በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“አልሞትኩም እኔ”

“አልሞትኩም እኔ”

“አልሞትኩም እኔ”

“ቆማችሁ አታልቅሱ፣ በመቃብሬ፤

እዚያ የለሁም፤

አልሞትኩም እኔ።”

● ይህ ስንኝ እንግሊዝኛ በሚናገሩ ሰዎች ዘንድ በሰፊው የሚታወቅ ግጥም መደምደሚያ ሲሆን በዚህ ግጥም የተዘጋጀ ዘፈንም አለ። ግጥሙ ላለፉት ጥቂት አሥርተ ዓመታት በመላው ዓለም የሚኖሩ ሰዎችን አጽናንቷል። የግጥሙ ደራሲ በትክክል ስለማይታወቅ የተለያዩ ሰዎች የግጥሙ ደራሲ እንደሆኑ ሲነገር ቆይቷል። እንዲያውም አንዳንዶች፣ የናቫሆ ሕንዶች የቀብር ሥርዓት ላይ የሚያቀርቡት ጸሎት ነው እስከማለት ደርሰዋል።

ከጥቂት ዓመታት በፊት በጃፓን አገር በዚህ ግጥም የተሠራው ዘፈን ተወዳጅነት ያተረፈ ቢሆንም በብዙ ሰዎች ዘንድ ግራ መጋባት ፈጥሯል። ጃፓናውያን ለሞቱ ዘመዶቻቸው አክብሮት እንዳላቸው ለማሳየት ወደ መቃብራቸው የመሄድ ልማድ አላቸው፤ ይህን የሚያደርጉት ዘመዶቻቸው በዚያ ስፍራ በሕይወት እንደሚኖሩ ስለሚያስቡ ነው። ይህ ዘፈን እነሱ ከሚያስቡት የተለየ መልእክት ስለሚያስተላልፍ ብዙዎች “በእርግጥ ሙታን የት ናቸው?” የሚለውን ጥያቄ እንዲያነሱ አድርጓቸዋል።

የጃፓን ቡድሂስቶች ከሞት ጋር በተያያዘ የተለያዩ ልማዶችን ለረጅም ጊዜ ሲከተሉ ቆይተዋል፤ ከእነዚህ መካከል የቀብር ሥነ ሥርዓት፣ አስከሬን የመጠበቅ ልማድና የመታሰቢያ ሥነ ሥርዓት ይገኙበታል። ይሁን እንጂ አብዛኞቹ ቡድሂስቶች፣ ለሚከተሉት ጥያቄዎች መልስ መስጠት አልቻሉም፦ ሙታን የት ናቸው? የተለያየ ሃይማኖትና ዜግነት ያላቸው ሰዎች ሲሞቱ የሚሄዱት ወደ አንድ ቦታ ነው? ሙታን ምላሽ የማይሰጡት ለምንድን ነው?

ብዙ ሰዎች እንዲህ ያሉ ጥያቄዎች መልስ የማይገኝላቸው እንደሆኑና የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ለመፈለግ ጥረት ማድረግ ጊዜ ማባከን እንደሆነ ይሰማቸዋል። ያም ሆኖ ‘ስንሞት ምን እንሆናለን?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። ደግሞስ ለጥያቄው መልስ ማግኘት የሚቻለው ከየት ነው? አምላክ የመጀመሪያዎቹን ባልና ሚስት ፍጹም አድርጎ እንደፈጠራቸውና ውብ የሆነ የአትክልት ስፍራ ለመኖሪያነት ሰጥቷቸው እንደነበረ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። አምላክን ቢታዘዙ ኖሮ በገነት ውስጥ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ነበራቸው። እነሱ ግን ሳይታዘዙ ቀሩ።

በመሆኑም አምላክ እርምጃ በመውሰድ እነዚህን ባልና ሚስት ገነት ከሆነችው መኖሪያቸው ያስወጣቸው ከመሆኑም በላይ ሕይወታቸው እንዲቀጥል ድጋፍ ማድረጉን አቆመ። አለመታዘዛቸው ያስከተለባቸውን ቅጣት ሲነግራቸው “ዐፈር ነህና ወደ ዐፈር ትመለሳለህ” ብሏል። ሰው የተሠራው ከአፈር ስለሆነ ከሞተ በኋላ ቀስ በቀስ ወደ አፈር ይመለሳል።​—ዘፍጥረት 2:7፤ 3:19

በኮፉ፣ ጃፓን የአንድ ትልቅ የመቃብር ቦታ ጠባቂ የሆነ ሰው እንዲህ ብሏል፦ “ማሰሮዎቹን በመቃብሩ ሳስቀምጣቸው አመድና አጥንት የሞላባቸው ነበሩ። ከአምስት ዓመታት ገደማ በኋላ በውስጣቸው የነበረው ነገር በግማሽ ጎድሎ አገኘሁት። ከአሥር ዓመት በኋላ በአብዛኞቹ [ክፍት] ማሰሮዎች ውስጥ ምንም የቀረ ነገር አልነበረም።” ሰውነታችን ከአፈር በተወሰዱ ንጥረ ነገሮች የተሠራ ስለሆነ ከጊዜ በኋላ ፈራርሶ እንደገና አፈር ይሆናል። ታዲያ ተስፋቸው ምንድን ነው?

ስንሞት ማንኛውም ዓይነት ስሜትም ሆነ የማሰብ ችሎታ የማይኖረን ቢሆንም የእያንዳንዷን ድንቢጥ መሞትም እንኳን ሳይቀር የሚያውቀው ፈጣሪያችን በመልካም ያስታውሰናል። (ማቴዎስ 10:29-31) ቃል በገባው መሠረት ያስነሳናል፤ በእርግጥም፣ ወደ ሕይወት ይመልሰናል። ካንቀላፋንበት የሞት እንቅልፍ ይቀሰቅሰናል።​—ኢዮብ 14:13-15፤ ዮሐንስ 11:21-23, 38-44

ስለዚህ ጉዳይ ተጨማሪ እውቀት ለማግኘት የምትፈልግ ከሆነ ለዚህ መጽሔት አዘጋጆች መጻፍ ትችላለህ፤ እነሱም ተጨማሪ እውቀት እንድታገኝ ሁኔታዎችን ሊያመቻቹልህ ይችላሉ። አሊያም www.watchtower.org የተባለውን ድረ ገጻችንን እንድትጎበኝ እናበረታታሃለን።