በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ናዚዎች እምነቴን ሊያስቀይሩኝ አልቻሉም

ናዚዎች እምነቴን ሊያስቀይሩኝ አልቻሉም

ናዚዎች እምነቴን ሊያስቀይሩኝ አልቻሉም

ኸርሚነ ሊስካ እንደተናገረችው

አዶልፍ ሂትለርና የናዚ ፓርቲው የትውልድ አገሬ የሆነችውን ኦስትሪያን በ1938 ሲቆጣጠሩ የተረጋጋ የልጅነት ሕይወቴ በድንገት ደፈረሰ። ብዙም ሳይቆይ እኔም ሆንኩ አብረውኝ የሚማሩ ልጆች “ሃይል ሂትለር” የሚለውን ሰላምታ እንድንሰጥና የናዚ መዝሙሮችን እንድንዘምር እንዲሁም የሂትለር የወጣቶች ንቅናቄ አባል እንድንሆን ግፊት ይደረግብን ጀመር። እኔም እነዚህን ነገሮች አላደርግም በሚለው አቋሜ ጸናሁ። እስቲ የነበረውን ሁኔታ በዝርዝር ልግለጽላችሁ።

ያደግኩት ኦስትሪያ ውስጥ በሚገኝ ከሪንቲያ በሚባል ከተማ፣ ሴንት ቫልበርገን በሚባል መንደር ውስጥ ባለ አንድ የእርሻ ቦታ ሲሆን አራት ታላላቅ ወንድሞች ነበሩኝ። ወላጆቼ ዮሃንና ኤሊዛቤት ኦብቬገ ይባላሉ። በ1925 አባቴ ቢበልፎርሸር ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ሆነ፤ በዚያን ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች የሚጠሩት በዚህ ስም ነበር። ከዚያም እናቴ በ1937 ተጠመቀች። ወላጆቼ ከልጅነቴ ጀምሮ የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች አስተምረውኛል፤ እንዲሁም ለአምላክና ለፈጠራቸው ነገሮች ፍቅር እንዲኖረኝ ረድተውኛል። ለምሳሌ ያህል፣ ለማንም ሰው አምልኮታዊ ክብር መስጠት ስህተት እንደሆነ አስረድተውኛል። ኢየሱስ ክርስቶስ “ይሖዋ አምላክህን ብቻ አምልክ፤ ለእሱም ብቻ ቅዱስ አገልግሎት አቅርብ” በማለት ተናግሯል።​—ሉቃስ 4:8

እናቴና አባቴ እንግዳ ተቀባዮች ናቸው። ሊጠይቁን የሚመጡ ብዙ ሰዎች ነበሩ፤ እንዲሁም ሰባት አባላት ካለው ቤተሰባችን ጋር የሚኖሩ በርካታ ተቀጣሪ የእርሻ ሠራተኞች ነበሩ። በከሪንቲያ እስከ ዛሬም ድረስ ልማድ እንደሆነው ሁሉ መዝሙር በመዘመር ብዙ ጊዜ እናሳልፍ ነበር፤ አስደሳች የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይቶችንም እናደርግ ነበር። ሁልጊዜ እሁድ ጠዋት ቤተሰባችን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማድረግ ሳሎን ባለው ጠረጴዛ ዙሪያ ይሰበሰብ ነበር፤ ይህም እስከ ዛሬ ድረስ የማልረሳው አስደሳች ትዝታ ነው።

