በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የተሻለ ሥራ መረጥኩ

የተሻለ ሥራ መረጥኩ

የተሻለ ሥራ መረጥኩ

ፕላመን ኮስታዲኖቭ እንደተናገረው

ንቅልፌ ስነቃ እኩለ ቀን ሊሆን ተቃርቦ ነበር። ባዶ ጠርሙሶች በወለሉ ላይ በየቦታው ተዝረክርከው የነበረ ሲሆን ክፍሉም በሲጋራ ጠረን ተሞልቷል። ትናንትና ምሽት ላይ በነበረው ግብዣ ያገኘሁት ከፍተኛ ደስታ ከእንቅልፌ ስነቃ በንኖ ጠፍቷል። ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ብስጭትና ብቸኝነት ተሰማኝ። በዚህ ጊዜ ሁሉም ነገር ትርጉም የለሽ መስሎ ታየኝ! እንዲህ ባለ አሳዛኝ ሁኔታ ውስጥ ልገኝ የቻልኩት እንዴት እንደሆነ እስቲ ላጫውታችሁ።

የ14 ዓመት ልጅ ሳለሁ ሠዓሊ ለመሆን የሥዕል ትምህርት መከታተል ጀመርኩ። ጊዜው 1980 የበጋ ወቅት ነበር። በቡልጋሪያ፣ ትሮያን ከተማ የሚገኘው የሥነ ጥበብ ኮሌጅ እንደተቀበለኝ አባቴ ሲነግረኝ በጣም ተደሰትኩ። በዚያው ዓመት በመከር ወራት ላይ የትውልድ ከተማዬ የሆነችውን ሎቪችን ለቅቄ ወደ ትሮያን ተዛወርኩ።

ከወላጆቼ ርቄ መኖሬና የፈለግሁትን ሁሉ ማድረግ መቻሌ አስደሰተኝ። ሲጋራ ማጨስ እንዲሁም ከትምህርት ቤት ጓደኞቼ ጋር መጠጥ መጠጣት ጀመርኩ፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ የምጠጣው አልኮል መጠን እየጨመረ ሄደ። በትምህርት ቤቱ ውስጥ ሲጋራ ማጨስም ሆነ መጠጥ መጠጣት ክልክል ነበር። እኔ ግን የትምህርት ቤቱን ደንብ መጣስ እንኳ ያስደስተኝ ነበር።

ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ለሥዕል ያለኝ ፍቅር እያደገ ሄደ። የሥዕል ችሎታዬ ይበልጥ የተሻሻለ ከመሆኑም ሌላ ዝነኛ የመሆን ፍላጎትም በውስጤ እያየለ መጣ። በትሮያን የተከታተልኩትን የአምስት ዓመት ትምህርት ሳጠናቅቅ በቡልጋሪያ ዋና ከተማ በሶፊያ በሚገኘው የሥነ ጥበብ አካዳሚ ገብቼ ትምህርቴን ለመቀጠል ፈለግሁ። ይህ አካዳሚ በመላው ቡልጋሪያ ካሉት የማሠልጠኛ ማዕከሎች ሁሉ የበለጠ ስመ ጥር ነበር። በ1988 ከመላ አገሪቱ ከተመረጡ ስምንት ስኬታማ ዕጩዎች መካከል አንዱ በመሆን አካዳሚውን መቀላቀል ቻልኩ። እዚህ ስኬት ላይ በመድረሴ ኩራት ተሰምቶኝ ነበር! አንድ ቀን ራሴን በመስታወት እየተመለከትኩ በኩራት ስሜት ‘እንግዲህ ፕላመን፣ ዝነኛ ሠዓሊ እንደምትሆን ምንም ጥርጥር የለውም!’ አልኩ።

