በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ራስን ማሠቃየት ወደ አምላክ ለመቅረብ ሊረዳህ ይችላል?

ራስን ማሠቃየት ወደ አምላክ ለመቅረብ ሊረዳህ ይችላል?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ራስን ማሠቃየት ወደ አምላክ ለመቅረብ ሊረዳህ ይችላል?

አብዛኞቹ ሰዎች ራስን ማሠቃየት የሚለው ሐሳብ ይዘገንናቸዋል። ሆኖም ራስን መግረፍን፣ ምንም ሳይቀምሱ ረዘም ላለ ጊዜ መፆምንና ቆዳቸውን የሚኮሰኩስ ማቅ መልበስን በመሳሰሉት ተግባሮች ራሳቸውን ያሠቃዩ ሃይማኖተኛ ግለሰቦች አምላክን ለሚፈሩ ሰዎች አርዓያ እንደሆኑ ተደርገው ሲወደሱ ኖረዋል። እነዚህ ተግባሮች በመካከለኛው ዘመን ብቻ ይደረጉ የነበሩ አይደሉም። በዘመናችንም ታዋቂ የሆኑ የሃይማኖት መሪዎች እንኳ ሳይቀር ራሳቸውን በመግረፍ እንደሚያሠቃዩ በቅርብ የወጡ የዜና ዘገባዎች ገልጸዋል።

ሰዎች አምልኳቸውን እንዲህ ባለ መንገድ እንዲያቀርቡ የሚያነሳሳቸው ምንድን ነው? ክርስቲያን ነኝ የሚል አንድ ድርጅት ቃል አቀባይ የሆኑ ሰው እንደተናገሩት “በፈቃደኝነት ሥቃይን መቀበል አንድ ሰው ኢየሱስ ክርስቶስን የሚመስልበትና እሱ እኛን ከኃጢአት ለመዋጀት በፈቃደኝነት ከተቀበላቸው መከራዎች ተካፋይ የሚሆንበት መንገድ ነው።” የሃይማኖት መሪዎች ምንም አሉ ምን፣ መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይላል?

ሰውነትህን ተንከባከብ

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ራስን በማሠቃየት አምልኮን ማቅረብን የሚደግፍም ሆነ የሚያበረታታ ሐሳብ አናገኝም። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ፣ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ሰዎች ሰውነታቸውን እንዲንከባከቡ በተደጋጋሚ ጊዜ ያበረታታል። በባልና በሚስት መካከል ያለውን ፍቅር የሚገልጽበትን መንገድ ልብ በል። አንድ ሰው በተፈጥሮ ለራሱ አካል የሚያደርገውን እንክብካቤ እንደ ምሳሌ በመጥቀስ እንደሚከተለው የሚል ምክር ይሰጣል፦ “ባሎች ሚስቶቻቸውን እንደ ገዛ አካላቸው አድርገው ሊወዷቸው ይገባል። . . . የገዛ ሥጋውን የሚጠላ ማንም ሰው የለም፤ ከዚህ ይልቅ ይመግበዋል እንዲሁም ይሳሳለታል፤ ክርስቶስም ለጉባኤው ያደረገው እንደዚሁ ነው።”​—ኤፌሶን 5:28, 29

አምላክ፣ አገልጋዮቹ ለእሱ አምልኮ ሲያቀርቡ በራሳቸው አካል ላይ የጭካኔ ድርጊት እንዲፈጽሙ የሚጠብቅባቸው ቢሆን ኖሮ አንድ ሰው ሚስቱን እንደ ራሱ አካል አድርጎ እንዲወዳት የተሰጠው ትእዛዝ ትርጉም ይኖረው ነበር? በግልጽ ማየት እንደሚቻለው የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች የሚያከብሩ ሰዎች፣ የራሳቸውን ሰውነት እንዲንከባከቡ እንዲያውም በተወሰነ ደረጃ አካላቸውን እንዲወዱና ለራሳቸው ያላቸውን እንዲህ ያለውን ጤናማ ፍቅር ለትዳር ጓደኛቸውም ጭምር እንዲያሳዩ ይጠበቅባቸዋል።

