በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መርቸሰን ፏፏቴ—የኡጋንዳው ናይል ልዩ ገጽታ

መርቸሰን ፏፏቴ—የኡጋንዳው ናይል ልዩ ገጽታ

መርቸሰን ፏፏቴ—የኡጋንዳው ናይል ልዩ ገጽታ

“ይህ በጣም ትልቁ የናይል ፏፏቴ ነው።”—እንግሊዛዊው አሳሽ ሰር ሳሙኤል ዋይት ቤከር

ፏፏቴዎች ቀልብ የሚስቡ ከመሆኑም በላይ በሰዎች ላይ የአድናቆት ስሜት ይፈጥራሉ። የፏፏቴ ውኃ ከሥሩ ካሉት ዓለቶች ጋር ሲላተም የሚያሰማው መንፈስ የሚያረጋጋ ድምፅና ብዙ ጊዜ ከፏፏቴው እንደ ጉም እየተነነ የሚወጣው ቀዝቃዛ የውኃ ብናኝ ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ጎብኚዎች ለረጅም ሰዓት ዘና ያደርጋቸዋል።

በኡጋንዳ ያለው መርቸሰን ፏፏቴም * ቢሆን ከዚህ የተለየ አይደለም። የናይል ወንዝ ከ6,400 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝማኔ ያለው ሲሆን አንዳንዶች ይህን ፏፏቴ ዕፁብ ድንቅ የሆነው የናይል ገጽታ ብለው ይጠሩታል። እርግጥ ነው፣ ይህ ፏፏቴ በደቡብ አሜሪካ ያለውን የኤንጅል ፏፏቴ ያህል ከፍታ የለውም፤ የውኃውም መጠን ቢሆን በአፍሪካ ከሚገኘው የቪክቶሪያ ፏፏቴ ወይም በሰሜን አሜሪካ ካለው የኒያጋራ ፏፏቴ አንጻር ሲታይ አነስተኛ ነው። ሆኖም የመርቸሰን ፏፏቴ ያለው ውበትና ኃይል ባዩት ሰዎች ላይ የማይረሳ ትዝታ ጥሎ ያልፋል።

የመርቸሰን ፏፏቴ ታሪክ

የመርቸሰን ፏፏቴ፣ 3,841 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው የመርቸሰን ፏፏቴ ብሔራዊ ፓርክ አንዱ ገጽታ ብቻ ነው። በሰሜናዊ ምዕራብ ኡጋንዳ የሚገኘው ይህ ፓርክ የተቋቋመው በ1952 ነበር። ቤከር ይህን ፏፏቴ በ1860ዎቹ መጀመሪያ ላይ ጎብኝቶት ነበር። ይህን ፏፏቴ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲያየው ያደረበትን ስሜት ዚ አልበርት ኒያንዛ በተሰኘው መጽሐፉ ላይ ገልጿል።

ቤከር እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በአካባቢው እየተዘዋወርን ሳለን ዓይናችን ፍጹም ማራኪ በሆነ አንድ ነገር ላይ ድንገት አረፈ። . . . የፏፏቴው ውኃ እንደ በረዶ ነጭ ሲሆን በወንዙ ግራና ቀኝ ካሉት ጥቋቁር ቋጥኞች አንጻር ሲታይ አስደናቂ እይታ ይፈጥራል፤ ግርማ ሞገስ የተላበሱት ዘንባባዎችና በአካባቢው የሚበቅለው የሙዝ ተክል የቦታውን ውበት ምሉዕ አድርጎታል። በእርግጥም ይህ በጣም ትልቁ የናይል ፏፏቴ ነው።” ፏፏቴውን ለመጀመሪያ ጊዜ መርቸሰን ፏፏቴ ብሎ የሰየመው ቤከር ሲሆን ይህንን ስያሜ የሰጠው ለሮያል ጂኦግራፊ ማኅበር ፕሬዚዳንት ክብር ሲል ነበር።

ፏፏቴውን ማየት የሚቻልባቸው መንገዶች

ፏፏቴውን ማየት የሚቻልበት የተሻለው መንገድ ከጀልባ ላይ ሆኖ መመልከት ነው። የጀልባ ጉዞው የሚጀምረው ፓራ ከሚባለው የመነሻ ስፍራ ሲሆን ጎብኚዎች በጀልባ መጠቀማቸው በናይል ላይ ለመንሸራሸር የሚያስችል ግሩም አጋጣሚ ይፈጥርላቸዋል። እግረ መንገዳቸውንም ለጉዳት በማያጋልጥ ርቀት ላይ ሆነው የዱር አራዊቶችን ለማየት ያስችላቸዋል። በብዛት የሚታዩት ጉማሬዎች ቢሆኑም ትልልቅ የአፍሪካ ዝሆኖችን፣ አዞዎችንና ጎሾችንም መመልከት ይቻላል። በናይል አካባቢ የሚገኙት አስደናቂዎቹ የዱር እንስሳት አንድን ጎብኚ ፏፏቴውን የማየት ግቡን ለጊዜውም ቢሆን ሊያስረሱት ይችላሉ። ይሁን እንጂ ይህ ጎብኚ ከዓለቶቹ ውስጥ ፈንድቶ የሚወጣ የሚመስለውና እንደ በረዶ ነጭ የሆነው ፏፏቴ ጋ ሲደርስ ቤከር በጣም የተደመመው ለምን እንደሆነ ግልጽ ይሆንለታል።

