በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ማኅበራዊ ድረ ገጾችን በተመለከተ ምን ማወቅ ይኖርብኛል? ክፍል 1

ማኅበራዊ ድረ ገጾችን በተመለከተ ምን ማወቅ ይኖርብኛል? ክፍል 1

የወጣቶች ጥያቄ

ማኅበራዊ ድረ ገጾችን በተመለከተ ምን ማወቅ ይኖርብኛል? ክፍል 1

“በሌላ አገር የሚኖሩ ጓደኞች አሉኝ፤ ስለዚህ ከእነሱ ጋር መገናኘት የምችልበት ከሁሉ የተሻለው መንገድ ማኅበራዊ ድረ ገጽ ነው። የሚኖሩበት አገር በጣም ሩቅ ቢሆንም ከእነሱ ጋር ማውራት መቻሌ ደስ ይለኛል።”​—ሱ፣ ዕድሜ 17 *

“በማኅበራዊ ድረ ገጽ መጠቀም ጊዜ እንደማባከን ሆኖ ይሰማኛል፤ በአንድ ሰው ማኅበራዊ ሕይወት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳድር ይመስለኛል። ጓደኝነትን ጠብቆ ለማቆየት የሚያስችለው ብቸኛው መንገድ በአካል መገናኘት ነው።”​—ግሪጎሪ፣ ዕድሜ 19

ከላይ ከተገለጹት ሐሳቦች ውስጥ ከአንተ አመለካከት ጋር ይበልጥ የሚቀራረበው የትኛው ነው? በዚያም ሆነ በዚህ፣ ማኅበራዊ ድረ ገጽ በብዙ ሰዎች ዘንድ እጅግ ተወዳጅ መሆኑ አሌ የማይባል ሐቅ ነው። * ይህን ልብ በል፦ ሬድዮ 50 ሚሊዮን አድማጭ ለማግኘት 38 ዓመት፣ ቴሌቪዥን ደግሞ የዚህኑ ያህል ተመልካች ትኩረት ለመሳብ 13 ዓመት ፈጅቶበታል፤ ኢንተርኔት 50 ሚሊዮን ተጠቃሚ ለማግኘት የወሰደበት 4 ዓመት ነው። ፌስቡክ የሚባለው ማኅበራዊ ድረ ገጽ በቅርቡ፣ በ12 ወራት ጊዜ ውስጥ ብቻ 200 ሚሊዮን ተጠቃሚዎችን አፍርቷል!

ቀጥሎ የሰፈረውን ዓረፍተ ነገር ካነበብክ በኋላ እውነት ወይም ሐሰት በል፦

የማኅበራዊ ድረ ገጽ ተጠቃሚዎች ከሆኑት ውስጥ አብዛኞቹ በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል የሚገኙ ወጣቶች ናቸው። ․․․․․ እውነት ․․․․․ ሐሰት

መልስ፦ ሐሰት። ይበልጥ ታዋቂ የሆነውን ድረ ገጽ ከሚጠቀሙት ሰዎች መካከል ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑት ዕድሜያቸው 25 ዓመትና ከዚያ በላይ ነው። በ2009 የድረ ገጹ ተጠቃሚዎች ቁጥር በመቶኛ ሲሰላ ከፍተኛ ጭማሪ ያሳየው ዕድሜያቸው ከ55 ዓመት በላይ የሆኑት ሰዎች ቁጥር ነበር!

የሆነ ሆኖ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች በማኅበራዊ ድረ ገጽ የሚጠቀሙ ሲሆን እንዲያውም ለአንዳንዶቹ ከሌሎች ጋር ለመገናኘት የሚያስችል ተመራጭ ዘዴ ሆኖላቸዋል። ጀሲካ የምትባል በአሥራዎቹ ዕድሜ ክልል የምትገኝ አንዲት ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “የኢንተርኔት አካውንቴን ዘግቼው ነበር፤ ይሁን እንጂ በስልክ ሊያገኘኝ የሚፈልግ ሰው ባለመኖሩ አካውንቴን እንደገና ለመክፈት ተገድጃለሁ። በማኅበራዊ ድረ ገጽ የማትጠቀም ከሆነ ሰዎች ጨርሶ የሚረሱህ ይመስላል!”

