በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሊደረስባቸው የሚችሉ ግቦች አሉህ?

ሊደረስባቸው የሚችሉ ግቦች አሉህ?

ሊደረስባቸው የሚችሉ ግቦች አሉህ?

● በሕይወትህ ውስጥ ምን ለማግኘት ትፈልጋለህ? ወደፊት የምትጠብቃቸው ነገሮች ልትደርስባቸው የምትችላቸው ናቸው? ወይስ ካለህ ችሎታና አቅም በላይ የሆኑ ነገሮችን ለማግኘት እያለምክ ነው? የሰው ልጆችን አፈጣጠር በጥንቃቄ የተመለከተ አንድ ግለሰብ እንዲህ የሚል ጥበብ የተንጸባረቀበት ምክር ሰጥቷል፦ “ለምኞት ከመገዛት ይልቅ ባለ ነገር መርካት ይሻላል፤ ይህም ደግሞ ከንቱና ነፋስን ለመጨበጥ እንደ መሞከር ነው።”—መክብብ 6:9 የታረመው የ1980 ትርጉም

“ባለ ነገር” የሚለው አገላለጽ አሁን ያለንበትን ተጨባጭ ሁኔታ ያመለክታል። እርግጥ ነው፣ ሕይወታችንን ለማሻሻል ጥረት ማድረጋችን ምንም ስህተት የለውም። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ከላይ ያለውን ሐሳብ ሲናገር ሊያስተላልፍ የፈለገው ነጥብ ብልህ ሰው የማይደርስባቸውን ግቦች አያሳድድም የሚል ነው። ዝና፣ ሀብት፣ ፍጹም የትዳር ጓደኛ ወይም ፍጹም የሆነ ጤንነት ለማግኘት መጣር እንዲህ ካሉ ግቦች ሊፈረጅ ይችላል።

ከዚህም በላይ እንዲህ ያሉ ግቦች ላይ የደረሱ ለምሳሌ ቁሳዊ ሀብት በማካበት የተሳካላቸው ሰዎች አሁንም ቢሆን ተጨማሪ ነገር ለማግኘት ሊቋምጡ ይችላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ “ገንዘብን የሚወድ፣ ገንዘብ አይበቃውም፤ ብልጽግናም የሚወድ፣ በትርፉ አይረካም፤ ይህም ከንቱ ነው” በማለት በግልጽ ይናገራል። (መክብብ 5:10) በመሆኑም መንፈሳዊ ማስተዋል ያላቸው ሰዎች ‘ባላቸው ነገር ለመርካት’ ጥረት ያደርጋሉ። በእርግጥም እንዲህ ያሉ ሰዎች “ወደ ዓለም ያመጣነው ምንም ነገር የለም፤ ምንም ነገር ይዘን መሄድም አንችልም” የሚለውን ሐቅ ይቀበላሉ።—1 ጢሞቴዎስ 6:7

የሰው ልጆች ተፈጥሮ እንደሚያሳየው በሕይወት ውስጥ ከፍተኛ ደስታ ማግኘት የሚቻለው መንፈሳዊ ፍላጎትን በማርካት ነው። (ማቴዎስ 5:3) ታዲያ ይህን ፍላጎት ማርካት የምንችለው እንዴት ነው? ኢየሱስ ክርስቶስ “ሰው ከይሖዋ አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በምግብ ብቻ ሊኖር አይችልም” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 4:4) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን እነዚህን ውድ ቃላት ማንም ሰው በነፃ ሊያገኛቸው ይችላል።

ከእነዚህ ውድ ቃላት መካከል መዝሙር 37:4 ላይ የሚገኘው “በእግዚአብሔር ደስ ይበልህ፤ የልብህንም መሻት ይሰጥሃል” የሚለው ሐሳብ ይገኝበታል። ይሖዋ ሁሉን ቻይ አምላክ እንደመሆኑ መጠን ለታማኝ አገልጋዮቹ የትኛውም ሰው ሊሰጣቸው የማይችለውን ነገር ማለትም ፍጹም ጤንነት፣ የሚያስፈልጋቸውን ቁሳዊ ነገርና ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት ይሰጣቸዋል። (ሉቃስ 23:43፤ ራእይ 21:3, 4) በእነዚህ ቃላት ላይ እምነት መጣል ሊጨበጥ የማይችል ግብ ማሳደድ አይደለም።