ከነፃነት ወደ ፍርሃት

የስምንት ዓመት ገደማ ልጅ ሳለሁ ጀርመን ኦስትሪያን በግዛቷ ውስጥ ጠቀለለች። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የናዚ ፓርቲ የሚፈልገውን ሁሉ ለማስፈጸም በዜጎች ላይ የሚያሳድረው ጫና እየጨመረ መጣ፤ በዚህም ምክንያት ሁሉም ሰዎች ለሌሎች ሰላምታ ሲሰጡ “ሃይል ሂትለር” እንዲሉ ይጠበቅባቸው ጀመር። “ሃይል” የሚለው ቃል በጀርመንኛ “መዳን” ማለት ሲሆን እኔ ደግሞ መዳን በሂትለር ይገኛል ብዬ ስለማላምን እንዲህ ብዬ ሰላምታ ለመስጠት እምቢ አልኩ! አዳኜ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ አውቃለሁ። (የሐዋርያት ሥራ 4:12) በአቋሜ የተነሳ አስተማሪዎችም ሆኑ አብረውኝ የሚማሩ ልጆች ሁልጊዜ ያሾፉብኝ ነበር። ዕድሜዬ 11 ዓመት ሲሞላ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህሬ “ኸርሚነ፣ ወደ አንደኛ ክፍል ልመልስሽ ነው። እንዳንቺ ያለ ግትር ልጅ እኔ በማስተምርበት ክፍል ውስጥ እንዲኖር አልፈልግም!” አለኝ።

እኔና ወንድሞቼ ሂትለር አዳኝ ነው አንልም በሚለው አቋማችን ስለጸናን አባታችን ፍርድ ቤት እንዲቀርብ ተደረገ። ከዚያም እምነቱን እንዲክድ በሚጠይቅ አንድ ሰነድ ላይ እንዲፈርም ተጠየቀ። ሰነዱም አባታችን ልጆቹን በናዚ ርዕዮተ ዓለም መሠረት እንዲያሳድግ የሚጠይቅ ነበር። ይህን ሰነድ ለመፈረም እምቢ በማለቱ እሱና እናቴ እኛን የማሳደግ መብታቸውን ተነጠቁ፤ ከዚያም እኔ 40 ኪሎ ሜትር ርቆ ወደሚገኝ የተሃድሶ ትምህርት የሚሰጥበት ተቋም ተላክሁ።

ብዙም ሳይቆይ ቤተሰቤን በጣም ናፈቅኩ፤ ከዚህም የተነሳ ዝም ብዬ አለቅስ ነበር። ይህ በእንዲህ እንዳለ እንድታስተምረኝ የተመደበችልኝ ሴት የሂትለር ወጣቶች ንቅናቄ አባል እንድሆን ልታስገድደኝ ብትሞክርም ፈቃደኛ አልሆንኩም። የናዚ ባንዲራ በሚሰቀልበት ጊዜ ሰላምታ እንድሰጥ ለማድረግ ሌሎች ልጃገረዶች ቀኝ እጄን ወደ ላይ አንስተው ለመያዝ ይሞክሩ የነበረ ቢሆንም አልተሳካላቸውም። በዚያን ጊዜ “ሌሎችን አማልክት ለማምለክ ብለን እግዚአብሔርን [“ይሖዋን፣” NW] መተው ከእኛ ይራቅ” በማለት እንደተናገሩት የጥንቶቹ የአምላክ አገልጋዮች ዓይነት ስሜት ተሰምቶኝ ነበር።​—ኢያሱ 24:16

ወላጆቼ መጥተው እንዳይጠይቁኝ ተከለከሉ። ይሁን እንጂ ወደ ትምህርት ቤት ስሄድ መንገድ ላይ በመጠበቅና ትምህርት ቤት ድረስ በመምጣት በድብቅ የምንገናኝበትን ዘዴ ፈጥረው ነበር። በዚህ መንገድ ለአጭር ጊዜም ቢሆን ከወላጆቼ ጋር መገናኘቴ ለይሖዋ ታማኝ ሆኜ እንድጸና በእጅጉ ረድቶኛል። ከወላጆቼ ጋር በተገናኘሁበት በአንድ ወቅት አባቴ አንዲት ትንሽ መጽሐፍ ቅዱስ ሰጠኝ፤ እኔም አልጋዬ ውስጥ ደበቅኳት። ምንም እንኳ የማነበው ተደብቄ ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ በጣም ያስደስተኝ ነበር! እርግጥ አንድ ቀን እያነበብኩ ሳለ ልያዝ ነበር፤ ሆኖም መጽሐፍ ቅዱሷን ቶሎ ብዬ ብርድ ልብሴ ውስጥ ደበቅኳት።