ማኅበራዊ ድረ ገጽ የብዙዎችን ቀልብ የሚስበው ለምንድን ነው? የዚህ ጥያቄ መልስ ግልጽ ነው፦ ሰዎች ከሰዎች ጋር ማኅበራዊ ግንኙነት የመመሥረት ተፈጥሯዊ ፍላጎት ስላላቸው ነው። የዚህ ድረ ገጽ ዓላማም ይኸው ነው። ብዙ ሰዎች በእነዚህ ድረ ገጾች ለመጠቀም የሚፈልጉት ለምን ሊሆን እንደሚችል ተመልከት፦

1. አመቺ መሆኑ።

“ከጓደኞችህ ጋር መገናኘት ከባድ ሊሆን ይችላል፤ ሆኖም ሁሉንም በአንድ ድረ ገጽ የምታገኛቸው ከሆነ ሁኔታው ይቀላል!”​ሊያ፣ ዕድሜ 20

“በድረ ገጹ ላይ አስተያየቴን ስጽፍ፣ በአንድ ጊዜ ለጓደኞቼ በሙሉ ኢሜይል የላክሁላቸው ያህል ነው።”​ክሪስቲን፣ ዕድሜ 20

2. የእኩዮች ተጽዕኖ።

“ሰዎች በድረ ገጹ ላይ በሚገኘው የጓደኞቻቸው ስም ዝርዝር ውስጥ እንድካተት ሁልጊዜ ጥያቄ ያቀርቡልኛል፤ እኔ ግን አካውንት ስላልከፈትኩ እንዲህ ማድረግ አልቻልኩም።”​ናታሊ፣ ዕድሜ 22

“ለሰዎች፣ አካውንት ላለመክፈት እንደወሰንኩ ስነግራቸው ‘ምን ነካሽ?’ ዓይነት አስተያየት ያዩኛል።”​ኢቭ፣ ዕድሜ 18

3. መገናኛ ብዙኃን የሚያሳድሩት ተጽዕኖ።

“የመገናኛ ብዙኃን፣ በተለያዩ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች አማካኝነት ከሰዎች ጋር ቶሎ ቶሎ የማትገናኝ ከሆነ ጓደኞች አይኖሩህም የሚል አመለካከት ያስፋፋሉ። ጓደኞች ከሌሉህ ደግሞ ምኑን ኖርከው! ስለዚህ ማኅበራዊ ግንኙነት ከሌለህ ሕይወትህ ትርጉም አይኖረውም።”​ካትሪና፣ ዕድሜ 18

4. ትምህርት ቤት።

“አስተማሪዎቼ በማኅበራዊ ድረ ገጽ ይጠቀማሉ። አንዳንዶቹ አስተማሪዎች ፈተና መቼ እንደሚኖረን ለማሳወቅ በድረ ገጹ ላይ መልእክት ይጽፋሉ። ወይም ደግሞ ያልገባኝ ነገር ሲኖር ለምሳሌ ያህል፣ ከሒሳብ ትምህርት ጋር የተያያዘ ጥያቄ ሲኖረኝ፣ ጥያቄውን በአስተማሪዬ ድረ ገጽ ላይ እጽፈዋለሁ፤ እሱም በኢንተርኔት ተጠቅሞ ጥያቄውን መሥራት እንድችል ይረዳኛል።”​ማሪና፣ ዕድሜ 17

5. ሥራ።

“ሥራ የሚያፈላልጉ ሰዎች ከሌሎች ጋር ለመገናኘት በማኅበራዊ ድረ ገጽ ይጠቀማሉ። ይህም አንዳንድ ጊዜ ሥራ ለማግኘት ይረዳቸዋል።”​ኤሚ፣ ዕድሜ 20

“ሥራዬን ለማከናወን በማኅበራዊ ድረ ገጽ እጠቀማለሁ። ይህም ደንበኞቼ እየሠራሁላቸው ያለሁትን ዲዛይን እንዲያዩ ያስችላቸዋል።”​ዴቪድ፣ ዕድሜ 21

