በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጥበብ ያዘሉ ሰባት ምሳሌዎች

ጥበብ ያዘሉ ሰባት ምሳሌዎች

ጥበብ ያዘሉ ሰባት ምሳሌዎች

ከታች የተዘረዘሩት ምሳሌዎች ወቅታዊና ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ በርካታ ምሳሌዎች ከሚገኙበት አንድ ጥንታዊ መጽሐፍ ላይ የተወሰዱ ናቸው። እነዚህ ምሳሌዎች በገንዘብ አያያዝህ ረገድ ሊጠቅሙህ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

1. “ገንዘብን የሚወድ፣ ገንዘብ አይበቃውም፤ ብልጽግናም የሚወድ፣ በትርፉ አይረካም።” (መክብብ 5:10) ይህን ሐሳብ የተናገረው በሀብታሞች የሚቀና አንድ የተቸገረ ሰው አይደለም። ከዚህ ይልቅ በምድር ላይ ከኖሩት እጅግ ባለጠጋ ሰዎች መካከል አንዱ የሆነው የእስራኤሉ ንጉሥ ሰለሞን ነው፤ ይህ ንጉሥ ከራሱ ተሞክሮና ካያቸው ነገሮች በመነሳት እንዲህ ብሎ ሊጽፍ ችሏል። በዘመናችን ያሉ ሀብታም ሰዎችም ተመሳሳይ አስተያየት ሰጥተዋል።

2. “ምግብ እንዲሁም ልብስና መጠለያ ካለን በእነዚህ ነገሮች ረክተን መኖር ይገባናል። ይሁን እንጂ ሀብታም ለመሆን ቆርጠው የተነሱ ፈተናና ወጥመድ ውስጥ ይወድቃሉ።” (1 ጢሞቴዎስ 6:8, 9) ይህን ሐሳብ የጻፈው ከፍተኛ እውቅና ሊያስገኝለት የሚችለውን ሙያ ትቶ የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታይ የሆነው ሐዋርያው ጳውሎስ ነው። ጳውሎስ በዘመናችን ካሉ አንዳንድ ሃይማኖታዊ መሪዎች በተለየ መልኩ ከተማሪዎቹ ወይም ከእምነት አጋሮቹ ቁሳዊ ጥቅም ለማግኘት ፈጽሞ አልሞከረም። ከዚህ ይልቅ እንደሚከተለው ሲል በሐቀኝነት ተናግሯል፦ “የማንንም ብር ወይም ወርቅ ወይም ልብስ አልተመኘሁም። እነዚህ እጆቼ ለእኔም ሆነ ከእኔ ጋር ለነበሩት የሚያስፈልጉንን ነገሮች ለማሟላት እንዳገለገሉ እናንተ ራሳችሁ ታውቃላችሁ።”​—የሐዋርያት ሥራ 20:33, 34

3. “ከእናንተ መካከል፣ ግንብ ለመገንባት ፈልጎ ለመጨረስ የሚያስችል በቂ ገንዘብ እንዳለው ለማወቅ በመጀመሪያ ተቀምጦ ወጪውን የማያሰላ ማን ነው?” (ሉቃስ 14:28) የኢየሱስ ምሳሌ በዕለት ተዕለት በሚያጋጥምህ ሁኔታ ላይም ሊሠራ ይችላል፦ አንድን ነገር ከመግዛትህ በፊት (በተለይም ደግሞ በዱቤ) ቆም ብለህ ወጪህን ታሰላለህ? ወይስ በስሜት ተገፋፍተህ ትገዛለህ? ደግሞስ በእርግጥ ዕቃው ያስፈልግሃል? ዕቃውን ለመግዛትስ አቅምህ ይፈቅዳል?

4. “ተበዳሪም የአበዳሪ ባሪያ ነው።” (ምሳሌ 22:7) በቅርቡ በዓለም ላይ የደረሰው የገንዘብ ቀውስ ክሬዲት ካርድና ሌሎች የብድር ዓይነቶች ውድቀት ላይ እንደሚጥሉ በግልጽ አሳይቷል። ማይክል ዋግነር፣ በ2009 ባሳተሙት ዩር መኒ፣ ደይ ዋን በተባለው መጽሐፋቸው ላይ “በዛሬው ጊዜ አንድ ሰው በአራትና ከአራት በሚበልጡ ክሬዲት ካርዶች ተጠቅሞ በአማካይ ከ9,000 ዶላር በላይ (151,200 ብር በላይ) ዕዳ ውስጥ መግባቱ የተለመደ ነገር ሆኗል” ብለዋል።

5. “ኃጢአተኛ ይበደራል አይከፍልምም፤ ጻድቅ ግን ይራራል ይሰጣልም።” (መዝሙር 37:21 የ1954 ትርጉም) አንዳንድ ሰዎች ከስሬያለሁ ብሎ ማወጅ ከዕዳ የሚገላገሉበት ቀላል መንገድ እንደሆነ አድርገው ያስባሉ። ከአምላክ ጋር ያላቸውን ጥሩ ዝምድና ከፍ አድርገው የሚመለከቱ ሰዎች ግን ዕዳቸውን በትጋት ለመክፈል ብቻ ሳይሆን ከቻሉ ያላቸውን ነገር ለሌሎች በልግስና ለማካፈል ይጥራሉ።

6. “ጐልማሳ ነበርሁ፤ አሁን አርጅቻለሁ፤ ነገር ግን ጻድቅ ሲጣል፣ ዘሩም እንጀራ ሲለምን አላየሁም።” (መዝሙር 37:25) ይህን ሐሳብ የጻፈው ብዙ በደል የደረሰበት ሰው ነው። በርካታ ዓመታት በስደት ያሳለፈ ሲሆን በዋሻ ውስጥ ለመኖርና በባዕድ አገር ጥገኝነት ለመጠየቅ የተገደደበትም ጊዜ ነበር። ይህ ስደተኛ ማለትም ዳዊት ውሎ አድሮ የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ ለመሆን በቅቷል። ዳዊት ከላይ የተናገረውን ሐሳብ እውነተኝነት ከራሱ የሕይወት ተሞክሮ ተገንዝቧል።

7. “ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል።” (የሐዋርያት ሥራ 20:35) ይህን የተናገረው በምድር ላይ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው ነው። ኢየሱስ “ከፊቱ ለሚጠብቀው ደስታ ሲል” ምድራዊ ሕይወቱን ሌሎችን ለማገልገል ተጠቅሞበታል። በአሁኑ ጊዜ ደግሞ በሰማይ የማይሞት መንፈሳዊ ሕይወት አግኝቶ ‘ደስተኛ በሆነው አምላክ’ በይሖዋ ቀኝ ተቀምጧል።​—ዕብራውያን 12:2፤ 1 ጢሞቴዎስ 1:11

እኛም አቅማችን በፈቀደልን መጠን ሌሎችን በማገልገል የኢየሱስን ምሳሌ መከተል እንችላለን፤ ደግሞም ሕይወታችን ትርጉም ያለው እንዲሆን የሚያደርግ ከዚህ የተሻለ ነገር የለም። እንግዲያው ‘በራስ ወዳድነት ስሜት ገንዘብ ከማባከን ይልቅ ጠንቃቃ ቆጣቢ በመሆን ለሌሎች በልግስና መስጠት የተሻለ ነው’ በሚለው ሐሳብ እንደምትስማማ ምንም ጥርጥር የለውም።