ብዙ ጎብኚዎች ከጀልባ ላይ ሆነው ፏፏቴውን ማየት በጣም የሚያስደስታቸው ቢሆንም ፏፏቴውን ከላይ ሆኖ መመልከትም የራሱ የሆነ የሚማርክ ልዩ ውበት አለው። እንዲያውም አንዳንዶች ከላይ ሆኖ ማየቱ እጅግ የተሻለ ነው ይላሉ። አንድ ሰው ከላይ ሆኖ 49 ሜትር ስፋት ያለው የናይል ወንዝ በግምት 6 ሜትር ያህል ስፋት ባለው ክፍተት በኩል እየተጋፋ በማለፍ 40 ሜትር ቁልቁል ሲወረወር ማየት ይችላል። ይህ ፏፏቴ “በዓለም ላይ ካሉት በጣም ከፍተኛ ኃይል ያላቸው የውኃ ፍሰቶች መካከል አንዱ” እንደሆነ ተደርጎ ተገልጿል። ውኃው ግራና ቀኝ ካሉት ዓለቶች ጋር እየተላተመ ቁልቁል ሲወርድ ጎብኚዎች አንዳንድ ጊዜ መሬቱ በመጠኑ እንደመንቀጥቀጥ ሲል ይሰማቸዋል።

ቤከር ፏፏቴውን ከማየቱ በፊት ያደረበትን ስሜት ገልጿል። ጠዋት ላይ በእግሩ ለመንሸራሸር ወጥቶ ሳለ እንደ ነጎድጓድ ያለ ድምፅ እንደሰማ ተናግሯል። ይህ ድምፅ ራቅ ካለ ስፍራ የሚሰማ ነጎድጓድ ነው ብሎ አስቦ የነበረ ቢሆንም ፏፏቴው የፈጠረው ድምፅ መሆኑን ሲረዳ በጣም ተደንቆ ነበር።

እንደ ቤከር ሁሉ በየዓመቱ በሺህ የሚቆጠሩ ጎብኚዎችም፣ ይህ ፏፏቴ ባለው መሳጭ ውበትና ኃይል በደስታ ይዋጣሉ። የፏፏቴው ውኃ ቁልቁል ተወርውሮ ሲወርድ ያለውን ኃይል መመልከት ከአእምሮ የማይጠፋ ትውስታ እንዲኖር ያደርጋል። በእርግጥም የመርቸሰን ፏፏቴ የናይል ልዩ ገጽታ ነው።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.4 ካባሌጋ ወይም ካባሬጋ ፏፏቴ በመባልም ይታወቃል።

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

የመርቸሰን ፏፏቴ ብሔራዊ ፓርክ

በ1969 በተደረገ ቆጠራ መሠረት በፓርኩ ውስጥ 14,000 ጉማሬዎች፣ 14,500 ዝሆኖችና 26,500 ጎሾች እንደነበሩ ማረጋገጥ ተችሏል። በቀጣዮቹ አሥርተ ዓመታት ግን የእነዚህ እንስሳት ቁጥር በአስገራሚ ሁኔታ አሽቆልቁሏል። ሆኖም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለአካባቢው ጥበቃ ለማድረግ በተካሄደው ጥረት የእንስሳቱ ቁጥር እንደገና ወደ ቀድሞው ሁኔታ እየተመለሰ ነው። በአሁኑ ጊዜ በፓርኩ ውስጥ ያለው ደን እንደ ቺምፓንዚና ዝንጀሮ ላሉት በርካታ አጥቢ እንስሳት መኖሪያ እየሆናቸው ሲሆን በሣር የተሸፈነው ምድር ደግሞ እንደ ቀጭኔና ቆርኬ ለመሳሰሉት እንስሳት የግጦሽ መሬት ሆኖላቸዋል። እንዲያውም በፓርኩ ውስጥ ከ70 በላይ የአጥቢ እንስሳት ዝርያዎችና ከ450 በላይ የወፍ ዝርያዎች አሉ።

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

All photos pages 16 and 17: Courtesy of the Uganda Wildlife Authority