ታዲያ አንተ የማኅበራዊ ድረ ገጽ አካውንት ሊኖርህ ይገባል? የምትኖረው ከወላጆችህ ጋር ከሆነ ይህን የሚወስኑት እነሱ ናቸው። * (ምሳሌ 6:20) ወላጆችህ እንዲህ ባለው ድረ ገጽ እንድትጠቀም የማይፈልጉ ከሆነ ውሳኔያቸውን ማክበር ይኖርብሃል።​—ኤፌሶን 6:1

በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ ወላጆች የጎለመሱ ልጆቻቸው በማኅበራዊ ድረ ገጾች እንዲጠቀሙ የሚፈቅዱ ሲሆን አጠቃቀማቸውንም ይቆጣጠራሉ። የአንተ ሁኔታ እንዲህ ከሆነ ወላጆችህ የኢንተርኔት አጠቃቀምህን መቆጣጠራቸው በግል ሕይወትህ ውስጥ ጣልቃ ገብተዋል ሊያስብላቸው ይችላል? በጭራሽ! ማኅበራዊ ድረ ገጽ በጣም ጠቃሚ መሣሪያ መሆኑ ባይካድም ካሉት አንዳንድ አደጋዎች አንጻር ወላጆችህ እንዴት እየተጠቀምክበት እንዳለ ለማወቅ ቢፈልጉ አይፈረድባቸውም። ማኅበራዊ ድረ ገጽ፣ እንደማንኛውም የኢንተርኔት አጠቃቀም ሁሉ የራሱ የሆኑ አደጋዎች እንዳሉት የተረጋገጠ ነው። ታዲያ ወላጆችህ በማኅበራዊ ድረ ገጽ እንድትጠቀም ከፈቀዱልህ ከእነዚህ አደጋዎች ራስህን መጠበቅ የምትችለው እንዴት ነው?

በጥንቃቄ “ማሽከርከር”

ኢንተርኔት መጠቀም በአንዳንድ ሁኔታዎች መኪና ከማሽከርከር ጋር ሊመሳሰል ይችላል። መንጃ ፈቃድ ያላቸው ሰዎች ሁሉ ኃላፊነት የሚሰማቸው አሽከርካሪዎች እንዳልሆኑ ሳታስተውል አትቀርም። እንዲያውም ብዙ ሰዎች ግዴለሽ ወይም ቸልተኛ ከመሆናቸው የተነሳ ለአሰቃቂ አደጋ ተዳርገዋል።

ኢንተርኔት ከሚጠቀሙ ሰዎች ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። አንዳንዶች ኃላፊነት እንደሚሰማቸው በሚያሳይ መንገድ “ያሽከረክራሉ”፤ ሌሎች ደግሞ ግዴለሾች ናቸው። ወላጆችህ በማኅበራዊ ድረ ገጽ እንድትጠቀም ፈቅደውልህ ከሆነ አስቸጋሪ በሆነው የኢንተርኔት “መንገድ” ላይ እንድታሽከረክር እምነት ጥለውብሃል ማለት ነው። ታዲያ ምን ዓይነት “ሾፌር” መሆንህን አሳይተሃል? ‘ጥበብና የማመዛዘን ችሎታ’ ያለህ መሆንህን አስመሥክረሃል?​—ምሳሌ 3:21 NW

በዚህ ርዕሰ ትምህርት ላይ ከማኅበራዊ ድረ ገጽ ጋር በተያያዘ በቁም ነገር ልታስብባቸው የሚገቡ ሁለት ነገሮችን እንመለከታለን፤ እነሱም የግል ሚስጥርህና ጊዜህ ናቸው። በሚቀጥለው የንቁ! መጽሔት እትም ላይ “የወጣቶች ጥያቄ” በሚለው ዓምድ ሥር ደግሞ በሌሎች ዘንድ ያለህን ስምና ከሌሎች ጋር ያለህን ጓደኝነት በተመለከተ ተጨማሪ ሐሳብ ይወጣል።