ያዳበርኩት አሮጌ ስብዕና

ብዙም ሳይቆይ ጥቁር ልብስ መልበስ ጀመርኩ፤ ፀጉሬንና ጺሜን አሳደግሁ። ይህ የአንድ የሥነ ጥበብ ባለሙያ ሊያደርገው የሚገባ ነገር እንደሆነ ተደርጎ ይቆጠር ነበር። የሥነ ጥበብ ሰው የሚከተለውን የሂፒ ዓይነት አኗኗር መከተል ጀመርኩ። ይህ ደግሞ ሠዓሊዎች በሚኖሩበት ሠፈር ቤት መከራየትንና ቤቱ በተቻለ መጠን የተመሰቃቀለና የተዝረከረከ እንዲሆን ማድረግን ይጨምራል። ከዚያም ሦስት ልጆች ያላት አንዲት ድመትና አንድ ትንሽ ውሻ ማሳደግ ጀመርኩ። ገንዘብ ማባከን የሕይወቴ ክፍል ሆነ።

ሆኖም ለሥነ ጥበብ የነበረኝ ፍቅር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጣ። በምናቤ የማስበውን በጣም ልዩ የሆነ ዓለም የሚያሳዩ በገሐዱ ዓለም ውስጥ የሌሉ ሥዕሎችን ዘወትር እሠራ ነበር። በመኖሪያ ክፍሌ ግድግዳዎች ላይ እንኳ ሳይቀር ሥዕሎችን እሠራ ነበር። ይህ የአንድ ታላቅ ሥራ ጅምር ነው ብዬ አሰብኩ።

አብረውኝ ከሚማሩ ተማሪዎች ጋር ዘወትር መገባበዝ የሕይወቴ ክፍል ነበር። በመኖሪያ ክፍሌ ውስጥ አዘውትረን እየተሰበሰብን ሙዚቃ እናዳምጥ ብሎም ብዙ አልኮል እንጠጣ ነበር፤ ይህን የምናደርገው ለፈተና በምንዘጋጅበት ጊዜም እንኳ ሳይቀር ነበር። የምናደርጋቸው ፍልስፍና የሚንጸባረቅባቸው ውይይቶች በሙዚቃ፣ በሥነ ጥበብና በሕይወት ዓላማ ዙሪያ ያጠነጠኑ ነበሩ። ብዙውን ጊዜ ከሰው በላይ ስለሆኑ ኃይሎችና ከምድር ውጭ ስለሚኖሩ ፍጥረታት እናወራ ነበር። እነዚህ ውይይቶች ደግሞ በውስጤ ምናባዊ ሐሳቦችን በመጫር ለሚቀጥለው ሥዕሌ አዳዲስ ሐሳቦችን እንዳፈልቅ ይረዱኝ ነበር። የሚሰማኝ ከፍተኛ የደስታ ስሜት በውስጤ ለዘለቄታው እንዲቆይልኝ እፈልግ ነበር፤ ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው ስሜት የሚቆየው ስካሩ እስኪለቀኝ ድረስ ብቻ ነበር። አብዛኛውን ጊዜ ይህ ስሜት በማግስቱ እልም ብሎ ይጠፋል።

እንዲህ በመሰለው አኗኗር ለአሥር ዓመታት ያህል ከቆየሁ በኋላ እርካታ እያጣሁ መጣሁ። ለሥዕሌ ከምጠቀምባቸው ብሩሕ ቀለማት በተቃራኒ ውስጤ እያደር ጨለማ እየሆነ ሄደ፤ ከፍተኛ የሆነ የብቸኝነት ስሜት ይሰማኝ ጀመር። ዝነኛ ሠዓሊ የመሆን ሕልሜም መክሰም ጀመረ። በሐዘን ስሜት ተዋጥኩ፤ በዚህ ሁኔታ ሕይወቴን እንዴት እንደምመራ ግራ ገብቶኝ ነበር። ታሪኬን ስጀምር የገለጽኩት ስሜት የተሰማኝ በዚህ ወቅት ነበር።

