የሕክምና አገልግሎት መስጠት እንዲሁም ጥሪ በደረሰን ጊዜ ሁሉ በተቻለን መጠን በአፋጣኝ በቦታው መድረስ ነው” ብለዋል። በትላልቅ ከተሞች ውስጥ የእርዳታ ቡድኑ በአብዛኛው በ10 ደቂቃ ውስጥ ይደርሳል።

በብራዚል እንደምትገኘው እንደ ሳኦ ፓውሎ ባሉ አንዳንድ ከተሞች ውስጥ የሚፈጠረው የትራፊክ መጨናነቅ የአምቡላንስ ሹፌሮች ቶሎ መድረስ አስቸጋሪ ስለሚያደርግባቸው የሕክምና ባለሙያዎች በሞተር ብስክሌቶች ይሄዳሉ። እነዚህ የሕክምና ባለሙያዎች ከአምቡላንሱ ቀድመው በመድረስ የተፈጠረውን ድንገተኛ ሁኔታ ይገመግማሉ እንዲሁም የመፍትሔ እርምጃ ይወስዳሉ። እንዲህ ዓይነቱ ፈጣን የሕክምና አገልግሎት የሚሰጥባቸው ሌሎች ከተሞች ለንደን እንግሊዝ፣ ኩዋላ ላምፑር ማሌዥያ እና ማያሚ ዩናይትድ ስቴትስ ናቸው።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.3 አሽከርካሪዎቹ በአምቡላንሱ ላይ የሚገኙ የሕክምና መሣሪያዎችን እንዴት መጠቀም እንደሚችሉ እንዲሁም የታካሚውን ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት እንዴት ማሽከርከር እንዳለባቸው ማወቅ ይገባቸዋል።

^ አን.4 የኅዳር 2004 ንቁ! ገጽ 19⁠ን ተመልከት።

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

አስፈላጊውን ትብብር ማድረግ የምትችሉበት መንገድ

ድንገተኛ ሁኔታ ሲያጋጥም ተንቀሳቃሽ የሕክምና ቡድኑ ሕይወት አድን ተግባሩን እንዲያከናውን እገዛ ለማድረግ ልትወስዷቸው ከምትችሏቸው መሠረታዊ እርምጃዎች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፦

1. እርዳታ ለማግኘት ወዲያውኑ ስልክ ደውሉ። በአውሮፓ ኅብረት አገሮች የስልክ ቁጥሩ 112 ሲሆን በዩናይትድ ስቴትስ ደግሞ 911 ነው።

2. ድንገተኛ አደጋ የተፈጠረበትን ቦታ በትክክል ተናገሩ።

3. በግልጽ የሚታዩትን የችግሩን ምልክቶች ግለጹ። ለምሳሌ ያህል፣ ሰውየው ትንፋሹ አለ? ራሱን ስቷል? ደም እየፈሰሰው ነው?

4. ግለሰቡ ብዙ ቦታዎች ላይ ጉዳት ከደረሰበት ጉዳቱ የከፋ እንዳይሆን አታንቀሳቅሱት።

5. ግለሰቡ እያስመለሰ ከሆነ ትን ብሎት እንዳይሞት በጎኑ አስተኙት።