በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ከሥራ አሰናብተንሃል”

“ከሥራ አሰናብተንሃል”

“ከሥራ አሰናብተንሃል”

አስተዳደሩ ታታሪው ፍሬድ እያለ ይጠራው ነበር። * ፍሬድ ልዩ ችሎታ ያለው መሆኑ በዚህ ድርጅት ውስጥ ተቀጥሮ በሠራባቸው ስድስት ዓመታት ውስጥ ድርጅቱን ከከፍተኛ ወጪ አድኗል። ስለዚህ ፍሬድ ወደ አስተዳደሩ ቢሮ ሲጠራ የደሞዝ ጭማሪ ወይም የሥራ እድገት አገኛለሁ ብሎ ጠብቆ ነበር። ይሁንና አስተዳደሩ በድንገት “ከሥራ አሰናብተንሃል” ብሎ አረዳው።

ፍሬድ ጆሮውን ማመን አቃተው። “ጥሩ ደሞዝ ይከፈለኝ የነበረ ሲሆን በሥራዬም ደስተኛ ነበርኩ፤ ሆኖም ሁሉ ነገር ከመቅፅበት ተለወጠ” በማለት ተናግሯል። በኋላም ፍሬድ ከሥራ መባረሩን ለባለቤቱ ለአዴሌ ሲነግራት እሷም ሰማይ ምድሩ ዞረባት። አዴሌ ያን ጊዜ የተሰማትን ስትናገር እንዲህ ትላለች፦ “ደሜ ከሰውነቴ ፈስሶ ያለቀ ያህል ሆኖ ተሰማኝ። ‘እስቲ አሁን ምንድን ነው የምናደርገው?’ ብዬ አሰብኩ።”

በዓለም ዙሪያ በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የፍሬድ ዓይነት ሁኔታ እንደሚያጋጥማቸው ከታች የሚገኘው ሠንጠረዥ ይጠቁማል። ሆኖም አኃዛዊ መረጃ ብቻውን ከሥራ መፈናቀል በሰዎች ላይ የሚያስከትለውን የስሜት ቀውስ ሊጠቁም አይችልም። ከፔሩ በስደት የመጣውና በኒው ዮርክ ሲቲ በሚገኝ በአንድ ትልቅ ሆቴል ውስጥ ለ18 ዓመታት ሲሠራ ከቆየ በኋላ ከሥራ ገበታው የተባረረውን ራውልን እንመልከት። ራውል ሥራ ቢያፈላልግም አልተሳካለትም። “ወደ 30 ለሚሆኑ ዓመታት ለቤተሰቤ የሚያስፈልገውን ሳቀርብ ኖሬያለሁ። አሁን ግን ምንም የማይሳካለት ሰው እንደሆንኩ ይሰማኛል” በማለት ተናግሯል።

የራውል ተሞክሮ ከሥራ የተፈናቀሉ ሰዎች በደንብ የሚያውቁትን አንድ ሐቅ ያስገነዝባል፤ ይኸውም ከሥራ መፈናቀል ከገንዘብ ችግር የበለጠ የሚያስከትለው ሌላ ነገር አለ። ብዙውን ጊዜ ከባድ የስሜት ሥቃይ ያስከትላል። ማቲው ከሥራ ከተፈናቀለ ከሦስት ዓመት በላይ ሆኖታል፤ ባለቤቱ ረኔ እንዲህ ብላለች፦ “ዋጋ ቢስ እንደሆንኩ ይሰማኝ ጀመር። ምንም ከሌላችሁ፣ ሰዎች ከምንም አይቆጥሯችሁም፤ ብዙም ሳይቆይ እናንተም ስለ ራሳችሁ ተመሳሳይ ስሜት ያድርባችኋል።”

ከሥራ የመፈናቀል ዕጣ የደረሰበት ሰው የሚያጋጥመው የስሜት ቀውስ ሳያንስ ዝቅተኛ ኑሮ ለመኖር ይገደዳል። ፍሬድ “ገንዘብ በነበረን ጊዜ ቁጠባ ስለሚባል ነገር አስበን አናውቅም። ወጪው እንዳለ ሆኖ ሥራ ሲታጣ ግን ኑሮን ቀላል ከማድረግ ውጪ ሌላ አማራጭ አልነበረንም።”

ሥራ አፈላልገህ እስክታገኝ ድረስ ከሥራ መፈናቀል በአእምሮህና በስሜትህ ላይ የሚያስከትለውን ጫና መቋቋም ያስፈልግሃል። በተጨማሪም የምታገኘውን አብቃቅተህ ለመኖር ጥረት ማድረግ ይኖርብሃል። በመጀመሪያ ሥራ ማጣት በስሜትህ ላይ የሚያስከትለውን ጫና ለመቋቋም ልትወስዳቸው የሚገቡህን ሁለት አስፈላጊ እርምጃዎች እንመልከት።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.2 በዚህ ተከታታይ ርዕሰ ትምህርት ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንድ ስሞች ተለውጠዋል።

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ግራፍ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

በ2008 በሦስት አገሮች ውስጥ ብቻ እንኳ የነበረው የሥራ አጥ ቁጥር

ጃፓን 2,650,000

ስፔን 2,590,000

ዩናይትድ ስቴትስ 8,924,000