እውነት ታደገኝ

በ1990 የሥዕል ሥራዬን በሎቪች ለሕዝብ ለማሳየት ወሰንሁ። በሶፊያ በሚገኘው አካዳሚ የተዋወቅኋትን ያኒታ የተባለች ሴት በሥዕል ኤግዚቢሽኑ ላይ እንድትካፈል ጋበዝኳት፤ ያኒታ የተወለደችው በሎቪች ከተማ ነው። እኔና ያኒታ ከኤግዚቢሽኑ በኋላ ለመጨዋወት በአቅራቢያው ወደሚገኝ አንድ ምግብ ቤት ሄድን። በጭውውታችን መሃል ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ስታጠና የተማረቻቸውን ነገሮች ትነግረኝ ጀመር። መጽሐፍ ቅዱስ ወደፊት እንደሚመጣ ስለሚናገረው አዲስ ዓለም አስረዳችኝ። ከእሷ ጋር ያደረግነው ውይይት የማወቅ ፍላጎቴን ቀሰቀሰው።

ያኒታ በሶፊያ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናቷን ቀጠለች፤ ለእኔም በየጊዜው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን ታመጣልኝ ነበር። “እነሆ፣ ሁሉን አዲስ አደርጋለሁ” የተሰኘውን ብሮሹር ምን ያህል በጉጉት እንዳነበብኩት ፈጽሞ አይረሳኝም። በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ * የተባለውን መጽሐፍ በጥቂት ቀናት ውስጥ እንዴት በከፍተኛ ጉጉት እንዳነበብኩት እስካሁን ድረስ ትዝ ይለኛል። አምላክ መኖሩን አምኜ ለመቀበል አልተቸገርኩም፤ በመሆኑም እንዴት መጸለይ እንደሚቻል ወዲያውኑ ማወቅ ፈለግሁ። ለመጀመሪያ ጊዜ ያቀረብኩትን ጸሎት አስታውሳለሁ። በጉልበቴ ተንበርክኬ የሚያሳስቡኝን ነገሮች ከልቤ ለይሖዋ ነገርኩት። አምላክ ጸሎቴን እየሰማ እንደነበር ቅንጣት ታክል እንኳ አልተጠራጠርኩም። የብቸኝነት ስሜቴ እየጠፋ በምትኩ ውስጣዊ ደስታና ሰላም ይሰማኝ ጀመር።

ያኒታ፣ በሶፊያ ከሚኖሩ የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ባልና ሚስት ጋር አስተዋወቀችኝ። እነሱም መጽሐፍ ቅዱስን እንዳጠና ሐሳብ ያቀረቡልኝ ሲሆን በስብሰባቸውም ላይ እንድገኝ ጋበዙኝ። በሰኔ ወር 1991 ለመጀመሪያ ጊዜ ስብሰባ ላይ የተገኘሁበትን ቀን አስታውሰዋለሁ። ስብሰባው ከመጀመሩ ከሁለት ሰዓት በፊት ቀድሜ ደረስኩና በአንዲት ትንሽ መናፈሻ ውስጥ ጠበቅኳቸው። በዚያን ሰዓት ጭንቀት፣ ያለመረጋጋትና የጥርጣሬ ስሜት ይሰማኝ የነበረ ከመሆኑም ሌላ ‘ሰዎቹ በጥሩ ሁኔታ ይቀበሉኝ ይሆን?’ የሚል ስጋት አድሮብኝ ነበር። ምንም እንኳ ውጫዊ ገጽታዬ የሂፒዎች ዓይነት ቢሆንም በስብሰባው ላይ ሁሉም ሰው ሞቅ ባለ መንፈስ ሲቀበለኝ ተገረምኩ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በስብሰባዎች ላይ አዘውትሬ እገኝ የነበረ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስን በሳምንት ሁለት ጊዜ አጠና ነበር።