ወደ ገዳም ተላክሁ

እኔን በተሃድሶ ትምህርቱ አማካኝነት ለመለወጥ የተደረገው ጥረት ሁሉ ስላልተሳካ ባለሥልጣኖቹ አሁንም ከወላጆቼ ጋር እንደምገናኝ ጠረጠሩ። በመሆኑም መስከረም 1942 ሙኒክ፣ ጀርመን ውስጥ ወደሚገኝ አዴልጉንደን የሚባል የካቶሊክ ትምህርት ቤት እንድገባ በባቡር አሳፍረው ላኩኝ፤ ትምህርት ቤቱ የሴቶች ገዳምም ነበር። ወደዚያ በተዛወርኩበት ወቅት መነኮሳቱ መጽሐፍ ቅዱሴን አዩብኝና ቀሙኝ።

ይሁን እንጂ በእምነቴ ለመጽናት ቆርጬ ስለነበር በቤተ ክርስቲያን በሚካሄደው የአምልኮ ሥርዓት ላይ ለመገኘት እምቢ አልኩ። ከመነኮሳቱ አንዷ፣ ወላጆቼ እሁድ እሁድ መጽሐፍ ቅዱስን ያነቡልኝ እንደነበረ ስነግራት ያደረገችው ነገር አስገረመኝ። መጽሐፍ ቅዱሴን መልሳ ሰጠችኝ! እንዲህ ያደረገችው የተናገርኩት ነገር ልቧን ስለነካት መሆን አለበት። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስን ሳነብላት ታዳምጠኝ ነበር።

በአንድ ወቅት አንዲት አስተማሪ “ኸርሚነ፣ አንቺ ፀጉርሽ ወርቃማ ነው፤ ዓይንሽም ሰማያዊ ነው። ስለዚህ አንቺ ጀርመናዊ ነሽ እንጂ አይሁዳዊ አይደለሽም። ይሖዋ ደግሞ የአይሁዶች አምላክ ነው” አለችኝ።

እኔም “ግን እኮ ሁሉንም ነገር የፈጠረው ይሖዋ ነው። እሱ የሁላችንም ፈጣሪ ነው!” ብዬ መልስ ሰጠኋት።

ርዕሰ መምህሩም ተጽዕኖ ሊያደርግብኝ ሞክሮ ነበር። በአንድ ወቅት “ኸርሚነ፣ ከወንድሞችሽ አንዱ እኮ ሠራዊቱን ተቀላቅሏል። አንቺም የእሱን ምሳሌ ብትከተዪ ይሻልሻል!” አለኝ። ከወንድሞቼ አንዱ ሠራዊቱን እንደተቀላቀለ አውቄ የነበረ ቢሆንም የእሱን ምሳሌ የመከተል ሐሳብ ግን አልነበረኝም።

“እኔ የወንድሜ ተከታይ አይደለሁም” አልኩት። “የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታይ ነኝ።” ከዚያም ርዕሰ መምህሩ የአእምሮ ሕሙማን ወደሚታከሙበት ክፍል እንደሚልከኝ በመናገር አስፈራራኝ፤ አልፎ ተርፎም አንዷን መነኩሲት እኔን ለመውሰድ እንድትዘጋጅ ትእዛዝ ሰጣት። ይሁን እንጂ እንደተናገረው አላደረገም።

በ1943 የበጋ ወራት ሙኒክ በቦምብ ስትደበደብ በአዴልጉንደን የምንገኝ ልጆች ወደ ገጠር ተወሰድን። በዚያ ወቅት እናቴ “እኔና አንቺ ብንለያይና ደብዳቤዎቼ ባይደርሱሽ እንኳ ይሖዋና ኢየሱስ ምንጊዜም ካንቺ ጋር እንደሆኑ አስታውሺ። እነሱ ፈጽሞ አይተዉሽም። ስለዚህ ሳታቋርጪ ጸልዪ” በማለት የነገረችኝን ነገር ደጋግሜ አስታውስ ነበር።

ወደ ቤቴ እንድሄድ ተፈቀደልኝ

ሙኒክ በከፍተኛ ሁኔታ በቦምብ ትደበደብ ስለነበር መጋቢት 1944 እንደገና ወደ አዴልጉንደን ተወሰድኩ፤ በዚያም ሁላችንም ቀንም ሆነ ሌሊት በአየር ጥቃት መከላከያው ተጠልለን እናሳልፍ ነበር። ይህ በእንዲህ እንዳለ ወላጆቼ ወደ እነሱ እንድመለስ አዘውትረው ይጠይቁ ነበር። ይህ ጥያቄ በመጨረሻ ተቀባይነት አገኘና በ1944 በሚያዝያ ወር ማለቂያ ላይ ወደ ቤት ተመለስኩ።

