በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

“በ2008 በዓለም ዙሪያ ለወታደራዊ አገልግሎት የወጣው ጠቅላላ ወጪ 1464 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር እንደነበር ተገምቷል። ይህ ደግሞ ወጪው ከ1999 ወዲህ 45 በመቶ . . . ከፍ ማለቱን ያሳያል።”—የስቶክሆልም ዓለም አቀፍ የሰላም ምርምር ተቋም፣ ስዊድን

“ጉግል [Google] እንደገለጸው ከሆነ በየቀኑ በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠሩ ድረ ገጾች [በኢንተርኔት ላይ] ይጨመራሉ።”—ኒው ሳይንቲስት፣ ብሪታንያ

“[ባለፈው ዓመት] በዓለም ዙሪያ በየዕለቱ 1 020 ሚሊዮን ሰዎች በመራባቸው በ2009 ከፍተኛ የረሀብተኞች ቁጥር ተመዝግቧል።”—የተባበሩት መንግሥታት የምግብና የእርሻ ድርጅት፣ ጣሊያን

በክሎኒንግ የተገኘው የመጀመሪያው ግመል

ተመራማሪዎች በ1996 ክሎኒንግ በሚባለው ዘዴ ተጠቅመው መጀመሪያ አንድ በግ በላብራቶሪ ከሠሩ በኋላ በዚሁ ዘዴ ተጠቅመው ላሞችን፣ በጎችንና ፈረሶችን ጨምሮ ሌሎች በርካታ አጥቢ እንስሳትን ሠርተዋል። አሁን ደግሞ በዱባይ የእንስሳት ሕክምና ምርምር ተቋም የሚገኙ የሳይንስ ሊቃውንት በክሎኒንግ ዘዴ ተጠቅመው ለመጀመሪያ ጊዜ አንዲት ግመል ሠርተዋል። በዚህ መንገድ የተገኘችው እንስት ግመል በአረብኛ ኢንጃዝ የሚል ስም የተሰጣት ሲሆን ትርጉሙም “ስኬት” ማለት ነው። “በክሎኒንግ ዘዴ ተጠቅሞ እንስሳትን በላብራቶሪ መሥራት ከሙከራ አልፎ ሄዷል” በማለት ዘ ናሽናል የተሰኘው የአቡዳቢ ጋዜጣ ይናገራል። “ለወደፊቱ ይህ ተቋም በክሎኒንግ ዘዴ በመጠቀም ለውድድር ተፈላጊ የሆኑና ወተት የሚሰጡ ግመሎች ዝርያ እንዳይጠፋ ማድረግ የሚቻልበትን መንገድ ይመረምራል።”

የሳተላይቶች “ግጭት

“ከመሬት በላይ ያለው የምሕዋር መንገድ ባለፉት ዓመታት እያደር እየተጨናነቀ ቢመጣም ሁለት ሳተላይቶች የካቲት [2009] ላይ ከባድ ግጭት እስካጋጠማቸው ድረስ ሁኔታው የከፋ አልነበረም” በማለት ሳይንስ ኒውስ ዘግቧል። ከሳይቤሪያ ወደ ሰማይ 800 ኪሎ ሜትር ያህል ርቀት ላይ ትገኝ የነበረች በሥራ ላይ ያለች አንዲት የአሜሪካ የመገናኛ ሳተላይት ከማይሠራ አንድ የሩሲያ ወታደራዊ መሣሪያ ጋር ተጋጨች። በአደጋው ምክንያት 700 የሚያህሉ ትላልቅ ስብርባሪዎች ሰማዩን አጥለቀለቁት። በሕዋ ውስጥ ስብርባሪዎች በበዙ ቁጥር አደጋ የመድረሱ አጋጣሚም የዚያኑ ያህል ከፍ ይላል። የሳተላይት መከታተያ ጣቢያዎች በአሁኑ ጊዜ በሕዋ ውስጥ ስፋታቸው ከ10 ሴንቲ ሜትር የሚበልጥ 18,000 የሚሆኑ ስብርባሪዎች እንዳሉ ደርሰውበታል። ሆኖም በከፍተኛ ፍጥነት የሚጓዝ መጠኑ የአተር ፍሬ የሚያክል አንድ ስባሪ እንኳ ከሳተላይቶች ሌላው ቀርቶ ሰዎች ከሚያበሯቸው የበረራ መሣሪያዎች ጋር ቢጋጭ ከፍተኛ አደጋ ሊያስከትል ይችላል።

የመኪና ሞተር ማጥፊያዎች

“የሞባይል ስልክ ክፍያቸውን ችላ የሚሉት ጥቂት ብቻ ናቸው፤ ምክንያቱም መክፈል ሲተዉ ስልኩ እንደሚቆረጥ ያውቃሉ” በማለት ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል ይዘግባል። በአሁኑ ጊዜ ይህ ዘዴ ለመኪኖችም በሥራ ላይ እየዋለ ነው። “ያገለገሉ መኪኖችን የሚሸጡ ነጋዴዎች መኪናውን የገዛው ሰው ዕዳውን ሳይከፍል በጣም ከዘገየ በርቀት መቆጣጠሪያ ተጠቅመው የመኪናውን ሞተር ለማጥፋት የሚያስችላቸውን መሣሪያ መኪኖቹ ላይ እየገጠሙ ነው” በማለት ጋዜጣው ይናገራል። ነጋዴዎቹ ይከፍላሉ ብለው የማይተማመኑባቸውን ደንበኞች ለማስከፈል ከሚጠቀሙባቸው ዘዴዎች መካከል አንዱ እነዚህን መሣሪያዎች ከመኪናው ኳድሮ ጋር በሽቦ ማገናኘት ሲሆን የዱቤ ክፍያው ሲያልቅ መሣሪያዎቹ ይነሳሉ። ይሁን እንጂ ጆርናል እንደዘገበው ተቆጣጣሪዎቹ አብዛኛውን ጊዜ እነዚህን የመኪና ሞተር ማጥፊያዎች ተጠቅመው መኪናው እንዳይሠራ አያደርጉም። ከዚህ ይልቅ የመሣሪያዎቹን ብልጭ ድርግም የሚሉ መብራቶችና የማስጠንቀቂያ ድምፆች መጠቀም “ደንበኞችን በጊዜው እንዲከፍሉ ለመጎትጎት” የሚረዳ ውጤታማ ዘዴ ሆኖ አግኝተውታል።