ለመጀመሪያ ጊዜ የራሴ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂ ሳገኝ በጣም ተደሰትኩ። ከዚያ በፊት ባሳለፍኩት ዕድሜዬ በሙሉ በተራራው ስብከት ላይ የተገለጸው ዓይነት ግሩምና ልብ የሚነካ ጥበብ የተንጸባረቀበት ሌላ ጽሑፍ አንብቤ አላውቅም! በጥናቴ እየገፋሁ ስሄድ በኤፌሶን 4:23 ላይ እንደተገለጸው የአምላክ ቃል ያለውን የመለወጥ ኃይል በእኔ ላይ ሲሠራ አይቻለሁ፤ ጥቅሱ “አእምሯችሁን በሚያሠራው ኃይል እየታደሳችሁ መሄድ አለባችሁ” ይላል። ሲጋራ ማጨስ አቆምኩ፤ እንዲሁም የተዝረከረከ ውጫዊ ገጽታዬን ለወጥኩ። እንዲያውም ያደረግኩት ለውጥ ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ አንድ ቀን አባቴ በሎቪች በሚገኘው ባቡር ጣቢያ ሊቀበለኝ ሲመጣ ሊያውቀኝ ስላልቻለ በአጠገቤ አልፎኝ ሄደ።

በዙሪያዬ ያሉትን ነገሮች ልብ ብዬ ማየት ጀመርኩ። የተመሰቃቀለው ክፍሌ፣ ሥዕል የተሳለባቸው ግድግዳዎች እንዲሁም የሲጋራ መጥፎ ጠረን የፈጠራ ችሎታዬን አላነሳሱልኝም። ሁሉንም ነገር ለማጽዳት ልቤ ተነሳሳ። ግድግዳዎቹን ነጭ ቀለም ቀባኋቸው፤ በዚህም የተነሳ በግድግዳው ላይ ስዬው የነበረ ሦስት ዓይን ያለው እንግዳ ፍጥረት ተሸፈነ።

ብዙም ሳይቆይ ጓደኞቼ እርግፍ አድርገው ተዉኝ፤ ሆኖም በእነሱ ምትክ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ በርካታ ወዳጆችን ያገኘሁ ሲሆን እነሱም እስከ ዛሬ ድረስ የምቀርባቸው ጓደኞቼ ናቸው። እንዲህ ያለ የሚያንጽ ወዳጅነት በመመሥረቴም ፈጣን እድገት ማድረግ ቻልኩ። መጋቢት 22, 1992 ቡልጋሪያ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በተደረገው የይሖዋ ምሥክሮች ትልቅ ስብሰባ ላይ ተጠመቅሁ፤ ስብሰባው የተካሄደው በፕሎቭዲቭ ከተማ ነበር።

ወደ ሎቪች መመለስ

ለአንድ ሠዓሊ በትንሽ ከተማ ውስጥ መተዳደሪያ ማግኘት ቀላል እንደማይሆንለት ባውቅም ከተመረቅሁ በኋላ ወደ ሎቪች ለመመለስ ወሰንኩ። በአንድ በኩል በሥዕል ጥሩ የሚባል ሥራ ማግኘት በሌላ በኩል ደግሞ በሕይወቴ ውስጥ የአምላክን መንግሥት እያስቀደምኩ መኖር በጣም አስቸጋሪ እንደሚሆንብኝ ተገነዘብኩ። በመሆኑም ሥራዬን በመቀየር ፈቃደኛ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪ ለመሆን ወሰንኩ። በሥነ ጥበብ አካዳሚ ውስጥ በነበርኩበት ጊዜ ከእኔ ሦስት ዓመት ቀድማ የተመረቀችው ያኒታ በሎቪች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች በቅንዓት ታስተምር ነበር። በወቅቱ በዚያ ከተማ የነበረችው የይሖዋ ምሥክር እሷ ብቻ ነበረች።

ወደ ሎቪች ተመልሼ በሄድኩበት ወቅት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን የሚያጠኑ የተወሰኑ ሰዎች ነበሩ። ለሰዎች ቤታቸው ድረስ እየሄድኩ ያገኘሁትን የወደፊት ተስፋ መናገር በጣም ያስደስተኝ ነበር። ስለዚህ እኔም ሙሉ ጊዜዬን ለዚህ ሥራ ለማዋል ወሰንኩ።

ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ተከሰቱ። ሃይማኖታዊ ድርጅት በመሆን ያገኘነው ሕጋዊ እውቅና በ1994 የተሰረዘ ሲሆን በመገናኛ ብዙኃን መጠነ ሰፊ የሆነ ስም የማጥፋት ዘመቻ ተከፈተብን። * የይሖዋ ምሥክሮች ብዙውን ጊዜ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ይወሰዱ የነበረ ከመሆኑም ሌላ ጽሑፎቻችን ይወረሱ ነበር። በእነዚህ አስቸጋሪ ጊዜያት ሕጋዊ በሆነ መንገድ ስብሰባ ለማድረግ ለሕዝብ ክፍት በሆኑ የመሰብሰቢያ ቦታዎች መጠቀም አልቻልንም ነበር። እንደዚያም ሆኖ ከያኒታ ቤት አጠገብ በምትገኝ 12 ካሬ ሜትር ስፋት ባላት ክፍል ውስጥ አዘውትረን ስብሰባዎችን እናካሂድ ነበር። በአንድ ወቅት በዚያች አነስተኛ ክፍል ውስጥ 42 ሆነን ተሰብስበናል። መዝሙሮች ስንዘምር ጎረቤት ላለመረበሽ መስኮቶቹን እንዘጋ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ውጭ ያለው ሙቀት ሲጨምር በክፍሉ ውስጥ ከፍተኛ ሙቀት የሚኖር ቢሆንም አንድ ላይ በመሆናችን ደስተኞች ነበርን።

ከይሖዋ ያገኘኋቸው በረከቶች

ያኒታ ለእውነተኛው አምልኮ የነበራትን ቅንዓት በጣም አደንቅ ስለነበር ከጊዜ በኋላ እርስ በርስ መዋደድ ጀመርን። በመሆኑም ግንቦት 11, 1996 ተጋባን። ምንም እንኳ የባሕርይ ልዩነቶች ያሉን ቢሆንም አንዳችን የሌላውን ጉድለት ግሩም በሆነ መንገድ ማሟላት ችለናል። ያኒታ የቅርብ ጓደኛዬና ረዳቴ ናት። ይሖዋ ‘ከቀይ ዕንቁ እጅግ የሚበልጥ’ ዋጋ ያላት ሚስት ስለሰጠኝ አመስጋኝ ነኝ።—ምሳሌ 31:10

ከቀድሞ ጓደኞቼ መካከል አንዳንዶቹ በአንድ ወቅት እመኘው በነበረው የሠዓሊነት ሙያ ላይ ተሠማርተዋል። ይሁንና የተሻለ ነው ብዬ የማስበውን ሥራ በመምረጤ በጣም ደስተኛ ነኝ። ብዙ ሰዎች የሕይወትን ዓላማ እንዲያውቁ የረዳሁ ሲሆን እነዚህ ሰዎች በአሁኑ ጊዜ መንፈሳዊ ወንድሞቼና እህቶቼ ናቸው። ሠዓሊ በመሆን ላገኘው የምችለው የትኛውም ዝና ወይም ታዋቂነት ይሖዋን በማገልገል ካገኘሁት በረከት ጋር ሊወዳደር አይችልም። ታላቅ አርቲስት የሆነውን ይሖዋ አምላክን በቅርብ ማወቅ በመቻሌ ደስተኛ ነኝ።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.14 ሁለቱም በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጁ ናቸው። ለዘላለም መኖር የተሰኘው መጽሐፍ አሁን መታተም አቁሟል።

^ አን.22 የይሖዋ ምሥክሮች ድርጅት በ1998 ስትራዝቡር ለሚገኘው የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ይግባኝ ካቀረበ በኋላ በቡልጋሪያ ሕጋዊ እውቅና አግኝቷል።

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከባለቤቴ ከያኒታ ጋር