በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክ በመከራዬ ሁሉ አጽናንቶኛል

አምላክ በመከራዬ ሁሉ አጽናንቶኛል

አምላክ በመከራዬ ሁሉ አጽናንቶኛል

ቪክቶሪያ ኮጆኢ እንደተናገረችው

አንድ ዶክተር እናቴን “ከዚህ በላይ ለልጅሽ ምንም ልናደርግላት አንችልም። ሕይወቷን ሙሉ ክራንችና እግር ላይ የሚታሠር ብረት መጠቀም ያስፈልጋታል” በማለት ነገራት። ይህንን ስሰማ በጣም ደነገጥኩኝ! በእግሬ መራመድ የማልችል ከሆነ ምን ሊውጠኝ ነው?

ክሲኮ ውስጥ በቺያፓስ ግዛት ታፓቹላ በምትባል ከተማ ኅዳር 17, 1949 ተወለድኩ። ወላጆቼ ካሏቸው አራት ልጆች መካከል የመጀመሪያዋ ስሆን ጤናማና ፍልቅልቅ ልጅ ነበርኩ። ይሁንና ስድስት ወር ሲሞላኝ በድንገት መዳኽ ያቆምኩ ከመሆኑም በላይ እንቅስቃሴዬ ውስን ሆነ። ከሁለት ወር በኋላ ጭራሽ መንቀሳቀስ ተሳነኝ። በታፓቹላ የሚገኙ ሌሎች ሕፃናትም ተመሳሳይ ችግር ስላጋጠማቸው በአካባቢው ያሉ ዶክተሮች በሁኔታው ግራ ተጋቡ። በዚህ ምክንያት አንድ የአጥንት ስፔሻሊስት ከሜክሲኮ ሲቲ መጥቶ ምርመራ አደረገልን። ችግሩ ፖሊዮማይላይትስ ወይም ፖሊዮ የሚባል በሽታ መሆኑ ታወቀ።

የሦስት ዓመት ልጅ እያለሁ ወገቤ አካባቢ፣ ጉልበቴና ቁርጭምጭሚቴ ላይ ቀዶ ሕክምና ተደረገልኝ። ከጊዜ በኋላ ቀኝ ትከሻዬም በጣም ተጎዳ። ስድስት ዓመት ሲሞላኝ የሕክምና ክትትል እንዲደረግልኝ በሜክሲኮ ሲቲ ውስጥ ወደሚገኝ አንድ የሕፃናት ሆስፒታል ተወሰድኩ። እናቴ ቺያፓስ ውስጥ ባለ አንድ የእርሻ ቦታ ትሠራ ስለነበር እኔ ከአያቴ ጋር በሜክሲኮ ሲቲ ቀረሁ። ይሁንና አብዛኛውን ጊዜ የማሳልፈው በሆስፒታል ውስጥ ነበር።

ስምንት ዓመት ገደማ ሲሆነኝ የጤንነቴ ሁኔታ መሻሻል ማሳየት ጀምሮ ነበር። ከጊዜ በኋላ ግን ጤንነቴ እያሽቆለቆለ ሄዶ የበፊቱን ያህል እንኳ መንቀሳቀስ ተሳነኝ። ዶክተሮቹ ሕይወቴን ሙሉ ክራንችና እግር ላይ የሚታሠር ብረት መጠቀም እንደሚያስፈልገኝ የተናገሩት በዚህ ጊዜ ነበር።

ገና 15 ዓመት ሳይሞላኝ 25 ጊዜ ቀዶ ሕክምና ተደርጎልኛል። እነዚህ ቀዶ ሕክምናዎች የተደረጉልኝ በአከርካሪዬ፣ በእግሬ፣ በጉልበቴ፣ በቁርጭምጭሚቴና በእግሬ ጣቶች ላይ ነበር። እያንዳንዱን ቀዶ ሕክምና ካደረኩኝ በኋላ ለማገገም ረዘም ያለ ጊዜ ይወስድብኝ ነበር። አንድ ጊዜ ቀዶ ሕክምና ከተደረገልኝ በኋላ እግሬ በጀሶ ታስሮ ነበር። ጀሶው ከተፈታ በኋላ ከባድ የሆነ አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ነበረብኝ።

