በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የእሳት ራት ዓይን

የእሳት ራት ዓይን

ንድፍ አውጪ አለው?

የእሳት ራት ዓይን

አብዛኞቹ የእሳት ራቶች ብዙውን ጊዜ የሚበሩት ማታ ማታ ነው። አንዳንድ በማታ የሚንቀሳቀሱ ፍጥረታት ዓይናቸው ብርሃን ሲያርፍበት መልሶ ስለሚያንጸባርቅ ማንነታቸውና መኖራቸው ይጋለጣል። የእሳት ራት ግን ራሱን የሚሰውርበት መንገድ አለው፤ ኮርኒያ የሚባለው የዓይኑ ክፍል ብርሃን እምብዛም አያንጸባርቅም።

እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ የእሳት ራት ዓይን ለየት ያለ ኮርኒያ አለው፤ ኮርኒያው ስድስት ጎኖች ያሏቸውና በሥርዓት የተደረደሩ በዓይን የማይታዩ ጉብታዎች አሉት። በዩናይትድ ስቴትስ የፍሎሪዳ ዩኒቨርሲቲ የኬሚካል ምሕንድስና ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ፔንግ ጂያንግ ጉብታዎቹ “በዓይናችን ልናየው የምንችለው ብርሃን ካለው የሞገድ ርዝመት ያነሱ ናቸው” ብለዋል። እነዚህ ጉብታዎች የተደረደሩበት መንገድና መጠናቸው የእሳት ራት ዓይን ከተለያዩ የሞገድ ርዝመቶችና አቅጣጫዎች የሚመጡትን የብርሃን ጨረሮች ውጦ ለማስቀረት ያስችሉታል። ጥቃቅኖቹ ጉብታዎች ርዝመታቸው ከ200 እስከ 300 ናኖሜትር ብቻ ነው። ይህን ለማነጻጸር ያህል የአንድ ሰው ፀጉር በአማካይ 80,000 ናኖሜትር የሚያህል ውፍረት አለው።

መሐንዲሶች የእሳት ራትን ኮርኒያ አፈጣጠር በጥልቀት መረዳታቸው በብዙ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች ላይ እያገለገሉ ያሉትን ላይት ኤሚቲንግ ዳዮድስ (ኤል ኢ ዲ) እንዲሁም ሊክዊድ ክሪስታል ዲስፕሌይ (ኤል ሲ ዲ) አሠራር ለማሻሻል እንደሚረዳቸው ተስፋ ያደርጋሉ። ከዚህም በላይ የእሳት ራትን ዓይን ንድፍ በፀሐይ ኃይል ለሚሠሩ የኤሌክትሪክ ማመንጫዎች መጠቀም ይቻላል። ከሲሊከን የሚሠሩ የፀሐይ ኃይል መቀበያ መሣሪያዎች ከሚያርፍባቸው የፀሐይ ብርሃን እስከ 35 በመቶ የሚሆነውን አንጸባርቀው ይመልሳሉ፤ ይህ ደግሞ በቀላሉ የሚታይ ብክነት አይደለም። ይሁን እንጂ የእሳት ራት ዓይን ኮርኒያ ውስጥ ያሉት ጉብታዎች የተደረደሩበትን መንገድ ያጠኑት ጂያንግና ባልደረቦቻቸው ከ3 በመቶ ያነሰ ብርሃን ብቻ የሚያንጸባርቅ ሲሊከን መሥራት ችለዋል። ጂያንግ “እንደ እነዚህ ካሉት የተፈጥሮ መዋቅሮች በጣም ብዙ ትምህርት ማግኘት እንችላለን” በማለት ተናግረዋል።

ታዲያ ምን ይመስልሃል? ብርሃንን ውጦ የማስቀረት ንድፍ ያለው የእሳት ራት ዓይን እንዲሁ በአጋጣሚ የተገኘ ነው? ወይስ ንድፍ አውጪ አለው?

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የእሳት ራት ዓይን ስድስት ጎኖች ያሏቸውና በሥርዓት የተደረደሩ በዓይን የማይታዩ ጉብታዎች ያሉት ኮርኒያ አለው

[በገጽ 30 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ከፀሐይ ብርሃን ኃይል ለማመንጨት የሚረዳውና ብርሃንን ውጦ የማስቀረት ባሕርይ ያለው የሲሊከን ንብርብር

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Moth eye close-up: Courtesy of Dartmouth Electron Microscope Facility; silicon close-up: Courtesy Peng Jiang