ርዕሰ መምህሩን ልሰናበተው ስሄድ “ኸርሚነ፣ ቤትሽ ስትደርሺ ጻፊልን። በዚሁ ቀጥዪ እሺ” አለኝ። ከፍተኛ የአመለካከት ለውጥ አድርጎ ነበር! ተሰናብቼ እንደሄድኩ ዘጠኝ ልጃገረዶችና ሦስት መነኮሳት በቦምብ ጥቃት እንደተገደሉ ሰማሁ። ጦርነት እንዴት ያለ አሰቃቂ ነገር ነው!

በሌላ በኩል ደግሞ ከቤተሰቦቼ ጋር እንደገና በመገናኘቴ ተደስቼ ነበር። ግንቦት 1944 ጦርነቱ ገና ተጧጥፎ እያለ ለይሖዋ ራሴን መወሰኔን ለማሳየት በመታጠቢያ ገንዳ ውስጥ ተጠመቅኩ። ጦርነቱ በ1945 ሲያበቃ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ስለሚያመጣውና የሰው ልጅ ብቸኛ ተስፋ ስለሆነው ስለ አምላክ መንግሥት የሚገልጸውን ምሥራች ለሌሎች ለማካፈል ስለጓጓሁ ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት ገባሁ።​—ማቴዎስ 6:9, 10

በ1950 ከቪየና፣ ኦስትሪያ ከመጣ ኤሪክ ሊስካ የሚባል ወጣት ወንድም ጋር ተዋወቅኩ፤ እሱም የይሖዋ ምሥክሮች ተጓዥ አገልጋይ ነበር። በ1952 ከኤሪክ ጋር ከተጋባን በኋላ ጉባኤዎችን በመንፈሳዊ ለማጠናከር ሲጎበኝ ለአጭር ጊዜም ቢሆን አብሬው ተጉዣለሁ።

የመጀመሪያዋ ልጃችን በ1953 ተወለደች፤ ከዚያም ሁለት ልጆች ወለድን። ኃላፊነት ሲደራረብብን ልጆቻችንን ለማሳደግ ስንል የሙሉ ጊዜ አገልግሎታችንን አቋረጥን። አምላክን የሙጥኝ ብለን እስከኖርን ድረስ ፈጽሞ እንደማይተወን፣ ከዚህ ይልቅ ጥንካሬ እንደሚሰጠን በሕይወቴ ተምሬያለሁ። እሱ ፈጽሞ ጥሎኝ አያውቅም። በተለይም በ2002 ውድ ባለቤቴን በሞት ካጣሁ በኋላ ይሖዋ የመጽናናትና የብርታት ምንጭ ሆኖልኛል።

ስላሳለፍኩት ሕይወት መለስ ብዬ ሳስብ ወላጆቼ ገና ልጅ ሳለሁ በውስጤ ለአምላክና የእውነተኛ ጥበብ ምንጭ ለሆነው በጽሑፍ ለሰፈረው ቃሉ ፍቅር እንዲያድርብኝ ስላደረጉ እጅግ አመስጋኝ ነኝ። (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) ከሁሉ በላይ ግን በሕይወቴ ውስጥ የሚያጋጥሙኝን መከራዎች ለመቋቋም እንድችል ያለማቋረጥ ብርታት የሚሰጠኝን ይሖዋን በጣም አመሰግነዋለሁ።

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“እኔ የወንድሜ ተከታይ አይደለሁም . . . የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታይ ነኝ”

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በሴንት ቫልበርገን በሚገኘው የእርሻ ቦታችን ከቤተሰቤ ጋር

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኤሊዛቤትና ዮሃን ኦብቬገ የተባሉት ወላጆቼ

[የሥዕሉ ምንጭ]

Both photos: Foto Hammerschlag

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከባለቤቴ ከኤሪክ ጋር