የግል ሚስጥርህ

በማኅበራዊ ድረ ገጽ ስትጠቀም የግል ሚስጥርህን የመጠበቁ ጉዳይ እምብዛም አያሳስብህ ይሆናል። ደግሞስ የማኅበራዊ ድረ ገጽ ዓላማ ከሰዎች ጋር መወዳጀት አይደል? ይሁን እንጂ አንዳንድ ጥንቃቄዎችን አለማድረግ ለችግር ሊዳርግ ይችላል።

በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ አለህ እንበል። ከጓደኞችህ ጋር ሕዝብ በሚበዛበት ጎዳና ላይ ስትሄድ የያዝከውን ገንዘብ ሰው ሁሉ እንዲያየው ታደርጋለህ? ይህን ማድረግ ሞኝነት ነው፤ ምክንያቱም ‘ዝረፉኝ’ እንደ ማለት ይሆንብሃል! ብልጥ ከሆንክ ገንዘብህን ሰው እንዳያየው በጥንቃቄ ትይዛለህ።

የግል መረጃዎችህን እንደ ገንዘብህ አድርገህ ተመልከታቸው። ይህን በአእምሮህ በመያዝ ከዚህ በታች የቀረበውን ዝርዝር ተመልከት፤ ከዚያም ጨርሶ ለማታውቀው ሰው ማሳወቅ በማትፈልጋቸው ነገሮች ላይ ምልክት አድርግ።

․․․․․ የቤቴን አድራሻ

․․․․․ የኢሜይል አድራሻዬን

․․․․․ የምማርበትን ትምህርት ቤት

․․․․․ ቤት የምሆንባቸውን ጊዜያት

․․․․․ ቤት ማንም ሰው የማይኖርባቸውን ጊዜያት

․․․․․ ፍቶግራፎቼን

․․․․․ አመለካከቴን

․․․․․ የምወዳቸውንና የምፈልጋቸውን ነገሮች

የፈለገውን ያህል ግልጽ ሰው ብትሆን፣ ከላይ ከተዘረዘሩት ነገሮች ውስጥ ከተወሰኑ ሰዎች በስተቀር ሁሉም ሰው ሊያውቃቸው የማይገቡ ቢያንስ አንዳንድ ነገሮች እንዳሉ ሳትስማማ አትቀርም። ይሁን እንጂ በርካታ ወጣቶችና ትልልቅ ሰዎች ሳይታወቃቸው እንዲህ ያሉ ዝርዝር ጉዳዮችን ለማያውቁት ሰው አሳልፈው ሰጥተዋል! ታዲያ እንዲህ ዓይነቱን አደጋ ማስቀረት የምትችለው እንዴት ነው?

ወላጆችህ በማኅበራዊ ድረ ገጽ እንድትጠቀም ከፈቀዱልህ የግል ሚስጥርን ለመጠበቅ የሚያስችሉትን ዘዴዎች በደንብ ልታውቃቸውና ልትጠቀምባቸው ይገባል። የግል ሚስጥርህን የመጠበቁን ጉዳይ ለድረ ገጹ መተው የለብህም። ድረ ገጹ በራሱ ያስቀመጣቸው አማራጮች አንተ ከምታስበው በላይ ብዙ ሰዎች ድረ ገጽህን ለመመልከትና በእሱ ላይ አስተያየት ለመጻፍ የሚያስችላቸው ሊሆን ይችላል። አሊሰን የምትባል አንዲት ወጣት በድረ ገጿ ላይ የምትጽፋቸውን ነገሮች የቅርብ ጓደኞቿ ብቻ እንዲያዩት በሚያስችል መንገድ የድረ ገጹን አማራጮች ያስተካከለችበት አንዱ ምክንያት ይህ ነው። አሊሰን “አንዳንዶቹ ጓደኞቼ እኔ የማላውቃቸው ጓደኞች አሏቸው” ብላለች፤ “እኔ ደግሞ እነዚህ ሰዎች ስለ እኔ እንዲያነቡ አልፈልግም።”

የሐሳብ ልውውጥ የምታደርገው ከቅርብ ጓደኞችህ ጋር ብቻ ቢሆንም እንኳ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልግሃል። “የጓደኞችህን አስተያየት የማንበብ ሱስ ሊይዝህ ይችላል” በማለት የ21 ዓመቷ ኮሪን ተናግራለች፤ “ይህ ከሆነ ደግሞ በድረ ገጽህ ላይ ከሚገባው በላይ ስለ ራስህ የሚገልጽ ብዙ መረጃ ማስፈር ትጀምራለህ።”