እውነተኛ ማጽናኛ አገኘሁ

አንደኛውን ቀዶ ሕክምና ያደረኩት የ11 ዓመት ልጅ ሳለሁ ነበር፤ በዚህ ጊዜ እናቴ ልትጠይቀኝ መጣች። ኢየሱስ በሽተኞችን እንደፈወሰ ሌላው ቀርቶ ሽባ የሆኑትን እንኳ እንዲራመዱ ማድረግ እንደቻለ በወቅቱ ተምራ ነበር። እናቴ ይህን ልታውቅ የቻለችው በይሖዋ ምሥክሮች የሚዘጋጀውን መጠበቂያ ግንብ የተባለ መጽሔት አንብባ ሲሆን ለእኔም አንድ መጽሔት ሰጠችኝ። መጽሔቱን ትራሴ ሥር የደበቅሁት ቢሆንም አንድ ቀን ካስቀመጥኩበት ቦታ አጣሁት። መጽሔቱን ያጣሁት ነርሶቹ ስለወሰዱት ነበር። ነርሶቹ መጽሔቱን በማንበቤ ተቆጡኝ።

ከአንድ ዓመት በኋላ እናቴ ልትጠይቀኝ ከቺያፓስ መጣች። በወቅቱ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀምራ ነበር። በዚህ ጊዜ ፍሮም ፓራዳይዝ ሎስት ቱ ፓራዳይዝ ሪጌይንድ የሚባለውን መጽሐፍ አመጣችልኝ። * ከዚያም “ኢየሱስ ከሕመምሽ ፈውሶሽ አምላክ ቃል በገባው አዲስ ዓለም ውስጥ መኖር የምትፈልጊ ከሆነ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት አለብሽ” አለችኝ። አያቴ ብትቃወምም 14 ዓመት ገደማ ሲሆነኝ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ማጥናት ጀመርኩ። በነበርኩበት ሆስፒታል ውስጥ ሕክምና የሚሰጠው ለትናንሽ ልጆች ብቻ ስለነበር በቀጣዩ ዓመት ሆስፒታሉን ለቅቄ መውጣት ግድ ሆነብኝ።

ተፈታታኝ ሁኔታዎችን መቋቋም

ከዚያ በኋላ ያጋጠሙኝ ሁኔታዎች በጣም አስጨናቂ ነበሩ። አያቴ ትቃወመኝ ስለነበር ወደ ቺያፓስ ተመልሼ ከወላጆቼ ጋር መኖር ነበረብኝ። አባቴ የአልኮል መጠጥ ሱሰኛ ስለነበር እዚያም ቢሆን ከችግር ነፃ አልሆንኩም። በአንድ ወቅት በሕይወት መኖር ስላስጠላኝ ራሴን በመርዝ ለማጥፋት አሰብኩኝ። ይሁንና በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቴ ስገፋ አመለካከቴ እየተቀየረ መጣ። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ገነት የሚናገረው ተስፋ ደስተኛ እንድሆን አደረገኝ።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለውን ዕጹብ ድንቅ የሆነ ተስፋ ለሌሎች መናገር ጀመርኩ። (ኢሳይያስ 2:4፤ 9:6, 7፤ ራእይ 21:3, 4) ከጊዜ በኋላ ግንቦት 8, 1968 ማለትም በ18 ዓመቴ ተጠምቄ የይሖዋ ምሥክር ሆንኩ። ከ1974 ጀምሮ በሕይወት ለመቀጠል ምክንያት የሆነኝን ተስፋ ለሌሎች በማካፈሉ ሥራ በየወሩ ከ70 ሰዓት በላይ አሳልፍ ነበር።