ከዚህ ጋር በሚስማማ ሁኔታ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሰዎች የራሳቸውን ሰውነት እንዲንከባከቡ የሚረዱ ብዙ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ይዟል። ለምሳሌ ያህል፣ መጠነኛ የሆነ የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረግ ጥቅም እንዳለው ይናገራል። (1 ጢሞቴዎስ 4:8) አንዳንድ ምግቦች ሕመምን ለማስታገስ እንደሚረዱ የሚገልጽ ሲሆን መጥፎ አመጋገብ ስለሚያስከትላቸው ጉዳቶችም ይጠቅሳል። (ምሳሌ 23:20, 21፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:23) ሰዎች ጤንነታቸውን መጠበቃቸው ብርታትና ጥንካሬ እንዲኖራቸው ስለሚያስችላቸው ይህን እንዲያደርጉ ቅዱሳን መጻሕፍት ያበረታታሉ። (መክብብ 9:4) መጽሐፍ ቅዱስን የሚያነቡ ሰዎች በእነዚህ መንገዶች ጤንነታቸውን እንዲንከባከቡ የሚጠበቅባቸው ከሆነ የራሳቸውን ሰውነት የሚጎዳ ነገር እንዲያደርጉ እንዴት ሊጠበቅባቸው ይችላል?​—2 ቆሮንቶስ 7:1

ክርስቲያኖች ኢየሱስ የደረሰበትን ሥቃይ በራሳቸው ላይ ማድረስ ይኖርባቸዋል?

ያም ሆኖ አንዳንድ ሃይማኖቶች፣ ኢየሱስና የቀድሞ ተከታዮቹ በጽናት በተቋቋሟቸው መከራዎች ላይ የሚያተኩሩ ሲሆን ይህንንም በዛሬው ጊዜ ራስን ማሠቃየትን እንደሚደግፍ አድርገው በተሳሳተ መንገድ ይረዱታል። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ፣ የአምላክ አገልጋዮች መከራ እንደደረሰባቸው ቢገልጽም ይህን ያደረጉት ራሳቸው እንደሆኑ ፈጽሞ አይናገርም። መጽሐፍ ቅዱስን የጻፉት ሰዎች፣ ክርስቶስ ስለተቀበለው መከራ የገለጹት ክርስቲያኖች የሚደርስባቸውን ስደት በጽናት እንዲቋቋሙ ለማበረታታት እንጂ በራሳቸው ላይ ስደት እንዲያደርሱ ለማነሳሳት አልነበረም። በመሆኑም በራሳቸው ሰውነት ላይ ሥቃይ የሚያደርሱ ሰዎች ኢየሱስን እየመሰሉት አይደለም።

ይህን በምሳሌ ለማስረዳት፣ በቁጣ የተነሳሱ ረብሸኞች በጣም የምታደንቀውን አንድ ጓደኛህን ሲሰድቡትና ሲመቱት ተመለከትህ እንበል። ጓደኛህ መልሶ ለመማታት ወይም ለመሳደብ ሳይሞክር በተረጋጋና ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ ጥቃቱን እንደተቋቋመ አስተዋልህ። የጓደኛህን ምሳሌ መከተል ብትፈልግ ራስህን መምታትና መስደብ ትጀምራለህ? እንዲህ እንደማታደርግ የታወቀ ነው! እንዲህ ብታደርግ ጓደኛህን ሳይሆን ረብሸኞቹን ትመስላለህ። ከዚህ ይልቅ አንተም በጓደኛህ ላይ የደረሰው ዓይነት ጥቃት ቢደርስብህ አጸፋውን ላለመመለስ በመጣር የጓደኛህን ምሳሌ ትከተላለህ።

እንግዲያው የክርስቶስ ተከታዮች፣ ኢየሱስን ያሠቃዩትንና ሊገድሉት የፈለጉትን በቁጣ የተነሳሱ ረብሸኞች አድራጎት መኮረጅ የሚያስፈልጋቸው ይመስል በራሳቸው ላይ ሥቃይ ማድረስ አይጠበቅባቸውም። (ዮሐንስ 5:18፤ 7:1, 25፤ 8:40፤ 11:53) ከዚህ ይልቅ ስደት በሚደርስባቸው ጊዜ እንደ ኢየሱስ በእርጋታና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለመቋቋም ይሞክራሉ።​—ዮሐንስ 15:20

ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚቃረን ተግባር

ከክርስትና ዘመን በፊትም እንኳ አይሁዳውያን ምን ዓይነት አኗኗርና አምልኮ ሊኖራቸው እንደሚገባ የሚገልጹት በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙት መመሪያዎች አይሁዶች ሰውነታቸውን የሚጎዳ አንዳች ነገር እንዳያደርጉ ይከለክሉ ነበር። ለምሳሌ ሕጉ፣ አይሁዳዊ ባልሆኑ የጥንት ሕዝቦች ዘንድ የሚዘወተረውን ሰውነትን የመቦጨቅ ወይም የመተልተል ልማድ እንዳይከተሉ አይሁዳውያንን በግልጽ ይከለክላል። (ዘሌዋውያን 19:28፤ ዘዳግም 14:1) አምላክ፣ ሰዎች አካላቸውን እንዲተለትሉ የማይፈልግ ከሆነ ሰውነት ሰንበር እስኪያወጣ ድረስ በጅራፍ መግረፍንም እንደማይደግፍ የታወቀ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ ግልጽ ነው፦ በማናቸውም መንገድ ሆን ብሎ በሰውነት ላይ ጉዳት ማድረስ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት የለውም።

አንድ የሥነ ጥበብ ሰው ሥራው በክብር እንዲያዝ እንደሚፈልግ ሁሉ ፈጣሪያችን የሆነው ይሖዋም የእጁ ሥራ የሆነው የሰው አካል በአክብሮት እንዲያዝ ይፈልጋል። (መዝሙር 139:14-16) እንደ እውነቱ ከሆነ ራስን ማሠቃየት አንድ ሰው ከአምላክ ጋር ያለውን ዝምድና አያጠናክርለትም። ይልቁንም ዝምድናውን የሚያበላሽ ከመሆኑም ሌላ በወንጌሎች ውስጥ የሰፈረውን ትምህርት በተዛባ መንገድ እንድናየው የሚያደርግ ተግባር ነው።

ሐዋርያው ጳውሎስ እንደዚህ ያሉትን ጨቋኝና ሰዎች የፈጠሯቸው ትምህርቶች በተመለከተ በመንፈስ መሪነት እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “እነዚህ ነገሮች በገዛ ፈቃድ በሚደረግ አምልኮ፣ በአጉል ትሕትናና ሰውነትን በመጨቆን የሚገለጹ ናቸው፤ በእርግጥ ጥበብ ያለባቸው ይመስላሉ፤ ነገር ግን የሥጋን ፍላጎት በማሸነፍ ረገድ አንዳች ፋይዳ የላቸውም።” (ቆላስይስ 2:20-23) በእርግጥም ራስን ማሠቃየት አንድ ሰው ወደ አምላክ እንዲቀርብ በመርዳት ረገድ ምንም አይጠቅምም። የእውነተኛው አምልኮ መሥፈርቶች ግን እረፍት የሚሰጡ፣ ደግነት የሚንጸባረቅባቸውና ቀላል ናቸው።​—ማቴዎስ 11:28-30

ይህን አስተውለኸዋል?

● አምላክ ስለ ሰው አካል ምን አመለካከት አለው?​መዝሙር 139:13-16

● ሰውነትህን ማሠቃየት ተገቢ ያልሆኑ ፍላጎቶችን ለማሸነፍ ሊረዳህ ይችላል?​ቆላስይስ 2:20-23

● አምላክ፣ እውነተኛው አምልኮ ሸክም ወይም የሚያስጨንቅ እንዲሆንብን ይፈልጋል?​ማቴዎስ 11:28-30

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳበ]

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ ግልጽ ነው፦ በማናቸውም መንገድ ሆን ብሎ በሰውነት ላይ ጉዳት ማድረስ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት የለውም

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንድ ሃይማኖተኛ ሰው ወደ ቤተ ክርስቲያን እየዳኸ ሲሄድ

[የሥዕሉ ምንጭ]

© 2010 photolibrary.com