ከኢንተርኔት ጋር በተያያዘ “የግል ሚስጥር” የሚባለው ነገር አንጻራዊ መሆኑን ምንጊዜም መዘንጋት የለብህም። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? “ትልልቅ የድረ ገጽ ድርጅቶች የያዟቸውን መረጃዎች ቅጂ ያስቀምጣሉ” በማለት ግዌን ሹርገን ኦኪፍ የተባሉ አንዲት ሴት ሳይበርሴፍ በተሰኘ መጽሐፋቸው ላይ ገልጸዋል፤ እኚህ ሴት አክለው እንዲህ ብለዋል፦ “በኢንተርኔት ላይ ያሰፈርነው መረጃ ፈጽሞ ይጠፋል ብሎ መናገር አይቻልም። የመረጃው ቅጂ የሆነ ቦታ መኖሩ ስለማይቀር ለዘለቄታው እንደተቀመጠ አድርገን ማሰብ ይኖርብናል፤ መረጃው ይጠፋል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው።”

ጊዜህ

የግል ሚስጥርህ ብቻ ሳይሆን ጊዜህም ጭምር እንደ ገንዘብ ሊቆጠር ይችላል። በመሆኑም ጊዜህን በጥበብ መጠቀም ይኖርብሃል ማለት ነው። (መክብብ 3:1) ማኅበራዊ ድረ ገጽን ጨምሮ በማንኛውም የኢንተርኔት አጠቃቀም ረገድ የሚያጋጥመው ትልቁ ተፈታታኝ ሁኔታ ይህ ነው። *

“ብዙውን ጊዜ ‘አንድ ደቂቃ ብቻ ነው የምጠቀመው’ ብዬ ድረ ገጹን እከፍታለሁ። ሆኖም ከአንድ ሰዓት በኋላም እንኳ ከእሱ ላይ አልነሳም።”​አማንዳ፣ ዕድሜ 18

“ሱስ ይዞኝ ነበር። ከትምህርት ቤት በተመለስኩ ቁጥር አንዳንድ ሰዎች ድረ ገጹ ላይ ስለጻፍኩት ነገር የሰጡትን አስተያየት ሳነብ እንዲሁም በራሳቸው ድረ ገጽ ላይ ያሰፈሩትን መረጃ ስመለከት ሰዓታት ያልፋሉ።”​ካራ፣ ዕድሜ 16

“በሞባይሌ አማካኝነት ድረ ገጹን መመልከት እችል ነበር፤ በመሆኑም ወደ ትምህርት ቤት ስሄድ፣ ትምህርት ቤት ስሆንና ወደ ቤት ስመለስ ድረ ገጹን እመለከት ነበር። ከዚያም ቤት ስደርስ ኮምፒውተሩን እከፍታለሁ። ሱስ እንደያዘኝ ባውቅም ማቆም አልፈለግኩም ነበር!”​ሪያን፣ ዕድሜ 17

ወላጆችህ በማኅበራዊ ድረ ገጽ እንድትጠቀም ከፈቀዱልህ በቀን ውስጥ ለዚህ ዓላማ ምን ያህል ጊዜ መመደብ እንደሚገባህ አስብ። ከዚያም የጊዜ አጠቃቀምህን ተቆጣጠር። ለአንድ ወር ያህል በማኅበራዊ ድረ ገጽ በመጠቀም ምን ያህል ጊዜ እንዳሳለፍክ በማስታወሻ ላይ መዝግበህ ያዝ፤ እንዲሁም ባወጣኸው ፕሮግራም መሠረት እየሄድክ መሆን አለመሆንህን ገምግም። ጊዜህ እንደ ገንዘብ መሆኑን አስታውስ። ስለዚህ ማኅበራዊ ድረ ገጽ “ለኪሳራ” እንዲዳርግህ አትፍቀድ። ደግሞም በሕይወት ውስጥ ቅድሚያ ልንሰጣቸው የሚገቡ ይበልጥ አስፈላጊ ነገሮች አሉ!​ኤፌሶን 5:15, 16፤ ፊልጵስዩስ 1:10

