በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለማስቀረት ኃይለኛ እርምጃ በተወሰደበት የአንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ “ቻይናውያን ፖሊሶች ታፍነው የተወሰዱ 10,621 ሴቶችንና 5,896 ልጆችን አስለቅቀዋል።” በዚሁ ጊዜ 15,673 የሚያህሉ ተጠርጣሪዎች ተይዘዋል።​—ቻይና ዴይሊ፣ ቻይና

“በኬንያ፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ በትምህርት ቤት ያሉ ሴቶች ልጆችን በፆታ በማስነወራቸው ምክንያት ከ1,000 በላይ አስተማሪዎች ከሥራ ተባርረዋል። . . . በሚስጥር የምክር እርዳታ ከሚሰጥበት አገር አቀፍ የስልክ መሥመር የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው ችግሩ ቀደም ሲል ከታሰበው በላይ በጣም ተስፋፍቷል።”​—ዴይሊ ኔሽን፣ ኬንያ

አንድ ጥናት በገለጸው መሠረት ቆዳን ለማጠየም በሚረዳ መሣሪያ የሚጠቀሙ ሰዎች በእንደዚህ ዓይነት መሣሪያ ተጠቅመው ከማያውቁት ሰዎች ይልቅ ሜላኖማ ለሚባለው የቆዳ ካንሰር የመጋለጥ አጋጣሚያቸው በ75 በመቶ ይጨምራል። ቆዳን በሚያጠይም መሣሪያ ከ50 ሰዓት ለሚበልጥ ጊዜ የተጠቀሙ ሰዎች በሜላኖማ የመያዝ አጋጣሚያቸው ከ2.5 እስከ 3.0 ጊዜ ከፍ ያለ ነው።​—ካንሰር ኤፒዲሚዮሎጂ፣ ባዮማርከርስ ኤንድ ፕሪቬንሽን፣ ዩናይትድ ስቴትስ

“[ለማግባት ከተዘጋጁ ካናዳውያን ሴቶች] መካከል ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት ከመፈጸም መታቀብ ጥሩ እንደሆነ የሚያስቡት 8 በመቶ ብቻ” ሲሆኑ “74 በመቶ የሚሆኑት ከመጋባታቸው በፊት አብረው መኖር የጀመሩ ናቸው።”​—ዌዲንግቤልስ፣ ካናዳ

የተበከለ ውኃ የሚያስከትላቸው አደጋዎች

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባወጣው ዘገባ መሠረት “በአሁኑ ጊዜ ጦርነትን ጨምሮ በማንኛውም ዓይነት ዓመፅ ከሚሞቱት ሰዎች የበለጠ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በተበከለ ውኃ ምክንያት ይሞታሉ።” የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደዘገበው ከግብርና እና ከኢንዱስትሪ መስክ የሚወጣውን ቆሻሻ እንዲሁም ከሽንት ቤትና ከሌሎች ቦታዎች የሚወጣውን ፍሳሽ ጨምሮ በየዕለቱ ሁለት ሚሊዮን ቶን ቆሻሻ ወደ ወንዞችና ባሕሮች ይለቀቃል፤ ይህ ደግሞ በሽታ የሚያዛምት ከመሆኑም ሌላ ሥነ ምህዳርን ያበላሻል። ከዚህም በላይ በየ20 ሴኮንዱ ከአምስት ዓመት በታች የሆነ አንድ ሕፃን በውኃ ወለድ በሽታ ሳቢያ ይሞታል። የተባበሩት መንግሥታት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አከም ሽታይነ እንደተናገሩት ‘ዓለም የተሻለ ቦታ እንዲሆን ከተፈለገ ሁላችንም ተባብረን ቆሻሻን ለመቀነስና በአግባቡ ለማስወገድ፣ ተቀባይነት ያለው ብሎም ኃላፊነት እንደሚሰማን የሚያሳይ መፍትሔ ማግኘት ይኖርብናል።’

የመናገር ችሎታን ለመመለስ መዘመር

በአንጎል ውስጥ ደም መፍሰስ ካጋጠማቸው በኋላ የመናገር ችሎታቸውን ያጡ በርካታ ሕመምተኞች፣ መዘመራቸው የመናገር ችሎታቸውን መልሰው ለማግኘት አስችሏቸዋል። በአንጎል ውስጥ የደም መፍሰስ ያጋጠማቸው በሽተኞች፣ ሊናገሩ የሚፈልጉትን ነገር በመዝሙር መልክ እንዲገልጹት የነርቭ ሐኪሞች ያበረታታሉ። ሜሎዲክ ኢንቶኔሽን ቴራፒ ተብሎ የሚጠራው ይህ ሕክምና አስደናቂ ውጤት አስገኝቷል። ከ15 ሳምንታት ሕክምና በኋላ “ሕመምተኞች የሚዘምሯቸውን ቃላት ቀስ በቀስ ወደ ንግግር መለወጥን ይማራሉ” በማለት ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል ዘግቧል።

‘የክፍል ውስጥ ማጭበርበር መጨመር’

በካናዳ 20,000 በሚሆኑ የመጀመሪያ ዓመት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ላይ በተካሄደ ጥናት ላይ 73 በመቶ ያህሉ “በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሳሉ በጽሑፍ በሚቀርቡ የትምህርት ቤት ሥራዎች ላይ በተለያዩ መንገዶች እንዳጭበረበሩ አምነዋል” በማለት የካናዳው የትምህርት ምክር ቤት ይናገራል። አንድ ዩኒቨርሲቲ፣ ማጭበርበርና ኩረጃ በ2003 እና በ2006 መካከል ባሉት ዓመታት ውስጥ በ81 በመቶ መጨመሩን ሪፖርት አድርጓል። የካናዳው የትምህርት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት የሆኑት ዶክተር ፖል ካፐን እንዲህ ብለዋል፦ “ኢንተርኔትና ዘመናዊ የቴክኖሎጂ መሣሪያዎች ባለፈው አሥር ዓመት ውስጥ የክፍል ውስጥ ማጭበርበር በጣም እንዲጨምር አድርገዋል።”