ውጤታማና አስደሳች የሆነ ሕይወት

ከጊዜ በኋላ እኔና እናቴ፣ በሜክሲኮና በዩናይትድ ስቴትስ ድንበር አቅራቢያ ወደምትገኘው ቲዩዋና የተባለች ከተማ ተዛወርን። በዚያም ከሁኔታችን ጋር የሚስማማ ቦታ አግኝተን አብረን መኖር ጀመርን። በክራንች እንዲሁም እግሬ ላይ በታሰረው ብረት እየታገዝኩ ቤት ውስጥ የምንቀሳቀስ ሲሆን ተሽከርካሪ ወንበር ላይ ሆኜ ደግሞ ምግብ ማብሰል፣ ልብሶቼን ማጠብና መተኮስ እችላለሁ። ወደ አገልግሎት ስወጣ ደግሞ እኔ ላለሁበት ሁኔታ ተስማሚ ሆና በተሠራች በኤሌክትሪክ የምትንቀሳቀስ ተሽከርካሪ እጠቀማለሁ።

የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት በመንገድ ላይና በቤታቸው ለማገኛቸው ሰዎች የምናገር ከመሆኑም ባሻገር በአቅራቢያችን ወደሚገኝ አንድ ሆስፒታል አዘውትሬ በመሄድ ሕክምና ለማግኘት ወረፋ ከሚጠብቁ ሰዎች ጋር መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይት አደርጋለሁ። ከእነሱ ጋር የማደርገውን ውይይት ሳበቃ በኤሌክትሪክ የምትሠራውን ተሽከርካሪዬን እየነዳሁ አንዳንድ የሚያስፈልጉንን ነገሮችን ለመግዛት ወደ ገበያ እሄዳለሁ፤ ከዚያም ወደ ቤት ተመልሼ ምግብ በማብሰልና ሌሎች የቤት ውስጥ ሥራዎችን በመሥራት እናቴን አግዛለሁ።

ወጪዎቻችንን ለመሸፈን የሚያስፈልገንን ገንዘብ ለማግኘት ልባሽ ጨርቆችን እሸጣለሁ። በአሁኑ ጊዜ እናቴ 78 ዓመቷ ሲሆን ሦስት ጊዜ ከፍተኛ የሆነ የልብ ሕመም አጋጥሟት ስለነበር እንደልብ መንቀሳቀስ አትችልም። በመሆኑም መድኃኒት እንድትወስድና ምግብ እንድትበላ የምረዳት እኔ ነኝ። የጤና ችግር ቢኖርብንም እንኳ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት ከፍተኛ ጥረት እናደርጋለን። ባለፉት ዓመታት መጽሐፍ ቅዱስን ያስጠናኋቸው ከ30 የሚበልጡ ሰዎች በክርስቲያናዊ አገልግሎት እየተካፈሉ ነው።

አምላክ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ “አንካሳ እንደ ሚዳቋ ይዘላል” የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ እንደሚፈጸም ሙሉ እምነት አለኝ። እስከዚያው ድረስ ግን አምላክ “እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፤ አምላክህ ነኝና አትደንግጥ። አበረታሃለሁ፤ እረዳሃለሁ፤ በጽድቄም ቀኝ እጄ ደግፌ እይዝሃለሁ” በማለት የተናገረው ሐሳብ ያጽናናኛል።—ኢሳይያስ 35:6፤ 41:10 *

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.10 በ1958 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ፤ አሁን መታተም አቁሟል።

^ አን.18 ቪክቶሪያ ኮጆኢ ኅዳር 30, 2009 በ60 ዓመቷ በሞት አንቀላፍታለች። እናቷ ደግሞ ከዚያ ትንሽ ቀደም ብሎ ነሐሴ 5, 2009 አርፈዋል።

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በሰባት ዓመቴ በእግሬ ላይ ብረት ታስሮልኝ

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አገልግሎት ላይ እኔ ላለሁበት ሁኔታ ተስማሚ ሆና በተሠራች በኤሌክትሪክ የምትንቀሳቀስ ተሽከርካሪ እጠቀማለሁ