አንዳንድ ወጣቶች ጊዜያቸውን በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችሏቸውን እርምጃዎች ወስደዋል። ለምሳሌ ያህል፣ የሚከተሉትን ተመልከት፦

“አካውንቴን ዘግቼው ስለነበር የተትረፈረፈ ጊዜ አገኘሁ። ነፃ እንደወጣሁም ሆኖ ተሰማኝ! በቅርቡ አካውንቴን እንደገና የከፈትኩት ቢሆንም በጊዜ አጠቃቀሜ ረገድ ራሴን በሚገባ እቆጣጠራለሁ። አንዳንድ ጊዜ ለብዙ ቀናት ሳልከፍተው እቆያለሁ። እስከነመኖሩም የምረሳበት ጊዜ አለ። ማኅበራዊ ድረ ገጹ እንደገና ችግር ከፈጠረብኝ ያለ ምንም ጥያቄ እዘጋዋለሁ።”​አሊሰን፣ ዕድሜ 19

“ለሁለት ወራት ያህል አካውንቴን በመዝጋት ‘እረፍት’ ወስጄ ነበር፤ ከዚያ በኋላ እንደገና ከፈትኩት። ድረ ገጹን በመጠቀም ብዙ ጊዜ እያጠፋሁ እንዳለ በተገነዘብኩ ቁጥር ይህን እርምጃ እወስዳለሁ። አሁን እንደቀድሞው ሕይወቴን እንደተቆጣጠረው ሆኖ አይሰማኝም። ይልቁንም የምፈልገውን ነገር ካደረግኩ በኋላ ድረ ገጹን ወዲያውኑ እዘጋዋለሁ።”​አን፣ ዕድሜ 22

ሊታሰብበት የሚገባው ዋነኛ ጉዳይ

ከማኅበራዊ ድረ ገጽ ጋር በተያያዘ ልታስብበት የሚገባ ሌላም ጉዳይ አለ። ይህ ጉዳይ ምን እንደሆነ ማስተዋል እንድትችል ከታች የቀረበውን ዓረፍተ ነገር ያሟላል ብለህ ከምታስበው ሐረግ አጠገብ ✔ አድርግ።

ማኅበራዊ ድረ ገጽ የሚቋቋምበት ዋነኛ ዓላማ . . .

(ሀ) ․․․․․ ንግድ ነው።

(ለ) ․․․․․ ከሰዎች ጋር ወዳጅነት መመሥረት ነው።

(ሐ) ․․․․․ ሰዎችን ማዝናናት ነው።

ትክክለኛው መልስ የቱ ነው? ብታምንም ባታምንም መልሱ ‘ሀ’ ነው። የማኅበራዊ ድረ ገጽ ተቀዳሚ ዓላማ ንግድ ነው። ግቡ በዋነኝነት ማስታወቂያዎችን በማቅረብ ትርፍ ማግኘት ነው። ማስታወቂያውን ለሚያስተላልፉት ድርጅቶች ድረ ገጹ ይበልጥ ጠቃሚ የሚሆነው በድረ ገጹ የሚገለገሉ ሰዎች ቁጥር ሲጨምርና እነዚህ ሰዎች በዚያ ላይ የሚያሰፍሯቸው ነገሮች ይበልጥ ለብዙ ሰዎች መድረስ ሲችሉ ነው። ደግሞም አንተም ሆንክ ሌላ ሰው ድረ ገጹን በመጠቀም ብዙ ጊዜ ባጠፋችሁ መጠን ብዙ ማስታወቂያዎችን የማየት አጋጣሚያችሁ ሰፊ ይሆናል።

ይህን ማወቅህ፣ አንተ መረጃዎችህን ለብዙ ሰዎች የምትልክ ወይም በድረ ገጹ በመጠቀም ብዙ ጊዜ የምታጠፋ እስከሆነ ድረስ የማኅበራዊ ድረ ገጹ ብዙም የሚከስረው ነገር እንደሌለ፣ ከዚህ ይልቅ ማስታወቂያዎችን የሚያስተላልፉ ድርጅቶች ብዙ እንደሚያተርፉ እንድትገነዘብ ይረዳሃል። ያም ሆነ ይህ፣ በማኅበራዊ ድረ ገጽ የምትጠቀም ከሆነ የግል ሚስጥርህን ለመጠበቅ እንዲሁም ድረ ገጹን በመጠቀም የምታጠፋውን ጊዜ ለመቆጣጠር ጥረት አድርግ።

በሚቀጥለው ጊዜ የሚወጣው “የወጣቶች ጥያቄ” . . .

ማኅበራዊ ድረ ገጽ በስምህና ከሌሎች ጋር ባለህ ጓደኝነት ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር የሚችለው እንዴት እንደሆነ ያብራራል።

www.watchtower.org/ype በሚለው ድረ ገጽ ላይ “Young People Ask” በሚለው ዓምድ ሥር ተጨማሪ ርዕሶችን ማግኘት ይቻላል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.3 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት ስሞች ተቀይረዋል።

^ አን.5 ማኅበራዊ ድረ ገጽ የራሳቸውን አድራሻ (አካውንት) የከፈቱ ሰዎች ከሚፈልጓቸው ጓደኞቻቸው ጋር ለመገናኘት የሚያስችላቸው ድረ ገጽ ነው።

^ አን.24 የንቁ! መጽሔት የትኛውንም ዓይነት ማኅበራዊ ድረ ገጽ ለይቶ በመጥቀስ አይደግፍም አሊያም አያወግዝም። ክርስቲያኖች የኢንተርኔት አጠቃቀማቸው ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር እንደማይቃረን ማረጋገጥ አለባቸው።​—1 ጢሞቴዎስ 1:5, 19

^ አን.47 ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በጥር 2011 ንቁ! ላይ “የወጣቶች ጥያቄ . . . በኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች መጠቀም ሱስ ሆኖብኛል?” በሚል ርዕስ የቀረበውን ሐሳብ ተመልከት። በተለይም በገጽ 26 ላይ ያለውን “ማኅበራዊ ግንኙነት የሚመሠረትበት ድረ ገጽ ሱሰኛ ነበርኩ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ሬድዮ 50 ሚሊዮን አድማጭ ለማግኘት 38 ዓመት ፈጅቶበታል

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳበ]

ፌስቡክ የሚባለው ማኅበራዊ ድረ ገጽ በቅርቡ፣ በ1 ዓመት ጊዜ ውስጥ ብቻ ከ200 ሚሊዮን በላይ ተጠቃሚዎችን አፍርቷል

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለምን ወላጆችህን አትጠይቃቸውም?

በኢንተርኔት ስትጠቀም እንዴት ሚስጥርህን መጠበቅ እንደምትችል ከወላጆችህ ጋር ተወያይ። በሚስጥር ሊያዙ የሚገባቸው ነገሮች የትኞቹ ናቸው? ለምንስ? ከኢንተርኔት ጋር በተያያዘ በየትኛውም ዓይነት የመልእክት ማስተላለፊያ ዘዴ ስንጠቀም ምን ዓይነት መረጃዎችን ማስፈር ለአደጋ ሊያጋልጥ ይችላል? በተጨማሪም በኢንተርኔት አማካኝነት የሚደረገውን ግንኙነት ከሰዎች ጋር በአካል ተገናኝቶ ከመጨዋወት ጋር ማመጣጠን የምትችለው እንዴት እንደሆነ ምክር እንዲሰጡህ ወላጆችህን ጠይቃቸው። ወላጆችህ ምን ማስተካከያዎችን እንድታደርግ ነገሩህ?

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በማኅበራዊ ድረ ገጽ ላይ የምታስቀምጠው መረጃ የምታስበውን ያህል ከሌሎች እይታ የተሰወረ ላይሆን ይችላል

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጊዜ ልክ እንደ ገንዘብ ነው። ሁሉንም በአንድ ነገር ላይ ካዋልከው፣ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን የምታከናውንበት ጊዜ አታገኝም